ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 5, 2016

ጀግናው አርበኛ ኮ/ል አብዲሳ አጋ የቦሌ ቅዱስ ሚካኤልን ታቦት ካስተከሉ አባቶች ውስጥ አንዱ ናቸው።እውነተኛ ታሪክ (የጉዳያችን ማስታወሻ - Gudayachn Exclusive)

ኮ/ል አብዲሳ አጋ 
ከጌታቸው በቀለ  

የኮ/ል አብዲሳ አጋ ሃውልት አዲስ አበባ ላይ ባለመቆሙ ሁል ጊዜ ይፀፅተኛል።የኮ/ል አብዲሳ ቤት እኔ አዲስ አበባ ካደኩበት ቤት ቅርብ ስለነበር እና አባቴ ደግሞ አርበኛው ከእዚህ ዓለም ሳያርፉ በጣም ያውቃቸው ስለነበር  ስለ እርሳቸው ብዙ እንዳውቅ እና ትልቅ ክብር እንዲኖረኝ አድርጎኛል።በልጅነቴ ፀበል ቅመሱ ወይንም ሌላ መልዕክት ተልኬ እቤታቸው ስሄድ የኮ/ል አብዲሳ ባለቤት ብዙ ጊዜ ሰፊው ግቢያቸው ላይ በተንጣለለው ቤት በረንዳ ላይ ሆነው አገኛቸዋለሁ። ስለ አባቴ እና  ቤተሰቡ ደህንነት ከጠየቁኝ በኃላ ነው የመጣሁበትን ጉዳይ የሚጠይቁኝ።ከግቢያቸው ጎን ያለው ወፍጮቤትም አንዱ በኮ/ል አብዲሳ በር በኩል የሚያመላልሰን ሌላው ምክንያት ነበር።

የግቢውን የብረት በር አልፌ ስገባ ውሻቸው ለአመል ያህል በታሰረበት ሲጮህ ትዝ ይለኛል። ከሁሉ ትዝ የሚለኝ የኮ/ል አብዲሳ አጋ ወንድ ልጃቸው ነው።ስሙ  ዲያቆን ሳሙኤል ይባላል (የፊቱ ቅላት አሁን ድረስ አይረሳኝም) ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በትርፍ ጊዜው ይቀድስ ነበር። በተለይ በፆመ ፍልሰታ ወቅት በአባታችን ቭኦልስ መኪና ውስጥ ሆነን እቤታቸው ድረስ አብሮን ይመጣ ነበር።አባቴ ስለ ኮ/ል አብዲሳ አጋ አውርቶ አይጠግብም። ቦሌ መንገድ የሚገኘው ወሎ ሰፈር ላይ ከአባቴ ጋር ድሮ ቤት ሲሰሩ አንድ ላይ ነው የሰሩት።ኮ/ል አብዲሳ ቤቱም መሬቱም በንጉሡ እንደተሰጣቸው ሰምቻለሁ።ኮ/ል አብዲሳ ቤት ሳሎን ስትገቡ (እኔ ስለገባሁ በኩራት አወራለሁ) የኮ/ል አብዲሳ በወታደራዊ ማዕረግ የተንቆጠቆጠ የቁም ፎቶ እና በአርበኝነት የነበሩበት ፎቶ ይገኛል።በመካከል ደግሞ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ፎቶ ተሰቅሏል።
ኮ/ል አብዲሳ አጋ ከክብር  ኒሻን ጋር 

ሌላው የማውቀው ጉዳይ ደግሞ ቦሌ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ካስተከሉት አባቶች ውስጥ አንዱ ጀግናው ኮ/ል አብዲሳ አጋ እንደ ነበሩ ነው።በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኑ ሊሰራ የታሰበው ወሎ ሰፈር ፊት ለፊት (ካራማራ ሆቴል የነበረበት ፊት ለፊት) የሚገኘው ሜዳ ላይ ነበር።ይህ  ቦታ እስከ ቦሌ ማተምያ ቤት ማዶ ያለው ቦታ  የራስ ብሩ ቦታ  ይባል ነበር አሉ።ቀድሞ እዚህ ቦታ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ነበር። ጣልያን ነው ያቃጠለው ሲሉ አባቶች ነግረውኛል።ቦታውም ላይ ታቦት የነበረበት ቅዱስ ቦታ ትቼ አልሄድም ብለው የሚኖሩ መነኩሴ ነበሩ።ስለሆነም ቦታው ''የአባ ሜዳ'' ተባለ።ኢህአዴግ መጥቶ ቦታው ላይ ህንፃ እስኪሰራ ድረስ ቦታው 'አባ' አንዳንዴ በልማድ 'አባይ ሜዳ'  ይባል ነበር።እዚህ ቦታ ላይ ነበር ኮ/ል አብዲሳ የሰበካ አባል የነበሩበት የቦሌ ሚካኤል ታቦት ሊተከል የታሰበው።በኃላ ግን  በምክር እንደ ገዳም ይሁን ተብሎ ያን ጊዜ የነበረውን ጫካ አልፈው አሁን ካለበት ቦታ ተተከለ።

ይህ ቀድሞ አባ ሜዳ የተባለው ቦታ ላይ የአካባቢው ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን ሊሰራ በኢህአዴግ ዘመን 1987 ዓም ከ10 ሺህ ሕዝብ በላይ ፍርም ፈርሞ (እራሴም ነበርኩበት) ለአቡነ ጳውሎስ ማመልከቻ አስገባ።አቡኑም ደብዳቤ ለማዘጋጃ ቤት በወቅቱ ለነበሩት ተፈራ ዋልዋ ፃፉ።አንድ ወቅትም ወርደው ቦታውን አዩት።የራስ ብሩ የልጅ ልጅ የነበሩት (አሁን አርፈዋል) ወ/ሮ በልዩ ቦታው የአያታቸው በነበረ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት እንደነበረበት በፅሁፍ መሰከሩ።ማዘጋጃ ቦታውን ምልክት አደረገ።ካርታ ክፍል ተመራ። ጉዳዩን የሚከታተሉት አባቶች ጋር ቦታው ላይ ተከታታይ እሁዶች ፀሎት ተደረገ።በመካከል አሊ አብዶ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነ።ፋይሉ ተደበቀ።ሕዝብ ጮሆ ቢናገር የሚሰማው አጣ። አሊ አብዶ ካርታ ለቤተ ክርስቲያንነት ካርታ የተሰራለትን ቦታ ለልማት በሚል ህንፃ እንዲሰራ አደረገ።አሁንም ግን ወንዙ ተጠግቶ የቤተ ክርስቲያኑ ቦታ አለ።የፍትህ ያለህ እያለ።ለሁሉም ኮ/ል አብዲሳ አጋ ሊያስተክሉበት የነበረበት ቦታ ታሪክ ይህን ይመስላል።ለኮ/ል አብዲሳ ግን ሃውልት ያስፈልጋቸዋል።የሁላችንም ታሪክ የሆነ ያውም በጣልያን ምድር ላይ ሠርተዋልና።ዛሬ ዛሬ የኮ/ል አብዲሳን ቤተሰብ እና ስለ እርሳቸውም የቀረበ ግንዛቤ ሳይኖረው በጎሳ ስሜት እየተነዳ የሚፅፍ ሰው ፅሁፍ ስመለከት በጣም ያንስብኛል።

በነገራችን ላይ ወሎ ሰፈር የሚገኘው በንጉሡ የተበረከተላቸው የኮ/ል አብዲሳ አጋ ቦታ በኢህአዴግ የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ቦታው ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ተነስተዋል።ድሮም ስርዓቱ ስለ ብሔር ይዘፍናል እንጂ አርበኛ ማክበር አልፈጠረበትም።ዛሬ 75ኛው የድል ቀን ሲዘከር ኮ/ል አብዲሳ አጋን ማንሳት ተገቢ ነው።ክብር በክብር እንድንቆም ላደረጉን አርበኞቻችን።

