ጉዳያችን GUDAYACHN
ጳጉሜን 1/20119 ዓም (ሴፕቴምበር 7/2019 ዓም)
ያሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሲኖዶሳዊ እውቅና ውጪ በኦሮምያ ክልል የቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ነን ያሉ በእነ ቀሲስ በላይ የሚመራው ቡድን ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።በሰላሳ ቀናት ውስጥ ምላሽ ይሰጠኝ የሚል የማስፈራርያ መግለጫ የሰጠው ኮሚቴ መግለጫ ከመስጠቱ በፊት መግለጫ ይሰጥበታል በተባለው አዳራሽ (በኦሮምያ የባህል ማዕከል) ወጣቶች ጉዳዩን በመቃወም ተሰብስበው ከሄዱ በኃላ፣ ወጣቶቹን ለመበተን ብቻ መግለጫው ቀርቷል በሚል የማታለያ ንግገር ወጣቶቹ እንዲሄዱ ከተደረገ በኃላ፣ኦኤምኤን እና አዲስ ቲቪ ወደኃላ ቀርተው መግለጫው እንዲሰጥ መደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
መግለጫው ሕጋዊ ሰውነት ያላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብላ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት በኦሮምያ የቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ የተባለ አካል እንደማታውቅ አስታውቃ ነበር። ጉዳዩን ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ከነሐሴ 30 ጀምሮ በተፈጠረው ቤተክርስቲያንን የማወክ ሙከራ ዙርያ ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን በእዚሁ ዕለት የኦሮምያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተወካይ ሙ/ጥ/ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተገኙ ሲሆን በቀጣዩ ቀን ጳጉሜን 1 ቀን ብፁዓን አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጋር በቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ዙርያ ተወያይተዋል።
በኦሮምያ ክልል የተቀጥላ ቤተ ክህነት አደራጆች ጀርባ
በኦሮምያ ክልል የተቀጥላ ቤተ ክህነት ለማደራጀት የተገዳደሩት አካላትን በመደገፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው ያለበት አካሎች የመንግስት ባለስልጣናት፣የፅንፍ ጎሳ ፖለቲካ አራማጆች፣የአክራሪ እስልምና ተከታይ የሆኑ እና የህወሓት አክትቪስቶች አሉበት።በመሆኑም እነኚህ አካላት በፕሮፓጋንዳ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር መገዳደር ሽፋን ሲሰጡ ተስተውለዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የታየው በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና በህወሓት ቡድን መሃል እንደአገናኝ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አካሎች በኦሮምያ የቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ እያለ እራሱን የሚጠራውን ቡድን ሲያወድሱ ተስተውሏል። ለምሳሌ የሰሜን አሜሪካ የትግራይ ልማት ማኅበር ሰብሳቢ አቶ አሉላ በኦኤምኤን ቴሌቭዥን ላይ ቀርቦ ሲናገር የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያሉት ቤተ እምነቶች ''የደርግ ቤተ እምነቶች ናቸው'' በማለት ሲነቅፍ ተሰምቷል።
ቀጣይ የቤተ ክርስቲያን አደጋዎች
አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግልጥ በሆነ አደጋ ላይ እንደሆነች እየታየ ነው።ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ማደርያ ሆና አደጋ ላይ ነች ማለቱ በራሱ አስቸጋሪ ቢሆንም፣በሰው ሰውኛው የመረዳት አቅም ግን ግልጥ የሆኑ አደጋዎች ከፊቷ ተደቅነዋል።የመጀመርያው አደጋ በኦሮምያ ክልል ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማወክ የሜፈልጉ ቡድኖች ሙከራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ቤተ ክርስቲያኒቱን በኃይል ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት ነው።ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የመሞከር ሂደት ከጀርባው ሌላ ኃይል ያለ በማስመሰል እና ተራ ውንብድና አስመስሎ በማይፈልጉት ካህን ላይ ጥቃት ማድረስን ሁሉ ይጨምራል።ባጭሩ ተራ ዱርየዎች በማደራጀት የሚፈልጉትን ለማስፈፀም መሞከርን ሁሉ ይጨምራል ማለት ነው።በእዚህ ሂደት ውስጥ ግን መንግስት በአግባቡ መቆጣጠር ካልቻለ የቤተ ክርስቲያን ጉዳት ብቻ ሳይሆን የሚከተለው የሰው እና የንብረት መጥፋትም ሁሉ ሊያስከትል ይችላል። ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የታችኛው የመንግስት መዋቅር ተገቢ ጥበቃ ለቤተ ክርስቲያን እያደረገ አለመሆኑ ነው።
ወደፊት ለችግሩ መፍትሔነት ምን ይሰራ?
የሚከታተሉት ዋና ዋና ተግባራት መሰራት የሚገቡ ስራዎች ቢሆኑ ተገቢ ይመስለኛል። እነርሱም -
ቤተ ክርስቲያን
- በፍጥነት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ልዕልናዋን መልሳ ማስከበር።በሀገር ውስጥ በራሷ መርሃግብር በመሄድ ሃገራዊ የእርቅ ፣የሰላም እና የልማት መርሃግብሮች እያዘጋጀች መሄድ ይኖርባታል፣ለምሳሌ በትግራይ ሕዝብ እና በዓማራ መካከል ሕዝብ ለሕዝብ የማገናኝት ሥራ፣የፀጥታ አደጋ ይኖርባቸዋል በተባሉ ቦታዎች ቀድማ በመገኘት፣
- ለእዚህም ውስጣዊ አስተዳደሯን በአጭር ጊዜ ማዘመን፣
- በቤተ ክርስትትያንቱ የገንዘብ ብክነት የሚጠየቁ ሰዎች በቤተክርስቲያኒቱ ፍትህ መንፈሳዊ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ስርዓት መሰረት ብይን እየሰጠች ከቦታቸው እያነሳች ውስጧን ማስተካከል እና በሁሉም የአገልግሎት ክፍሎቿ አቅም ያለው የሰው ኃይል ማግኘት፣
- ብቃት ያለው የሚድያ አገልግሎት እንዲኖራት ማድረግ፣
- የውጭ ግንኙነቷን ማሳደግ ለምሳሌ ከእህት አብያተ ክርስቲያናት ጋር፣
- ሀገር አቀፍ የወጣቶች መርሃ ግብር በብዛት ማዘጋጀት
- በማኅበራዊ ዘርፍ አገልግሎቷን ማስፋት፣
ከምእመናን ከሚጠበቁት ውስጥ
- ምእመናን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በየትኛውም የቤተክርስትያኒቱ ጉዳይ መከታተል ፣
- በቤተ ክርስቲያን እና ልጆቹ ላይ ምንም አይነት የማስፈራርያ አደጋ ቢፈፀም በፅናት ከቤተ ክርስቲያን ጋር መቆም እና መመከት፣
- ምዕመናን ከፖለቲካ ጉዳይ ራሳቸውን ማራቅ አቁመው በብዛት እና በጥራት ወደ ፖለቲካው ዓለም ገብተው ሀገራቸውን የመምራት እና ኃላፊነት የመውሰድ እንቅስቃሴ ማድረግ፣
- የቤተ ክርስቲያን የሕግ ክፍል በአዲስ መልክ ማጠናከር እና ጀረጃውን ከፍ እንዲል ማስድረግ።
የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ርስቲያንን የማያውቁ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥላቻ ያለባቸው ግለሰቦች በኢትዮጵያ የፖለቲካ የስልጣን ተዋረድ ውስጥ ስልጣን ላይ በብዛት መኖራቸው ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳ ለመሆኑ ምንም አሌ የሚባል ጉዳይ የለውም።ሁኔታው ለቤተ ክርስቲያን ደወል ነው።ደውሉን ሰምቶ ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ መነሳት ከምእመናን ይጠበቃል።
የዓለም ማዕበል ጎርፍ
ጉዳያችን/Gudayachn
ሴፕቴመብር 7/2025 ዓም)
ሴፕቴመብር 7/2025 ዓም)
No comments:
Post a Comment