ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, April 20, 2019

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር በማያዳግም መልኩ ለመፍታትት ሁሉም ይነሳ!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ቡራኬ ሲቀበሉ 

ጉዳያችን / Gudayachn
ሚያዝያ 12/2011 ዓም (አፕሪል 20/2019 ዓም)


በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉት ርዕሶች ስር ሀሳቦች ተነስተዋል።እነርሱም : -

>> የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ከአሁን በኃላ አንዲት የዶሮ ላባ መሸከም አይችልም ፣
>> የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር መፍትሄ ከውስጥ ይምጣ ወይስ ከውጭ?
>> የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ችግር አለመፈታት ማለት የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ማለት ነው፣
>> የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ችግሯን ለመፍታት ማን፣መቼ፣ምን  ያድርግ? 
>> በ21ኛው ክ/ዘመን ''የአይቲ''  (የዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ክፍል (ዲፓርትመንት) በመዋቅር ደረጃ የሌላት በሚልዮን የሚቆጠር ምዕመን የያዘች ቤተ ክርስቲያን -የአስተዳደር ችግሯ አንዱ መገለጫ

በ1953 ዓም ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ የተፃፈው ፍኖተ አእምሮ - የዕውቀት ጎዳና የተሰኘው መፅሐፍ  ምዕራፍ 24 ስለ እግዚአብሔር ፍቅር በሚለው ርዕስ ስር እንዲህ ይላል : -
''ሰው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የሚጨመረውን የፍጥረትን ፍቅር ያላግባብ ካደረገው ወደድኩህ በሚለው በፈጣሪው መዘበት ይሆናል።ምነው እግዚአብሔርን ቢወድ ዘበተ እንዴት ይባላል? ቢሉ ምላሹ - ሰው እግዚአብሔርን የሚወድበት ምክንያት ንብረቱ ስለ ሞላለት፣ ወይም እንዲሞላለት፣ ወይም ዕድሜው እንዲረዝምለት፣ ወይም ልጅ ስላገኘ፣ የሚወደውን ተድላ ስላደረገለት፣ ወይም እንዲደረግለት እንደሆነ። ይህ ሰው ፈቃደ ስጋውን ወደደ ይባላል እንጂ፣ እግዚአብሔርን ወደደ አያሰኘውም እንዲያውም ስጋዊ ነገር ሲደረግለት፣የሚወድ ስጋው ነገር ሲቀርበት የሚጠላ ነውና ስለዚህ ለእግዚአብሔር የታመነ ወዳጅ አይባልም። እግዚአብሔርን መፍቀደ ሥጋን ሲደርግ ቢወዱት እንዲያደርግ ቢለምኑት ስለምን ዘበትና የማይገባ ይሆናል? ቢሉ ምላሹ - እንዲህ ያለው ጠባይ በፊት በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆኖ የሚኖር ነበር። በየጊዜው ከክህደት አደረሳቸው እንጂ አልረባቸውም።በተደረገላቸው ወራት እየወደዱ ባልተደረገላቸው ወራት እየጠሉ መጎዳታቸውን አሳዩ።የእዚህ ዓለም ገንዘብ እንደ ትርፍ እንደ ጉርሻ ለበጎዎችም ለክፉዎችም የሚደረግ ነውና መንግስተ ሰማያትን ለምኑኝ እንጂ ይህን ዓለምስ እንዲያውም አትለምኑኝ ማለቱ መወደሻውና መጠያው በእዚህ ምክንያት እንዳይሆን ነውና ። '' 

ከላይ የቀረበው ፅሁፍ ታትሞ ከወጣ ሀምሳ ስምንት ዓመታት ሆኖታል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምዕመናን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት በምድራዊ ምቾት እና ቁሳዊ ነገር የማግኘት እና አለማግኘት ጋር አብሮ የሚለካ መሆን እንደሌለበት ለማመናቸው አንዱ ማሳያ ነው።በስጋዊ ምቾት አብዛኛው ምዕመንም ሆነ አገልጋይ ካሕናት ደልቷቸው የሚኖሩ አይደሉም።ይልቁንም በፍፁም ዕምነት ከምድራዊ ምቾት ጋር ባልተገናኘ ፍፁም እግዚአብሔርን የመውደድ  ታላቅ ሀብት የቤተክርስቲያኒቱ እና የተከታዮቿ አንዱ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበቁ ቅዱሳን፣ለስጋቸው ሳይሆን ለነፍሳቸው ያደሩ ሊቃውንት ዛሬም  ከአጥብያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ገዳማት፣ከገዳማት እስከ በረሃ ተሰውረው የሚኖሩባት፣ስለ ሰውልጅ እና መላው ዓለም የሚፀልዩ፣ስለ እራሳቸውም ሆነ ስለ ሀገራቸው እግዚአብሔር ጋር ጧትና ማታ የሚነጋገሩ ምዕመናን ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዛሬም ድረስ የታደለቻቸው ፀጋዎቿ ናቸው። ይህንን መንፈሳዊ ሀብት በሰው አዕምሮ መለካት ፈፅሞ አይቻልም።እግዚአብሔር በሚለካበት ምስጢራዊ መለክያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ሀብት ይለካዋል።