ከእዚህ በታች ከድረ ገፅ ስለ ጀግናው አርበኛ ኮ/ል አብዲሳ አጋ የተገኘውን ታሪክ እንደሚከተለው ይቀርባል 

አብዲሳ አጋ ጣልያን በአድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ባደረገው የ1928ዓ.ም ወረራ ወቅትበምርኮኝነት ጣልያን ተወስዶ ከታሰረ በኋላ የተሰጠውንብርድልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል ማምለጡ ጎልቶ የሚወሳለት አርበኛ ነበር። ተሳክቶለት ቢያመልጥ እንግዳ የሆነ አገር እንደሚቀላቀል እና ለሃገሩም እሩቅ መሆኑን እያወቀ እንኳን ነጻነቱን አሳልፎላለመስጠት በሚል ብልጠት በታከለበት ሁኔታ ያመለጠው አብዲሳ አጋ አስገራሚ ጀግንነቱን ያሳየው ከእስር ቤቱካመለጠ በኋላ ነበር።በኦሮሚያ ወለጋ የተወለደው አብዲሳ የኢትዮጲያን ጦር የተቀላቀለው በ14 አመቱ ሲሆን ጣልያን ኢትዮጲያን ስትወር አገሩን ለመከላከል በውጊያ ላይ በአስደናቂ ወኔ ይዋጋ ነበር። በውጊያ ከተማረከ በኋላ ጣልያኖች አገራቸው ወስደው በሲሲሊ ደሴት ላይ ባሰሩት ግዜ ነበር አብሮት የታሰረውን የዩጎዝላቪያ ምርኮኛ ሁሊዮ የተወዳጀው። በጋራ እቅድ ካወጡ በኋላ ከእስር ቤት ያመለጡት እነ አብዲሳ በሲሲሊ ደሴት ላይ ተደብቀውአልተቀመጡም። ካመለጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ በአብዲሳ መሪነት እና እቅድ አውጪነት በሌሊት ታስረው ወደነበረበት እስር ቤት በመሄድ እና ጥቃት በመፈጸም የታሰሩትን እስረኞች ነጻ በማውጣት የኢትዮጲያውያንን ጀግንነት በአድዋ ብቻ ሳይሆን በጣልያን ምድርም ያስመሰከረ ድንቅ ተዋጊ ነበር። 

የአብዲሳ ጀግንነት በዚህ አላበቃም ከእስር ቤት ያስመለጧቸውን ሰዎች በማሰባሰብ የራሱን ጦር ካደራጀ በኋላ ጣልያኖችን በገዛ አገራቸው ያንቆራጥጣቸው ገባ። ከአድዋ ጀምሮ የኢትዮጲያውያንን ወኔ የተረዱት ጣልያኖች የአብዲሳን ጦር በፍርሃት ያዩ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች ከጣልያን ጦር ጋር በመዋጋት ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነበር። ቆራጥነቱን የተረዱት ጣልያኖች የሚያረጉት ግራ ቢገባቸው ከበርካታ ስጦታዎች ጋር ጦሩን ይዞ የጣልያንን ሰራዊት እንዲቀላቀል መማጸን ጀምረው ነበር። ለፋሺስት ጦር መዋጋት አገር መክዳት እንደሆነ አስረግጦ የተናገረው አብዲሳ ትግሉን አፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። የተባበሩት የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ከጀርመን ጋር ያበረችውን ጣልያንን እየተዋጉ በነበረ ሰዓት ስለ አብዲሳ ዝና ከሰሙ በኋላ ለጦሩ የሚገባውን ድጋፍ በማድረግ ፋሺስት ስራቱን ለማዳከም እንደ ዋንኛ መንገድ ሆኗቸው ነበር። 

በድጋፉ በመጠናከርም የጣልያንን ሰራዊት ድባቅ በመምታት ጦሩን እየመራ ሮም ከተማ ከአሜሪካኖቹ ሁላ ቀድሞ የኢትዮጲያን ባንዲራ እያውለበለበ የገባው ጀግናው አብዲሳ አጋ ነበር። በኋላ ሮም የደረሰው የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ጦር አብዲሳን በማሞካሸት ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ አድርገው ሾመውት ነበር። በኋላም ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ወቅት የአብዲሳ አመራር መኖር ያመኑበት እንግሊዞች ወደ ጀርመን ልከውት ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታየጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። 

ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካመንግስታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። እብዲሳ ግን ኢትዮጲያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ህዝቡን እና መንግስቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር ጥያቄውን ውድቅ አደረገ። በዚህ የተናደዱምዕራብውያንም በፈጠራ ወንጀል ከሰው ወደ እስር ቤት አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ከተከፈለ በኋላ በክብር ወደ ሃገሩ ሊመለስ ችሏል።ወደ ኢትዮጲያ ከተመለሰ በኋላ ሰራዊቱን በቅንነት ያገለገለው አብዲሳ በኮረኔልነት ማዕረግ የአጼ ሃይለስላሴ ልዩ ጠባቂ ጦር እየመራ ቆይቶ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱከጥቂት አመታት በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል። የአብዲሳ አጋን ሙሉ የህይወት ታሪክ በደንብ ማወቅከፈለጉ “በኢጣሊያ በረሃዎች (ሻምበል አብዲሳ አጋበአርበኝነት ጀብዱ የሰራ ኢትዮጵያዊ ታሪክ) “ የተሰኘየህይወት ታሪክ መጽኃፉን ማንበብ ይችላሉ።ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments: