ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 12, 2016

አርበኞች ግንቦት 7 ወታደራዊ መግለጫ አወጣ።በአርባምንጭ አካባቢ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ላይ የተወሰደው ጥቃት በግንባሩ ኃይሎች መፈፀሙን ገለጠ።

የአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ምረቃ ላይ 


  • አቶ ጌታቸው ረዳ ጥቃቱን በድጋሚ በዛሬ መግለጫቸው አምነዋል፣
  • ጥቃቱ በህወሓት መንደር ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል፣
  • ፕሮፌሰር ብርሃኑ በመጪው ወር መግቢያ ወደ አውሮፓ ላጭር ጊዜ ያቀናሉ፣
  • የኢትዮጵያ ሰራዊት አርበኞች ግንቦት ሰባትን እንደ ስጋት አያየውም ይልቁንም በከፍተኛ ደረጃ   እምነት ጥሎበታል። 


ትናንት ግንቦት 3/2008 ዓም በአርባምንጭ አካባቢ በታጣቂዎች እና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት መኖሩን ከአምስተርዳም የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) እና አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እኩል አስታውቀው ነበር። ኢሳት በግጭቱ አንድ ከፍተኛ የአካባቢው  የኃይል አዛዥን ጨምሮ 20 የሚሆኑ የመንግስት ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸውን ከማስታወቁም በላይ ጥቃት የፈፀሙት የአርበኞች ግንቦት 7 ኃይሎች ናቸው በማለት የአካባቢው ሕዝብ እየተነጋገረ መሆኑን ገልጧል።የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሌላ በኩል ከመንግስት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ደረሰኝ ባለው ዜና ታጣቂዎቹ ከኤርትራ ተነስተው በዑጋንዳ አድርገው በሞያሌ  በኩል የገቡ ናቸው ብሏል።

ዛሬግንቦት 4/2008 ዓም ደግሞ የአርበኞች ግንቦት 7 ወታደራዊ መግለጫ አውጥቷል።በእዚሁ ኢሳት በተሰጠው መግለጫም በአርባምንጭ አካባቢ የተፈፀመው ጥቃት የንቅናቄው የደቡብ ግንባር አንዱ ኃይል ብቻ የፈፀመው መሆኑን ገልጦ ''ጥቃቱ የተፈፀመው ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 1/2008 ዓም ድረስ በተደረገው የመረረ ፍልሚያ ከ20 በላይ የጠላት ኃይል ገድሎ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑትን ማቁሰሉን እና ከግንባሩም የተሰዉ አሉ'' በማለት ያብራራል።በመቀጠልም መግለጫው  በወጣት አርበኞች የጎሬላ የውግያ ብቃት አስደናቂነትን ጠቅሶ ቀጣይ ጥቃቶች በሰሜን፣በደቡብ እና በመሃል እንደሚኖር ያብራራል።

 የአርበኞች ግንቦት 7 ግንባር ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጥር 22/2008 ዓም ዋሽንግተን፣ደብል ትሪ ሂልተን ላይ በተጠራ ሕዝባዊ ስብሰባ  ባደረጉት ንግግር “ወታደሮቻችን ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ትግላችንን ለመቀላቀል ካሁን በኋላ  ለምትፈልጉ  ወደ  ሰሜን ብቻ  መሄድ  የለባችሁም”  ማለታቸው ይታወሳል።(ለዝርዝሩ ይህንን ተጭነው ይመልከቱ አርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊቱ ከኤርትራ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን ገለጠ)።

በሌላ በኩል የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ሐሙስ ግንቦት 4/2008 ዓም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ጥቃቱን በድጋሚ አምነው ''ከአስመራ ሲነሱ እናውቅ ነበር''በማለት ጋዜጠኞቹን ግራ አጋብተዋል። አንድ ጋዜጠኛ የአቶ ጌታቸውን ቃል እንደማያምን ሲገልጥ እንዲህ ብሏል ''በቀላል አመክንዮ (ሎጂክ) ለማየት የሚሞክር ማንም ሰው የአቶ ጌታቸው ንግግር የሚታመን አለመሆኑን ለማወቅ ይችላል።ምክንያቱም ከአስመራ ጀምሮ የሚያውቁ ከሆነ እንዴት ሞያሌ ሲገቡ ዝም አሉ።ደግሞስ ገብተው አርባምንጭ እስኪጠጉ ምነው ምንም እርምጃ አልተወሰደም?'' በማለት ጠይቆ  '' ይልቁንም አውቀው ዝም ብለናል ካሉም አርበኞች ግንቦት 7 ምን ያህል አራት ኪሎ ውስጥ ሰርጎ መግባቱን እና የድርጅቱ አቅም ትልቅ ደረጃ መድረሱን ያሳያል'' በማለት ገልጧል።

ከእዚሁ ጋር በተያያዘ የአርበኞች ግንቦት 7 ጥቃት በህወሓት መንደር ከፍተኛ ድንጋጤ ከመፍጠሩ በላይ አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ያለው የመንግስት ሰራዊት አርበኞች ግንቦት 7 ኃይልን እንደ ስጋት እንደማይመለከተው እና ይልቁንም ከፍተኛ መተማመን እንዳደረበት የመከላከያ ምንጮች ይጠቁማሉ።ለእዚህም ምክንያቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በተለያየ ጊዜ ለኢሳት በሰጡት መግለጫ አርበኞች ግንቦት 7 ከህወሓት መወገድ በኃላ ሰራዊቱን እንደማይበትን በሰጡት ቃል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ዘግይቶ በደረሰ ዜና ደግሞ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ግንቦት 4/2008 ዓም ምሽት ለኢሳት ራድዮ የአርባንጭ ዙርያ ጥቃትን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ መንግስት አውቅ ነበር ማለቱን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ይህ የማይመስል ነገር ነው እንዴት ነው አንድ መንግስት  ወታደሮቹ እስኪያልቁ ድረስ አውቄ ነው ዝም ያልኩት ማለት  ፈፅሞ ሐሰት መሆኑን ገልፀው ተዋጊው ኃይል ከኤርትራ ተነስቶ በአይሮፕላን በኡጋንዳ በኩል ገቡ የሚለው ሌላው አሳፋሪ አገላለፅ መሆኑን ሲያብራሩ እነኝህ ሰዎች በአይሮፕላን ሲመጡ መሳርያ ጭነው ነው የመጡት ማለት ነው? ማንም እንደሚያውቀው የአለምን የአየር መንገድ ጉዞ አንዲት የጥፍር መቁረጫ ማሳለፍ በማይፈቀድበት ሁኔታ እንዴት ተብሎ ነው መሳርያ ተጭኖ የሚኬደው በማለት ሃሳቡን አጣጥለውታል።

በመጨረሻም የግንባሩ ወታደራዊ መግለጫ በወጣበት በዛሬው ተመሳሳይ ቀን ዘሐበሻ የተሰኘው ድረ-ገፅ እንደዘገበው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመጪው ወር መጀመርያ ሳምንት ከኤርትራ ወደ አውሮፓ መጥተው ከሕዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ እና ጁን 4 የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ዝግጅት  በኦስሎ እንደሚደረግ ያብራራል።

ዘሐበሻ የተገኘው ፅሁፍ እንደሚከተለው ቀርቧል።


ጁን 4፥ 2016 የሚያካሂደዉን የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሰሜን አዉሮፓ አቀፍ ህዝባዊ ውይይትና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በተመለከተ የተሰጠ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ
ሃገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካለችበት ውስብስብ ችግር ለመታደግ ለሃገሪቱና ህዝቧ ቅን የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ህወሓትን ለማስወገድ በሚደረገዉ ተግባራዊ ትግል ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፍ የሚኖርበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ኢትዮጵያ በአጣብቂኝና በመንታ መንገድ ላይ በምትገኝበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ከዳር ሆኖ መታዘብ ዘረኛውን፣ አምባገነኑንና፣ ፋሽስቱን የህወሓት አገዛዝ ከመደገፍ ተለይቶ እንደማይታይ ብዙዎቻችን እንስማማበታለን።
አርበኞች ግንቦት ሰባት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህሊናውና አቅሙ በሚፈቅድለት የትግል ዘርፍ መሰማራት ይችል ዘንድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጥሪዉን ካስተላለፈ ሰንበት ብሏል። በዚህም መሠረት የህወሓትን አፈና በጠነከረ ክንድ ለመመከት የቆረጡ አርበኛ ታጋዮችና ከፍተኛ የአመራር ብቃት ያላቸዉን ምሁራን ጨምሮ በረሃ ወርደው የወያኔን አገዛዝ መፋለም ጀምረዋል። በግምባር መሰለፍ ያልቻሉት ደግሞ በገንዘባቸዉና በእዉቀታቸዉ የሚፈለግባቸዉን በማበርከት ላይ ይገኛሉ፣
ትግሉ የሚካሄደዉ ሃገሪቱን ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረ፣ ብሎም የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት፣እንዲሁም በልመናና በብድር የሚገኘዉን መዋእለ ንዋይ በማሟጠጥ ተቃዋሚዎቹን ለማጥፋት በሚንቀሳቀስ የወንበዴ ቡድንና ከሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዉጭ ሌላ ምንም አጋር በሌለዉ የነጻነት ታጋይ መካከል ነዉ፣፣
ለነጻነት የሚደረግ ትግል እልህ አስጨራሽና አድካሚ ነዉ፣ ዉድ ዋጋና በገንዘብ የማይተመነዉን ህይወትም ያስከፍላል፣ዉጤቱ ግን ከሁሉም ነገር የበለጠና ዉድ ነዉ፣፣ በመሆኑም ይህ ወሳኝ ሐገርን የማዳን ጥረት ዉጤታማ እስኪሆን ድረስ ነጻነት ናፋቂ የሆን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ያላሳለሰና ሁለገብ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፣፣
ይህንን መሰረት በማድረግ June 4, 2016 የሰሜን አዉሮፓ ሃገራትን ያማከለ ታላቅ ህዝባዊ ዉይይትና የገቢ ማሰባሰብያ ፕሮግራም በኖርዌ ሃገር ኦስሎ ከተማ ተዘጋጅቷል፣፣
በዚህ ፕሮግራም ላይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ መሪ ታጋይ አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከበረሃ በመንቀሳቀስ በመካከላችን በአካል በመገኘት ስለትግሉ ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ፕሮግራሙ የተዘጋጀዉ ከተለያዩ የሰሜን አዉሮፓ ሃገሮች ተዉጣጥቶ በተቋቋመ ግብረ ሃይል ሲሆን በኖርዌ ሃገር በሚገኘዉ የዲሞክራሲያዊ ለዉጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት የበላይ አሰተባባሪነት ነዉ፣፣ በዚህ ታላቅ አህጉራዊ ስብሰባ ላይ በኖርዌይና በተለያዩ የሰሜን አዉሮፓ ሃገራት የሚኖሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በብዛት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፣
ፕሮግራሙ ከየትኛዉም የአለማችን ክፍል ለሚመጣ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጅ ክፍት ነዉ፣፣ በተለይም በስካንዲኒቪያንና፣ በአጎራባች የአውሮፓ ሃገራት የምንኖር ነጻነት ናፋቂ ዜጎች የፕሮግራሙ ታዳሚዎች በመሆን የበኩላችንን እንድንወጣ ግብረሃይሉ በትህትና ያሳስባል፣፣
በተለያዩ አህጉራት ያላችሁና በአካል መገኘት የማትችሉ ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ሃገር የማዳን ጥሪ የትግል አጋርነታችሁን በሚያመቻችሁ መንገድ ታሳዩ ዘንድ አስተባባሪ ግብረ ሃይሉ በአክብሮት ይጋብዛል።
የፕሮጋራሙ ቀን፣ June 4, 2016
ሰአት፣ ከ14፣00 ሰአት ጀምሮ
የፕሮግራሙ ቦታ፣ በቀጣይ የሚገለጽ ይሆናል
ተጋባዥ እንግዳ፣ የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከፍተኛ መሪ ከኤርትራ

ኢትዮጵያችን በክብር ለዘላለም ትኖራለች!!
የዲሞራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ
ሜይ 13፣ 2016 ኖርዌይ፣ ኦስሎ,




ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።