ከላይ ከተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ሀብት በተቃራኒው ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን በውስጧ ተሰግስገው የወጠሯት ሶስት ዓይነት አስተዳደራዊ ችግሮች አሉ። እነርሱም ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት እጦት፣የገንዘብ ምዝበራ እና የጎሰኝነት አስተሳሰብ ያላቸው ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሰረተ ዕምነት ውጭ አገልግሎቷንም ሆነ አስተዳደራዊ መዋቅሯን ማወካቸው የሚሉት ቀዳሚ ናቸው።እነኝህ ሶስቱ ችግሮች ከእዚህ በፊት በሰፊው በተለያዩ መንገዶች ሲወሱ ስለነበሩ ስለምንነታቸው መዘርዘሩ እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ ማጥፋት ነው።ከእዚህ ይልቅ ወደ መሰረታዊ መፍትሄዎቹ ላይ ላተኩር።

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ከአሁን በኃላ አንዲት የዶሮ ላባ መሸከም አይችልም 

አንድ ነገር ከእዚህ በኃላ ሊቀጥል አይችልም። የሚለውን አባባል ለመግለጥ በቁልሉ ላይ አንድ የዶሮ ላባ ብታስቀምጥበት ቁልሉ ይናዳል የሚለው አገላለጥ ጥሩ አገላለጥ ነው።አባባሉ ከእዚህ በላይ ምንም አይነት ችግር ለማስተናገድ አቅም የማጣት ደረጃ የሚገለጥበት ጥሩ አባባልም ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ላለፉት ሶስት አስር ዓመታት በተለይ ያሳለፈችው አስተዳደራዊ ፈተና ይህ ነው የሚባል አይደለም።የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት እና ሀብት በግለሰቦች የግል ኩባንያ መመስረቻ ብቻ ሳይሆን የማያልቅ የሚታለብ ጥገት ሆኖ ኖሯል።አሁንም የደረሰውን ስንዘረዝረው ብንውል ቀናት አይበቁንም።

ዛሬ ላይ ሆነን ግልጥ የሚሆነው ጉዳይ ግን የነበረው የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግር ውሎ ለማደር የአንዲት የዶሮ ላባ ያህል ሊሸከም አይችልም።ቢያንስ በማያዳግም ደረጃ እንዲፈታ አስፈላጊው ሥራ መልክ ባለው መንገድ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ሁሉን ባሳተፈ መንገድ መጀመር አለበት።ለእዚህም ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ ቤተ ክርስቲያን፣ከሰንበት ትምህርት ቤት እስከ አብነት ትምህርት ቤቶቿ፣ከምእመናን እስከ መንፈሳዊ ማኅበራት በአንድነት የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር መፍትሄ ከውስጥ ይምጣ ወይስ ከውጭ?

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ይህንን ያህል እየባሰ ለምን ምዕመናኗ እንደ ሩስያው የጥቅምት አብዮት ሆ! ብለው ወጥተው አልተፋለሙም? የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማኅበራትስ ለምን መስቀል አደባባይ  አልተሰለፉም? ወይንም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዘራፊዎች ጋር ዱላ አልተማዘዙም? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች አንዳንዶች ሲያነሱ ይሰማሉ።እነኝህ ጥያቄዎች በተለይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሮች የአንድ ሰሞን የዜና ርዕሶች ሲሆኑ የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው። እነኝህ ጥያቄዎች ግን የሚነሱት በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሮች ብቻ ያሉ የሚመስሏቸው እና የበለጠ የሚያናጉ ጉዳዮች በተለይ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች እንዴት በገንዘብ ምዝበራው እና በዘረኝነት መስመሮች ስር እያለፉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደተወሳሰበ ችግሮች ለመክተት ይዳዱ እንደነበር ካለመረዳት ነው። 

