ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, September 23, 2017

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ስርጭት በአቡነ ማቲያስ መታገድ የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ አቅም የመፈታተን ሌላው እኩይ ተግባር ነው።


ጉዳያችን/ Gudayachn
መስከረም 13 / 2010 ዓም (ሴፕቴምበር 23 / 2017)
+++++++++++++++++++++++++++
  • በወጣቶች የተገነባው እና ለእሩብ ክፍለ ዘመን አገልግሎቱን በነፃ የሚሰጥ ማኅበር - ማኅበረ ቅዱሳን በሕዝብ መሀክል ሰላም፣እርቅ እና መግባባት እንዲኖር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም።
  • በቅርቡ በአማርኛ፣ኦሮምኛ እና ትግርኛ የጀመረው መንፈሳዊ መርሃ ግብርም ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተለየ ሀገራችን ለገጠማት የመለያየት ችግር አንዱ እና አይነተኛ የእርስ በርስ መከባበር ፣መተሳሰብ እና ትልቅ ትስስር የመገለጫ መንገድ ተደርጎ መታየት ይገባው ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ መሰረትነት ላይ ስለታነፀች እና ሐዋርያዊት በመሆኗ አሰራሯ በአንድ ፓትሪያርክ ወይም ሊቀ ጳጳስ የግል ውሳኔ ላይ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስን አጋዥ አድርጎ በሚሰራው በ50 ዓም  ሐዋርያት በመሰረቱት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት ነው።አባቶቻችን አንድን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብስባ ሲወስኑ '' እኛና መንፈስ ቅዱስ'' ብለው ውሳኔያቸውን አስረግጠው ነገር ግን በትህትና ያሳውቁ ነበር።አሁን ባለንበት ዘመን ይህ ጉዳይ  በተለይ  ከዘመነ አቡነ ጳውሎስ ጀምሮ የአንድ አባት ውሳኔ የቤተ ክርስቲያኗ ውሳኔ እየተደረገ ብዙ ነገሮች እንዳይስተካከሉ እየተደረጉ ሲበላሹ ተመልክተናል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከ40 ሚልዮን ምእመናንን በላይ በስሯ ይዛ በ21ኛው ክ/ዘመን ለምእመናን የምትደርስበት አንድ ቴሌቭዥን ስለሌላት የማይቆጭ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅ አልነበረም።ይህንን የተገነዘበው ማኅበረ ቅዱሳን ከኢቢኤስ ሳምንታዊ የአየር ጊዜ በመግዛት በሳምንት አንድ ጊዜ የትምህርት እና ልዩ ልዩ ገዳማት የተመለከተ ዘገባዎችን  ለምእመናን ማድረስ ጀመረ።ሆኖም ግን ከትንሽ ጊዜ በኃላ መርሃ ግብሩ እንዲቆም ተደረገ።ይህም ሆኖ ማኅበሩ በኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎች በመጠቀም  መርሃ ግብሩን ቀጥሎ ነበር።ሆኖም የኤሌክትሮኒክስ ስርጭቱ በተለይ በኢትዮጵያ ለሚኖረው ምእመን በኢንተርኔት መቆራረጥ ሳቢያ እና ያለውም የኢንተርኔት አገልግሎት ለጥቂቶች ከመድረሱ አንፃር አገልግሎቱ በሚገባ መድረስ አልቻለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገር ቤት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የሳተላይት ቴሌቭዥን ቤተ ክርስቲያን ልትጀምር ነው የሚል ዜና ሲነገር እና ተጀመረ ሲባል ማኅበረ ቅዱሳን ሁል ጊዜ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ባፈነገጠ መልኩ ላለመሄድ ለሚያደርገው ጥረት አንዱ በጎ መንገድ ስለሆነ በቴሌቭዥን ጣቢያው ላይ አገልግሎቱን በነፃ እንዲሰጥ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የቴሌቭዥን ጣቢያውን በበቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የተክኖሎጂ ግብዓት ለማሟላት ጠየቀ።ይህንን አስመልክቶ ሐራ ዘተዋህዶ ትናንት መስከረም 12፣2010 ዓም  ጉዳዩን አስመልክቶ በዘገበው ዘገባ ላይ ማኅበሩ ለምን ከአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት ለመግዛት እና በአማርኛ፣ኦሮምኛ እና ትግርኛ መርሃ ግብሩን ለመጀመር እንደተገደደ ገልጦ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ሲያስረዳ እንዲህ ማለቱን ፅፏል : -

ማኅበሩ፣ ከቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ውል በመግባትና የአየር ሰዓት በመግዛት ለማገልገል ብቻ ሳይኾን፤ ድርጅቱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ለማጠናከር በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄና ልመና አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ትምህርተ ወንጌልን በዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲያስፋፋ ሙሉ እውቅና በተሰጠው መተዳደርያ ደንቡ የተጣለበትን ሓላፊነት ለመወጣት ሌላ አማራጭ ለመፈለግ መገደዱን በዋና ጸሐፊው በኩል በሰጠው ምላሽ አስታውቋል....ፓትርያርኩም፣ ከቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት እንደማይሰጠውና ከሌላ አካል የአየር ሰዓት በመግዛት መጠቀም እንደሚችል፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቀረበላቸው ጥያቄ ቁርጥ ምላሽ የሰጡበት በመኾኑም፣ ደግሞ መጠየቁ አስፈላጊ ኾኖ እንዳላገኘው አስረድቷል''  ይላል።

