ከመንግሥቱ ጎበዜ
ሉንድ ዩንቨርስቲ፣ ስዊድን
1. ምክንያተ ጽሑፍ
በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያዊነት መከበሪያ፣ መታፈሪያ እና ተፈልጎ የማይገኝ ማንነት ነበር፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም የፍትህ አደባባይ፣ የስደተኞች መጠጊያ፣ ለግፉዓን ዘብ የምትቆም፣ በእምነቷ የምትታወቅ መንፈሳዊት ሀገር ነበረች፡፡ዛሬ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ኀያላን መንግሥታት እንደ ሀገር ሳይቆሙ እና መኖራቸውም ሳይታወቅ ኢትዮጵያ ኀያል ገናና እና በስልጣኔዋ የታወቀች ስለመሆኗ የጥንት መዛግብት ተባብረው ይመሰክራሉ::
ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ በኢትዮጵያዊነትና በአገር አንድነት ዙሪያ በማኀበራዊ የመገናኛ ብዙኀን እየተደረጉ ያሉ ሙግቶች ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ገጾች ከሚሰራጩት ጽሑፎች መረዳት እንደሚቻለው በስደት ባሉ አንድአንድ ወገኖች ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኝነት በታች የሆነ: ከዚህም አልፎ በጥቂቶች የተጫነ ማንነት ተደርጎ በመወሰድ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአብሮነት ልዩነትን: ከትልቅነት ትንሽነትን መርጠው የፈጠራና የተዛባ ታሪክ በመጥቀስ ኢትዮጵያዊነትን በማንኳሰስ ጎሰኝነትን ለማንገስ እና የአገር አንድነትን ለማፍረስ ሲቃዡ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ በአያት ቅድመ አያቶቻችን ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት ተከብሮ የኖረው ኢትዮጵያዊነትና የአገር አንድነት አዲስ እንደተፈጠረ ማንነት የመነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ከማየት በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ?
በመሆኑም ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልምና እኔም በኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መነሻ ዙሪያ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ይህችን መጣጥፍ ሳቀርብ የጎደለውን ሞልታችሁ የተሳሳተውን አርማችሁ በጥሞና እንደምታነቡልኝ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ የጽሑፉ ዋና አላማ ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያ በጥንቱ መዛግብት እንዴት እንደተገለፁ ማሳየት እንጂ መረጃዎችን መተንተን ወይም መተቸት አይደለም።
2. ስያሜ
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እጅግ ጥንታዊ የሆነና ያልተቋረጠ ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ ያላት አገር ነች፡፡ ብዙዎቹ እንደሚስማሙበትና የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ታሪክ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ይሳባል፡፡
አገራችን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን የስያሜዋን ምክንያት በተመለከተ ሦስት አይነት ትውፊታዊ ግምቶች ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክኛ ቋንቋ የተወሰደና ትርጉሙም ፊቱን ፀሃይ ያቃጠለው (burned face) ማለት ነው ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቅዱስ መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሰውና ኢትዮጵያን ያቀና ነው ተብሎ የሚነገርለት የካም ልጅ ኩሽ (ዘፍ 10÷6) “ኢትዮጵስ” በሚባለው ሌላኛው ስሙ ምክንያት አገራችን ኢትዮጵያ ተብላ መጠራት እንደጀመረች ያትታል፡፡ ሦስተኛው በቅድመ ልደት ክርስቶስ በአገራችን ከነበሩ ነገሥታት መካከል አንዱ ’ኢትዮጵስ’ ይባል ስለነበር አገራችንም በኢትዮጵስ ኢትዮጵያ የሚለውን መጠሪያ አግኝታለች የሚለው ግምት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ’ኢትዮጵያ’ የሚለውን የአገራችን መጠሪያ ስም ከክርስቶስ ልደት ስምንት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ በጽሑፍ መዛግብት ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡
ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለመጠቀም ጥንታውያን ግሪኮች የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ለዚሁም ከክርስቶስ ልደት ስምንት መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የታላቁ ባለቅኔ ሆሜር ኦልያድና ኦዲሴ የተባሉ ድርሰቶችና የታሪክ አባት ተብሎ የሚጠራው ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የሄሮዶቱስ መጽሐፍ ዓይነተኛ ምስክሮች ናቸው፡፡ ከጥንት ግሪኮች በፊት ኢትዮጵያ በጥንት ግብፃውያን የኩሽ ምድር ተብላ ትጠራ እንደነበር የሚያመክቱ ማስረጃዎችም አሉ፡፡ አገራችን አቢሲኒያ: ምድረ ሀበሻ ወዘተ የሚባሉ ሌሎች መጠሪያዎችም እንደነበሯት ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ የሚለው ስም በቅዱስ መጽሐፍ ከአርባ ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በእብራውያን (አይሁዶች) ዘንድ ቶራህ ተብሎ በሚታወቀው እና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓመተ ዓለም ገደማ እንደተጻፈ በሚታመነው በመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ቀድማ በሁለተኛነት ተጠቅሳለች (ዘፍጥረት 2÷13)፡፡
ኢትዮጵያ ከሚለው ጥንታዊ መጠሪያ ጋር የቀደምት ነዋሪዎቹ (የሕዝቦቹ ) ማንነት ጉዳይ ተያይዞ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ በቁጥር ቀላል የማይባሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ማለት በግሪክኛ ፊቱን ፀሃይ ያቃጠለው (burned face) ማለት ስለሆነ ቀደምት ነዋሪዎቹም ጥቁር (deep dark skin) ሕዝቦች ነበሩ ብለው ይገምታሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ተጨማሪ የታሪክ መዛግብትን በአስረጅነት በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከመሠረቱ ጥቁሮችን ጨምሮ ስብጥር መልክ (mixed color) ሕዝቦች መኖሪያ ነበረች ይላሉ፡፡ ለምሳሌም በቅዱስ መጽሐፍ ነብዩ ኤርምያስ ‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን: ነበር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን›› (ኤር 13÷23) የሚለውን በመጥቀስ በንፅፅር የተነገረ የኢትዮጵያውያንን ሕብረ ቀለም (መልከ ብዙኀነት) የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡ ግሪካዊ ሆሜር በኦልያድ ቅኔው የኢትዮጵያ ሰዎች በውበት የተደነቁ ናቸው በማለት ገልጿቸዋል፡፡ የታሪክ አባት ሄሮዶቱስ ደግሞ በሦስተኛው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ከሰዎች ሁሉ በውበትና በቁመት የሚበልጡ ኃያላን ናቸው ይላል፡፡ ከነዚህ እና ከመሳሰሉት ጥንታዊ መዛግብት በመነሳት አገራችን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በዚያን ዘመን በነበረው መልከዓ ምድራዊ ክልል ይኖሩ የነበሩ የቀደምት የሕዝቦቿን ህብረ መልክዕ (ስብጥር የቆዳ ቀለም) መሠረት በማድረግ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አለ፡፡
3. ወሰነ ክልል
የጥንቷን ኢትዮጵያ ወሰነ ክልል በተመለከተ ከዚህ እስከዚህ ድረስ ነበር ብሎ በትክክል ለመናገር አያስደፍርም፡፡ እንደ ጥንታዊ መዛግብቱ ከሆነ እጅግ ሰፊ የሆነና በተለያየ ዘመናት አንዴ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ጠበብ ሲል የነበረ ሆኖም ግን የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማዕከል ያደረገ እንደነበር መረዳት አያዳግትም:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 1400 ዓ.ም. ገደማ የተጻፈው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ (ኦሪት ዘፍጥረት) ከኤደን ገነት የሚመነጨው ሁለተኛው ወንዝ ጊዮን የኢትዮጵያን መሬት ይከባል በማለት የዛን ጊዜዋ ኢትዮጵያ መሠረቷ የአሁኗን ኢትዮጵያን ጭምር እንደሚያካትት ይጠቁማል (ዘፍ. 2÷1):: በሌላ የብሉይ ኪዳን የዕብራውያን መጽሐፍ ‹‹አርጤክስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በ127 አገሮች ላይ ነገሠ (አስቴር 1÷1÷8÷9) በማለት መልክዓ ምድራዊ ፍንጭ ሰጥቷል:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 687 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረው ነብዩ ኢሳያስ ደግሞ ቲርሐቅ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ግብፅ ድረስ ያስተዳድር እንደነበረ ገልጿል (ኢሳ. 37 ÷9-11፣ 1ኛ ነገሥት 19:9)፡፡ የዚህ ጥቁሩ ፈርኦን በመባል የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ንጉስ በአርኪኦሎጂ ጥናትም የተረጋገጠ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ690-664 ዓ.ዓ. ግብፅን ያስተዳድር አንደነበር ተመዝግቧል፡፡
የጥንት ግሪኮች ኢትዮጵያ ደግሞ ሰፊ መልከዓ ምድራዊ ግዛትን ያካለለ ሲሆን ከግብፅ በስተደቡብ ያለውን አጠቃላይ የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ክፍል ‹‹ኢትዮጵያ›› በማለት ይጠሩት ነበር፡፡ ሆሜር በድርሰቶቹ ኢትዮጵያ ትሮይንና የዓረቡን ምድር ትገዛ እንደነበር ገልጿል፡፡ ሄሮዱቱስ ስለኢትዮጵያ ሲያነሳ የአባይ ወንዝና ትልቁን ሐይቅ በማመልከት የመልከዓ ምድራዊ ጥቆማ ሰጥቷል፡፡ ፕሊኒ የተባለው ሌላው ግራካዊ ኢትዮጵያ በጥንቱ ዘመን ሃያልና ዝነኛ እንደነበረችና ሶሪያንና እስከ ሜድትራኒያን የባህር ዳርቻ ድረስ ትቆጣጠር እንደነበር ጽፏል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት 60 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረ ዲኦዶረስ ሲኩለስ የተባለ ጸሐፊ ደግሞ ኢትዮጵያ የግብፅ ትውፊትና ስልጣኔ መነሻ መሆኗንና ኢትዮጵያውያን እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ ያስተዳድሩ እንደነበር ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን የነበረ ትራቦ የተባለ ሌላኛው የግሪክ ጸሐፊ የኢትዮጵያ ግዛት ዓረብን ብቻ ሳይሆን እስከ አውሮፓ ድረስ እንደሚዘልቅ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የግዛት ክልል ቀይ ባህርን ተሻግሮ ደቡብ ዓረቢያ ድረስ ይዘልቅ እንደነበር የታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመኑ ኢዛናና የ6ኛው መቶ ክ/ዘመኑ ካሌብ የመታሰቢያ ሃውልት ጽሑፎች አይነተኛና ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ አስቀድሞ እንደተገለጸው ምንም እንኳ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ወሰነ ክልል በትክክል ለመናገር ባይቻልም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ3ኛውና ከ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ያሉ ማስረጃዎች የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ አክሱምን ማዕከል ያደረገና ከአሁኑ ኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደነበር ያመለክታሉ፡፡
4. የጥንት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መታወቂያዎች
የጥንቷ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሌሎች ዘንድ የተከበሩ፣ የሚታፈሩ፣ የሚደነቁ፤ በእምነታቸው ቀናኢነት፣ በፍትሃዊነት፣ በደግነት፣ በትህትና እና በሌሎች መሰል መልካም ምግባራት የሚታወቁ እንደነበር የሚመሰክሩ በርካታ መዛግብት አሉ፡፡ ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር ኢትዮጵያውያን በጠባይ ጭምቶችና ትህትናን የተሞሉ ናቸው በማለት ጽፏል፡፡ ሆሜር በማከልም ኢትዮጵያውያን በፍትሃዊነት እና እኩልነት የታወቁ በመሆናቸው አምላክ ከመኖርያው ከሰማይ ወርዶ ዘወትር እነርሱን ይጎበኝ ከእነርሱም ጋር በዓል ያደርግ ነበር ብሎ ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረው የቢዛንታይኑ እስጢፋኖስ ኢትዮጵያውያን በፍህታዊነታቸው ምክንያት በአምላክ የተወደዱ ነበሩ በማለት ገልጿል፡፡ በመቀጠልም ይሕ ጸሐፊ ኢትዮጵያ በምድራችን መጀመሪያ የተመሠረተች አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያውያንም አምልኮተ እግዚአብሔርን በማስተዋወቅና ህግን በመስራት በዓለም የመጀመሪያ ህዝቦች ናችው ብሏል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን በእምነታቸው የታወቁ በምግባራቸው የተደነቁ እንደነበሩና አገሪቱም ሀገረ እግዚአብሔር እንደሆነች በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› (መዝ. 67 (68)÷31) በማለት የገለጸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እስራኤላውያንን ከግብፅ የፈርኦኖች አገዛዝ ነፃ ያወጣቸውና ባህረ ኤርትራን ከፍሎ ያሻገራቸው ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ለጋብቻ መርጧል (ዘኁልቁ 12÷1)፡፡ ከኢትዮጵያዊ አማቱም ልዩ ልዩ ምክሮችን ይቀበል ነበር፡፡ በቤተመንግሥት ባለሟል የነበረው ኢትዮጵያዊ አቤሜሌክ ነብዩ ኤርምያስን ከጉድጓድ እንዲወጣ አድርጎ ከሞት አትርፎታል (ኤር. 38÷7¬-13)፡፡ በትንቢተ አሞፅም “የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም” (አሞፅ 9÷7) በማለት በእግዚአብሔር ዘንድ ልቀው የተገኙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ነብዩ ኢሳኢያስ ግብፅን ይገዛ የነበረው ቲርሐቅ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ከአሦራውያን ጥፋት እንዳዳነ ጽፏል (ኢሳ. 137÷10-11)፡፡ ነብዩ ናሆም ኢትዮጵያና ግብፅ የነነዌ ጠንካራ ደጋፊዎች እንደነበሩ ገልጿል (ናሆም 3÷9)፡፡ የሰለሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘችው ንግሥት ሳባ ‹‹አንተን የወደደ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን›› (1ኛ ነገ.10÷25) በማለት እምነቷን ገልፃለች: ፈጣሪዋን አመስግናለች፡፡ በትንቢተ ሶፎንያስ ‹‹ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበተኑት ሴት ልጆቼ ቁርባኔን ያመጡልኛል›› (ሶፎንያስ 3÷10) በሚል ተመዝግቧል፡፡ መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ኢትዮጵያውያንን የፅዮን ልጆች ብሎ ጠርቷቸዋል (መዝ 86(87) ÷ 4-5) ፡፡በዘመነ ሃዲስ የትንቢተ ኢሳኢያስን መጽሐፍ በማንበብ ላይ የነበረውን ኢትዮጵያዊውን የንግሥት ህንደኬ ባለሟል (ጃንደረባው) ሐዋርያው ፊሊጶስ የምታነበውን ታስተውለዋለህን ብሎ ሲጠይቀው የሚመራኝ (የሚነግረኝ) ሳይኖር ይህ እንዴት ይሆናል በማለት የመለሰው መልስ ፍፁም ትህትናውንና መንፈሳዊነቱን ይገልጻል (የሐዋ. ሥራ 8÷26-40) ፡፡
ስለነብዩ ሙሐመድ የህይወት ታሪክ በሚያወሳው ታላቁ የእስልምና የትውፊት መጽሐፍ ነብዩ ሙሐመድ በወገኖቻው በመካ ቋሪሾች ሲሳደዱ ለነበሩት ተከታዮቹ ‹‹ወደ አቢሲኒያ ብትሄዱ ማንንም የማያሳድድ ደግ ንጉሥ ታገኛላችሁ:: ይህ አገር የእውነተኞች ምድር በመሆኑ እግዚአብሔር ከመከራችሁ ያሳርፋችኋል›› በማለት ወደ ኢትዮጵያ እንደላካቸው ተዘግቧል፡፡ በወቅቱ የነበረው ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ንጉሥም ከየት መጣችሁ፣ እነማን ናችሁ፣ እምነታችሁ ምንድን ነው ሳይል በክብር ተቀብሎ ማረፊያ በመስጠት ክፉውን ቀን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ ከልዩ ልዩ የግሪክና የሮማ ግዛት በሃይማኖታቸው ምክንያት የተሰደዱ ክርስቲያን መነኮሳት ኢትዮጵያ መጠጊያ እንደሆነቻቸውና እነርሱም በምድረ ኢትዮጵያ ገዳማትን በማስፋፋትና መጽሐፍትን በመተርጎም ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ታሪኮች ከሆነ ኢትዮጵያ እምነት፣ ቀለምና ዘር ሳትለይ የስደተኞችን መብት በማክበር በዓለማችን ቀዳሚዋ አገር ሳያደርጋት አይቀርም፡፡
በርካታ ጥንታዊ መዛግብት ኢትዮጵያ ሃያል አገርና በልዩ ልዩ ማዕድናት የበለፀገች ምድር እንደነበረች ይገልፃሉ፡፡ ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር ኢትዮጵያውያን በጉልበት ሃያላን ነበሩ በማለት ጽፏል፡፡ ሄሮዶቱስ ደግሞ የአባይ ወንዝ የሚመነጭበት፣ የወርቅ ማዕድን በብዛት የሚገኝበት ትልልቅ ዝሆኖች ያሏት እና የተለያዩ ዓይነት ዛፎች (ዕፅዋቶች) የሚበቅሉባት አገር እንደሆነች መዝግቧል፡፡ ዴኦዶሮስ የተባለው ጸሐፊ ደግሞ ኢትዮጵያ ሀብታም፣ በወርቅ ማዕድን የበለፀገች፣ ጠንካራ አስተዳደር ያላት፣ በጠንካራ ነገሥታትና በህግ የምትመራ አገር እንደነበረች ገልጿል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ዛራህ የተባለ ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰራዊት ይመራ እንደነበር ተገልጿል (2ኛ ዜና 14÷9)፡፡ የሳባ ንግሥት ለጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን በርካታ የከበሩ ማዕድናትን በስጦታ ማበርከቷ ተጽፏል (1ኛ ነገሥት 10÷1-13)፡፡ በነብዩ ኢዮብ ደግሞ ኢትዮጵያ ከጥበብ ጋር የተነፃፀረ ቶጳዝዮን የተባለ የከበረ ማዕድን መገኛ እንደሆነች ተጠቁሟል (ኢዮብ 28÷9)::
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረው ማኒ የተባለው ጸሐፊ አክሱምን ማዕከል ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል በሦስተኛ ደረጃ አስቀምጧታል (መንግሥታቱም ሮም፣ ፐርሺያ፣ አክሱምና ቻይና ነበሩ)፡፡ የቢዛንታይኑ ንጉሥ ኮንስታንቶስ 2ኛ (ነገሠ እ.ኤ.አ 335-336 ዓ.ም) ኢትዮጵያን ከጎኑ ለማሰለፍ የዲፕሎማቲክ መልዕክት በመላክ ጥረት አድርጓል፡፡ ሌላኛው የቢዛንታይን ንጉሥ ጁሰቲን ቀዳማዊ (ነገሠ እ.ኤ.አ 518-526 ዓ.ም) በደቡብ ዓረቢያ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ከአይሁድ መከራ እንዲታደጋቸው ለኢትዮጵያዊ ንጉሥ አፄ ካሌብ ተማፅኖ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ አፄ ካሌብም ባደረገው ዘመቻ ክርስቲያኖችን ነፃ አውጥቷል፡፡ ተከታዩ የቢዛንታይን ንጉሥ ታዋቂው ጁስቲንያን (ነገሠ እ.ኤ.አ 526-565 ዓ.ም) ደግሞ ከፐርሺያ ጋር ሊያካሂድ ላሰበው ጦርነት የኢትዮጵያን ድጋፍ ለማግኘት የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞቹ መላኩ ታውቋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ማሳያዎች አገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሕዝቦችና አገሮች ደህንነትና ነፃነት ታደርግ የነበረውን ድጋፍና በወቅቱ የነበራትን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት፣ ክብርና ሚና የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
በጥንቱ የታሪክ ዘመን ስለነበረው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ብዙ ነገር ለማንሳት ቢቻልም አንባቢን ላለማሰልቸት ስል በቀጥታ ወደማጠቃለያየ አልፋለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በወፍ በረር የተነሱት እስከ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ያሉት የተወሰኑ ታሪካዊ ኩነቶችና ማስረጃዎች ስለሆኑ እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ከሰጠኝ ሌሎች ያልተነሱ ጉዳዮችንና የቀጣይ ዘመናት ታሪካዊ ክስተቶች በሌላ ጽሑፍ የምመለስባቸው ይሆናል፡፡
5. ማጠቃለያ
አስቀድሞ ከቀረበው ጽሑፍ መረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምሥረታ በጥቂት ጎሳዎች፣ በውስን የቦታ ክልል፣ በጥቂት ቋንቋ ተናጋሪዎች ወዘተ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ዘር፣ ቋንቋ፣ ጎሳ፣ ቀለም፣ የተወሰነ የቦታ ክልል በመስፈርትነት አልተቀመጠም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሁሉም የአገራችን ሕዝቦች መኖሪያና ማንነት እንጅ ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መስጠት ያልተጻፈ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ራስን የመግደል/ አጥፍቶ የመጥፋት/ ወንጀል መፈጸም ነው፡፡ በዘመናችን የሚገኙ አንድ አንድ ጎሰኞች ወደኋላም ወደፊትም መሄድ የማይችሉ የአእምሮ ህሙማን በመሆናቸው ዛሬ የሆነ ነገር ላይ ተቸክለው ከትናንት የማይማሩ ለነገ ደግሞ የማይኖሩ ናቸውና ሊታዘንላቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ሰዎች ትናንትን ስለማያውቁ መሰረት የላቸውም ነገንም እንዳያዩ ርእይ አልባ ናቸው፡፡
የጥንቱ ዘመን ኢትዮጵያ ግዛት አልፎ አልፎም ቢሆን በስተሰሜን እስከ ግብፅ ድረስ፣ ቀይ ባህርን ተሻግሮ እስከ ደቡብ አረቢያ እንዲሁም በርካታ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎችን ያካትት እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ በአንፃሩ በዘመኑ የምንገኝ ሰዎች የዛሬዋን ኢትዮጵያ እንደ ገና ዳቦ ሸንሽነን ሸንሽነን /በሃሳብም ቢሆን/ የት ልናደርሳት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ የቀድሞዋ ኢትዮጵያ የስደተኞች መጠጊያ፣ የደካሞች ምርኩዝ፣ የችግረኞች ተስፋ፣ የፍትህ ማዕከል፣ የእውነተኞች ምድር እንዳልነበረች፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ልጆቿ መጠጊያ የሌላቸው ስደተኞች፣ ርዳታ የሚለምኑ ርሃብተኞች፣ የሌሎችን ድጋፍ የሚሹ ደካሞች፣ በፍትህ እጦት የሚሰቃዩ ምስኪኖች ሆነዋል፡፡
በጥንቱ ዘመን ምድቧ ከኃያላን መንግሥታት ጋር ሆኖ በማንነቷ ታፍራና ተከብራ የዓለም ቁንጮ የነበረችው አገር ዛሬ በማናቸውም መስፈርት የዓለም ግርጌ ላይ ተቀምጣ ልጆቿ አንገታቸውን ሲደፉ በየሄዱበት ሲገፉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እርስ በርሷ የምትለያይ መንግሥት ትጠፋለች እንደተባለው: ለዚህ ሁሉ ውርደትና መከራ ካበቁን ነገሮቸ አንዱና ዋነኛው ከአብሮነት ልዩነትን፣ ከመተባበር መነቃቀፍን፣ ከአንድነት መነጣጠልን፣ ከኢትዮጵያዊነት ጎሰኝነትን፣ ከቅንነት ምቀኝነትን፣ ከመደጋገፍ መጠላለፍን መምረጣችን ነው፡፡ አሁንም ከታሪክና ከሌሎች የማንማርና በዚሁ የምንቀጥል ከሆነ አወዳደቃችን የከፋ እንዳይሆን ያስፈራል፡፡ ስለሆነም የአብሮነታችንን ጥንታዊ መሠረት እንወቅ፣ የጎሰኝነት ድሪቷችን እናውልቅ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እናጥብቅ፡፡
በመሠረቱ መታወቅ የሚገባው:-
• ኢትዮጵያዊነት ከፈጣሪ የተሰጠን ፀጋ እንጅ ለድርድር የሚቀርብ የሸቀጥ ዕቃ አይደለም፡፡
• ኢትዮጵያዊነት የደም ማተባችን እንጅ ሲያሻን የምናጠልቀው ሳንፈልግ የምናወልቀው
አርቴፊሻል ጌጥ አይደለም፡፡
• ኢትዮጵያዊነት ሳንፈልገው በግድ የተጫነብን ዕዳ ሳይሆን የተዋብንበት ጌጣችን፣ የከበርንበት
ዘውዳችን፣ የወረስነው ቅርሳችን ነው፡፡
• ኢትዮጵያዊነት ክብር እንጅ ውርደት ሽልማት እንጅ ቅጣት አይደለም፡፡
• ኢትዮጵያዊነት አንድነት በብዙኀነት ብዙኀነት በአንድነት የሚመሰጠርበት የህብር ቅኔ፣
በጎሰኞች የማይፈታ ሰምና ወርቅ ነው፡፡
• ኢትዮጵያዊነት የማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት፣ ዘመን የማሽረው ማንነት፣ የማይቋረጥ ጅረት ነው፡፡
• ኢትዮጵያዊነት ዘመንን ከዘመን ትውልድን ከትውልድ የሚያገናኝ ህያው ድልድይ ነው፡፡
• ኢትዮጵያዊነት በጎሰኞች ጫጫታ የማይፈርስ በደም የተገነባ የመስዋዕትነት ታሪካችን ነው፡፡
• ኢትዮጵያዊነት በወጀብና አውሎ ነፋስ የሚፈርስ የድቡሽት ቤት ሳሆን በፅኑ መሠረት ላይ
የተጣለ የአብሮነት ሃውልት ነው፡፡
ማጣቀሻዎች /References/
Budge, Wallies E.A., 1928. History of Ethiopia, Nubia and Abyssinia (Vol. I). Routledge: Taylor and Francis Group.
Ethiopian Orthodox Tewahdo Church Holy Synod, 1990. Today’s Ethiopia is Ethiopia of the Holy Scriptures, History and Antiquity: Resolution of the Holy Synod of the Ethiopian Orthodox Tewahdo Church. Addis Ababa.
Frank M. & Snowden, Jr. 1970. Blacks in Antiquity: Ethiopia in the Greco-Roman Experience. The Belknap Press of Harvard University Press; Cambridge, Massachusetts, London.
Levine, Donald N. 1974. Greater Ethiopia: the Evolution of a Multiethnic Society. The University of Chicago Press: Chicago and London.
Mohammed Girma, 2012. Understanding Religion and Social Change in Ethiopia: Toward a Hermeneutic of Covenant. Palgrave: Macmillan
Sergew Hable Sellassie, 1972. Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. Addis Ababa.
Tekeste Negash, 2016. Woven into the Tapestry: How Five Women Shaped Ethiopian History.
The Holy Bible (Amharic Version)
http//www.taneter.org/Ethiopia.htm/