ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, September 8, 2019

በዘር የሚያምኑ ሚድያዎች ዕድሉ እስከተሰጣቸው ድረስ የሩዋንዳ ችግር ኢትዮጵያ በር ላይ እንደሆነ ማወቅ አለብን።ኢትዮጵያ ''ሲሬስ'' ችግር ውስጥ ገብታለች:: አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ኦስሎ፣ኖርዌይ የተናገሩት (ጉዳያችን ልዩ ዘገባ -Gudayachn exclusive)


ከጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል 

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ጳጉሜን 2/2011 ዓም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ በኦስሎ፣ኖርዌይ የምስጋና ዝግጅት ተዘጋጅቶላቸው ነበር።በዝግጅቱ ላይ ቁጥሩ ከፍ ያለ የኖርዌይ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 በኖርዌይ ለሚኖሩ እና ባለፉት ዓመታት ለዲሞክራሲ ትግል  አስተዋፅኦ ላደረጉ ኢትዮጵያውያን የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን  የምስክር ወረቀቱን የቀድሞው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ዶ/ር ሙሉዓለም እና አቶ አንዳርጋቸው ሰጥተዋል።

በዝግጅቱ ላይ አቶ አንዳርጋቸው በቅርቡ ያሳተሙትን ''ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር'' ቅፅ 1 መፅሐፍ ዙርያ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን ከመፅሐፉ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ከመስጠታቸው በላይ በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ ያላቸውን ሃሳብ ለተሰብሳቢዎች አካፍለዋል።በእዚህ ዘገባ ላይ በተለይ በዋናነት  በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተናገሩትን እና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በመፅሐፋቸው ዙርያ ያነሷቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይደረጋል።

ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ

አቶ አንዳርጋቸው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የገለጡበትን ዓረፍተ ነገር የኢትዮጵያ ጉዳይ ግልጥ ያልሆነ መንገድ ላይ ነው ያለው። የመፍረስ አደጋ ያንዣበባት ለመሆኑ ምክንያቱ ብሔርን መሰረት ያደረገው ህገ መንግስት ነው በሚሉ ዓረፍተ ነገሮች ሲሆን በመቀጠል ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተዋል።እነርሱም -
  • የማዕከላዊ መንግስት የመምራት ሚና በሌለበት ሁኔታ እና ክልሎች በታጠቀ ኃይል ተጠናክረው እያለ ማንኛውንም ችግር  ለመፍታት አስቸጋሪ ነው።
  • የተረኝነት ስሜት የሚለው ችግር አሁን ቢሰማም ነገ የሚያስበውም እንዳይቀጥል የሚሰራው ሥራ ነው  ወሳኙ።ተረኛ ስሜት ሁሉም ጋር አለ።ኦሮሞው ውስጥ ኦዴፓ የተረኝነት ስሜት የሚያራምድ እንዳለ ሁሉ ዓማራ ውስጥም እንዲሁ አለ።
  • እኔ መቼም አልጋ በአልጋ ላይ ነን ብዬ አላውቅም።እኔ ከእዚህ በፊት እንዳልኩት ለውጡ ትልቁ ስህተቱ በራሱ ኢህአዴግን ይዞ ለለውጥ መነሳቱ በራሱ ስህተት አለው።
  • ትልቁን አጀንዳ ትተን ትንንሾቹ አጀንዳ ላይ ብቻ ከተጠመድን ሳናውቀው ከጠላቶች ጋር እየተባበርን ነው ማለት ነው።
  • ኢትዮጵያ ''ሲሬስ'' ችግር ውስጥ ገብታለች።ከእዚህ በፊትም እንዳስቀመጥኩት በእዚህ የጎጥ ፖለቲካ ከቀጠልን  በፐርሰንት እንዳልኩት 80% አደጋ ውስጥ ስትሆን 20% ነው የመዳን ዕድሏ።
  • የኢትዮጵያ ፈዲራሊዝም ለክልሎች ስልጣን ሰጥቶ ማዕከላዊውን አዳክሟል።ይህ በየትም ዓለም የሌለ ነው።ህንድ ትልቅ የፌድራል አስተዳዳር ያላት ሀገር የክልል አስተዳደሮች መሳርያ የመታጠቅ መብት የላቸውም፣ሌላው ቀርቶ ማዕከላዊ መንግስት የክልል ምክር ቤቶች የወሰኑትን ውሳኔዎች ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አለው።
  • በዘር የሚያምኑ ሚድያዎች ዕድሉ እስከተሰጣቸው ድረስ የሩዋንዳ ችግር ኢትዮጵያ በር ላይ እንደሆነ ማወቅ አለብን።

  • ኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎችን መለያየት እና ሀገር ማድረግ ፈፅሞ አይቻልም።የሚሞክር ካለ ቀጥታ ማባርያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ነው የሚገባው።ቼክ እና ስሎቫክ ሲለያዩ በቀጥታ መለያየት የቻሉት ጥርት ያለ ልዩነት ከድንበር ጋር  ስላላቸው ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋሃደ ሕዝብ ነው ያለው።ነገ ተነስቶ አንዱ ክልል ልገንጠል ቢል በማግስቱ ድንበሩ ላይ ያለ ነው ጦርነት የሚከፍቱት።
  • አሁን መሰራት ያለበት ትልቁ ስልታዊ ሥራ ማዕከላዊ መንግስትን ማጠናከር ነው።የታጠቁ የክልል ኃይሎች ትጥቅ መፍታት እና የዘር ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ሚድያዎች መስተካከል አለባቸው።ማዕከላዊ መንግስት ስልጣን በሌለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ እና ሌሎች ስራዎች ሁሉ ከባድ ናቸው።
  • ዓማራን በተመለከተ ''ታርጌት'' ሆኗል ወይ? አዎን! ይህንን እኔ ወያኔዎች ውስጥ ቀድሜ የተናገርኩ እኔ ነኝ። 
  • ኢትዮጵያ ውስጥ ዓማራነት ከኢትዮጵያዊነት የሚለይ ነገድ ማውጣት ከባድ ነው።አማርኛ በራሱ ያሰባሰበው ማኅበረሰብ እንጂ ወደ ነገድ አደገ ማለት አይቻልም።ይህ ነው ኢትዮጵያን እስካሁን እንደ ኢትዮጵያ ሆና ፀንታ እንድትቆም ያደረጋት።
  • ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚባለው ቢያንስ ከሁለት ብሔር የወጣ ውሁዱ ኢትዮጵያዊ እስከ 40% መድረሱ ነው የሚነገረው እና ኢትዮጵያዊነትን ትተን ወዴት ነው የምንሄደው?


ለአቶ አንዳርጋቸው ስጦታ ሲበረከትላቸው 

ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር በተሰኘው መፅሐፍ በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል -


  • መፅሐፉን እንድፅፍ ያነሳሳኝ ከ1966 ዓም ጀምሮ የተንሳው እንቅስቃሴ መሰረቱ ምን እንደሆነ ለመግለጥ ነው ከ1870 የጀመርኩት።
  • መፅሐፉን በተመለከተ የሚነሱ ሃሳቦች በትክክል አንብቦ ወጥ የሆነ ሂስ ሳይሆን ብጥስጣሽ  ሃሳቦች ናቸው ያየሁት። ከእዚህ የተገነዘብኩት ብዙዎች መፅሐፉን አላነበቡትም ብዬ ገምቻለሁ።
  • መፅሐፉ ላይ ከተነሱት ሃሳቦች አንዱ ''የአያቶቼ ጥጃ ማሰርያ'' የሚለው አዲስ አበባን በተመለከተ የጠቀስኩት ላይ ሃሳቡን ብዙ ሰው የተገነዘበው አይመስለኝም።እኔ ሃሳቤ አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ሆና ሳለ ከተማዋ ላይ የሌለ የይገባኛል ጥያቄ  እና ሌሎች ቃላት የሚያነሳው ከአዲስ አበባ በርቀት ወለጋ ወይንም አርሲ ያሉ ናቸው።እኔ ያልኩት ከተማው ጉዳይ ያገባኛል ለማለት ከሆነ እዚሁ የኖርኩት እኔም የሚመለከተኝ የቅርቡ ሰው አያቶቼ ጥጆች ያሰሩበት እያለሁ የሩቁ ሰው ለምን መለያየት ይፈጥራል ከሚል ነው።ይህ ነው የሃሳቡ ጭብጥ።
  • አዲስ አበባ የሰፋችው በሠራዊት እነርሱን ተከትሎ በመጣው የሴተኛ አዳሪ፣ሰራተኛው ነው የሚለውን ከራሴ ያመጣሁት ከራሴ አይደለም ከራስ ዕምሩ የወሰድኩት ነው።ይህ ሃሳብም በከተማው ባለቤትነት ካነሳችሁ የከተማው ባለቤትነት እና ከተማዋን የገነቡት ዝቅተኛው የከተማው ነዋሪ ነው፣ይህንን ሕዝብ ወዴት ልትገፉት ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንዲሆን ነው።
  • መፅሐፉን እስከመጨረሻው ያነበበ ሰው የሚረዳው እና እኔም ላንፀባርቀው የሞከርኩት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ነው።መፅሐፉን አንብቡት እና ሂስ ብትሰጡ ደስ ይለኛል።መፅሐፉ ላይ ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉበት። የቻይናው ማኦ ሴቱንግ በፃፈው ላይ ከጃፓን ጋር ለመዋጋት እንደ ኢትዮጵያውያን የደፈጣ ውጊያ ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው ልናሸንፍ የምንችለው ያለበት እና ሌሎች በርካታ ነጥቦች መፅሐፉ ውስጥ ተካቷል።
በመጨረሻም አቶ አንዳርጋቸው በመርሃግብሩ ከመዘጋቱ በፊት የተዘጋጀላቸው ልዩ ስጦታ ተበርክቶላቸው የመርሃግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: