ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, February 8, 2013

ነፃነት ከየት ይጀምራል? (ግጥም) ለ እኔ ትውልድ

ዓመታት የቆዩ ሙታኖች ተነስተው ፣
ጉባኤ ከፈቱ ከሰማይ  ቤታቸው፣ 
ምንም እንኳ  ዘመን  ቢያልፉ በላያቸው ፣
የአመታት ክምር ቢያስጎነብሳቸው፣ 
ክፉ ቢሰሙባት ስለሀገራቸው ፣
ሁሉም ተንጠራሩ  አላስተኛ አላቸው፣ 
ጉባኤም ከፈቱ ከሰማይ ቤታቸው። 

ምኒልክ ካንኮበር ፣ዮሐንስ መተማ፣
ከዶጋሊ  አሉላ፣ ገብርዬ ካድዋ፣
የ አክሱሙ ካሌብ፣ ተከትላ ሳባ፣
ተፈሪ ንጉሡ ብሎም ላሊበላ፣
በ እልፍ አእላፍ ታጅበው  ጅፋር አባ መላ፣
ከያሉበት ነቁ፣ 
ግራ የተጋባን ትውልድ ሊጠይቁ።

አለህ? አንተ ትውልድ ትተነፍሳለህ? 
ነፃነት ትርጉሙ ዛሬም አልተረዳህ? 
ድርሻህስ ምንድነው? ጠይቀህ ታውቃለህ? 
ወይንስ እኛ ዳግም  ሀገር እናቅናልህ? 

ነፃነት ምንድነው?
ምንድነው ነፃነት ሰው የመሆን እውነት? 
ዝምታ?! አድርባይነት? ወይንስ ምትሃት መጠበቅ? 
አንዱ ውስጡ ሲነድ መዘበት መሳለቅ።

ምንድነው ነፃነት? ሰው የመሆን እውነት? 
መማር ዲግሪ መያዝ?ማግባት ልጅ ወልዶ ማሳደግ?
ለራስ ጥሩ መኖር ለአጥፊ ማደግደግ?
በዘር፣ በመንደሩ ከሚያስቡቱ ጋር ማሸብሸብ ማሸርገድ?
ምንድነው ነፃነት? ሰው የምሆን እውነት?

እንዲያ ቢሆንማ የነፃነት ትርጉም የተተገበረ፣
እምነት ነፃነትህ በመቃ ተመጦ ባዶ በነበረ።
ግና እንድያ አልተገኘም ነፃነት ሀገርህ ፣
ዛሬ እምትደምቅበት ክብር አንተነትህ።

ታድያ ምንድነው ነፃነት ሰው የመሆን እውነት?
ከነባራዊው አለም  'ሚታረቅበት።

እስኪ እንጠይቅህ ውስጥህ ምን ያወራል?
 ነፃነትህስ ከየት ይጀመራል?
ከ አደባባይ፣ ሜዳ? ወይንስ ከጫካ ውስጥ?
ወይንስ ከ ጉርቢያው ነው ከሸለቆው ከስርጥ?
ከየት ይጀመራል የነፃነት ወሽመጥ?


አመታት የቆዩ ሙታኖች ተነስተው ፣
ጉባኤ ከፈቱ ከሰማይ  ቤታቸው፣ 
ምንም እንኳ  ዘመን ቢያልፉ በላያቸው ፣
የአመታት ክምር ቢያስጎነብሳቸው፣ 
ክፉ ቢሰሙባት ስለሀገራቸው ፣
ሁሉም ተንጠራሩ  አላስተኛ አላቸው፣ 
ጉባኤም ከፈቱ ከሰማይ ቤታቸው። ግራ አትጋባ ነፃነት አንተው ነህ፣
መጀመርያ አንተ እራስህ ከራስህ፣
ነፃነትህን አውጅ፣
የውስጥ ስሜትህን፣አንተን የሚልህን፣
ስማው ህሊናህን እምነትህ ያለህን።
ግለፅ ሀሳብህን ተናገር ስሜትህን፣
አንተ ካንተው ሽሽተህ፣
የት ትደበቃለህ?
በማጀት ሌላ ሰው በአደባባይ ሌላ ለምን ታወራለህ?
ተናገር ይውጣልህ ስሜትህን አትደብቅ?
ሕሊናህን ካፍህ አስማማና አስታርቅ።

እናም ነፃነት፣
ሰው የመሆን እምነት፣
ካንተው ይጀምራል ፣
ሳትፈራ ተናገር በኑሮህ አታብል፣
ፃፈው ተናገረው ውስጥህ የሚልህን፣
አዋየው ለሌላ መራብ መጠማትህን፣
ነፃነት ለራስህ በራስህ ማወጅህን።

ስለዚህ ነፃነት አንተው ነህ ካንተው ይጀመራል፣
መናገር ስትጀምር እርሱም ይናገራል፣
ዝም ካልክ ዝም ነው ተጣጥፎ ይተኛል፣
ነፃነት አንተው ነህ አንተን ይማፀናል።


አመታት የቆዩ ሙታኖች ተነስተው ፣
ጉባኤ ከፈቱ ከሰማይ  ቤታቸው፣ 
ምንም እንኳ  አመታት  ቢያልፉ በላያቸው ፣
ዘመን በዘመን ላይ ቢደራርባቸው፣ 
ክፉ ቢሰሙባት ስለሀገራቸው ፣
ሁሉም ተንጠራሩ  አላስተኛ አላቸው፣ 
ጉባኤም ከፈቱ ከሰማይ ቤታቸው።

ጌታቸው በቀለ 
የካቲት 1፣ 2005 ዓም  

No comments:

በአማራ ክልል በሚደረገው ጦርነት ሳብያ የአማራ ክልል ህዝብ ላይ እየደረሰ ስላለው ሰቆቃ ያልሰማነው ከሰማነው ይበልጣል።

መከላከያ ክልሉን ለቆ ይውጣ የሚለው  አባባል የአማራ ክልል ጥያቄ ነው? ========== ጉዳያችን ምጥን ========= ወቅታዊው ሁኔታ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትልቁ አጀንዳ በአማራ ክልል በታጣቂዎች እና በ...