ይህ ሁሉ ጉዳይ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው በኢትዮጵያ ከተቋማዊ አሰራር  መስፈን ይልቅ የግለሰቦች ወይንም ቡድሎች የግል ውሳኔ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቋማትን ምን ያህል እየገደለ መሆኑን እንመለከታለን።ማኅበረ ቅዱሳን የአየር ሰዓት ገዝቶ በአማርኛ፣ትግርኛ እና ኦሮምኛ መንፈሳዊ መርሃ ግብሩን ሲጀምር ቤሳ ቤስቲ ገንዘብ ከቤተ ክህነት ወስዶ ሳይሆን አባላቱ በሚያወጡት የገንዘብ ወጪ፣ነፃ የሰው ኃይል እና ምእመናን በጎ ፍቃድ ነው።ይህ በእራሱ ሊበረታታ እና ሊደገፍ የሚገባው ቅዱስ ተግባር ነበር። ሆኖም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ነችና በነፃ የማገልገል መብትህም በግለሰቦች እንደፈለገ ሊገታ ይችላል።ይህ ደግሞ ሌላ ችግር ማስከተሉ አይቀርም። እዚህ ላይ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ ከመሄድ አንፃር ሌላ ሚድያ ለምን አስፈለገ? ብለው የሚጠይቁ ሊኖሩ ይችላሉ። ጥያቄው በቅን እስከተነሳ ድረስ ጉዳዩን ከማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው የመተዳደርያ ደንብ ልክ እየሰራ መሆኑን ከመገንዘብ አንፃር መመልከት ያስፈልጋል። የቤተ ክህነቱ አቅም በሰው ኃይል አንፃር ውሱን ከመሆኑ አንፃር ማኅበሩ  በነፃ ለማገልገል ዕድል አልተሰጠውም።ይህ አልሆን ሲል በቤተ ክርስቲያን መዋቃር ስር ሆኖ በተሰጠው የአገልግሎት ደንብ መሰረት ስብከተ ወንጌልን በተገኘው ዘመናዊ መንገድ ለማሰራጨት አስቦ በጥረቱ በገዛው የቴሌቭዥን የአየር ሰዓትም እንዳያገለግል እገዳ ተጣለበት።ምናልባት የሚሰራጨው ስርጭት ላይ ኤዲቶርያል ቦርድ ከቤተ ክህነት እንዲጨመር እና ይዘቱ ሃይማኖታዊ መሰረቱን እንዳይለቅ እና የሚድያ ፖሊሲው ላይ ይህ ቢገባ ይህ ቢወጣ ማለት የቤተ ክህነቱ አባታዊ ድርሻ ነበር።ሆኖም ግን ስብከተ ወንጌል በቴሌቭዥን ' አታስተላልፉም አግጀዋለሁ ' የሚለው አገላለጥ ግን በእራሱ ሌላ አዲስ ችግር የመፍጠር አባዜ ተደርጎ መወሰድ አለበት። 

እንደ ኢትዮጵያ ላለች በሚልዮን የሚቆጠር ህዝቧ ሃይማኖትን የሁለንተናው መገለጫ ለሆነ ሕዝብ ከልዩነት እና እርስ በርስ በጎሳ ከመናቆር የመውጫው መንገድ አንዱ የጋራ እሴቱን ማለትም ሃይማኖቱን አክብሮ የመያዙ ፋይዳ ነው።በእዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና  በቀላሉ የሚታይ አይደለም።በተለይ በወጣቶች የተገነባው እና ለእሩብ ክፍለ ዘመን አገልግሎቱን በነፃ የሚሰጥ ማኅበር - ማኅበረ ቅዱሳን በሕዝብ መሀክል ሰላም፣እርቅ እና መግባባት እንዲኖር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም።በቅርቡ በአማርኛ፣ኦሮምኛ እና ትግርኛ የጀመረው መንፈሳዊ መርሃ ግብርም ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተለየ ሀገራችን ለገጠማት የመለያየት ችግር አንዱ እና አይነተኛ የእርስ በርስ መከባበር ፣መተሳሰብ እና ትልቅ ትስስር የመገለጫ መንገድ ተደርጎ መታየት ይገባው ነበር።ሲሆን ማኅበሩ የቤተ ክህነቱን የቴሌቭዥን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ በአደራ እንዲያስተዳድር እና ሕዝብን እንዲያስተምር ማድረግ  ይህ ካሳሳቸው ደግሞ የአየር ሰዓት ገዝቶ የሚያስተላልፈውን መርሃ ግብር አለማወክ ጤነኛ አስተሳሰብ ነው።


ከእዚህ በታች በአዲስ መልክ በአሌፍ ቴሌቭዥን የተጀመረው መርሃ ግብር ማስታወቂያ ቪድዮይመልከቱ።

ከእዚህ በታች ማኅበረ ቅዱሳን ነገ መስከረም 14፣2010 ዓም በሀገር ውስጥ እና በውጭ በምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጠው የተሃድሶ እንቅስቃሴ በተመለከተ አዘጋጅቶ ለምእመናን በነፃ ሊያድለው የተዘጋጀውን ቪድዮ ቅንጫቢ ይመልከቱ።

ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...