ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, May 24, 2016

ማኅበራዊ እሴት እንደ አገር እንድንኖር ካደረጉን ነገሮች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛ መሆኑን በኦስሎ የተደረገ ስብስባ ላይ ተገለጠ (ጉዳያችን ዜና)

የስብሰባው ማስታወቂያ 

በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ሚያዝያ 29፣2008 ዓም ባባተሪ አዳራሽ በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ አዘጋጅነት በማኅበራዊ እሴት ላይ ያተኮረ ትምህርታዊ  ውይይት ተደርጎ ነበር።በውይይቱ  ላይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዙፋንን ጨምሮ ሌሎች ምሁራን እና በኦስሎ እና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

የውይይቱ መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት የመርሃ ግብሩ መሪ የስብሰባው አላማዎች ማህበራዊ እሴት ምንነትን ማሳወቅ፣እንደ ሕብረተሰብ እና እንደ አገር ያለንበትን ደረጃ ማጤን እና ለመፍትሄው ያለንን ድርሻ መለየት መሆኑ ገልጦ ማሕበራዊ እሴት በሰዎች መካከል እና በማህበራዊ ተቋማት መካከል እና ግለሰቦችም ከእነኝህ ማህበራዊ ተቋማት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሁሉ መሆኑን እና የእዚህ ሁሉ ትልቁ ዋጋ መተማመን መሆኑን አብራርቷል።

በመቀጠልም  በማኅበራዊ እሴት ዙርያ ፅሁፎችን ይዘው የቀረቡትን ሶስት እንግዶች ወደ መድረኩ ጋብዟል።

ፅሁፎች ይዘው የቀረቡት: 

1ኛ/ ወ/ሮ ዙፋን አማረ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር፣ 

2ኛ/ አቶ እንግዳሸት ታደሰ የኖርወጅኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት መፅሐፍ አዘጋጅ እና 

3ኛ/ አቶ አጥናፉ ወ/ማርያም በኖርዌይ አገር ከ24 አመታት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ እና አሁንም እያገለገሉ ያሉ ናቸው።

በመጀመርያ ፅሁፋቸውን ያቀረቡት ወ/ሮ ዙፋን ሲሆኑ የእርሳቸው ፅሁፍ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነበር።ይሄውም: 
- ሀብት በእራሱ ሁለት አይነት መሆኑን እርሱም ሙት ሀብት ወይንም ፍሬ የማያፈራ እና ትርፍ የሌለው እና ሕይወት ያለው እና ፍሬ የሚያፈራ መሆኑን፣
- ሕይወት ያለው ወይንም ፍሬ የሚያፈራ ከሚባለው ውስጥ ማሕበራዊ እሴት አንዱ መሆኑን፣
- ማኅበራዊ እሴት ከሌላው የሚለየው የጋራ መሆኑ እንደሆነ፣
- አስፈላጊነቱ ለጋራ መተማመን፣ስነ ምግባር እና ማሕበራዊ ትስስሮች መሆኑን፣
- ማኅበራዊ እሴት የማይዳሰስ ሀብት እና ከተንከባከብነው እየዳበረ የሚሄድ መሆኑን፣
- ማህበራዊ እሴት በጥርጣሬ በተሞላ መንፈስ ለማስኬድ ከተሞከረ ደግሞ እየቀጨጨ የሚሄድ እና በኃላ አገርንም አደጋ ላይ የሚጥል ደረጃ እንደሚያደርስ ገልጠዋል።

በመቀጠል አቶ እንግዳሸት ታደሰ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል። እነርሱም: 
- ማኅበራዊ ካፒታል ማለት የማኅበረሰብ የባህል ካፒታል (ፋይናንሻል ያልሆነ) ለምሳሌ አመጋገብ፣ትምህርት፣አለባበስ ሁሉ ላይ እንደሚቀለጥ፣
- የቋንቋ አጠቃቀም አስፈላጊነትን በ1916 ዓም ወደ አውሮፓ የሚመጣ ተማሪ ይሰጠው የነበረው ዝርዝር መረጃ አብራርተዋል፣
- የእድር አስፈላጊነት እና በተለይ በውጭ አገር ለሚኖሩ  ኢትዮጵያውያንም ያለውን ፋይዳ ከኦስሎ አንፃር  በማገናዘብ አቅርበዋል፣
- ከሃይማኖት ተቋማት አንፃር እና አሁንም በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ አንፃር በምሳሌ አስረድተዋል።

