ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, February 22, 2019

ይድረስ ለተከበሩ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ

 Bildergebnis für takele uma

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ 

ጉዳያችን /Gudayachn
የካቲት 16/2011 ዓም (ፈብሯሪ 23/2019 ዓም)
  • ክቡር ምክትል ከንቲባ ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ የኦሮምያ ተወላጆችን ከሱማሌ ኦሮምያ ድንበር ብቻ ከሚያስመጡ የጎንደር ተፈናቃዮችንም፣የጉጂ ዞን ተፈናቃይም፣የቤንሻንጉል ተንከራታችንም እና ሌሎችንም አምጥተው በአዲስ አበባ ዙርያ አስፍሩልን እና አዲስ አበባ የበለጠ ሕብረ ብሔርነቷን ታድምቅልን።

ክቡር ምክትል ከንቲባ -

በቅድምያ የከበረ ሰላምታ እያቀረብኩ።ለጤናዎ እንዴት ሰነበቱ? ክቡር ምክትል ከንቲባ ለአዲስ አበባ ያለዎት መልካም ምኞት እና በሚያሳዩት ትጋት በአንክሮ እና በደስታ እየተከታተልን ነው።ቀደም ብለው ከኪነጥበብ ሰዎች ጋር የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ችግር አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ለስራው ያለዎትን ቁርጠኝነት እና ችግሩን በምን ያህል ደረጃ እንደተረዱት ገልጠው ነበር።ይህንኑ ንግግርዎን ተከትሎም በአዲስ አበባ የጎና ተዳዳሪዎች ዙርያ የተጀመሩት ስራዎች እና እርስዎም የአዲስ አበባ የምሽት ብርድ ሳይበግርዎት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማሰባሰቡ ሥራ ላይ ሁሉ መሳተፍዎ እንደማንም  በጎ እንደሚያስብ ኢትዮጵያዊ እኔንም አስደስቶኛል።ወደፊትም ይህ ቅዱስ ተግባር ሊቀጥል እንደሚገባው ከሚያስቡት ሰዎች ውስጥ ነኝ።

በቅርቡ ከአዲስ አበባ መምህራን ጋር ባደረጉት ውይይትም የገበሬ ልጅ መሆንዎን እንዴት ተቸግረው እንደተማሩ እና የአንድ መምህር አስተዋፅኦ ለአንድ ተማሪ ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን አንድ የስድስት ኪሎ አካባቢ ያለ ትምህርት ቤት መምህር ማበረታቻ የእርስዎን ሕይወት እንደቀየረ ሲያብራሩ መምህራኑን በሀሳብ ይዘዋቸው እረጅም እርቀት ሄደው ነበር።

ክቡር ምክትል ከንቲባ -
ከላይ የጠቀስኩት መንደርደርያ ዛሬ ለመላክ ከፈለኩት ጉዳይ ጋር ቀጥታ ተያያዥ አይደለም።የዛሬው መልዕክቴ ዋዜማ ራድዮ ላይ የተገለጠው አስደሳች ዜና ይመለከታል።ዜናው ''ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በአዲስ አበባ እና በዙርያዋ በቋሚነት እንዲሰፍሩ በከተማው ቦታዎች እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው'' ይላል ዜናው።ይህ ዜና ትክክል ከሆነ እሰይ! ወንድሞቻችን ሊመጡልን ነው።አብሮ መብላት፣አብሮ መኖር፣ተሳስቦ እና አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ብሎ ክፉ ዘመንን ማሳለፍ በጣም አስደሳች ነው። ወትሮም የኢትዮጵያውያን ባህል ነው።ከደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት ከጅጅጋ የምትርቀው አዲስ አበባ ላይ እነኝህን ወገኖቻችንን በብዙ ወጪ አሳፍረው አምጥተው ለአዲስ አበባ ዙርያ ውበት እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑ ለኢትዮጵያውያን ሌላ አስደሳች ዜና ነው።

አዲስ አበባ እንደሚያውቁት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተሰብስቦ የሚኖርባት ድንቅ ከተማ ነች። እንደሚያስታውሱት በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች በርካታ ሕዝብ ተፈናቅሏል።ጎንደር አዘዞ ብቻ ከአርባ ሺህ ሕዝብ በላይ ተፈናቅሏል።ደቡብ ጉጂ ዞን እና ቴፒ፣ወደ ምዕራብ ስንሄድ ቤንሻንጉል እና ወለጋም ሕዝብ ተፈናቅሏል።

ክቡር ምክትል ከንቲባ : -
ከአዲስ አበባ ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት የነበሩ ወገኖቻችን የኦሮሞ ተወላጆችን በአዲስ አበባ ዙርያ እንዲሰፍሩ ሲያደርጉ አርባ ሺህ የጎንደር ተፈናቃዮችንም አደራ አይርሷቸው።አዲስ አበባ ዙርያ አምጥተው ያስፍሩልን።ከጉጂ ዞን የተሰደዱትንም እንዲሁ በሌላው የአዲስ አበባ መውጫ በኩል አምጥተው ያስፍሩልን። ለምሳሌ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉትን ከገርጂ ማዶ ካለው ተራራ ላይ ቢሰፍሩ፣ከጉጂ ዞን የተፈናቀሉትን በቡራዩ መስመር፣ ከጎንደር የተፈናቀሉትን ደግሞ በቢሸፍቱ መስመር ከቢሸፍቱ ማዶ እንዲሰፍሩ ቢደረግ  እና ከቴፒ የተፈናቀሉትን ከቡራዩ ወጣ አድርገው ቢያሰፍሩልን አዲስ አበባን እንዴት የበለጠ ውበት በጨመረላት ነበር ብዬ አስባለሁ። ሰፈራውን ከሱማሌ የመጡ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ከሚያደርጉ እንዲህ  ሕብረ ኢትዮጵያዊ ዙርያዋን በከበባት አዲስ አበባ በራሱ መኖር ለአዲስ አበቤ ትልቅ ዕድል ይመስለኛል። በተለይ ሰፋሪዎቹ የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት ስለሆኑ ለአዲስ አበባ አዲስ የኢኮኖሚ ጥቅም ያስገኛል።ለምሳሌ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ በከብት እርባታ ስልጡን ስለሆኑ የአዲስ አበባ ሕዝብ የወተት እና ሥጋ ችግሩ ተፈታ ማለት ነው።ከጎንደር ተፈናቅለው በአዲስ አበባ የምያሰፍሯቸው ደግሞ የሩዝ እና የጤፍ እርሻ ጎበዞች ናቸው አሉ።ይህ ማለት ለአዲስ አበባ ሕዝብ መንግስት ሩዝ ከሕንድ ማስመታት ቀረለት ማለት ነው።ሱፐር ማርኬቶችም የፈረንጅ ሩዝ ከማገላበጥ የጎንደር ገበሬ ያመረተውን በጆንያ ማገላበጥ ጀመሩ ማለት ነው። ከቴፒ የተፈናቀሉት ደግሞ በቅመማ ቅመም እርሻ የሚያክላቸው የለም አሉ።ይህ ማለት ከደቡብ እየተጫነ የሚመጣ ቅመማ ቅመም በአዲስ አበባ ዙርያ ሲመረት የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እንዴት እንደሚያስመነድገው አይታይዎትም?

ስለሆነም ክቡር ምክትል ከንቲባ ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ የኦሮምያ ተወላጆችን ከሱማሌ ኦሮምያ ድንበር ብቻ ከሚያስመጡ የጎንደር ተፈናቃዮችንም፣የጉጂ ዞን ተፈናቃይም፣የቤንሻንጉል ተንከራታችንም እና ሌሎችንም አምጥተው በአዲስ አበባ ዙርያ አስፍሩልን እና አዲስ አበባ የበለጠ ሕብረ ብሔርነቷን ታድምቅልን።

አክባሪዎ የጉዳያችን ገፅ አዘጋጅ

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...