ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, February 22, 2013

ሃሳቤን እንዳልገልፅ የታገድኩት የ እኔ አውነተኛ ታሪክ

ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ በ እዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች የተጀመረው ''ሃሳብን የመግለፅ መብት ይከበር'' የሚለው ነው። ስለራስ ማውራት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን ይህ ታሪክ ብዙ በእኔ ትውልድ ያሉ የገጠማቸው እና አሁንም ሃሳብም ከማፈን ጋር የሚመጣው ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን ለማሳየት ዛሬ ስለ እራሴ ትንሽ ላውራ።

ጉዳያችን ጡመራን መጻፍ ስጀምር ብዙ ቅን የሆኑ ሃሳቦችን ለመጻፍ በማሰብ ነበር።በተፈጥሮዬ ዜጋ መንግስትን ሲቃወም ስርዓት ባለበት መንገድ ከሆነ ነገሮች ይስተካከላሉ እያልኩ የማስብ ሰው ነበርኩ።ዩጋንዳ ሳለሁ  ወደ ሌላ ሃገር የመሔድ እድል (እድል ከተባለ) እና እዛው ሃገር ያገኘሁትን ስራ አቁሜ ወደ ሃገሬ ስመለስ በውስጤ የነበረው ህልም በሃገሬ የልማት ጥናት በመጀመርያ ዲግሪ ደረጃም ሆነ በዲፕሎማ ደረጃ አለመሰጠቱ በጣም ይቆጨኝ ነበር እና ስራ ለማግኘት ትንሽ ጊዜ ብወስድም ትምህርቱ ቢያንስ በሃገር ውስጥ ባሉ ተቋማት ቢስፋፋ ትልቅ ለውጥ ይመጣል በሚል  ተስፋ ነበር ሃገሬ የገባሁት።

ከዩጋንዳ እንደተመለስኩ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የልማት ጥናት ዲፓርትመንት ሃላፊን አንድ ቀን ከቢሮአቸው አነጋገርኳቸው። በተለይ የ ኢኮኖሚክስ ትምህርት በባለ ብዙ ዘርፍ ትምህርቱ የ ልማት ጥናት እየታገዘ  በ አስተዳደር ስራ ከ ክፍለ ከተማ እስከ ቀበሌ ያሉ የልማት ባለሙያዎች በ ዲፕሎማ ደረጃ እንዲማሩ ብታደርጉ ብዬ የዩጋንዳን፣የሩዋንዳን እና የታንዛንያን ተሞክሮ አስረዳሁ።የሚገርመው ነገር በወቅቱ (በ1997ዓም) የ ዲፓርትመንቱ ሃላፊ ወደ ክፍሉ የሚመጡት ግማሽ ቀን ሲሆን ግማሹ ቀን ከዩንቨርሲቲ ውጭ በሚያገለግሉበት የ ኢህአዲግ አጋር ድርጅት ውስጥ ይሰሩ ነበር። ይህ ክፍል የሙሉ ጊዜ ስራ የሚሰራ እና በሙያው በ ፒኤችዲ ዲግሪ የጨረሱ ባለሙያዎች ቢኖሩም ለመስራት ያልቻሉበት ጉዳይ ተከሰተልኝ። 
በእዚህ አላቆምኩም ከ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር ተነጋግሬ  ''የልማት ጥናት (Development Studies) ትምህርት በኢትዮጵያ አስፈላጊነት'' በሚል ርዕስ በ ሳይንስ እና  ቴክኖሎጂ አዳራሽ (በወቅቱ ከብሄራዊ ቲያትር ጀርባ ከ ብሔራዊ ባንክ ፊትለፊት ይገኝ ነበር) ውስጥ የግል ጋዜጦች የ ሪፖርተር ጋዜጣንም ጨምሮ በተገኘበት የ ጥናት ፅሁፍ እና የ ፓናል ውይይት አዘጋጀሁ ።በ ፕሮግራሙ ላይ ከ ግል ኮሌጆች እና ከ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የተገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ስለ ትምህርቱ አስፈላጊነት በተለይ በታችኛው ሕብረተሰብ ደረጃ ላሉ ሁሉ በሰርተፍኬት እና በ ዲፕሎማ ደረጃ ማስተማር ወሳኝ ነው። የልማት ፕሮጀክቶች ከላይ ጥሩ ሆነው ቢሰሩ እንኳን ከታች ያለው አስፈፃሚው አካል ዘርፈ ብዙ የሆነ (multi dimentional) ክህሎት እንዲኖረው ስለ ወጪ እና ገቢ ብቻ ሳይሆን ማወቅ የሚገባው ስለ ማህበራዊውም፣ፖለቲካውም፣በስራው ላይ ስለሚፈጠሩት  ውጭያዊ እና ውስጣዊ ተፅኖዎች ሁሉ መረዳት ይገባዋል የሚለው የትምህርቱ  አስፈላጊነት ዋና ነጥብ ነበር።
ይህንኑ ተከትሎ በወቅቱ ከነበሩት ጋዜጦች  የ ሪፖርተር ጋዜጣ በ ግንቦት 1/1996ዓ ም  በወጣው ዕትም ላይም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስለቀረበው ወረቀት እና እና ስለ ውይይቱ  ያቀረበልኝ ቃለ መጠይቅ  በፎቶግራፍ ተደግፎ ይገኛል።

አሁንም ይህንን ሃሳብ በሚገባ በፖሊስ አውጭዎች ዘንድ ከግንዛቤ እንዲገባ በነበረኝ ጉጉት የተነሳ ቀድሞ እሰራበት የነበረው የ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች ላለመስራት ነገር ግን ከልማት ሥራ ጋር የተያያዘ ሥራ መስራት አለብኝ ብዬ በ 1996 መጨረሻ ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት የስራ መደቡ ''የ ሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ኤክስፐርት'' ሥራ በ አዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ስር በነበረው የአነስተኛና ጥቃቅን ንግድስራ ማስፋፍያ ክፍል ውስጥ ተቀጠርኩ።ከነበሩት ፕሮጀክት ስራዎችን በተለይ በአነስተኛ እና ጥቅቅን ንግድ ዘርፍ ላይ የ ኢህአዲግ ትልቅ የአስራር ግድፈት የታየኝ ያኔ ነው።

አነስተኛ እና ጥቃቅን ንግድ ዘርፍ ለማንኛውም ሀገር ልማት ወሳኝ ነው።በምጣኔ ሀብት ጥናትም ይህ ዘርፍ ብዙ የሰው ኃይል ስለሚይዝ  እና የስራ ዕድል የመፍጠር ችሎታ ብቻ ሳይሆን ወደከፍታኛ ንግድም የማደግ እድሉ ብዙ ስለሆነ በእጅጉ ይበረታታል።ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የወጣለትን ገንዘብ ያህል ውጤት እያመጣ ነው ለማለት ይከብዳል። አዎን ብዙዎች ከእለት ጉርስ አልፈው ለጥሩ ነጋዴነት በቅተውበታል።ጥያቄው ግን በሚልዮን የሚቆጠር ብር በትክክል ሥራ ላይ አለመዋሉ እሙን ነበር።ይህ ብቻ ሳይሆን የሚደራጁት የንግድ ማህበራት የኢህአዲግ ደጋፊ እንዲሆኑ ተፅኖው ከባድ ነው።አንድፍሬ የሚያህሉ ልጆች ለመስራት ብድር ሲጠይቁ ወደፊት ምን እንደሚጠበቅባቸው ያውቃሉ። ቢያንስ በክፉ ኢህአዲግን አለማማት ለበረቱ ደግሞ አባል መሆን መጥቀሙን ለአራዳ ልጆች ግልፅ ነበር። የ 1997 ዓም ምርጫ ዋዜማ ሚያዝያ ሰላሳ ቀን  አንድ ወደ ስድስት ኪሎ አካባቢ ያለ ማህበር (ከ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በወሰደው ብድር የሚሰራ) አባላት ሰልፉ ላይ ነበሩ ተብለው በቀጣዩ አመት ብድር ከመከልከል አልፈው የተቀበሉትን ፈተና በወቅቱ የነበረ ሰው ያውቀዋል።ብድሩ ግን የሚያገኙት በኢትዮጵያዊነታቸው እንጂ በኢህአዲግ ደጋፊነት ፈፅሞ ሊሆን አይገባውም ነበር።
የአመለካከት ችግር አለባችሁ  የምንባለው ባለሙያዎችማ እንደጠላት መመልከት ልማድ ነበር።እኛ በአይምሮ የማሰብ መብታችንን  ማንም እንዳይነጥቀን እንሞክር ነበር። የግል ጋዜጣ መያዛችን ያውም በምሳ ሰዓታችን ላይ ብዙ ቅር ያሰኛቸው የነበሩ የስርዓቱ ደጋፊዎች ነበሩ። ለሁለት አመት  በ እዚህ ክፍል  ውስጥ ስሠራ ብዙ ፈተናዎችን አሳለፍኩ። የኢህአዲግን ግድፈት እና ችግር በትክክል እንድረዳም  አደረገኝ።
ቀድሞ እሰራ የነበረበት ሀብታሞች ብቻ የሚመጡበት ባንክ ትቼ  እታች ያለው የሸማነውን ችግር፣የ አነስተኛ ነጋዴውን ብሶት፣ሥራ ያጣው ወጣት ወገኔን እንግልት አየሁት። አንድ ቀን ''የ አመለካከት ችግር አለበት'' ተብዬው  እኔው ላይ የቡድን መሪው አንዲት ወረቀት እንዲፅፍብኝ     እንደተነገረው ነገረኝ። ለምን?አልኩት ''እኔም አላምንበትም ግን የአመለካከት ችግር አለብህ ደግሞ የግል ጋዜጣ ታበዛለህ'' አለኝ። እያፅናና ፃፈብኝ።ግን አላመንኩበትም አለኝ።ይህን የሚለኝ በጣም ስለሚያዝንልኝ እና  ህሊናው ስለከበደው ነበር። በሚቀጥለው ቀን ግቢው ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? አለ። የአለቃዬ አለቃም ሁኔታው አሳዘናቸው።ጠሩኝ እና ''ያ ደብዳቤ እንዳለ ይሁን አኔ ግን የምስጋና ደብዳቤ እፅፋለሁ አሉኝ።'' እሳቸው ደግሞ የምስጋና ደብዳቤ ፃፉልኝ ለእኔ የምስጋና ደብዳቤ ሲፅፉ ግን ለአንተ ብቻ ማለት ስለከበዳቸው ባንተ ሰበብ ለጠቅላላ ለክፍሉ ልጆች በሙሉ አደርገዋለሁ አሉኝ። አደረጉት።የወቀሳ ደብዳቤ ባመለካከት የምስጋና ደብዳቤ በስራዬ ተሰጠኝ።የሚገርመው ነገር የቅርብ አለቃዬ በምስጋናው ደብዳቤ ስላመነበት ማህተም ያደረገው እርሱው ሆነ።አልፈረድኩበትም የኢትዮጵያን ኑሮ የሚያውቅ ያውቀዋል።

በ እዛው ሰሞን የፍትህ ማጣት ስሜት ውስጤን ናጠው።እኔ ለሀገሬ  የማስበው እና እየሆነብኝ ያለው ተለያየ።ፒያሳ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፀዱ ጋር ቆሜ  አለቀስኩ።በሕይወቴ እንደዛች ቀን አልቅሼ አላውቅም።ከ ቤተክርስቲያኑ ወጣሁ እና ቭኦልስ መኪናዬን  አስነስቼ ወደ ሰፈሬ ነጎድኩ  ሰፈሬ ከመድረሴ በፊት ከነበረው ካፌ ገብቼ ሻይ መጠጣት አማረኝ ገባሁ።ቀድሞ ንግድ ባንክ አውቀው የነበረ ወዳጄ ሲያገኘኝ በደስታ አቀፈኝ።ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዘኔን እንደሰማኝ ታወቀኝ።'ፍጡነ ረድኤት' የሚለው መዝሙር ትዝ አለኝ።የድሮ ወዳጀ አሁን በወጋገን ባንክ  የክፍል (dipartment) ኃላፊ መሆኑን አጫወተኝ።ባንኩ ያወጣውን የስራ ማስታወቂያም ከያዘው ጋዜጣ ላይ አሳየኝ እና ለምን አታመለክትምም? አለኝ።ከዩጋንዳ እንደተመለስኩ የልማት ጥናት እያልኩ የምጮህለት ጉዳይ በሀገሬ ላይ አንደማይሆን  ከተረዳሁ ሰነበትኩ።እኔ ደግሞ የማላምንበትን የኢህአዲግ አባል ለመሆን አልችልም።(ላመኑበት አባል የመሆን መብታቸውን ባከብርም)።ስለሆነም ወደቀደመው የባንክ ሙያዬ መመለስ የግድ ሆነ።አስቤበት እደውልልሃለሁ አልኩት።በሚቀጥለው ቀን ተመልሶ ቢሮ መሄድ አስጠላኝ።ደወልኩለት እና አመለከትኩ።ለቃለመጠይቅ ተጠራሁ።አለፍኩ። ሌላ ሁለት አመት በደንበል ስድስተኛ ፎቅ ሥራ ተጀመረ።ከሙያው ስነምግባር አንፃር የባንክ ሥራ ዝርዝር አይወራም።ቢያንስ ለጊዜው እዚህ ላይ መግታት ይገባኛል። 

ሆኖም ግን አንዳንድ ሰዎች የምሰጣቸው አስተያየቶች ከባዶ ጥላቻ የሚመስላቸው ካሉ በሥራ አለም የነበረኝን ያህል የኢህአዲግን አሰራር በቅርብ የማወቅ ዕድል እንደነበረኝ እና  ችግሩን የምረዳው ባላየሁት ነገር ከሩቅ የሚመስላቸው ካሉ እንደተሳሳቱ  ይወቁልኝ።

እዚህ ኖርዌይ በጋብቻ እንደመምጣቴ ክፉ ደግ ሳይናገሩ ሀገርቤት እየገባሁ የመውጣት ችግር የሚኖርብኝ ሰው አይደለሁም።አንዳንድ ብሎጎች የስደተኛ መኖርያ ወረቀት ለማግኘት ተብለው የሚከፈቱ እንዳሉ አውቃለሁ።ስደተኘነትን የሚናፍቅ ሰው ማንም የለም።እኔም አልናፍቅም።ነገር ግን በውጭ ሀገር ሲኖር ለሀገር አንዳንድ ሃሳቦችን ማበርከት ይገባል ብዬ 'ጉዳያችን' ጡመራን ጀመርኩ። 
ምስጋና ለምዕራቡ አለም ሰው ሃሳቡን እንዲገልፅ ዕድል በመስጠቱ።ሆኖም ግን ማንም ምንም እንዳይተነፍስ አንቆ እረግጦ መያዝ የሚፈልገው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን 'የጡመራ'  መድረኩን ሲያውከው እና ከ አንድ አመት ወዲህ ደግሞ በመዘጋቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በተዘጉ ድህረገፆች መክፈቻ በኩል ከሚያነቡት በቀር ለተቀረው ሰው እንደማይነበብ ብዙ ወዳጆቼ ይነግሩኛል። ሆኖም ግን ብዙ ጊዜ ያዝ ለቀቅ ይደረግ ስለነበረ እና ደግሞስ 'ጡመራዬ  ታገደች' ብሎ ማውራት ምን ጥቅም አለው?የሚለው ሃሳብ ያይልብኝ ነበር እና ብዙ ማለቱ አላስፈላጊ ሆነ።ደግሞስ የስንቱ ሊቃውንት ጡመራ ታግዶ የእኔ ማን ሆና ይጮህላታል?ብዬ ማሰበም አልቀረም።ሰሞኑን ''የመናገር ነፃነት ይለቀቅ'' የሚለው ዘመቻ ሲጀመር ግን ''እኔን ያየህ አትቀጣ'' ለማለት ወሰንኩ።''ተቀጣ'' አደለም አትቀጣ ተስፋ አትቁረጥ ነው የምለው።የታደለ መንግስት መንገድ ላይ ከምለፈልፍ እብድ ይማራል።ያልታደለ ደግሞ ሃሳብ የመግለፅ ነፃነት አግዶ እንደጨለመበት ያሸልባል።

ባጠቃላይ የእኔ አይነት በ ሺህ የምትቆጠሩ የሀገሬ ዜጎች እንደኔ ይህን ለሀገሬ ብሰራ ብላችሁ ብትነሱ፣ህልማቸሁ ሁሉ የ ኢህአዲግ አባል ባለመሆናችሁ ብቻ የሚሰማችሁ ብታጡ፣አባል ለመሆን ደግሞ ያላመናችሁበትን ለመምሰል ቢያቅታችሁ፣ በአንድም በሌላም ከሀገር ወጥታችሁ ሃሳቤን በ ጡመራ መድረክ ልግለፅ ስትሉ ሀሳባችሁ ወደ ወገናችሁ እንዳይደርስ ብትታገዱ ተስፋ አትቁረጡ።

ይብቃኝ

ጌታቸው

ኦስሎ   

3 comments:

Teklu said...

ጌታቸው
ይሄ የብዙዎቻችን ችግር ነው ግን እንዳልከው ተስፋ አንቆርጥም ሊነጋ ነው ሚጨልመው እንደሰው ማሰበና ያመንበትን ከመናገርና ከመጻፍ ማንም አያግደንም በከባድ ርምጃ ወደፊት

ተክሉ

Anonymous said...

This short history need to be a case study which indicates how eprdf political system forced people to be its member. I have two friends who come across almost the sam history. Thank u Getachew. Instead of opposing just with out any base let us we also bring out our similar cases.
BH

Anonymous said...

ayanchi ager sntu endih yale chigr wust ynoral stamnbet hlinan meshet amlak yrdah sleewunet yeminageru betefubet zemen brta amlak yrdah