ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, February 5, 2019

መጪው የኢትዮጵያ ዘመን ብርሃን ወይንም ጨለማ ነው።ለሁለቱም እያንዳንዳችን ተጠያቂ ነን (የጉዳያችን ልዩ ወቅታዊ ትንታኔ)


በእርስ በርስ ጦርነት የፈረሰችው የሶርያን ከተማ ቆሞ በትካዜ የሚመለክት ሶርያዊ  ወታደር (ከማኅበራዊ ሚድያ የተገኘ) 

ጉዳያችን GUDAYACHN 
ጥር 29/2011 ዓም (ፈብሯሪ 6/2019 ዓም) 
============================

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ተብራርተዋል - 

አሁን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ያሉት ስድስት አደገኛ ጉዳዮች እና 

የችግሮቹ  ሶስት መፍትሄዎች 

ወቅቱ 1928 ዓም ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ የሚወስደው ባቡር  የኢትዮጵያ ከፍተኛ ስልጣን የይዙትን ንጉሰ ነገሥቱን እና ጥቂት ባለስልጣናት አብረው እየሄዱ ነው።ትካዜ፣ሃዘን እና ተስፋ መቁረጥ በባቡሩ ውስጥ የተሳፈሩት ሁሉ ላይ ሰፍኗል።ንጉሡ በያኔው የፈረንሳይ ቅኝ የነበረችው በቀድሞ ስሟ አፋር እና ኢሣ የዛሬዋ ወደ ጅቡቲ እያመሩ ነበር።ጉዞው በጅቡቲ የሚቆም አልነበረም። ከጅቡቲ ወደ እየሩሳሌም በመቀጠል ወደ ጄኔቭ  ተጉዘው ለያኔው የዓለም ማኅበር (የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት) የፋሽሽት ጣልያንን የግፍ ወረራ አቤት ለማለት እየሄዱ ነበር።በጉዞ መሃል ባቡሩ የቆመበት ድሬዳዋ ከተማ ሲደርስ ንጉሡ ጣብያው ላይ ወርደው ቀጣይ ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት በስልክ ወደ አዲስ አበባ ደውለው ሁኔታውን መከታተል ፈልገው በወቅቱ ቀጥታ ስልክ ባለመኖሩ በኦፕሬተሩ በኩል ከአዲስ አበባ ጋር እንዲያገገናኛቸው ይጠይቃሉ።የታዘዘው ኦፕሬተር  ከእዚህ በፊት በድምፅ ያውቁታል። ጣልያን ከመምጣቱ በፊት አክብሮ ያናግራቸው ነበር።ያን ቀን ሲያናግራቸው ግን ስርዓት በያዘ መልክ አልነበረም።ጣልያን እየመጣ መሆኑን ያወቀው ኦፕሬተር ጥርት ባላለ አማርኛው ክብር በማይሰጥ አነጋገር ሲናገር ንጉሡ ሰሙት።ንጉሡ ይህ ሰው ጊዜ ያዘነበለ መስሎት ስርዓት ባጣ መልኩ በመናገሩ ሃገሩን ከአሁኑ መክዳቱ ተሰምቷቸዋል።ጣልያን ምን ይዞ እንደመጣ ያላወቀ የምስራቅ ኢትዮጵያ ሰው ስርዓት ያጣ የስልክ አነጋገር እና ድፍረት በራሱ ለንጉሡ  ሌላ ሃዘን ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው ታሪክን ንጉሡ ከነፃነት በኃላ ተመልሰው በፃፉት ''ሕይወተኛ የኢትዮጵያ ርምጃ'' በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል። ታሪኩን የእዚህ ፅሁፍ መግቢያ ያደረኩበት ምክንያት ኢትዮጵያ በዘመኗ እንዲህ አይነት የሐዘን ሰዓታት አሳልፋ ነበር።ጣልያን ከሰሜን እየመጣ፣ንጉሷ በጅቡቲ እየወጡ።ያንን ወቅት ዛሬ ላይ ሆነን በምናባችን ብናስበው የንጉሡ ልብ ምን ያህል ያዘነበት፣አንዳንዶች ኢትዮጵያ አበቃላት ያሉበት፣ሌሎች በእኔ አጥንት ላይ ተረማምደው ብቻ ነው የኢትዮጵያን ሞት የሚያረጋግጡት ያሉ አርበኞች የተነሱበት  ፈታኝ ወቅት ነበር።ይህ ማለት ኢትዮጵያ ምንም የማይነካት ካለ አንዳች እንከን የምትኖር ሀገር ነች ብሎ ደምድሞ መቀመጥ አይቻልም።የሚሆነው ሁሉ በዛሬ ስራችን፣ትጋታችን እና ተግባራችንም የሚወሰን መሆኑን ማወቅ እንጂ በተዓምር  ብቻ ምንም አትሆንም በሚል መዝናናት ስሕተት መሆኑን ለመጠቆም ነው።በ1928 ዓም በፀሎት የማይተጉ የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያ ስለሌላት አይደለም።ሆኖም ግን የደረሰባት ሁሉ ደረሰባት።ነገር ግን ተመልሳ በመለኮታዊ ኃይልም በመርዎቿ ትጋትም ተነስታለች።ዛሬም ላይ ሆነን በሶርያ የደረሰ የማይደርስብን ልዩ ሀገር ነን አልያም ኢትዮጵያ ፈፅሞ ምንም አትሆንም የሚለውን አባባል ትተን አሁን የመጣውን መልካም ዕድል  ኢትዮጵያ እንድትጠቀም የእያንዳንዱ ሚናውን ዝቅ አድርጎ የሚያይ ግለሰብ ሁሉ  መጪው የኢትዮጵያ ዘመን ብርሃን ወይንም ጨለማ መሆኑን የዘነጋ ሰው ብቻ ነው ።ለሁለቱም  መጪዎች ግን እያንዳንዳችን ተጠያቂ እንደሆንን መሰብ አለብን።መስራት ያለብንን ትንንሽ ድርሻ ባለመስራት።