ቀደም ባሉ ዓመታትም ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሮቿን ለመፍታት መፍትሄው ከውስጥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ መምጣት አለበት? ወይንስ ከውጭ? የሚሉት ጥያቄዎች ሁል ጊዜ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው።ከውስጥ ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ በራሷ ባላት ከፍተኛ መዋቅር ማለትም በቅዱስ ሲኖዶስ በራሱ አስተዳደራዊ ችግሮቹን ለመፍታት አስፈላጊውን ሥራ እንዲሰራ ሲሆን ከውጭ ማለት ምዕመናን አስተዳደራዊ ችግሮቹን ወደ አደባባይ አውጥተው እና አስገድደውም ቢሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመዘብሩትን በሙሉ ለሕግ በማቅረብ እና መንግስትም በጉዳዩ ላይ እንዲገባ ማድረግ የሚለው መንገድ ነው። እውነታው ግን ላለፉት በርካታ ዓመታት ውስጣዊ መፍትሄ ይመጣል ተብሎ ቢጠበቅም ቀደም ባሉት ዓመታት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀሩ የቤተክርስቲያንቱን ንብረት እና ሀብት ተካፋይ ስለነበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ይፈታ የሚሉትን ሁሉ የፖለቲካ እና የጎሳ ስም እየተለጠፈባቸው ብዙ ፈተና ሲቀበሉ ኖረዋል። አሁን ቢያንስ የፖለቲካ ቅብ ለመቀባት የወቅቱ የሥርዓት ለውጥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ለውጥ ያልተነሱት ከውስጥ ብፁዓን አባቶች፣ከውጭ ደግሞ ምዕመናን መሆናቸው ግልጥ ሆኗል። ስለሆነም የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግር መፍትሄ በቅንጅት ማለትም ከውስጥ፣ከውጭ እና ከመንግስት በአንድነት የሚሰሩት ተግባር ውጤት ነው።

መንግስት -

መንግስት ለአስተዳደር ችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተነሱትን አካላት ደኅንነት ከመጠበቅ አንስቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባስቀመጠችው መንፈሳዊ መፍትሄ ያጠፉትን በሕግ አግባባ የመዳኘት ሥራ ሁሉ የመንግስት ሥራ ነው።መንግስት ለቤተ ክርስቲያኒቱ መፍትሄ ማገዝ፣መስራት እና መከላከል ግዴታው ነው።እዚህ ላይ መንግስት ማለት ከሌላ ቦታ የመጣ ልዩ አካል ማለት ሳይሆን መንግስት ውስጥ ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት መንግስትን ወክለው እና የአስተዳደራዊ ለውጡን አግዘው እንዲገኙ ማድረግ በቀላሉ የመንግስት እገዛ ማለት ነው።

ከውስጥ -

ከውስጥ ደግሞ ለመፍትሄ የሚነሱትን የሚያደናቅፉትን አጥብቆ መቃወም እና እውነት እና እግዚአብሔርን ይዘው ለአስተዳደራዊ መፍትሄው የሚሰሩ አባቶች ያስፈልጋሉ።በተለይ ትልቁ ችግር እና አደናቃፊው ጉዳይ ከውስጥ ከመሆኑ አንፃር የነበረ አስተዳደራዊ ችግርን ሰብረው የሚወጡ አባቶች ያስፈልጋሉ።ከእዚህ በኃላ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአንድ ዶሮ ላባ ያህል በንበረባት የአስተዳደራዊ ችግር ላይ የመሸከም አቅም እንደሌላት መረዳቱ ወሳኝ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ከውጭ ከሚመናንም ሆነ ከልዩ ልዩ አካላት የሚመጣው ግፊት ባልታሰበ ሰዓት እና ጊዜ በግድ አስተዳደራዊ ችግሩን ለመፍታት መምጣቱ ስለማይቀርና ይህ ደግሞ የሚያስከትለው ብዙ መፋተጎች ስለሚኖሩ የውስጡ ቢያንስ ከእዚህ ከግንቦቱ የሲኖዶስ ጉባኤ ያላለፈ ወሳኝ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል።እዚህ ላይ ከእዚህ በፊት ኮሚቴ ተመስርቷል፣ውሳኔው እየተጠና ነው እና የመሳሰሉት የመጎተት ሥራ ከአሁን በኃላ ብዙ የሚያስኬድ አይመስለም።ይልቁንም ይህ ጉዳይ ውጫዊው ኃይል ሰብሮ እንዲመጣ በር የሚከፍት ነው። 

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ችግር አለመፈታት ማለት የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ማለት ነው።


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንፃር ቆመው የንብረቷ ተጠቃሚ የሆኑ ነቀርሳዎች ሰንሰለታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ይህ በራሱ ሰፊ ጥናት ይፈልጋል።ይህ ማለት ግን ያጠኑት የሉም የማይታወቅ ነው ማለት ደግሞ አይደለም።ስለሆነም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ችግር በማያዳግም ደረጃ ለመፍታት የውስጥ፣የውጭው እና መንግስት ከምንጊዜውም በላይ መነሳት ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሀምሳ ሚልዮን በላይ ምዕመን፣ከአምስትመቶ ሺህ በላይ አገልጋይ ካህናት እና በአስር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ተከታዮች፣በሺህ የሚቆጠሩ ምሑራን የያዘች የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላት ነች።ይህ ማለት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ችግር አለመፈታት ማለት የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ማለት ነው። ሌላው ቀርቶ ላለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች የተነሱት የጎሳ ቁርሾዎች ይህንን ያህል የተባባሱት  መንግስት በሚገባ ፀጥታውን የማስከበር ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ብቻ ሳይሆን  ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሯን ፈትታ በብዙ ቦታዎች ለምመናኗ መንፈሳዊም ሆነ ስጋዊ ችግር የመድረስ አቅሟ መመናመኑ እና በሚያጠቁት አካላት አንፃር ምእመናኗን አስተባብራ ተፅኖ የመፍጠር አቅሟን አለመጠቀሟ እንዲሁም ችግሩ ከደረሰ በኃላ በፍጥነት ሰፊ ሀብት አንቀሳቅሳ ለመርዳት ያላት አቅም አለመጠቀም የሚያስቆጭ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ችግሯን ለመፍታት ማን፣መቼ፣ምን  ያድርግ? 

ማን  ያድርግ?

ችግሩን ለመፍተት ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ካህናት ከውጭ ምዕመናን እና መንግስት በአንድ ልብ በተናበበ መንገድ ስራቸውን ሊሰሩ ይገባል።

ምን ያድርጉ?

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት ከእዚህ በፊት ኮሚቴ፣ጥናት እየተባለ የተሞከሩ የግብር ይውጣ ስራዎች ነበሩ።አሁን ግን በእዚህ አይነቱ ሂደት እየሄዱ በእግዚአብሔር ላይ ''ማላገጥ'' የሚቻልበት ጊዜ ሊሆን አይገባም።ሊደረግ ከሚገባው ጉዳይ ውስጥ አንዱ በቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ ስብሰባ፣በምዕመናን ቆራጥ እና አፋጣኝ ውሳኔ እና በመንግስት ልዩ ተከታታይ አካል ጥምር ልዩ ቢሮ ማዋቀር እና አስተዳደራዊ ጉዳዩን ወደ ዘመናዊ አሰራር ማሻገር ነው። በቅርቡ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለአደባባይ ሚድያ እንደተናገረው ''ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ መስርያቤቶች ስንት ጊዜ አስተዳደራዊ መዋቅራቸውን ወደ ዘመናዊ እና ተጠያቄ አሰራር ሲቀይሩ እንደነበረ ከመቶ ዓመት በፊት እንዳለ የምታገኘው የቤተ ክህነቱ ዘመናዊነት የሌለበት አስተዳደራዊ አሰራር ነው'' ነበር ያለው። ይህ የሚያሳየው ጉዳዩ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት ሃይማኖታዊ ዶግማ እና ሥርዓቷን ሳይሆን አስተዳደራዊ አሰራሯን ቤተ ክርስቲያን ለማዘመን መነሳት እና የገንዘብ መዝባሪዎቿን በሙሉ ነቅላ ስርዓት ማስያዝ ወሳኝ ሥራ መሆኑን ነው።

 ከላይ የተጠቀሰው ልዩ ቢሮ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ምዕመናን፣የአስተዳደር ባለሙያዎች፣የፋይናንስ ባለሙያዎች፣የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች፣የሕግ ሰዎች እና የፖሊስ እና ፀጥታ ክፍል ሰራተኞች ሁሉ ያቀፈ ሆኖም ግን ሁሉም በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የተጉ ወይንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕምነት ውስጥ ያሉ አባላት ያሉት ጠንካራ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአስተዳደር እና የገንዘብ ብክነት ሁሉ የሚመለከቱ እና የመፍትሄ ሃሳብ ከማቅረብ ጋር መዋቅሩን አስተካክሎ እስከ የሰው ኃይል ቅጥር ድረስ መልክ አስይዘው የሚሄዱ ሙሉ የማስፈፀም አቅም ያላቸው መሆን አለባቸው።

የእዚህ አይነቱ ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ እስካልነካ ድረስ ምንም አይነት አደጋ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አያደርስም።ምክንያቱም ከመንግስትም ሆነ ከምእመናን የሚመጡት የኮሚቴው አባላት በሙሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከእዚህ በፊት በአንድም በሌላም ሲደክሙ የነበሩ ናቸውና።

በ21ኛው ክ/ዘመን ''የአይቲ''  (የዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ክፍል (ዲፓርትመንት) በመዋቅር ደረጃ የሌላት በሚልዮን የሚቆጠር ምዕመን የያዘች ቤተ ክርስቲያን -የአስተዳደር ችግሯ አንዱ መገለጫ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅሯ ከቤተ መንግስት እስከ ታች የገበሬው ጎጆ ድረስ ቢሆንም ይህንን አገልግሎቷን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ሌላው ቀርቶ አጥብያዎች ለሀገረ ስብከታቸው ጋር የሚገናኙበት የኔትወርክ ሥራ አለመኖሩ የገንዘብም ሆነ የአስተዳደራዊ ሪፖርቶች የሚቀርቡበት መንገድ ዘመናዊ አይደለም።ከእዚህ ይልቅ በቤተክርስትያኒቱ ስር ያሉ ማኅበራት ለምሳሌ የማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊ ማኅበር የአገልግሎት ክፍሎች የኢንፎርሜሽን መዋቅር ዘመኑን የዋጀ ሆኖ ይታያል።ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አቅርባ ለመጠቀም የአስተዳደራዊ ችግሯ ቀስፎ እንደያዛት ጉልህ ማስረጃ ነው።በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ሆነን አጥብያዎች ለሀገረ ስብከታቸው ሪፖርት በፖስታ ከመላክ ወጥተው የኢንፎርሜሽን አገልግሎቱ መላው አጥብያን የሚያገናኝ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ አጥብያዎች በሚደርሱበት  በመላው ዓለም ከቤተ ክህነቱ ጋር የማገናኘት እና አገልግሎቱን የቀለጠፈ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ አንዱ ተግባር ነው።

ማጠቃለያ 

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር ከአሁኑ የግንቦቱ ርክበካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወሳኝ መፍትሄ የሚያገኝበት ካልሆነ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ችግሩ አንዲት የዶሮ ላባ መጣያ ቦታ የለውም።ይህ ማለት ደግሞ ጠቅላላ ምዕመናን በገፋ መልኩ የሚጠይቁበት እና ችግሩ ወደ አልተፈለገ መፋተግ የመድረስ አደጋው ግልጥ ነው።ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ላሉ የፖለቲካ እና የጎሳ ግጭቶች ሌላ መልክ ያስይዘውና ጉዳዩ ወደ ተለያዩ ፍላጎት ወዳላቸው አካሎች እጅ እንዲገባ እና መንግስትም ሆነ ቤተክርስቲያኒቱ ሊቆጣጠሩት  ወደ ማይችሉት መንገድ ያመራል።ስለሆነም ወግ ባለው መልኩ ምእመናንም ሆኑ መንግስት የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ከልብ ሊነሱ ይገባል።ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ካህናት ባጠቃላይ፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ምዕመናን እና መንፈሳዊ ማኅበራት  እንዲሁም መንግስት በሙሉ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር  ለመፍታት የሚነሱበት ወሳኝ ጊዜ ነው። እዚህ ላይ ትዕግስቱ እና ምሕረቱን ላሰፋልን የቤተ ክርስቲያን ራስ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰውና ከአሁን በኃላ ግን እርሱም የዶሮ ላባው ያህል ጥፋት በቤተ ክርስቲያን ላይ የማይታገስበት ጊዜ መሆኑን አውቀን ለማይቀረው አስተዳደራዊ ችግር መፈታት አካል ለመሆን እንነሳ!

================///============

No comments: