ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, February 20, 2019

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሆነ በአቶ ለማ በኩል ከኢትዮጵያዊነት የወጣ የመስመር ለውጥ አለ ብዬ አላምንም።



ጉዳያችን / Gudayachn
የካቲት 14/2011 ዓም (ፈብሯሪ 21/2019 ዓም)
======================

ብዙዎች አጠቃላይ የለውጡን ሂደት በተናጥል ባለስልጣናት ድርጊት ለመለካት ፈጥነው ጫፍ የያዘ አመለካከት ለማንፀባረቅ ሲጥሩ መታዘብ ችያለሁ።በመጀመርያ የለውጡ ሐዋርያዎች የገብቡአት የፖለቲካ ከባቢ ሁኔታ በሚገባ የተረዳነው አይመስለኝም።ለውጡ ከተጀመረ ጀምሮ በሱማሌ ክልል የነበረው መፈናቀል፣የቤንሻንጉል ግድያ እና መፈናቀል፣የሲዳማ ግጭት፣የቡራዩ እልቂት፣በጠቅላይ ሚኒስትሩ  የተሞከረው የግድያ ሙከራ፣የወታደሮች ወደ ቤተ መንግስት ገብተው ለመረበሽ ያደረጉት ጥረት፣የሰሞኑ የለገጣፎ ማፈናቀል ሁሉ ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው።አንድ የለውጥ ሂደቱን በማደናቀፍ ከተጠያቂነት ለመዳን የሚጥሩ ኃይሎች ሥራ እና በሌላ በኩል ፅንፈኛ የኦዴፓን እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ አክራሪዎች ናቸው።

አሁን ብዙ ሰው የሚጠይቀው ለምን ከስር ያሉ በደሎች ሲፈፀሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም አቶ ለማ ቶሎ እንዲታረም አያደርጉም? የሚል ተገቢ ጥያቄ ነው።አዎን ይህ መሆን አለበት።ሆኖም  አንድ እውነታ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ።ተቃዋሚዎች በሙሉ ወደ ሀገር ሲገቡ እና በእስር የነበሩ በሙሉ ሲፈቱ ቀድመው በኦህደድ ስር የነበሩ ከፅንፈኛ ዓለም አቀፍ አሸባሪ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎች እስከ መሬት የቸበቸቡ ወንጀለኞች ቀስ በቀስ የኦህደድን ታችኛው መዋቅር እንደ ሸረሪት ድር  በማድራት ስፍራ ይዘዋል።

እነኝህ ግለሰቦች ደግሞ መዋቅራቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ያደሩ ናቸው።በእየቦታው ብቅ የሚሉ ኢትዮጵያዊ ላይ በተለይ ''የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስልታዊ ጠላቶች አከርካሪውን እንስበረው'' የሚሉትን ኢትዮጵያዊ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ማድረግ ዋነኛ ተልዕኮ አድርገው ተያይዘውታል።በኢትዮጵያ ሱማሌ ውስጥ ባለፈው ግርግር እጃቸውን የነከሩ የውጭ መንግሥታት ነበሩ።ጉዳዩ እንደማይቻል ሲመለከቱ እጃቸውን ሰበሰቡ። ሰሞኑን ከቱርክ ይነሳል የሚባለው የጦር መሳርይ ጎርፍ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር የመደበ የባዕድ ሀገር ከወያኔ  እየተቀባበለ እና የወያኔ  የቀድሞ ደህንነት በሚያውቀው መስመር እያሳለፈ ካልሆነ በእዚህ መጠን እንዴት ሊገባ ይችላል?  መንግስትም የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን አምኖ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሱዳን እና ቱርክ ጋር ንግግር ለማድረግ ማቀዱን እንስከመግለጥ የደረሰበት ጊዜ ነበር።

የለገጣፎ ጉዳይም የእጅ ጥምዘዛ ውጤት እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አቶ ለማ ተስማምተውበት ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ቢኖር  ተሳስቷል።ምክንያቱም ደብረ ፅዮን መቀሌ ላይ እየዛተ ምን ያህል ሞኝ ቢሆኑ ወይንም ቅድምያ የሚሰጠው ጉዳይ ሳይገባቸው ነው ስልሳ ሺህ ሕዝብ የሚፈናቀልበት ጉዳይ ላይ በውሳኔ ይስማማሉ  ብሎ ማሰብ የሚቻለው? ይህ  ከተራ የፖለቲካ ስሌትም አንፃር ጉዳዩ የእነርሱ ስምምነት ውጤት ነው ለማለት ይከብዳል።ይህ ማለት ግን የፅንፈኛው የሸረሪት ድር እያደራ በሁኔታዎች እንዳይከላከሉ ያደረጋቸው ጉዳይ አለ ወይ? ብሎ መመርመር  አይቻልም ወደሚል ጥያቄ አያመራም ማለት አይደለም።

በፖለቲካዊ ውሳኔ ሳትስማማ ግን በቡድን ውሳኔ ስትጠመዘዝ አስፈፃሚው ከህዝብ ጋር እንዲላተም ትተወዋለህ።ሌላ አማራጭ የለህማ! ውሳኔው የቡድን ሲሆን ደግሞ ክፋቱ በእርሱ መላተም አንተም መወቀስህ አይቀርልህም።ሆኖም ግን አሁንም  ሌላ አማራጭ የለም።ወዲህ የክልል ሕግ ጠርንፎ ይዞሃል፣ወዲያ ፅንፈኛ ተደራጅቶ ሕዝብ ይበጠብጣል፣ ማዶ የቀድሞ ገዢ ጦር ሊሰብቅ ያንኮራፋል።ይህ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አቶ ለማ የገቡበት  እውነተኛ ሁኔታ ነው።ይህንን በሚገባ መረዳት እና እንደ ለገጣፎ አይነት ግፍ የሰራው የታችኛው አካልን ሕዝብ ወጥሮ መያዙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለአቶ ለማ ጠቃሚ የሚሆነው እና ለውጡን ለማገዝ የሚረዳው ለእዚህ ነው።

መፍትሄው 
========
መፍትሄው ሁለት ነው።አንዱ ኢትዮጵያዊው ኃይል ፅንፈኛውን የማናፈጥ ሥራ መስራት አለበት።ፅንፈኛው ስርዓት እና ደንብ የሚገባው አይደለም።በዕብሪት እያስፈራራም ሊኖር አይገባም።እያከበርከው ለሀገር ሰላም ብለህ ብትኖርም አይረዳልህም።ይልቁንም ትዕቢቱ ያይላል። እንዳለፈው የነውጥ ትውልድ እስኪማር ሌላ አርባ ዓመታት  የመጠበቅ አቅም ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት አይመስለኝም።ሕግ ጥሶ ሲመጣ  ከማናፈጥ ሌላ ምንም የቃላት ድርድር አያስፈልገውም።በእዚህ ለውጡን ትጠብቃለህ።ኦነግ ወደ አዲስ አበባ በመስከረም ወር 2011 ዓም የገባ ጊዜ አዲስ አበባን ለመበጥበጥ የታዩትን ሙከራዎች ሕዝብ በማክሸፉ በዕለቱ ብፁዕ አቡነ መርቆርዮስን ለመጠየቅ ድንገት የተከሰቱት ዶ/ር አብይ ያሳዩት ደስታ ከፊታቸው ለመረዳት የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ተመልሶ ማዳመጥ ይጠይቃል።

ሁለተኛው መፍትሄ ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ ኢትዮጵያ የጎሳ ፈድራሊዝም ፈፅሞ እንደማይጠቅማት ግልጥ ባለ አነጋገር መናገር እና ፈድራልዝሙ በጎሳ መከለሉ የችግሮች ሁሉ መነሻ መሆኑን እንዲሁም  ፈድራሊዝም አስፈላጊ መሆኑን ግን በጎሳ መከለሉ ስህተት እንደሆነ ደግመው ለሕዝብ ማረጋገጥ አለባቸው።መስመራቸውን በግልጥ አለማስረገጥ ለደጋፊያቸውም ግራ ያጋባባቸዋል። በኦሮምያም፣ደቡብ፣ጋምቤላ፣አማራ፣አፋር እና መሃል ሀገር ያሉ የትግራይ ተወላጆች ሳይቀሩ ትልቁ ስጋት የጎሳ ፈድራሊዝም ነው።ይህንን በግልጥ መኮነን ማለት ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ የምርጫ ዘመቻቸውን በመጀመር ሕዝብ ከአሁኑ ከጎናቸው አሰለፉ ማለት ነው።

ባጠቃላይ ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ የፅንፈኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ልሁን ቢሉም ሁኔታው ፈፅሞ አይፈቅድላቸውም።እነርሱም የእዚህ አይነት ድብቅ አጀንዳ ፈፅሞ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ እኔን አያሳምነኝም።የወሰን አከላል ኮሚሽን አመራረጥ፣የሚድያ ነፃነት፣የጦር ሰራዊቱ እና ደህንነቱ አወቃቀር ላይ እየተሰራ ያለው ሁሉ ይህንን አያመለክትም።ይልቁንም ለፅንፈኛ አካል የሚያመች ሜዳ አይደልም።ሆኖም ግን ፅንፈኛው አካል ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ በፍፁም አረመኔነት የሚወስደው እርምጃ የጎሳ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አሸባሪ አክራሪዎች ሁሉ ወደ ኦዲፓ  ታችኛው መዋቅር ውስጥ እንደገቡ አመላካች ነው።ይህንን የታችኛውን መዋቅርም ለማፅዳት አቶ ለማ ብዙ መቶ አመራሮች በወረዳ ደረጃ ካባረሩ ገና ወራት መቆጠሩ ነው።ባጭሩ ለውጡ ከላይኛው አካል እንደመጀመሩ ታችኛው አካል የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ የታወቀ ነው።ኦዲፓ ፅንፈኛው አካሉን ድል ካላደረገ ሁሉን ነገር እንዳበላሸ ሊያውቀው ይገባል።

አሁን ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ እና አደጋዎች በተመለከተ ጉዳያችን ላይ ''መጪው የኢትዮጵያ ዘመን ብርሃን ወይንም ጨለማ ነው።ለሁለቱም እያንዳንዳችን ተጠያቂ ነን (የጉዳያችን ልዩ ወቅታዊ ትንታኔ)'' በሚለው ፅሁፍ ስር በረጅሙ ለማብራራት ስለሞከርኩ እርሱን አንብቡት 
=======/////===========


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...