በመጨረሻም አቶ አጥናፉ ወ/ማርያም በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል።እነርሱም:

- ትምህርት ከማህበራዊ እሴት አንፃር ያለው አስተዋፅኦ፣
- በተለይ ትምህርት ምን ያህል አንድን ማህበረሰብ እንደሚቀይር ሲያስረዱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ''መጪው የዓለም ዕድል የሚወሰነው  በተማሩ ሰዎች ነው'' የሚለውን አባባል በመጥቀስ ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል፣
- ከኖርዌይ የትምህርት ፖሊሲ አንፃር እንዴት አንድ ሕብረተሰብ እንደሚገነባ በዝርዝር ገልፀዋል፣
- ከኖርዌይ ጋር በማነፃፀር በኢትዮጵያ ያለው አምባገነናዊ ስርዓት ምን ያህል በትምህርት ላይ ውድቀት እንዳደረሰ እና  ተከትሎ የመጣው የትውልድ ክስረት ከቀድሞ የመምህራን ማኅበር ትግል ጋር እያነፃፀሩ አብራርተዋል፣
- በምሳሌነት የሂሳብ ትምህርትን አንስተው በኖርዌይ የሂሳብ ትምህርት ለበርካታ ጊዜ መሻሻሉን እና አሁን ሂሳብ ለማህበራዊ ትምህርት፣ሂሳብ ለተፈጥሮ ሳይንስ ወዘተ በሚል መሰጠት መጀመሩን አውስተው የኢትዮጵያ ትምህርት ለዘመናት መሻሻል የሌለው እና በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ አለመሰራቱ በማህበራዊ እሴት  ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅኖ አብራርተዋል።

በመቀጠለም የሻይ እረፍት ከተደረገ በኃላ የጥያቄ እና አስተያየት የመስጠት ጊዜ ተሰጥቶ በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ጥያቄ እና አስተያየቶች ተሰጥተዋል።በተሰጡት አስተያየቶች ላይም :

- ማሕበራዊ እሴት ለኢትዮጵያ የመኖር እና አለመኖር ጉዳይ ወሳኝ የመሆኑን ፋይዳ፣
- በቀደመ ታሪካችንም እድር፣እቁብ፣የቤተዘመድ ማህበር፣ የመሳሰሉት ሁሉ ሕዝብ አብሮ እንዲኖር ያደረጉ  የማኅበራዊ ቋማት መሆናቸው እና አሁን ያሉበት ሁኔታ እየመነመነ መሆኑ፣
- ለእዚህም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት እነኝህ ማሕበራዊ ቋማትን ሆን ብሎ የማዳከም ሥራ እንደሚሰራ እና በምሳሌነትም በእድሮች ላይ ያለው ማዋከብ እና የመቆጣጠር ተግባር ተጠቅሷል፣
- የሃይማኖት ቋማት እውነቱን የመናገር እና ስለ አገር የመጮህ፣ድሃ ተበደለ ፍትህ ጠፋ ብለው የመናገር ድፍረት አስፈላጊነት ተወስቷል።

በመጨረሻም የመድረክ መሪው የማጠቃለያ ሃሳቦች ሰጥቶ በቀጣይ ጊዜ ውይይቱ በስፋት እና በጥልቀት በኢትዮጵያውያን የጋራ መወያያ መድረክ የሚቀርብ መሆኑ ተገልጦ በዕለቱ ለተገኙት እንግዶች እና ተሳታፊዎች ከፍ ያለ ምስጋና ቀርቧል።ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com 

No comments: