የ ሰሞኑ የ አዲስ አበባ ከራሞት እና የ ቴሌቭዥን ጣቢያዋ የ ዜና ርዕስ ''የ መከላከያ ሰራዊት ሳምንት'' ተከበረ የሚል ነበር።በ አዲስ አበባም የ ኢትዮጵያ ሰራዊት'' የደረሰበት የ እድገት ድረጃ'' ተብሎ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰሩ፣የተገጠሙ፣እየተባሉ የተነገሩ አውደ ርዕዮች ከመታየታቸውም በላይ በትናንትናው እለት በ አዲስ አበባ ስታድዮም ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም በተገኙበት ኢህአዲግ ለመጀመርያ ጊዜ ወታደራዊ ትርኢት አሳይቷል። መቸም ማንም ዜጋ የሀገሩ ሰራዊት ጠንካራ መሆኑን እና ሃገርን የመጠበቅ አቅም እንዲኖረው ይመኛል።ይህ ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳይ ነው።
አሁን ባለንበት አለም ውስጥ የወታደራዊ ጥበብ የ ጉልበት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውስብስብ እውቀትን እና ግንዛቤን የሚጠይቅ ሳይንስ ነው። ወደሚፈለገው የ እውቀት ደረጃ ለመድረስ ግን አንድ ሰራዊት ማሟላት የሚገባው ብዙ ነገሮች አሉ። በ ኢህአዲግ የተደራጀው የ ኢትዮጵያ ሰራዊትን ሳስበው ብዙ ያልተመለሱልኝ ጥያቄዎች አሉ። ከ እነኝህ ጥያቄዎች ውስጥ -
- ሰራዊቱ የቆመው ለስልጣን መጠበቅያነት ነው ወይንስ ለ ሕግ እና ለ ስርዓት ብቻ?
- ሀገር የመከላከል ሥራ እግረመንገድ የሚስራ ሥራ ነው ወይንስ ቅድምያ የሚሰጠው?
- ሉአላዊነት (soverginity) የሚለውን ቁልፍ ቃል ሰራዊቱ ከ ከፍተኛ መኮንኖች እስከ የመስመር መኮንኖች ብሎም እስከ ተራው ወታደር ድረስ በምን ያህል የ ዲግሪ ደረጃ ይረዳዋል?
- ሰራዊቱ ኢትዮጵያን እንዴት ነው የሚገልፃት?
- ሰራዊቱ በምን ያህል ደረጃ ከ አካባቢያዊ የ ወንዝ ስሜት እርቆ በ ብሔራዊ ስሜት ውስጥ ነው? መኮንኖቹ ምን ይህል አለምአቀፋዊ ስልታዊ (strategic) የኃይል አስላለፎችን ይረዳሉ? የመተንተን አቅማቸውስ? ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የምነሱብኝ ጥያቄዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ታሪኮች ውስጥ ነፃነት እና ሉአላውነቷን አስከብራ የኖረችው በእየዘመኑ የነበሩት መሪዎቿ ለሁለት ነገሮች ተገዢ ስለነበሩ ነው። ይሄውም አንዱ ለ እግዚአብሔር ሁለተኛው ለ ሀገራቸው ፍቅር። ዛሬ ላይ ሆነን አፄ ምኒልክን ''ለምን ማይክሮሶፍት ኮምፕዩተር አልተጠቀሙም? አፄ ዮሐንስ ለምን በዶዘር የሊማሊሞን አቀበት አላፈረሱም? '' መሰል ጥያቄ ካልጠየቅን በስተቀር በዘመናቸው መስራት የሚገባቸውን በነበረው ቴክኖሎጂ፣የአቅም ውሱንነት፣ብድር እና እርዳታ ከመላው አለም እየጎረፈላቸው ሳይሆን በ ባዶ እግሩ የሚሄድ ሰራዊት ይዘው ይችን ሀገር እንደ ሀገር ከሙሉ ክብር እና ማዕረግ ጋር አስረክበውናል።
ጥንታዊው የ ኢትዮጵያ ወታደር
መደነቅ ከተገባን ከየትኛውም የ ወታደራዊ የትምህርት ተቁዋም ሳይመረቁ አለምን ባስደነቀ የ ወታደራዊ ስልት አድዋ ላይ ድል ያደረጉትን ፣ዶጋል ላይ ያንቀጠቀጡትን፣ምፅዋ ላይ የተናነቁትን ማሰብ እና መዘከር ተገቢ ነው። ኢህአዲግ የ ኢትዮጵያ ሰራዊት በዓል ብሎ ለማክበር ብቻ ሳይሆን ለማሰብ እራሱ ሃያ አንድ አመት ስለፈጀበት የሚያዝኑ የመኖራቸውን ያህል። ለምን አሁን? የሚሉ ጥያቄዎች ግን በብዛት የሚነሱ ናቸው።
ወንድምን ገድሎ ሃውልት መስራት
ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ የመጀመርያውን ወታደር (ወጥቶ አደር) በ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመን መመስረቷ እና በኃላ በፋሺሽት ጣልያን ላይ ከ አርበኞች ጋር የተፋለመው የ ጥቁር አንበሳ ጦር ቀጥሎም በቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ በምድር ጦር፣በ አየር ኃይል እና በ ባህር ኃይል ደረጃ መዋቀሩ ይታወቅል።ኢህአዲግ እንግዲህ ይህንን ለዘመናት የተገነባውን ሰራዊት በ 1983 ዓም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር መበተን የመጀመርያ ስራው ነበር።ሀገሪቱ የ ውጭ ምንዛሪ አውጥታ ያስተማረቻቸው ምርጥ መኮንኖችን ''የታገሉት ለህዝብና ለ ሃገር ነው'' ብሎ በሥራ ገበታቸው እንዲገኙ ከማድረግ ይልቅ በእየእስርበቱ 'ጉዳያችሁ እስኪጣራ' እያለ አጎራቸው።የተቀሩት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀገር ትተው እንዲሄዱ ተደርጉ የተረፉት ደግሞ በሀገርቤት ከግል ንግድ እስከ በመንገድ ላይ ወጥቶ እስከመለመን ደረሱ።በ ሽምቅ ውግያ እና በ ቆረጣ የሚታወቁት የ ኢህአዲግ ሰራዊት በ ተቀረው አለም ከ ሃያ አምስት እስከ ሰላሳ አመት የሚፈጀውን የ ከፍተኛ መኮንነት ማአረግ በ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጎናፀፉ ተደረጉ። ጀነራሎች፣ኮለኔሎች ሆኑ።
ይህ ብቻ አይደለም የ ሰራዊቱ ቤተሰቦች ከ ሁለት እና ከ እዛም በላይ ትውልድ ይኖሩበት የነበሩትን ቤቶች በተለይ በካምፕ አካባቢ የነበሩትን በሙሉ በ አንዲት ጀንበር እንዲለቁ ተደረጉ።ቤተሰብ ተበተነ ልጆች ለጎዳና ተዳዳሪነት ተጋለጡ። የቀድሞ ሰራዊት አባላት የነበሩት ምንም አይነት የ ዘር እና የወንዝ ስሜት የሌላቸው የ ሀገር ፍቅር እና ሉአላዊነት በሚል ፍቅር የተቃጠሉ ዜጎች በሜዳ ተበተኑ። ከ ኢህአዲግ ባለስልጣናት አንድም እነኚህ እኮ የሀገር ሰራዊት ናቸው። ዛሬ እንድንቆም ያደረጉን ከሱማሌ ጋር ተናንቀው ሀገር ያዳኑ ናቸው ያለ አልነበረም።
በ እዚህ ብቻ አልተገታም ኢትዮጵያ ሃውልት የምትሰራው ከ ባእዳን ጋር ላደረገችው ጦርነት እንዳልነበር ኢህአዲግ ወንድም ከወንድሙ ጋር ለተጋደለበት አሳፋሪ ታሪካችን እንደ ትልቅ ገድል ሃውልት አቆመ። ሃውልቱንም ''ድላችን'' አለው። ሆኖም ግን ከወንድምህ ጋር ላደረከው ጦርነት ሃውልት ማቆም መጪው ትውልድ እንዲቆስል ነው? ቀድሞ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ጊዜም ሆነ ከ እዛ በኃላ ብዙ የ እርስ በርስ ጦርነት ነበሩ። ግን ነገሥታቱ ወንድሜን ገድልኩ ብለው ሃውልት ሰርተዋል? ብሎ ለሚጠይቀው ኢህአዲግ መልስ የለውም። እውነት ግን የትኛው ንጉስ የቱን ደጃዝማች ገደልኩ ድል አደረግሁ ብሎ ሃውልት ሰራ? ኢህአዲግ ግን ከወገኑ ጋር ላደረገው ደም መፋሰስ አድርጎታል።
መቀሌ የሚገኘው ወንድማማቾች ደም መፋሰስ ተምሳሌት (የ ኢህአዲግ የ ''ድል'' ሃውልት)
እንግዲህ የ ኢትዮጵያ የ ሰራዊት ቀን ሲከበር ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ሁሉ መታሰብ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ብለን ስንጠራ ከ ሙሉ አካሏ እና ታሪክዋ ጋር መሆን አለበት። አንዲትን ሴት እጇን ትተን ወይንም እራሷን ቆርጠን ሌላ አካሏን እያነሳን ሴት ብለን መጥራት እንደማንችል ሁሉ ኢትዮጵያንም መነሻዋን ያወቀ ሰራዊት መድረሻውን የሚረዳ መኮንን ሲኖራት ነው ሰራዊቱ የ ሕዝብ ስሜትን የተጋራ አብሮት ሊሞት የቆመ ልብ ማግኘት የሚቻለው።ከ እዚህ ውጭ እንዴት ነው ገና በ ሀገሪቱ ያለፈ ታሪክ ላይ ሙሉ በሙሉ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን መተማመን ላይ ያልደረሱ መኮንኖች የ ኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚያስከብሩት?
አባት ያቆየውን በማፍረሱ የሚመፃደቅ ሰራዊት
የ ኢትዮጵያ ሰራዊትን ከ ጅቡቲ እና ሱዳን ጋር እያወዳደርን አድገናል ተመድገናል ማለት ተገቢ አይደለም። በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ የነበሩ እና ነፃነታቸውን ካገኙ ገና አመታት ያስቆጠሩ ሃገራት የ ኢትዮጵያ መለክያ እና ማነፃፅርያ ሊሆኑ አይችሉም። በመጀመርያ እኛ ማን ነን?የት ነበርን? አሁን የለንበት መድረስ የሚገባን እና ልካችን ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው።
አንድ ብርጭቆ ውሃ ያለውም ሆነ አንድ ባልዲ ውሃ ያገኘ ሁለቱም ብዙ ውሃ አለኝ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።ግን ባለ ብርችቆው ብዙ ውሃ አላኝ ያለው አቅሙን እና ሊኖር የሚገባውን ካለመረዳት ከሆነ ችግር ነው።ኢትዮጵያ በ አየር ኃይልም ሆነ በ ባህር ኃይል አቅሟ ሌላው ቀርቶ ስጋት ብላ ታስብ የነበረው ከ መካከለኛው ምስራቅሃገራት የሚሰነዘረውን ጥቃት እንጂ በ ጎረቤት ደረጃ አልነበረም።በ 1969 ዓም ሱማልያ በኢትዮጵያ ላይ የ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ ያነሳችው በወቅቱ የነበረው የ ሀገሪቱ ውስጣዊ ችግር የልብ ልብ መስጠቱ እንጂ የ ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም ከሚገባው በታች ወርዶ አይደለም።እርግጥ ነው በወቅቱ የ አሜሪካ መንግስት እስካፍንጫው በ ቀድሞዋ ሶቭየት የታጠቀውን የ ሶማልያ ጦር ኢትዮጵያ እንዳትዋጋ የ ጦር መሳርያ ግዢ ማዘግየት መፈፀሙ በወቅቱ ቶሎ ወደውግያው ላለመግባት የቀረቡ ምክንያቶች ነበሩ። ሆኖም ግን በ አየር ኃይሉም ሆነ በ ምድር ጦር ደረጃዋ ጥሩ ነበር።ለ እዚህም ነው ኢትዮጵያ ሱማልያን ባብዛኛው የተዋጋችው በ ሚሊሻ ጦር የሆነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከ አነሳሷ ጀምሮ ኢህአዲግ ሰራዊቱን በትኖ ወደኃላ ባይወስዳት ኖሮ ዛሬ መወዳደር ያለብን ከ ደቡብ አፍሪካ እና እንደ ቱርክ ከመሰሉ ሀገሮች ጋር ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።
የ ኢትዮጵያ የ ባህር ኃይልን አፄ ኃይለ ስላሴ ሲጎበኙ
ለ እዚህ ማስረጃ የሚሆነው የባህር ኃይላችን የነበረበት ደረጃ ነው።የ ኢትዮጵያ ባህር ኃይል አቅም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ጋር የሚወዳደር እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩለታል።በተደጋጋሚ ከ ሻብያ ጋር በተደረገው ውጊያ በሰው ኃይልም ሆነ በማቴርያል እያገዘ የኢትዮጵያን የ ባህር ኃይል ያዘጋው ኢህአዲግ ዛሬ የ ኢትዮጵያ የሰራዊት ቀን ብሎ ሲያከብር አያምርበትም።
ኢትዮጵያ በዘር በጎሳ የሚያስብ ሰራዊት ኖሯት አያውቅም።ዘራይ ድረስ እና አብዲሳ አጋ ጣልያንን በሀገሯ ያንቀጠቀጧት፣ አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን የተዋጉት፣ምፅዋ ላይ በ 1980ዎቹ መጀመርያ ላይ የረገፉት የ ኢትዮጵያ ወታደሮች ከምንም በላይ ክልላዊ ስሜት ሳይሆን ክብርት ለሆነች ለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መሆኑ መጀመርያ ማመን ከሁሉ በፊት ይቅደም።ወደድንም ጠላንም ዛሬ ላለንበት እኛነት መሰረቶቻችንን ማክበር ካልቻልን የሚያከብረን አለመኖሩን ማሰብ አለብን።
በመጨረሻም ከ ኢህአዲግ በፊት የነበረው የ ኢትዮጵያ ሰራዊት ከመኮንን እስከ ተራ ወታደር የሀገር ፍቅርን ቅድምያ የሚሰጥ የወንዝ ስሜት ያልገዛው መሆኑን ለመረዳት የ 1953ዓም የ መንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በ አፄ ሃይለስላሴ ላይ ያደረጉት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እና በ 1981ዓም በ ኮለኔል መንግስቱ ላይ የተሞከረው የመፈንቅል ሙከራ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል። ይሄውም ሰራዊቱ ምን ያህል የ ህዝብን እና የሀገርን ጉዳይ ከንጉሡ እና ከ ኮለኔል መንግስቱ በላይ እንደሚመለከት አመላካች ነው።
ለ እዚህ ማሳያ የ ሜጀር ጀኔራል ደምሴ ቡልቶን ታሪክ በትንሹ የሚያሳይ ቪድዮ ማየቱ ጠቃሚ ነው።ሜጀር ጀነራል ደምሴ የ ኢትዮጵያን አየር ወለድ ከመሰረቱት አንዱ ናቸው።በ ሱማሌም ሆነ በ ኤርትራ ጦርነት ላይ ሲዋጉ የኖሩ በኃላ ግን በ ኮሎኔል መንግስቱ ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሲያደርጉ በእራሳቸው በመሰረቱት የ አየር ወለድ የተገደሉ የጦር መኮንን ነበሩ።
ዛሬ የ ኢትዮጵያ የ ሰራዊት ቀን የሚከበረው እንዲህ አይነት ለሀገር የሞቱ ደርግን እራሱን ሲዋጉ የነበሩ ጀግኖች ተረስተው ነው።ባጭሩ ግን ኢህአዲግ የ አትዮጵያን የ ሰራዊት ቀን ሲያከብር አላማረበትም።
የ ጀነራል ደምሴ ቡልቴ(ቪድዮ)
አበቃሁ
ጌታቸው
ኦስሎ
2 comments:
betam tiliq netib new yanesahew. biruh astesaseb yaleh lij neh.berta
U r great. Ur focus point is very powerful.
Post a Comment