አሁን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ያሉት ወቅታዊ ስድስት አደገኛ ጉዳዮች 

መጋቢት 24/2010 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ፓርላማ ካደረጉት አቅጣጫ ቀያሪ ንግግር ወዲህ ኢትዮጵያ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት መንግድ ጀምራለች።የሚሰሩት ስራዎች ዘለቄታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው በራሱ ኢትዮጵያን እጅግ ተስፋ ያላት ሀገር እንድትሆን ማድረጉን  አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከገጠር እስከከተማ የሚያምንበት ዕውነታ ነው።ይህ መልካም ጅምር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም ግን የሚያሰጉኝ ስድስት አደገኛ ሁኔታዎች አሉ።እነኝህ ጉዳዮች በአግባቡ መፍታት ደግሞ የመንግስት ስራዎች ብቻ አይደሉም።የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ግን ናቸው።እነኝህ ስድስት ጉዳዮች : -

1ኛ) የሕዝብ እና ፊት ቀደም ሀገር ወዳድ የነበሩ ግለሰቦች የምቾት ቀጠና (comfort zone) መግባት 

ለውጡ ከመጣ ገና አንድ ዓመት አልሆነውም።ይህ ለውጥ በበርካታ ቅራኔዎች የኖረው የኢትዮጵያ ፖለቲካው ውስጥ በድንገት ብቅ ሲል የሚገጥመው ተግዳሮት ከቀድሞው ስርዓት ህወሓት እና ደጋፊ የኢሕአዴግ አባላት ጋር ብቻ አይደለም።ከአርባ ዓመታት በላይ የነበሩ የፖለቲካ ቅራኔዎች ሁሉ እንዲፈታ እና ኢትዮጵያን ወደተሻለ ዲሞክራሲ እና የሃሳብ ልዕልና ማሸጋጋር ሁሉ የሚጠበቅበት ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክት ነው።ይህ ሆኖ ግን በሕዝብ ዘንድ የሚታይ የምቾት ቀጠና መግባት እና ጉዳዮችን በንቃት ከመከታተል መዘናጋት ብቻ ሳይሆን ነገ እንዴት እንሂድ ለሚለው ሃገራዊ ጥያቄ የራስን ሚና አሁንም አደራጅቶ አለመጠበቅ በሕዝብ ዘንድ ይታያል። ይህ አደገኛ ሁኔታ ነው።ሕዝብ እንደ ሕዝብ ግለሰብም እንደ ግለሰብ መንግስት ዛሬ ምን አለ? ከሚል ስሜት ብቻ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን ዜና ከመከታተል ባለፈ የሚጠበቅ ትጋት ያስፈልጋል። ይህ የምቾት ቀጠና የመግባት አደጋ በጋዜጠኞች፣የፖለቲካ ሰዎች የኪነ ጥበብ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ይንፀባረቃል።የእዚህ አይነት ለውጥ ጋዜጠኞች ልዩ ሥራ የሚያሳዩበት፣የኪነጥበብ ሰዎች ከአእምሮ የማይጠፋ ሥራ ብቻ ሳይሆን ብስለት ያለው አቅጣጫ አመላካች ስራዎች ሁሉ ሊታዩ የሚገባበት ወቅት ነበር ።

2ኛ) አንዳንድ ወጣቶች በፅንፍ አመለካከት የተሞላ ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቅ 

ነገ የሚመነዘረው በዛሬው ወጣት አመለካከት ነው።በኢትዮጵያ አሁን ለመጣው ለውጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው ወጣት ባብዛኛው በማዕከላዊ አስታራቂ፣ይቅር ባይ እና ቀጣዩ ላይ የማትኮር ፖለቲካ ላይ በመስማማት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ሃሳብ የተቀበለ ቢሆንም የተወሰኑ ኃይሎች በተለይ በዓማራ  ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣በኦሮሞያ ደግሞ ከቄሮ ጋር በተያያዘ ''ዋልታ ረጋጭ'' (ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባለፈው ሳምንት ለየት ያሉ ሃሳቦችን ለመግለጥ የተቀሙበትን ቃል ተውሼ ነው) የሆነ ሃሳብ የያዙ አካሎች እንዳሉ ግልጥ ነው።የቄሮ ጉዳይ አሁንም በፓርቲነት ተገልጦ አይውጣ እንጂ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ተደስተው ከለውጡ ጋር በመልካም መንገድ የሚሄዱ ብዙዎች ቢኖሩም በአክትቪስትነት የሚታዩት ግን ግባቸውም ሆነ መድረሻ የፖለቲካ ዓላማቸው አሁንም ቢያንስ ለእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግልጥ አይደለም። 

ይህ በራሱ ምን ያህል ያስኬዳል? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ የነገ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዥታ  ግን አይሆንም ማለት አይቻልም።ጥርት ያለ የፖለቲካ ግቡ የማይታወቅ እና በህጋዊ መልክግ ተደራጅቶ ሃሳቡን የማይገልጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ደግሞ ባልሆነ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ አድፋጭ ኃይል የመጠለፍ እድሉ ቀላል አይደለም።ይህ ጉዳይ እራሱ ቄሮ ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ የመረጃ ክፍተት ስለሚኖርባቸው በራሳቸው ስለራሳቸው እንቅስቃሴ አንዳንዴ ትክክል በመዋቅር መስመር ላይ የቱ ጋር እንድተጠለፈ ለማወቅ የሚቸገሩበት ወቅት አይገጥምም ማለት በራሱ ከባድ ነው። ቄሮ በህወሓት እና በቀድሞው ታዛዥ ኦህደድ ላይ ዲሞክራሲ፣መብት፣ፍትሕ የሚሉ ጥያቄ የያዙ ወጣቶች እንቅስቃሴ ቢሆንም ዋልታ የረገጡ አስተሳሰቦች ማለትም በኢትዮጵያ ያለፈው ታሪክ ንትርክ ውስጥ በተዘፈቁ አክትቪስቶች  አገናኝነት ላይ ጥገኛ በመሆኑ የእነርሱን አስተሳሰብ የቄሮ (የኦሮሞ ወጣት) አስተሳሰብ እንደሆነ እየተደረገ የመወሰድ የተሳሳተ አስተሳሰብ አደጋ ተጋርጦበታል። 

በሌላ በኩል በዓማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጉዳይ ነው።የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አሁን በአማራ ክልል ከሚገኘው አማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዲፓ) ከሚያራምደው ለዘብ ያለ ፖለቲካ በአንፃራዊ መልኩ ''የከረረ'' የሚባል (የከረረ የሚለው አገላለጥ በራሱ ቢያከራክርም) ፖለቲካዊ ሃሳቦችን እንደሚያንፀባርቅ የሚሰማቸው ጥቂቶች አይደለም።በተለይ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ፓርቲዎችን በተለያየ ጊዜ ሲወርፍ ተደምጧል።እንደ አብን አገላለጥ የዜግነት ፖለቲካ ''ላም በሌለበት ኩበት ለቀማ'' አይነት ሃሳብ አለው።''ሀገሪቱ በሙሉ በዘር ፖለቲካ ስለተዋቀረች የዜግነት ፖለቲካ አማራውን ሊያዘናጋ ነው'' የሚል ትርክትም አብን ያስቀምጣል።እዚህ ላይ ግን ቤተ መንግስቱ እና ህወሓት ሰራሽ ፖለቲካ ላለፉት 28 ዓመታት በዘር ፖለቲካ ስለተዋቀረ፣ተራው የኢትዮጵያ  ሕዝብ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የቤተ መንግስቱ በሽታ ሙሉ በሙሉ ግልባጭ ነው፣ ሕዝቡም በቤተ መንግስቱ ደረጃ የጎሳ ፖለቲካ ተጋብቶበታል ብሎ ማመን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልጥ ትክክለኛ አገላለጥ ነው ወይ? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ አብን በማስረጃ ማሳየት አልቻለም።ይልቁንም ዶ/ር ዓቢይ ያነሱት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሚልዮኖችን ማሰለፉ በራሱ ኢትዮጵያዊነት ከጎሳ ፖለቲካ በተሻለ መልክ ገዢ ሃሳብ ለመሆኑ እንደ ትልቅ የጥናት ውጤትም መታየት የነበረበት መልካም ዕድል ነበር።

የሆነው ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ካላት መጪ አደገኛ የፖለቲካ ሁኔታዎች ውስጥ የወጣት ፅንፍ የያዙ ( ዋልታ ረጋጭ) ሃሳቦች ተጠተቃሾች ናቸው።አደጋው ደግሞ ሁለቱም ለዘብተኛ እና አሁን ላለው ለውጥ ዋና ተዋናይ የሆኑትን ኃይሎች ለመቀናቀን የሚያቀርቡት የፖለቲካ መስመር ምንም አይነት ስም ብንሰጠው አንፃራዊ አክራሪ አስተሳሰብ የያዙ መሆናቸው ነው።ይህ ደግሞ ወደ ርዕዮተ ዓለም አልባ እና ግብ የለሽ ክርክር ኢትዮጵያን እንዳይከታት ያሰጋል።

3ኛ) ከፍተኛ ሥራ አጥ ወጣት መኖር፣የሕዝብ ብዛት መጨመር፣ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት መኖር 

4ኛ)  ኢትዮጵያ የአፍሪካም ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ አቅጣጫ አስቀያሪ ስልታዊ ሀገር መሆኗ በዓለማችንም ሆነ ሃያላን ሀገሮች ሁሉ ዓይን ስር መሆኗ 

ይህኛው የሀገራችን ሚና ብዙ የተባለለት ቢሆንም አሁን አካባቢያዊ ኃያላን መንግሥታት ሹክቻ ለምሳሌ ኢራን እና ሳውዲአረብያን መጥቀስ ይቻላል። የእነርሱ ሹክቻ እና የጥቅም ፍላጎት ኢትዮጵያን በትኩረት ያሚያስመለክታት መሆኑ እና የቆየው የአረብ ናሽናሊዝም እንቅስቃሴ የገባበት አጥብቂኝ በተለይ ከኒውዮርኩ  የሽብር ጥቃት በኃላ የደረሰው ክፍፍል እና የክፍፍሉ እና የአረብ ሊግ መዳከም ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው  የራሱ ተፅኖ አለው።በተከፋፈለ  የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ እያንዳንዱ ተፎካካሪ የኢትዮጵያን ፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች በተለይ በየትኛውም አዋኪ ፖለቲካ ለመደገፍ የሚደረገው እሽቅድምድም ሁሉ የራሱ የሆነ የኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ፈተና ነው።በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ በእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ መሰረት የምዕራቡ ዓለም አሁን የኢትዮጵያ መረጋጋት እና ወደተሻለ ደረጃ ማለፍ ለመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ሚዛን መጠበቅያነት ብቻ ሳይሆን እንደ ስጋት ከሚያያት ሱዳን ጋር ያለውን ስጋት ሚዛን መጠበቅያ ኢትዮጵያን ማጠናከር የተሻለ መሆኑን ያመኑበት ይመስላል።የምዕራቡ  ዓለም በየመን፣ሊብያ፣ሶርያ ያሉት ቁርሾዎች ለምዕራቡ ዓለም የቦታ ሽግሽግ እንጂ ትርፍ እንዳላስገኘ ስለተረዳ ኢትዮጵያ ላይ ይህ እንዲደገም አልፈቀዱም።ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን ካለው ለውጥ እንድትጠቀም ካደረጋት ውጫዊ ዕድሎች ውስጥ ይህ የምዕራቡ አስተሳሰብ ተጠቃሽ ሳይሆን እንደማይቀር አለመጠርጠር አይቻልም።

በሌላ በኩል የአቶ ኢሳያስ ፖለቲካ ነው።አቶ ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር ተጋግዞ ከመሄድ በላይ ምንም አይነት በጎ ዘመን በተለይ ከገበያ አንፃር ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ምስራቅ ካቆጠቆጡት ትንንሽ ጉልበተኞች አንፃር አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የቀይ ባሕር መጠበቅ ከባድ መሆኑን በሚገባ ተረድተውታል።ይህንን የኃይል ሚዛን ለመጠበቅ አቶ ኢሳያስ የመቶ ሚልዮን ሕዝብ እና የተሻለ የገንዘብ አቅም  ያላት ኢትዮጵያ ያውም ባህል፣ታሪክ እና ፈተና ሁሉ ዘመናት አብረው ካሳለፈች ሀገራቸው ጋር በሆነ መልክ ስምምነት መፍጠሩ  አማራጭ እንደሌለው እያሰላሰሉ ነበር ተቃዋሚዎችን ሲረዱ የኖሩት።ስለሆነም አጋጣሚው የዶክተር አብይ መንግስት መምጣት የልባቸውን ጭንቀት ገላገለው። ወደፊትም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ በስጋት የሚያስቡ ሰዎች ይህንን ስልታዊ ትስስር ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማመን ብልህነት ነው።ቀይባህር ካለ መቶ ሚልዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕገዛ አደጋ ላይ ነው።ኢትዮጵያም ኤርትራ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ጋር በሚስጥር እየመከረች ሰላም የላትም።ስለሆነም ምጣኔ ሃብቱ እና የውጭ ፖሊሲ  እንዲሁም ወታደራዊ ጉዳዮች ሁሉ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በብልህነት አጣምረው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ አድርገው ካላስኬዱት  ለሁለቱም አደጋ አለው። ቀድሞውንም ቢሆን የኤርትራን መገንጠል አንዳንድ የአረብ ሃገራት ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ ሽንጣቸውን ገትረው የደገፉት ቀይ ባህርን  ኤርትራን ብቻዋን ካገኙ እንደሚቆጣጠሩት ስለሚያውቁ ነው።ከወራት በፊት የዶክተር ዓብይ አስመራ ድንገት መግባት አንዳንድ የአረብ መንግስታትን መጋኛ እንደመታው  ሰው ቢያስደነግጣቸው መገረም የማይገባው ለእዚህ ነው።

5ኛ) የሴቶች ዝምታ  

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎ እና የፊት የመምራት በተለይ ሕዝብ በማደራጀት፣በማንቃት፣ማኅበራዊ እሴቱን በመጠበቅ በአክትቪስቱ ሥራ ሁሉ እና በመሳሰለው ሁሉ የሴቶች ዝምታ ለኢትዮጵያ መጪ ፖለቲካ አደጋ ነው።አንዳንዶች በቅርቡ ዶ/ር አብይ ካብኔያቸውን ባብዛኛው በሴቶች መሞላቱ መልካም ጅማሮ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መልካም ተፅኖ ቢኖረውም እታች ህዝቡ ጋር ባሉ የፖለቲካ ጉዳይ ግን ሴቶቹ ዝምታቸው በዝቷል።ይህ ደግሞ የደፈረ ፖለቲካ እንዳይራመድ በተለይ በኢትዮጵያዊነት ዙርያ ዕንቅፋት አልሆነም ማለት አይቻልም።

6ኛ) የትግራይ ሕዝብ በህወሓት እንደታገተ መገኘቱ 

ህወሓት አፈገፈገ እንጂ ሙሉ በሙሉ ለዲሞክራሲያዊ ሃገራዊ ጉዳይ እጁን አልሰጠም።ይህ በራሱ ለኢትዮጵያ አደገኛ ሁኔታ ነው። አደጋው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ ባጠቃላይ አደገኛ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ መዳረጉ አልቀረም።በርግጥ የህወሓት ጉዳይ የትግራይ ተወላጅ በሙሉ በፍጥነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ህወሓት ወደ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ማስገደድ የግድ አስፈላጊ ተግባር ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ህወሓት ከባዕዳን ኃይሎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንባር በመግጠም  የኢትዮጵያ ዲሞክራሲም ሆነ ሉዓላዊነት አደጋ የማይጥል ሁኔታ አይፈጠርም ብሎ ማሰብ ከህወሓት ተፈጥሯዊ ባህሪ አንፃር አይቻልም።

የችግሮቹ  ሶስት መፍትሄዎች  

ከላይ የተጠቀሱት ስድስት አደገኛ የፖለትካችን እና የሉዓላዊነታችን አደጋዎች ሶስቱ መፍትሄዎች  : -

1) ንቃት   

በሕዝብ መሃል የነቁ ጥቂቶች ናቸው።አብዛኛው ሕዝብ አሁን የመጣው ለውጥ ምንም አይነት ተግዳሮች የማይገጥመው እና መንግስት ሁሉን ሥራ ይሰራል ብሎ የሚጠብቅ ነው።ይህ ጉዳይ አደገኛ ስሜት ነው።ስለሆነም ሕዝብ መስራት የሚገባው ጥቃቅን ስራዎች ሳይንቅ እንዲሰራ እና በመረጃም ከመንግስት ጋር ተባብሮ የሚሰራበት ልዩ መንገዶችን  በሚገባ መዘርጋት ይገባል።ይህ ደግሞ ህዝብን በመገናኛ ብዙሃን ሁሉ ማንቃት ሲቻል ነው።የነቃው ለራሱ ጠቅላላ ዕውቀት ከመቀመጥ ከሰፈሩ ጀምሮ ባለው ነፃነት ተጠቅሞ ሕዝቡን በሁሉም መስክ ማንቃት እና አዲሱን ለውጥ እንዲደግፍ እና ደጀን እንዲሆን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

2) ትጋት 

የነቃው ትጋት ያንሰዋል።የነቃው ጋዜጠኛ፣ፖለቲከኛ፣የፖለቲካ ፓርቲ፣አክቲቪስት፣ባለሀብት፣የጦር ሰራዊት አባል፣የኪነ ጥበብ ባለሙያ፣መምህሩ፣ተማሪው  ሁሉ ለውጡ ከመጣ በኃላ ሁሉ ነገር ያበቃ ይመስል በተከፈተው ዕድል ተጠቅሞ በመደራጀት፣አስደማሚ ስራዎችን በመስራት እና መንግስትን በሙሉ ኃይል ከመደገፍ ይልቅ ትጋት በጎደለው መልክ ከሚጠበቀው ትጋት ባነሰ ደረጃ ላይ እንደሆኑ ይሰማኛል።ይህንን በልኬት ለማስቀመጥ መለክያው በራሱ አስቸጋሪ ሊሆን ይቻላል። ትጋቱ ግን ለውጡን ለመጠበቅ መከፈል ያለበት ትጋት ደረጃ አይደለም።ለእዚህ ማሳያ እንዲሆን እነኝህን ጥያቄዎች በማስቀመጥ ላብራራ።
- ነፃነቱ ከመጣ በኃላ የበሰሉ ጋዜጠኞች ሀገር ውስጥ የሚድያውን አየር ቀየሩት? ጋዜጠኞች በምን ያህል ደረጃ እየተጉ ነው? ብቃት የሌላቸው የመንደር ወሬዎች የሚጠይቁ እርባና ቢስ ቃለ መጠይቆች በማሰማት ጊዜያችንን የሚያጠፉ ጋዜጠኞች ምን እየሰሩ ነው? እጅግ የበሰሉ ባለሙያዎች ወደ ሚድያው መጡ?
- የኪነ ጥበብ ሰዎች ለውጡን አስመልክቶ ሕዝብ አዕምሮ የተቀመጠ እጅግ ልዩ የሆነ አቅጣጫ አመላካች የበሰለ ሥራ አለ? እና ሌሎች ጥይቄዎች ብናነሳ የትጋት ማነስ አሁንም መኖሩ ያመላክታል።

3) የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን የጋራ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስማሙበት ቻርተር መፈራረም  እና የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ሥራ መስራት 

በኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ችግሮች ባብዛኛው በፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ጥራት እና ብቃት የሚፈታ ቢሆንም አሁን ባለንበት ዓለም የእነኝህ ሁሉ ጉዳዮች ማሰርያ የመገናኛ ብዙሃን ነው።የመገናኛ ብዙሃን ህዝብንም ሆነ መንግስትን የማረቅ፣የመግራት እና ሃሳብ የማፍለቅ ሚናቸው ትልቅ ነው።በመገናኛው ብዙሃን በኩል አሁን በኢትዮጵያ ያለው አንዱ ችግር ደግሞ የተለያዩ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች በርቀት እና በእርቀት የሚመሩ መሆናቸው ነው።ይህ ችግር ደግሞ የምርጫ ወቅት በቀረበ ቁጥር ሚድያዎቻችን የእርስ በርስ ጦርነት ምንጮች እና ቀስቃሾች ላለመሆናቸው ምንም ዋስትና የለንም።ይህ ደግሞ በምርጫው ሰሞን የመሸነፍ እና የማሸነፍ ጫፍ ሲደረስ የሚፈጠሩ ስሜታዊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ሚድያዎቻችን ወዴት እንደሚወስዱን  ስናስብ የብርድ ቆፈን ይይዘኛል። ይህ ችግር ለመፍታት የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃንን መንግስት በአንድ ምክክር ጠርቶ የጋራ ሃገራዊ ቻርተር ላይ እንዲፈራረሙ እና በእዚህ ቻርተራቸው መሰረት መረጃ እንዲያቀርቡ ማድረግ መቻል እጅግ አስፈላጊ ነው።ቻርተሩ ሕዝብ በጎሳ ለመከፋፈልም ሆነ ሀገራዊ ፀጥታን አደጋ ላይ የማይጥሉ ጉዳዮች ላይ አደጋ እንዳይፈጥሩ ቃል የሚገቡበት ሰነድ ይሆናል።ይህ ጉዳይ የሚድያ ነፃነት ዞሮ ማፈን አይደለም ወይ? ብለው የሚያስቡ ይኖራሉ።ሆኖም ግን በጋራ እራሳቸው ተመካክረው የሚስማሙበት ቻርተር ማድረጉ እና የሚዳኛቸው የሀገር ሕግ ብቻ ሳይሆን የራሳቸው የጋራ ቻርተር መኖሩ አስፈላጊ ነው።በተለይ ሚድያ በክልል ደረጃ የመሰረተች ሀገር አንድ አይነት ማሰርያ ሳታስቀምጥ ነገሮች በተካረሩ ወቅት  ሁሉ ሚድያው የውሸት መረጃ አገኘሁ በማለት ህዝብን በማስደንበር ጭምር ኢትዮጵያን  ወደ ግጭት አይመራም ብሎ ማሰብ አይቻልም።ስለዚህ ነው የሚዳኙበት እና የሚያከብሩት የጋራ ሰነድ ምድያዎቹን በተመለከተ የሚያስፈልገው።ሰነዱ ሀገራዊ ኃላፊነት የሚያሳይ የጎሳ ፖለቲካ ማንፀባረቂያ ሚድያዎች እንዳይሆኑ ያስገድዳቸዋል።

ከሚድያው ጋር መታየት ያለበት ሌላው መፍትሄ የምጣኔሀብት መዋቅራዊ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።አሁንም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ቅኝት በህወሓት ሰራሽ መሰረት ላይ የወደቀ ነው።የሚንቀሳቀሰው ሀብትም ሆነ አደረጃጀት የነበረው ነው።በእርግጥ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ተአምር እንዲፈጠር አይጠበቅም።ሆኖም ግን መሰረታዊ የሆኑት ጉዳዮች ላይ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት አደጋውን መከላከል ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሃብቱን ለማስፈንጠር እና ወደተሻለ ደረጃ ለመውሰድ ይረዳል።ለምሳሌ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ባለ ሀብቶች ወደ ሀገር ቤት መዋለ ንዋያቸውን ይዘው እንዲገቡ ልዩ ጥቅም መስጠት ሁሉ ይመለከታል። በሌላ በኩል ሃገራዊ ጥናት እና ምርምር የሚሰሩ ሀገር በቀል ድርጅቶችን ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር  የመሳሰሉ  ሃገራዊ ድርጅቶች ያለውን የምጣኔ ሀብት ጉድለት እና መጪ አደጋዎች እንዲጠቁሙ በሰው ኃይልም ሆነ በገንዘብ መደገፍን ሁሉ አስፈላጊ ነው።

ለማጠቃለል ኢትዮጵያ በመጪው የፖለቲካ መንገዷ ብርሃንም ሆነ ጨለማ ይታያሉ።ስላልደረስንበት ብርሃንም ሆነ ጨለማ የለም ማለትም ስህተት ነው። ዕድሉም ሆነ ርግማኑ ግን እያንዳንዱ ሰው በሚሰራው ሥራ የሚወሰን ነው።በዝምታ ብቻ ካለ አንዳች ንቃት እና ትጋት በዝምታ ብርሃን እየጠበቅን ከሆነ ተሳስተናል።ለውጡ በትክክል እንዲሄድ መንግስትን በሚገባ ማገዝ እና ጉልበት መሆን ከሁሉም ይጠበቃል።አንዳንዴ የሚጠበቀው ከባድ ላይሆን ይችላል።አንድ ዶላር በቀን ለማዋጣት ችላ ማለት የንቃትም የትጋትም ችግር ነው።ይህ እንግዲህ በዝቅተኛ ደረጃ የቀረበ ሃገራዊ ጥሪ ያውም በውጭ ላለው የቀረበው ነው።ከሀገር እስከ ባህር ማዶ ያለው ኢትዮጵያዊ ግን ነገ ጨለማን ሳይሆን ብርሃንን ለማየት በፅንፍ የቆሙ ሃሳቦች ላይ የእርግማን ውርጅብኝ ከማውረድ ይልቅ ወደ ማዕከላዊ እና የብዙሃኑ ጉዳይ ላይ እንዲመጡ የመተማመኛ መደላድሎችን በማመቻቸት ለማምጣት መሞከር ከሃይማኖት መሪ እስከ ዕድር ፀሐፊ ሚናቸውን ሳይንቁ የሚሰሩት ብዙ ተግባር አለ።ስለሆንም ጨለማ የለም ብሎ ተደላድሎ መቀመጥም ሆነ ብርሃን ላይ ነን ምንም አደጋ የለም ብሎ ጊዜን በፉጨት ማሳለፍ፣ሁለቱም አደጋዎች ናቸው።ሶርያን የተመለከተ በዲሞክራሲ አይቀልድም።ለሁሉም ደግሞ ተጠያቂ መንግስት ብቻ ነው ብሎ የመደምደም አባዜ መላቀቅ እና ሁላችንም ተጠያቂ ነን ብሎ ከማሰብ እና ወደ ሥራ ከመግባት ብርሃኑን የበለጠ የማቅረብ ሥራ ይጀመራል።ዛሬ ይህንን የዲሞክራሲ ወጋገን በሚገባ እንዲያበራ  መሰራት ያለበት ሕዝብ ተግቶ መስራት አለበት።ውጤቱን በጋራ ለማግኘት ደግሞ እያንዳንዱን ሰው እንደ ግለሰብ፣ሕብረተሰብ ደግሞ እንደስብስብ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments: