ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, April 7, 2019

ኦነግ ያለው ኦዴፓ ውስጥ ነው።ኦዴፓ ከኦነግ ጎን መሰለፍህን አሳውቅ! ወይንም ያስጠለልከውን ኦነግ ቆርጠህ ጥለህ ከኢትዮጵያ ጋር ወግን!


ጉዳያችን /Gudayachn
መጋቢት 30/2011 ዓም (April 8/2019) 
==================
በእዚህ ፅሁፍ ስር : -
የከረሙ ወንጀለኞች ዳቦ ሲጠግቡ፣
''በብረት የመጣ በብረት ነው የሚመለሰው'' የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ፣
-  ኦነግ ያለው ኦዴፓ ውስጥ ነው፣
የሰሜን ሸዋው የኦነግ ጥቃት ዓላማ፣
መወሰድ ያለባቸው አምስት መፍትሔዎች  በሚሉ ርዕሶች ስር የተከፋፈሉ አጫጭር ፅሁፎች ያገኛሉ።
========================
የከረሙ ወንጀለኞች ዳቦ ሲጠግቡ 

ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ በሰሜን ሸዋ ማጀቴ፣አጣዬ እና ካራቆሬ እንዲሁም በወሎ ከሚሴ የኦነግ ጀሌዎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል።የሰሜን ሸዋውን ግጭት ተከትሎ እስካሁን ቢያንስ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን መሰረቱን እንግሊዝ ያደረገው 7D የዜና አገልግሎት እሁድ ምሽት ሽብርተኝነት እና የፀጥታ ጉዳዮች በሚል ንዑስ አምዱ ስር ዘግቦታል።በኦነግ ስር የተጠለሉ ፅንፈኞች የከረሙ ወንጀለኞች ናቸው።ላለፉት ሠላሣ አምስት  ዓመታት ''ሐበሻ '' ''ሰሜኖች'' ''ነፍጠኞች'' እና ሌላም ስም እየሰጡ  ብዙ ንፁሃን የዓማራ ተወላጆችን ገድለዋል።የኦነግ ወለድ ትውልድ እና ተከታዮቹ በንፁሃን ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈፀማቸው ለሕዝብ የተነገረው በኮ/ል መንግስቱ ዘመን አሶሳ ላይ ''አማሮች'' ናችሁ ተብለው በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው እንደ ጧፍ የነደዱት ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ዛሬ ድረስ ሐውልት አልተሰራላቸውም።በመቀጠል በህወሓት ኢህአዴግ የስልጣን የመጀመርያ ዓመታት በአርሲ፣አርባጉጉ ፣በበደኖ የተፈፀሙት ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ናቸው።የሁሉም የዘር ማጥፋት ድርጊት አመራር ሰጪዎች ዛሬ እንደ ጵላጦስ እጃቸውን ታጥበው በፖለቲካ ድርጅቶች ስም ተሰይመው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየተንፈላሰሱ ይገኛሉ።መፅሐፍ ዓለም ከምትናወጥባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ ነው ይላል።አሁን ባለንበት ዘመን የከረሙ ወንጀለኞች ዳቦ የጠገቡበት ዘመን ነው።

''በብረት የመጣ በብረት ነው የሚመለሰው'' የሰሜን ሸዋ ሕዝብ 

በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት ገባሁ ያለው ኦነግ የጅላጅል እና የአጉል ብልጣብልጥነት ፖለቲካ ለማራመድ ሲውተረተር ይታያል።ፈሪ ሁል ጊዜ ጨካኝነት የጅላጅል ማምለጫ መንገዱ ነች።ላለፉት አርባ ዓመታት ያልተሳካለት ኦነግ በአይሮፕላን ወደ ሀገር ቤት ገብቶ አንዴ በወለጋ፣ሌላ ጊዜ በጌድዮ አሁን ደግሞ በሰሜን ሸዋ ላይ የትንኮሳ እና የሽብር ሥራ እየሰራ ነው።የእዚህ አይነት በጠበንጃ የመጣ ጀሌ በብዕር  አይመለስም።በብረት የመጣ መነጋገርያው ብረት ብቻ ነው።የትዕቢት መንፈስ ካልበረደ ጠበኛ የሰላም መንገድ አይታየውም።

ኦነግ ያለው ኦዴፓ ውስጥ ነው

ኦነግ የት እንዳለ እራሱን ለመደበቅ ብዙ ይጥራል።ኦነግ ያለው ፅንፈኛ አክትቪዝቶች ውስጥ ነው፣ኦነግ ያለው አክራሪ የእስልምና መንግስት ለማቆም ከሚውተረተሩ የለየላቸው አሸባሪዎች ጋር ነው።ኦነግ ይለው በብሮክራሲ እራሱን ደብቆ ኦዴፓ (ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ) ውስጥ ነው።ለእዚህም በኢትዮጵያ ባለፉት አንድ ዓመታት የተፈፀሙት ግድያዎች፣ሕዝብ የማፈናቀል እኩይ ተግባራት እና የኦዴፓ የተሳከሩ ዋልታ ረገጥ መግለጫዎችን መመልከት ይበቃል። ኦነግ በቅርብ እንደ አንድ ስልት መጠቀም የጀመረው በእርግጥ ቀደም ባሉ ዓመታትም በኦህደድ ስም ተሰግስገው ነገር ግን ፅንፍ ይዘው በብሮክራሲው ውስጥ ሕዝብ ያስለቀሱ የኦነግ ፅንፈኛ አስተሳሰብ አራማጆች ነበሩ።አሁን ግን ጉዳዩን የከፋ የሚያርገው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ዩኒፎርም የለበሱ ነገር ግን በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት ነው።
 ኦዴፓ በብሮክራሲውም ሆነ በአስተሳሰብ ይህንን ያህል ከኦነግ ጋር የተሞዳሞደበት ምክንያት በራሱ ለስልጣን ካለ ጥማት የሚመነጭ ነው።ኦዴፓ በምርጫው ለማሸነፍ ከኦነግ የተሻልኩ ነኝ የሚል አማራጭ ስልት ይዞ ከሆነ በጣም ተሳስቷል።አሁን የሚታየው ይልቁንም እራሱ ኦዴፓ እየከሰመ ኦነግ በኦዴፓ ቢሮክራሲ ውስጥ እየታየ ነው።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆርጦ ኦዴፓን እንዲዋጋው ያደርገዋል።በእዚህም የለውጡ ሂደት ሙሉ በሙሉ ሐዲዱን የመሳት አደጋ አለው። 

የሰሜን ሸዋው የኦነግ ጥቃት ዓላማ  

በእዚህ ሳምንት በማጀቴ፣አጣዬ እና ካራቆሬ ሰሜን ሸዋ እና ወሎ ከሚሴ  ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ጦርነት በቅጥረኘንት ኦነግ በተከፋፈለ አንጃዎቹ እና በህወሓት የውስጥ ድጋፍ ጭምር እንዲሁም ኦዴፓ ውስጥ በተሰገሰጉ የብርክራሲው አካላት ስልታዊ እና የመረጃ ድጋፍ የተቀናበረ ነው።የጥቃቱ ዓላማ ፍርሃት ነው።ፍርሃት ብቻ አይደለም። ኦነግ ከፅንፈኛ አቅትቪስቶች ጋር በፈፀመው ቁርኝት ጭምር የዶ/ር ዓብይን መንግስት መጣል ያስባል።ይህንን ሲያደርግ እንደ ቀዳሚ ስጋት የሚያየው የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ነው።ይህ ሕዝብ ለአዲስ አበባ ካለው ቅርበትም ጭምር ቢያንስ ለማሸበር ታቅዷል።እዚህ ላይ ግን ኦነግ ትልቅ ስህተት ማድረጉን እረስቶታል።በዓማራ ክልል በተለይ በሰሜን ሸዋ አይደለም ቤተ ክርስቲያን የሚያቃጥል ጀሌ መጥቶ ህዝቡ ዋጋ የሚሰጠው ለጀግና እንጂ ለፈሪ አይደለም።ወንዱ ቀርቶ ሴቷ ነብር ነች።ይህንን ያማይውቅ ብዙ ሊያወራ ይችላል።በአርሲ አርባ ጉጉ ኦነግ በፈፀመው የግፍ ሥራ በናዝሬት/አዳማ በኩል ዞረው የኦነግን ሰራዊት የቀጡት ከሰሜን ሸዋ ተነስተው የሄዱ አርበኞች ናቸው።ይህ አካባቢ እጅግ ሕግ አክባሪ ነገር ግን ፍትህ ለመጉደሉ እርግጠኛ ሲሆን ደግሞ ታቦት ይዘህ የማታቆመው ሕዝብ ነው።ኦደፓ እስካሁን በብሮክራሲው ውስጥ አቅፎ የያዛቸው የኦነግ ጀሌዎችን በግልጥ ቆርጦ መጣል አለበት።ይህ ካልሆነ ኦዴፓ ሙሉ በሙሉ በኦነግ ስር መግባቱ ተረጋግጦ የኢላማው አካል ይሆናል ማለት ነው። 

መወሰድ ያለባቸው አምስት መፍትሔዎች 
የእዚህ አይነት ፀብ ጫሪ ድርጊቶች በተለይ ንዝረቱ በሌሎች አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ እና ዓማራ ተወላጆች ላይ እንዳይንፀባረቅ ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል።የኦነግ ፅንፈኛ ሰራዊት በኤርትራ በኩል ሲገባ የምሳ ግብዣ አድርገው እንደሚባለውም አስታጥቀው የላኩት አቦይ ስብሐት እና የህወሓት ፅንፈኛ አካል አሁንም ስስ የሚሉትን አካባቢ እየመረጡ ግጭቶች የመፍጠር ስራዎችን ዛሬም አይሰሩም ማለት አቻልም።ይህ በሰሜን ሸዋ ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ጥቃት  በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ግልጥ ጥቃት ነው።ለሁሉም ችግሮች መፍትሄዎች አሉት።ይህም ችግር የሚተገብረው ቢያገኝ መፍትሄ አለው።ስለሆነም መፍትሄውቹ - 

1ኛ) ኦዴፓ ከኦነግ ጋር የመሞዳሞድ ስራውን ቆርጦ መጣል ወይንም እራሱን በኦነግ አሸባሪነት መድቦ መውጣት፣

2ኛ) ዶ/ር ዓቢይ ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ ጠፍቶ ሃገራዊ ፓርቲ ይኖረናል ያሉትን ንግግር በቶሎ ወደ ፊት ማምጣት በፓርቲያቸው ውስጥ  የተሰገሰገውን ኦነግ ወደ ጎን አድርገው ለማለፍ ያላቸው አንዱ የመውጫ ኮሪደር ነው፣

3ኛ) በኦሮምያ እና በፌድራል ደረጃ ያለው የቢሮክራሲ መዋቅር መልሰው ከኦነግ ማጥራት።

4ኛ) የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ አዲስ የተሻሻለ መመርያ ለጦር ሰራዊቱ መስጠት ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ እና 

5ኛ) በጎሳ ስም የተደራጁ የቴሌቭዥን እና ራዲዮ ጣቢያዎች በሙሉ ከጎሳ ስም ከፋፋይ ወደ አልሆነ ስም እንዲቀይሩ እና አሰራራቸው ላይም ምንም አይነት ግጭት የሚቀሰቅስ ተግባር እንዳይፈፅሙ ተቆጣጣሪ ቦርድ መመስረት።

መንግስት እነኝህን ተግባራት ካላከናወነ ግን በሁሉም በኩል ያሉት የፅንፍ ኃይሎች ኢትዮጵያን ወደ ለየለት የጦርነት አውድማ የመውሰድ አቅም አላቸው።በኦነግ ስም በግልጥ የታጠቀ ኃይል እየተንቀሳቀሰ እና በንፁሃን ላይ አደጋ እያደረሰ በሌላ በኩል ያለው ሕዝብ በዝምታ ያልፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም።ይልቁንም ጥቃቱ የበለጠ ሰላማዊ ሕዝብ ወደ ትጥቅ ትግል እንዳይሄድ እና ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ያሰጋል።አሁንም እውነታው አንድ ነው። ኦነግ ያለው በኦዴፓ እቅፍ ውስጥ ነው።መፍትሄው ደግሞ ኦዴፓ እራሱን ከኦነግ ለይቶ በግልጥ ማውገዝ የገባዋል።መንግስት እንደመንግስትም  ከአድሏዊ አሰራሮች እራሱን ጠብቆ አሸባሪዎችን መቅጣት ካልቻለ አደገኛ ነው።የዶ/ር ዓቢይ መንግስት በኦነግ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰደ ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ ብሔራዊ  የፀጥታ ችግር ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይል የመጠቃት አደጋም ሊያጋጥም ይችላል።ስለሆነም መሞዳሞዱ ይብቃ!


  
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...