ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, April 5, 2013

የኢትዮጵያ የተቃዋሚ አንድነት ኃይሎችን ወደ አንድ ግንባርነት የሚወስዷቸው ግን የዘነጓቸው ሶስቱ ኃይሎችአሁን ያለንበት ጊዜ የ ኢትዮጵያ የትግል አቅጣጫ መቀየርያ (turning point) ላይ ያለን ይመስለኛል።ብዙ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አሉ።ሁሉም ግን የሳቷቸው ወይንም  ዋጋ ያልሰጧቸው ሶስት ኃይሎች ይታዩኛል። እነርሱም የዘውድ ምክር ቤት፣ የደርግ የሰራውትም ሆነ የምሁራን እምቅ ኃይል እና ወያኔን ትተው የወጡ ወደ አንድነት ትግሉ መቀላቀላቸውን ያወጁ የቀድሞ የወያኔ አባላት ናቸው።

 እነኝህ ኃይሎች ለዛሬዋም ሆነ ለነገዋ ኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው አንደምታ ቀላል አይደለም።በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ታሪክ አካል በበጎም ሆነ በክፉ ሆነዋልና።በሌላ በኩል የተቃዋሚ የአንድነት ኃይሎች በአብዛኛው የተመሰረቱበት አላማ (በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር)  ባለፈ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ክስተት ላይ መነሻ ያደረጉ ናቸው። ታሪክን በመማርያነት መጠቀም ጥሩ ነው በዛሬ ትውልድ ላይ ግን ስላለፈው መፍረድ ሌላ ጉዳይ ነው።በየትኛውም የአለም ክፍል የሚገኝ ሀገር በታሪኩ አሳዛኝም  ሆነ አስደሳችም ኩነቶችን ያልፋል።ያንን ግን ለዛሬው ክስተት እንደ እንቅፋት አይመለከትም።ይልቁን በጋራ የምያስማሙት ነጥቦች ብቻ ይተኮርባቸውና እነርሱን አጉልቶ ለነገ ማቀድ ነው ዋጋ የሚሰጠው።
 በ ኢትዮጵያ አንድነት በሚያምኑ ወገኖች (በብሄር እና በጎጥ መከፋፈልን በማይደግፉ ወገኖች  ዘንድ ሁሉ) የሚያስማሙ ነገሮች  አሉ።

ይሄውም-
- የወያኔን ዘረኛ መንግስት መጣል፣
- የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚጠብቅ መንግስት ማምጣት፣
- የእያንዳንዱ ግለሰብ መብት በሕግ ጥላ ስር ዋስትና ያገኘ እንዲሆን ማረግ፣
- ለእዚህም ኢትዮጵያዊ የሆነ የህዝቡን አንድነት፣ሉዓላዊነት እና ክብር የሚያከብር ነፃ የሚድያ ተቋም መኖር፣ 
- ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያነት ማስቀጠል እና 
- ባላት የሰው እና የተፈጥሮ ሀብት ሀገሪቱን ማበልፀግ የሚሉት እና የመሳሰሉት  የሚጠቀሱ ናቸው።

በአንጻሩ ወያኔ ከስልጣኑ የሚገፋውን ማንኛውንም ኃይል የሚዋጋበት ብቸኛ መንገድ የዘር ፖለቲካ ማራመድ ነው። የዘር ፖለቲካ በ አሁኗ ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ ካርድ ከመሆኑም በላይ ወያኔ ከስልጣኑ በላይ የሚመለከተው ነገር ስለሌለ እንጂ ጦሱ እንደማይቀርለት ይረዳዋል ባይረዳውም አይቀርም።ነገር ግን ስለ ሶስት ምክንያቶች የዘር ፖለቲካን ያራግባል።እነርሱም-

1- የሚያሳምንበት ምንም አይነት የርዮት አለም መመርያ  ስለሌለው፣

2- ከ አፈጣጠሩ ዘረኛ ተፈጥሮ ስላለው እና በጥላቻ ስላደገ እና 

2- በውስጡ የተሰገሰጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እጅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስልጣኑን  ስለሚዘውሩትም ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የአንድነት ኃይሎች አዲስ ራዕይ አስፈላጊነት


የፖለቲካ ድርጅቶች አዲስ ራእይ ይዘው መቅረብ የመቻል እና ትግሉን በዘለቄታ ለመምራት  መሰረታዊውን  የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይን ትልቅ ራዕይ አድርገው ሊያነሱት የሚገባ ኃይል መሆኑን አሁንም መረዳት ተገቢ ነው። ይህንንማ ብዙ አመት ተቃዋሚዎች ሲናገሩት የኖሩት አይደለም እንዴ ? የሚል ጠያቂ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ።ነገር ግን እኔ እንደምረዳው ከፕሮግራሙ ባለፈ የስልታዊ አፈፃፀም መሰረታዊ ችግር በአንድነት ኃሎች በኩል ይስተዋላል። 

ወያኔ በቀደሙ የታሪክ ሂደቶች ላይ ቀድሞ የሰራው ፕሮፓጋንዳ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ላይ በእራሱ የ ስነልቦና ችግር ፈጥሮባቸዋል። ለምሳሌ የተቃዋሚ የአንድነት ኃይሎች ስለ ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ እና ስለ ደርግ በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ስለነበራቸውን አስተሳሰብ እና ለአሁኑ ትውልድ ሊያስተምሩ የሚችሉ ተግባራት ላይ ማተኮራቸው የሚያስከፉት የህብረተሰብ ክፍል ይኖራል ብለው ስለሚያስቡ ባለፉ ታላላቅ ነገር ግን አሁን ሊያስማሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማውራት ያፍራሉ። በመሆኑም የወያኔን ግፍ እና አደጋ በማውራት(ማውራቱ ተገቢ ቢሆንም) ብዙ ገለፃቸውን ያጠፋሉ። ወያኔ ግን አሁን ከሚያደርገው ሥራ የበለጠ አደጋው ባለፈ የሀገሪቱ ታሪክ ላይ ያልተስማማ የባዕድ አስተሳሰብ ይዞ የመጣ ለኢትዮጵያ ህዝብም  እንግዳ ለሕዝቡ ባዳ የሆነ የታሪክ ቀረፃ ላይ መሆኑን ይዘነጉታል።

በመጀመርያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ጋር የማይስማማው አሁን ባለው የወያኔ አፋኝ ስርዓት ብቻ አደለም ወያኔ ኢትዮጵያን አፍርሶ በሚፈልገው ድቡሽት ፅንሰ ሃሳቡ ላይ ኢትዮጵያን ሊሰራት የሚታትር ''ደፋርም'' ስለሆነ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የዛሬ ድልድይ እና መንገድ መሰራት ጉዳይ አይደለም። የተሰራውም ሆነ ወደፊት የሚሰራው ሥራ ሁሉ ለመጪው ትውልድ የመቆየቱ እና አስተማማኝ አብሮ የመኖር ዋስትናውን ነው ጉዳዬ ነው ፋይዳዬ ነው የሚለው።ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው። የዕለት ከዕለት ጉርሻውን እያመሰገነ የሚኖር እንስሳዊ ባህሪ ሰው ከፈጣሪው ገና አልታደለም(መታደል ባይሆንም)።

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ የመሆን እና የተቋማዊ ህብረት ብቻውን ኢትዮጵያን አይሰራትም።በታሪካዊ ሁነቶች ላይ የመነጋገር ባለፉ ስህተቶች መንቀስ እና ለሀገር አንድነት፣ለሕዝብ ልዕልና እና እድገት ለተሰሩ ስራዎች እና ለሰሩት  ግለሰቦች ዋጋ በመስጠት ግን የህዝብን አንድነት ማምጣት እና ወያኔን ባዶ ማስቀረት ይቻላል።

 የኢትዮጵያ የተቃዋሚ አንድነት ኃይሎች እንዴት ያስቡ?


በመጀመርያ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም  ሆነ ለኢትዮጵያ እሰራለሁ የሀገሬ  ጉዳይ ያሳስበኛል ያለ ዜጋ በሙሉ  ሶስት ነገሮችን መመርያው ማድረግ አለበት።እነርሱም-

1ኛ/ የአርበኝነት(patriotic feeling) ስሜት ማስፈን

  
አርበኛ (patriotic) የሚለው ቃል ለጦር ሜዳ ውሎ የተሰጠ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ለሀገራቸው ካለ አንዳች ዋጋ፣ዝና መፈለግ እና የግል ስሜትን ውጦ ለጋራ እና ለሀገር በነፃ የመስራት ክቡር ተግባር ነው።

ለሀገሩ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ግዴታው ስለሆነ ብቻ እንደሚያደርግ ማሰብ እና ነገ በምትኖረው ኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ዜጋ በሕግ ጥላ ስር ዋስትና ማግኘትን፣የኢትዮጵያ ሉአላዊነት እና አንድነት የመከበርን ፋይዳ እንጂ  ለግሉ ከነፃነት በኃላ ባገኘው የስራ መስክ ለመስራት እና በነፃነት ለመሞት ብቻ ማለም ማለት ነው። 

ነገ ኢትዮጵያ በተሻለ ደረጃ ስትሆን የአርበኛ ስሜት የተጋራ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ዜጋ በጥረቱ ብቻ ለመስራት ዛሬ ላይ ሆኖ የወሰነ ሊሆን ይገባል። ብዙ ችግሮች በተለይ በ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል በሚሉ  ዘንድ የሚስተዋለው ነገ ዛሬ ላደረጉት ተግባር እንዲከፈል የመፈለግ እና ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሂደቶች ናቸው። ይህ ሁሉንም ይመለከታል ባልልም ሆኖም ግን አንዳንዴ አከራካሪ ሆነው የሚቀርቡት ነጥቦች ለምሳሌ ''እኛ ከእዚህ አመት ጀምሮ ስንታገል፣እንዲህ አድርገን፣ይሄን ፈጥረን '' ወዘተ የሚሉ መግለጫዎች ከአሁኑ ትግል ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ወደፊት ምናልባት አዲስ አበባ ሲገቡ ትልቅ ሙዜም ሰርተው ሊያስቀምጡት የሚገባውን ጉዳይ ከመሆን ባለፈ ዛሬ ከሌላው ጋር የመጋጫ ነጥብ አድርጎ ማቅረብ ከሞራል የወረደ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ምድር ያልተፈጠሩም ያስመስላል።በመሆኑም በመጀመርያ የአርበኝነት ስሜት (ዋጋ የማይጠየቅበት ሥራ) ማስፈን ተገቢ ነው።

2ኛ/ ኢትዮጵያን እንደሀገር በሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ መጀመርያ መስማማት።

ኢትዮጵያን የማዳን ሥራ ላይ የሚያስብ ድርጅትም ሆነ ተፅኖ ፈጣሪ ግለሰብ ወይንም ቡድን በመሰራታዊው የ ኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ፣በሕዝቡ ህብረት፣በሕግ የበላይነት የሚያምን ወይንም ለማመን ዝግጁ ነኝ ካለ ማንኛውም አካል ጋር (ከድያብሎስ በስተቀር እርሱ ቃሉ ስለማይታመን) አብሮ ለ መስራት መዘጋጀት አለበት።
እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን በ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ሶስት የታሪክ አካላት ወሳኝ ሆነው ላለፉት አንድ መቶ --/ . . . አመታት ዘልቀዋል። 
. የዘውድ ስርዓት፣ 
. የደርግ ስርዓት  እና 
. አሁን ስልጣን ላይ ያለው የወያኔ ስርዓት ናቸው። 

በሶስቱም ስርዓቶች ውስጥ ዛሬ የምንጮህለት የኢትዮጵያ አንድነት እና የ ዲሞክራሲ ሂደት የሚደግፉ ለትግሉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው ኃይሎች አሉ።ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስም ስለተሰጣቸው የሚሰማቸውም ሆነ ከፍተኛ ልምዳቸውን የሚጠቀም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ቡድን የለም። ይልቁን ካለፈ የታሪክ ሂደት ጋር የእራሱን ስም የሚያጎድፍ ስለሚመስለው እና በተለይ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ (በሁሉም ላይ የከፈተው የማጥላላት ዘመቻው) በከፊል ስለተሳካለት እነኚህን የታሪክ አካላት ዛሬ ድረስ የሚያፍሯቸው በዝተው ወያኔ ግን ለግሉ እንዲጠቀምባቸው ተትቶለታል።

በሶስት የታሪክ ሁነቶች የተፈጠሩት ኃይሎች የማቀናጀቱ ሥራ ወያኔን በ አጭር ጊዜ ያፍረከርከዋል

በኢትዮጵያ ሕዝብ አስተሳሰብም ሆነ የፖለቲካ መድረክ ላይ በሶስት የታሪክ ሁነቶች የተፈጠሩት ኃይሎች ማለትም የዘውድ መንግስት፣የደርግ ኃይል እና ከወያኔ ያፈነገጡ (የኢትዮጵያን አንድነት ዘግይተውም ቢሆን ያመኑ) ኃይሎችን የማቀናጀቱ ሥራ ወያኔን በ አጭር ጊዜ ያፍረከርከዋል። የኢትዮጵያንም ትንሣኤ ያመጣል።አሁን ማሰብ የሚገባው በፓርቲ እና በድርጅት ስሜት መሆን እንደማይገባው ነገር ግን በአርበኝነት (patriotic) ስሜት መሆን እንዳለበት ከላይ ለመግለፅ ሞክርያለሁ።የአርበኝነት ስሜት ሲባል ደግሞ በስሙ የተደራጁ ድርጅቶችን(እንደ አርበኞች ግንባርን) መጥቀሴ ሳይሆን የቃሉን ለሀገራዊ ፍቅር ካለአንዳች ዋጋ የሚስራ ሥራን ለመግለጫነት መጠቀሜን ልብ ይባልልኝ ። የአርበኝነት ስሜት መለክያዎቹ ኢትዮጵያዊነት እና የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆን ብቻ ናቸው። አባቶቻችን ኢትዮጵያን የጠበቁት ደሞዝ ይከፈለኝ፣ዋጋ ይሰጠኝ፣ዝና ላትርፍበት ብለው ሳይሆን ካለዋጋ ከልብ በመነጨ ሃገራዊ ፍቅር ብቻ ነው። 
ለእዚህም ነው ከላይ የጠቀሱት ሶስቱ ኃይሉችን   ቢያንስ በሶስት ጉዳዮች ላይ የሚያስታርቁ ነጥቦች ላይ እስከተስማሙ ድረስ የኢትዮጵያን የማዳን ተግባር አካል አድርጎ የመስራት ሥራ አስፈላጊ የሚያደርገው። እነርሱም-

1/ በኢትዮጵያ ባለፈ በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ ታሪኮች፣

2/ በ ኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ እና 

3/ ዜጎች በዘር እና በቋንቋ ሳይሆን በሰውነታቸው ብቻ በሕግ ጥላ የመጠ በቃቸው ሂደት የሚሉት ናቸው።

ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ

ይህ ማለት በዲሞክራስያዊ ዘውድ መንግስት የሚያምኑም ሆኑ በደርግ ስርዓት ውስጥ ለኢትዮጵያ አንድነት የታገሉ የጦር ሰራዊት፣ ምሁራን ወዘት እንዲሁም የወያኔን ስርዓት አላማ የተቃወሙ የቀድሞ የድርጅቱ አባላት ሁሉ ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ነጥቦች እስካመኑ ድረስ ለአንድነት ትግሉ አስተዋፅኦ የማያደርጉበት ምንም ምክንያት የለም። ይህ ግን በአንድነት ኃይሎች አንፃር ያለፈ ታሪክን እየመዘዙ እንደወያኔ መውቀስ አቁመው አሁን አንገብጋቢው ጥያቄ ሀገር ን የማዳን ብቻ እና ብቻ መሆኑን ማመን ይገባቸዋል።በእዚህ ስሜት ሕዝቡን በሙሉ ለማግኘትም ሆነ ከጎሰኝነት የፀዳ በኢትዮጵያዊነት ርዕዮት ላይ የተመሰረተ ህብረት መፍጠር ይቻላል።
ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም 


የደርግ ከፍተኛ አባላት በፍርድ ቤት ውስጥ

''የኢትዮጵያ ችግር እግሩ ሀገርቤት ቢሆንም እራሱ ግን ከውጭ አለ'

እዚህ ላይ ''የኢትዮጵያ ችግር እግሩ ሀገርቤት ቢሆንም እራሱ ግን ከውጭ አለ'' የሚለውን አባባል ማጣጣል አይገባም።ከጉያችን የወጡ በዘር እና በሃይማኖት ለመከፋፈል ይታትሩ  እንጂ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በኢትዮጵያ ላይ ስትራተጃዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ብሎም እንደሀገር እንዳትቆም የሚተጉ ባእዳን ግለሰቦችም ሆኑ ሃገራት መኖራቸው ከእግዚአብሔር የተሰጠን ፀጋ ነው። ይህ ነው ባለፈ ታሪክ ኩነቶችን ትተን ኢትዮጵያን የማቆም ሥራ ላይ የማተኮር በደቂቃዎች የሚቆጠሩ ጊዜዎች እንዲኖሩን የሚያደርጉን።አዲሱ ትውልድም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የምፈልገው ይህንን ነው።በ1997 ዓም  የቅንጅትን ህብረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉበሙሉ ደግፎ የቆመው ከላይ የተጠቀሱት ስጋቶች በኢትዮጵያ በር ላይ መቆማቸውን ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነው።
ይህ ማለት በቆየ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው ከደርግ ጋር ልሰራ? ከቀድሙ የንጉሡ አስተሳሰብ ጋር ልሰራ? ወይንም ህዋሃትን ከመሰረቱት ከ እነ ገብረመድህን ጋር ልሰራ? እያሉ ለሚናገሩ  መልሱ  ኢትዮጵያን የማዳኛው ጊዜ ካለፈ በኃላ  ስሟን የሚጠሯት ሀገር እንደማይኖራቸው ለመንገር ምሁር መሆን አለመጠየቁን ነው።

ይህንን ሃገራዊ ህብረት ከድርጅታዊ ፍቅር በተለየ የአርበኘነት ስሜት(patriotic feeling) የተላበሰ ኃይል ለመፍጠር ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት እና ለ አመታት የያዙትን አሰራር የመፈተሽ ብሎም ስልትን የማስተካከል ሥራ ይጠይቃል።እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን የአንድነት ኃይሎች ሁሉን ያቀፈ መሰረት ላይ ያለፉ ኩነቶችን ቢያነሱም ወያኔ ግን ከላይ ከተጠቀሱት ኃይላት ጋር በ ፖለቲካ አካልነት ሳያስገባ ግን  ከአጠገቡ ባለማራቅ እየተጠቀመባቸው ነው። ሚስጥሩ ያለውም እዚህ ላይ ነው።
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ (የህወሓት መስራች ወያኔን በመቃወም በስደት የሚኖሩ)

ይሄውም የዲሞክራስያዊ  ዘውድ ተዋናዮች የንጉሳውያን ቤተሰቦችን በሀገርቤት አንዳንድ ንብረቶችን ለምሳሌ እንደ ዋቢሸበሌ ሆቴል፣ወዘተ በመመለስ እያባበለ ትንፋሻቸውን ያዳምጣል አልያም በአንዳንዶች ዘንድ ''ደጉ'' ተብሎ እንዲጠራ ይታትራል።የደርግ ባለስልጣናትን ደግሞ  ''በዘር ማጥፋት ወንጀል'' ከሰስኩ ብሎ ቆይቶ ግን ሁሉንም በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ፈቷል።ይህ ብቻ አይደለም በ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ የቀድሞ ጦር መኮንንኖችን በአማካሪነት ተጠቅሞ መልሶ አባሯል። በሶስተኛ ደረጃ ከድርጅቱ አፈንግጠው የወጡትን እንደእነ ስዬ አብርሃ ያሉትን ከሀገር ወጥተው የበለጠ ችግር እንዳይፈጥሩ ከስሩ አድርጎ የማይሞት የማይሽር አይነት የተቃዋሚ ድርጅት እንዲመሰርቱ ፈቅዶ ሞታቸውን እየጠበቀ ነው። 
ባጠቃላይ ወያኔ እንዲህ እያደረገ ነው። የአንድነት ኃይሎች ግን የተለያየ ስም እየሰጡ የትግሉ አጋር አድርገው ወደ ሃገራዊ ህብረት ለመምጣት ቀድሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካን በዘውድም፣በደርግም ሆነ በወያኔ ስር ሆነው የተረዱትን ልምድ መቀበል (ታሪክን ለታሪክ ሰዎች ትቶ) በአዲስ መንፈስ የመነሳት ጥያቄ ከፊት ለፊት ፈጦ  መጥቷል። 
ኦነግ በብዙ አመት ቆይታው ወደ ኢትዮጵያዊነት ስሜት መጥቶ ''ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር እንፈልጋለን'' (ለ ሩህ መፅሄት 1984ዓም አቶ ሌንጮ የሰጡትን መግለጫ ያስተውሉ) ያሉት የድርጅቱ አንጋፋ መስራች አቶ ሌንጮ ''በኢትዮጵያዊነት ስር ሆነን የሁሉም ችግር ሲፈታ ነው የ እኛም ችግር የሚፈታው'' ባሉበት ዘመን የደርግ፣የዘውድ እና የቀድሞ የወያኔ ባለስልጣን መባባል ለቃሉ ይቅርታ እየጠየቅሁ ''የፖለቲካ ጅልነት'' ሆኖ ይሰማኛል። 

ለመደምደምያ

ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄው ካለፈው ስህተት ተምሮ ባለፈው የታሪክ ስህተት ተፀፅቶ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ከዘረኞች እና ሉዓላዊነቷን ከሚፈታተኗት ባዕዳን ማዳን ነው ፈታኙ ጥያቄ።ስለሆነም  ማንም ቢሆን ማን  ኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያምም ሆኑ የቀድሞው ንጉስ ልጅ ልዑል ኤርምያስ አልያም  የቀድሞው የህወሓት መስራች አቶ ገብረመድህን አርአያ የትግሉ አካል ማድረግ ማክበር እና ወደ አርበኝነት(patriotic) ስሜት ውስጥ  መግባት ከፖለቲካ ድርጅቶችም፣ከተፅኖ ፈጣሪ  ግለሰቦችም ሆነ ከመገናኛ ብዙሃንም የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ መፈራራትን ትቶ ኢትዮጵያን የማንሳቱ ስራን በብልህነት እና በማስተዋል መከወን ያለበት ጊዜ ይመስለኛል። ይህም  ጊዜ የማይሰጠው አዲስ የአስተሳሰብ ለውጥ ውስጥ የመግቢያው የለውጥ ነጥብ (turning point) ላይ መሆናችንን ልብ ማለት ይገባል።የፖለቲካ አስገራሚ ክስተቱም ይህ ነው አይገናኙም የተባሉ ተገናኝተው አንድ ሆነው ለአንድ ግብ ሲሰሩ መመልከት በእኛ አልተጀመረም ያውም ኢትዮጵያን ያክል ሀገር ይዘን።በሉ የአንድነት ኃይሎች ታምር ሰርታችሁ አሳዩን።እየተበቅናችሁ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አበቃሁ

ጌታቸው በቀለ 

ኦስሎ 

ኖርዌይ 

1 comment:

Anonymous said...

This is a good document