ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, February 1, 2019

የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የመታሰብያ ሃውልት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መስርያበት በመጪው ሳምንት መጨረሻ ይመረቃል


ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ 
ጉዳያችን ልዩ ዜና /Gudayachn special report
ጥር 25/2011 ዓም (ፈብርዋሪ 2/2019 ዓም) 

  • የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ አርና ሶልበርግ፣ ቢልንየሩ ቢል ጌት  እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ  አንቶንዮ ጉተረስ ወደ አዲስ አበባ ያመራሉ። 

ሠላሳ ሁለተኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች መደበኛ ስብስባ በመጪው ሳምንት መጨረሻ የካቲት 2 እና 3/2011 ዓም (february 9 & 10/2019) አዲስ አበባ ላይ ይከፈታል።በቅዳሜው መክፈቻ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ''በአፍሪካ ጤና ላይ መዋለ ንዋያችንን እናፍስስ'' በሚል ርዕስ የሩዋንዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ፖል ካጋሜ በሚመሩት እና በሸራተን አዲስ በሚደረገው  ልዩ የከፍተኛ ልዑካን ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ መሪዎች በተጨማሪ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ አርና ሶልበርግ እና ቢልንየሩ ቢል ጌት በልዩ እንግዳነት ይገኛሉ። ይህ ከቀትር በኃላ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከ9 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት የሚደረገው ስብሰባ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብ ከጤና አገልግሎት የማያገኝ ከመሆኑ አንፃር ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።የመሪዎቹ ስብሰባ በሌላ በኩል የያዘው ዓብይ አጀንዳ የአፍሪካ ስደተኞች (ወደውጭ እና በሀገራቸው የተፈናቀሉትን) አስመልክቶ የሚያደርገው ውይይት የስብሰባው አንዱ አካል እንደሆነ ተሰምቷል። 

በተያዘው መርሐግብር መሰረት  የዕሁዱ ማለትም የካቲት 3/2011 ዓም የጧት የመሪዎች ስብስባ መርሐግብር በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 5 ሰዓት ከሩብ ጀምሮ ያለው ጊዜ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሐውልት በሕብረቱ ፅህፈት ቤት በሚገኝበት ቦታ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት የሚመረቅበት ጊዜ ነው።የአፍሪካ መሪዎች ከእዚህ ቀደም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ ኅብረትነት ሲሸጋገር የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ሐውልት ቻይና ሰራሽ በሆነው በአዲሱ የኅብረቱ ፅህፈት ቤት ለመስራት ፍላጎት በድርጅቱም ሆነ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ቢኖርም በወቅቱ የነበሩት አቶ መለስ ደስተኛ አለመሆናቸው በርካታ አፍሪካውያንን እና ኢትዮጵያውያውንን ያሳዘነ ጉዳይ ሆኖ አልፏል። ለእዚህም ማስረጃው አቶ መለስ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የጋናው ክዋሜ ንኩማ  ሃውልት ምን ያህል ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በላይ  አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳት የደከሙበት መንገድ ከፍተኛ ትዝብት ላይ ጥሏቸው አልፏል።

በግንቦት ወር 1963እኤአ  ዓም የአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ጉባኤ ላይ  ልዩነቶችን በመዳኘት ቻርተሩን ሳንፈርም አንወጣም የሚለው  የንጉሡ ተማፅኖ ለድርጅቱ መመስረት ወሳኙ ጉዳይ ነበር። 

ሆኖም ግን አቶ መለስ ከእዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኃላ የአፍሪካ ሕብረት መስርያ ቤትም ሆነ አፍሪካውያን መሪዎች እንዲሁም የንጉሡ የልጅ ልጅ ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን ታሪክ ተቀብሮ መቅረት የለበትም በሚል ሲሟገቱ የነበሩ ሲሆን በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሃውልቱ ይሰራ የሚል የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ሰርተው መንግሥትን ሞግተዋል።ቀድሞም የአፍሪካ ኅብረት እንደዋና ቢሮም ሆነ የአፍሪካ መሪዎች ፍላጎት የነበረው የሃውልቱን መስራት ጉዳይ አሁን ለኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ዋጋ የሰጠው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መንግስት ዘመን ሃውልቱ ለምርቃት የበቃበት ሁኔታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን የሚያስደስት ተግባር እንደሚሆን የሁሉም ዕምነት ነው። ይህ ታሪክ የመላው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ብቻ አይደለም።የአፍሪካውያን ታሪክም ነው።ኢትዮጵያውያን በክብር ልንጠብቀው የሚገባን ቅርሳችን ነው። 
የቀ/አፄ ኃይለስላሴ  የልጅ ልጅ ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን እና የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር  አምባሳደር ክወሲ ካርታይ (Kwesi Quartey)  ፎቶ የአፍሪካ ኅብረት (Photo=Africa Union) 

በመጨረሻም ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን  የአፍሪካን  ኅብረት ለማመስገን እኤአ ጥር 22/2019 ዓም  በድርጅቱ ፅህፈት ቤት በተገኙበት  ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር  አምባሳደር ክወሲ ካርታይ (Kwesi Quartey) የንጉሰ ነገሥቱን ሃውልት ምረቃ አስመልክተው  ሲናገሩ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ሃውልት መሰራት የፓን አፍሪካ መኖርን ያሳያል ብለዋል። ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን በበኩላቸው የአፍሪካ ኅብረት ሃውልቱን ለመስራት መወሰኑና መተግበሩ በራሱ የአፍሪካ መሪዎች አንድነትን አመላካች ነው ብለዋል።ንጉሰ ነገስቱ የደርግ አባላት ልይዟቸው ወደ ቤተ መንግስታቸው በሄዱበት በ1966 ዓም የክረምት ወር ሃምሳ አለቃ ደበላ ዴንሳ ንጉሡን ወደ ማረፍያ ክፍል ለመውሰድ እንደሚያስቡ ሲነግሯቸው የሰጡት ምላሽ '' ካልተሳካላችሁ የእኔ ታሪክ እንደ አዲስ ይነሳል'' የሚል ንግግር አድርገው ነበር።አርባ ዓመት ያልተሳካላት ኢትዮጵያ እንዳሉት የእርሳቸው ታሪክ ተነሳ ማለት ነው።ይህ ማለት የድሮው ስርዓት ተመልሶ መጣ ማለት አይደለም።ሀገር በፍቅር፣በአንድነት እና በመተሳሰብ የመምራት ጥበብ እንደገና ትንሣኤ የማግኘቱ ፋይዳ ነው። ዛሬ ሰዎች ስለ ክልላቸው እና ጎጣቸው በማውራት ብቻ ሳይሆን ጎጥ ፖለቲካ በሆነባት ሀገር  ላይ ሆነን ኢትዮጵያን አንድ አንድ የማድረግ ልዩ የፖለቲካ እና መንፈሳዊ ፀጋ ብቻ ሳይሆን አፍሪካን አንድ የማድረግ ጥበብ ያሳዩን ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን የማናደንቅበት ምን አዕምሮ አለን? ሃውልታቸው ለትውልድ ብዙ ማለት ነው።አዲስ አበባም  መሃል አደባባይ ላይ አንድ የንጉሡ ሃውልት ያስፈልጋታል።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)