ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, September 1, 2019

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚታየው የመንግስት አያያዝ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል (ጉዳያችን ልዩ እና ወቅታዊ )

 ''ቀሲስ'' በላይ ሐጂ ጃዋር እና ሌሎች የመታሰቢያ ፎቶ 

ጉዳያችን GUDAYACHN
 ነሐሴ 27/2011 ዓም (ሴፕቴምበር 2/2019 ዓም)
======================
በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉትን ርዕሶች ያገኛሉ - 
>>   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካ እና  
        የመካከለኛው ምስራቅ የኃይል ሚዛን መለኪያ ነች፣
>>    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ቋንቋ መቀደስ፣ማስተማር ትከለክላለች? 
>>   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚታየው የመንግስት አያያዝ በኢትዮጵያ 
        በአጭር ጊዜ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል:: እንዴት ?
>>   ቤተ ክርስቲያኒቱን የናቁ መንግሥታት ''የውሃ ላይ ኩበት'' እና 
>>    መፍትሄው።

         
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባጭሩ አገላለጥ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ሕዝብ የያዘች፣ከቤተ መንግስት እስከ ታች የገበሬ መንደር ድረስ መዋቅር ያላት፣በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ላይ የቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅኖ ያላት፣ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ህልውና፣መልካም ስም ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመን የማይሽረው ሚና ሁሉ የያዘች ታላቅ ተቋም ነች። ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከደቡብ ኮርያ እስከ ደቡብ አሜሪካ ከአውስትራልያ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሰሜን የአውሮፓ ጫፍ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ገዝታ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ሆናለች።ከእዚህ በታች ያለው ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ ስናነሳ እነኝህ ሁሉ ጉዳዮች ከግንዛቤ መግባት አለባቸው ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ የኃይል ሚዛን መለኪያ ነች። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያን የኃይል ሚዛን ብቻ ሳይሆን  የስነ-መንግስት፣የስልጣኔ፣የሰላም እና የጦርነት ሁኔታ ሁሉ የሚወስን ወሳኝ ኃይል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ ነበራት፣አሁንም አላት።ይህ አባባል የተጋነነ የሚመስለው ካለ በአንክሮ ከእዚህ በፊት የነበረውን ግንዛቤ እና እውቀት መልሶ ከመፈተሽ ሌላ አማራጭ የለውም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአራተኛው ክ/ዘመን ክርስትና ብሔራዊ ኃይማኖት ሆኖ  በታወጀበት በአክሱም ዘመነ መንግስት ንጉስ ኤዛና በሶስት ቋንቋዎች ማለትም በግሪክ፣ሳባዊ እና ግዕዝ ቋንቋዎች አስቀርፆ ባስቀመጠው የታሪክ ማስረጃ ንጉሡ እስከ መሐል አፍሪካ፣እና እስከ ደቡብ የዓረብ ግዛቶች ሁሉ ዘልቆ በሄደባቸው ዘመቻዎች ሁሉ ጉልበቱ ኃይማኖቱ እንደነበረ በገለጠበት ታሪካዊ ማስረጃ  የቤተ ክርስቲያኒቱ ወሳኝ ፖለቲካዊ ኃይል እና ወታደራዊ የበላይነት ከሞራል ልዕልና እስከ መንፈሳዊ ዕምነት መሰረት እንደሆነች ለመረዳት ይቻላል።

''የዘመነ ክርስትና አክሱም ተብሎ የሚታወቀውን ወቅት (ከ4ኛው እስከ 10ኛው ክ/ዘመን) የኢትዮጵያ ስልጣኔ በአሕጉሩ ካሉት ሌሎች ስልጣኔዎች የተለየ ሆኖ እንዲያድግ ካበቁት ነገሮች አንዱ ነው'' (የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከመጀመርያው እስካሁኑ ዘመን፣አንድርዘይ ባርትንስክ እና ዮአና ማንቴል-ኒችኮ፣ ትርጉም ዓለማየሁ አበበ፣2006 ዓም፣ገፅ 21)

የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ውድቀት በኃላ፣በ11ኛው ክ/ዘመን የተነሳው የዛግዌ ስርወ መንግስት ከቅዱስ ላልይበላ ድንቅ ስልጣኔ እስከ 16ኛው ክ/ዘመን ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ እና በ16ኛው ክ/ዘመን የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካን ታሪክ ለመቀየር የተነሳው በቱርክ የታገዘው የመሐመድ (ግራኝ መሐመድ) ዘመቻ ደቡብ ጎንደር ላይ እስኪቀጭ ድረስ ይህ ነው የማይባል ጥፋት አድርሷል። ጦርነቱ ባይቀጭ ኖሮ ዛሬ የምዕራብ፣የምስራቅ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች በሙሉ የጦርነቱ ገፈት መቅመስ ብቻ ሳይሆን የእስልምና እምነት በውድ ሳይሆን በግድ እንዲጫንባቸው በተደረገ ነበር። ሆኖም ግን የኃይል ሚዛኑን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ብሎም የመካከለኛው ምሥራቅን  ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የወረራ ተፅኖ ሁሉ  ሚዛኑን እንዲጠብቅ ያደረገችው በመንፈሳዊም ሆነ በሞራል ልዕልና ቀድማ የተገኘው እና በኢትዮጵያ የነገሱ ነገስታትን በሁለት በኩል የተሳሉ (በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው) ሰይፍ እንዲሆኑ ያበቃች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነች።ቤተ ክርስቲያኒቱ  ከመንፈሳዊ ተቋምነት ባለፈ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ የኃይል ሚዛን መሆኗ ያልገባቸው  መንግሥታት ከ1967 ዓም እስካለንበት ዘመን ድረስ፣ከላይ እንደተገልጠው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን ክብር፣ምክር እና ህልውና ተገቢውን ዋጋ ሳይሰጡ ''የውሃ ላይ ኩበት'' እንደሆኑ አልፈዋል።ወደፊትም ተገቢው መስመር ላይ እስካልመጡ ድረስ ይሆናሉ።

ቤተ ክርስቲያኒቱን የናቁ መንግሥታት ''የውሃ ላይ ኩበት'' 


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በተለይ ላለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመን ወደ ቤተ መንግስት የመጡ መንግሥታት ማለትም የደርግ መንግስት፣የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት እና በጥገናዊ ለውጥ ውስጥ የሚገኘው የአሁኑ የኢህአዴግ መንግስታት የቤተ ክርስቲያኒቱን አቅም፣የአለት ድንጋይነት እና ጥልቅ የሆነ ከህዝብ ጋር ያላት ቁርኝት ስላልተረዱት ወንበራቸው ሳይፀና ውኃ ላይ እንደሚንሳፈፍ ኩበት ስንገዋለሉ እየሰነበቱ ከስልጣናቸው አይወድቁ አወዳደቅ እየወደቁ ታሪካቸው እንደ ''ምናምንቴ'' ታሪክ ለወቅ ሳይበቃ እንደቀሩ እና እንደሚቀሩ  በግልጥ የታየ እና የሚታይ እውነታ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ የሚታየው የመንግስት አያያዝ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል:: እንዴት ?

መጋቢት 24/2010 ዓም የኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን በመሰየም ካስታወቅ በኃላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድ ወሳኝ ተግባር  በጠቅላይ ሚንስትሩ እና በአስተዳደራቸው  ተወስዷል።እርሱም ከ1984 ዓም በኃላ በስደት የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ፓትርያርክ  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበረ ጵጵስናቸው እንዲመለሱ እና የተሰደዱ አባቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በውጤቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲኖራት መደረጉ  ነው።ይህ ማለት ግን በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ አባቶች ቀደም ብለው ለእርቅ የሄዱባቸው  በርካታ ሂደቶች በህወሓት በተለይ በአቦይ ስብሐት የግል ጣልቃ ገብነት ሳይቀር መደናቀፉ ሳይዘነጋ ነው። 

ከእዚህ በተለየ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመት እና ለውጡ ከተጀመረበት ከ2010 ዓም አጋማሽ ጀምሮ ከፍተኛ መከራ በቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ፣ካህናት እና ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሳይቀር  ሆን ተብሎ የማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶ ቆይቷል።እነኝህን ጥፋቶች ደግሞ መንግስት ከመከላከል ይልቅ በአንድአንድ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት በቀጥታ ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው እና በማዕከላዊ መንግስትም ምንም አይነት የማረምም ሆነ የሕግ ማስከበር ሥራ አለመታየቱ  በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ይህ በእንዲህ እያለ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እጅግ አደገኛ የማናጋት ሙከራ በስልጣን ላይ ባለው የኢህአዴግ/ኦዴፓ ባለስልጣናት እና ፅንፈኛ የአክራሪ ኃይሎች ጥምረት ተጀምሯል።ጉዳዩ አደገኛ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በምስራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት  ሁሉ ጥብቅ የሆነውን የተዋረድ እና ወጥ የአስተዳደር መስመር ( Eastern Orthodox Church Hierarchy) በተፃረረ መስመር ማንም ያልደፈረውን አደገኛ መንገድ በተከተለ መልክ ''የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ'' በሚል እራሱን ያደራጀ ቡድን ቀሲስ በላይ የተባሉ ''ካህን'' ይዞ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅርንም ሆነ ማናቸውንም ጉዳይ  የማውጣት እና የማፅደቅ ስልጣን ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ስልጣን በመጋፋት መግለጫ  ነሐሴ 26/2011 ዓም በይፋ መግለጫ መስጠቱ ነው።ይህ ቡድን መግለጫውን ከመስጠቱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ ቡድን የማይታወቅ መሆኑን እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም መናገር እንደሌለበት በይፋ መግለጫ መስጠቷ ይታወቃል። ሆኖም ሕጋዊ ሰውነት ያላት ቤተ ክርስቲያን ቡድኑን አላውቀውም ብላ እየተናገረች ቡድኑ መግለጫ ሲሰጥ መንግስት ጥበቃ ከማድረግ አልፎ በኦሮምያ የባህል አዳራሽ መግለጫው እንዲሰጥ ማድረጉ  መንግስት እጁ እንዳለበት በግልጥ የሚያመላክት ነው።መንግስት እጄ የለበትም ካለ ለተሰራው ስህተት ይቅርታ ጠይቆ እና  ስህተቱን የማረምያ ጊዜውን ተጠቅሞ  ማስተካከል አለበት።

በቀሲስ በላይ እንደሚመራ የምናገረው ቡድን ውስጥ የተሰበሰቡ ''ካህናት'' በሚል ስም ሲሰባሰቡ የሰሩት መሰረታዊ ስህተት ከማተኮር በፊት ቡድኑ ለማስመሰል ''ሲኖዶስ በአንድ ሲኖዶስ ስር ነን፣የምንፈልገው ከእዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመንግስትን የአስተዳደር መስመር ተቀትላ የሀገረ ስብከት መዋቅሯን ታስተካክል ነበር እና አሁንም የኦሮምያ ቤተ ክህነት ያስፈልጋል ይህንን መዋቅር ደግሞ በ30 ቀን ውስጥ ካልተፈጠረልን የራሳችንን መዋቅር እንፈጥራለን'' የሚል ድፍረት፣ዕብሪት እና ማን አለብኝነት የተሞላበት  መግለጫ አውጥቷል።መግለጫውን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም ሆነ የመንግስት ሚድያዎች አላረገቡትም ብቻ ሳይሆን በመግለጫው ፊት የሚታየው ሁለቱም የኦዴፓ ቴሌቭዥን እና የሀጂ ጃዋር  ቴሌቭዥን መናገርያዎች ብቻ መሆኑ ጉዳዩ በአንድ ስብስብ ውስጥ ያሉ የፅንፍ ኃይሎች ሥራ መሆኑን በትክክል  የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያፈርስ ተልኮ የተሰጠው ቡድን መሰረታዊ ተቃርኖ ከክርስትና ከራሱ  ጋር ነው።ክርስትና የጎጥ አሰስላለፍ የሚያስቀድም ሃይማኖት አይደለም።ክርስቶስ አሕዛብን ከአይሁድ፣ምሥራቅን ከምዕራብ ሰሜንን ከደቡብ ሳይለይ ለሁሉም ራሱን ሰጥቶ ከሲኦል የሰውን ልጅ ሲያድን የእዚህ አካባቢ ሕዝብ ከሌላው በላይ ክርስትና ይቀበል ብሎ አይደለም።የቄስ በላይ እና ቡድናቸው መሰረታዊ ስህተት  አስተዳደራዊ መሻሻሎች ላይ ጥይቄ ያለው አካል የቤተ ክህነቱ አስተዳደር እንዲሻሻል አብረን እንጠይቅ ብቻ ሳይሆን አይደለም በኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ያለው መዋቅሯ እንዲስተካከል  በቅዱስ ሲኖዶስ መስመር በኩል መጠየቅ ሲገባው የኦሮምያ ክርስቲያኖች የኔን መንደር ልጆች ብቻ ለማፅደቅ እሰራለሁ የሚለው ዕሳቤ በራሱ ትልቅ ስህተት እና ጎጠኛ የመከፋፈል ተግባር ነው።ከእዚህ በተጨማሪ ግን  የቡድኑን መሰረታዊ ስህተት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በአገልግሎት ላይ የሚገኙት  መምህር ቀሲስ ታደሰ ወርቁ እንደሚከተለው የሂደቱንም ሆነ የድርጊቱን ህገ ወጥነት በማኅበራዊ ሚድያ  ገፃቸው ይገልጣሉ። 
''ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሞ ባሕል ማዕከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም የሚካሔደው መርሐ ግብር÷ የኦሮሚያ ‹‹ቤተ ክህነትን›› የማወጅ መርሐ ግብር እንጂ÷ የጋዜጣዊ መግለጫ መርሐ ግብር አይደለም፡፡ ለዚህ የዕወጃ መርሐ ግብር ከፍተኛ የገንዘብ እና የፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ከአሮሞ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች እንደተደረገም መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ገንዘቡም የሚውለው በዋነኝነት ከአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚመጡ ተመልማይ ተሳታፌዎች ለአበልና ለመጓጓዣ ወጪዎች እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ ዐይነቱን ግብራዊ ተጓዳኝነት ስንመለከት÷ ራሱን የኦሮሚያ ‹‹ቤተ ክህነት›› አደራጅ ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው ስብስብ አጀንዳው ‹‹በቋንቋችን እንማር›› ሳይሆን÷ጽንፋዊነት በወለደው መለካዊነት(በቅጥረኝነት) በሀገራዊና በቤተ ክርስቲያናዊ አንድነት ላይ ስንጥቅ መፍጠር መሆኑን እንረዳለን፡፡
ለዚህም ይመስላል ሦስት ነገሮችን የደፈሩት፡፡ የመጀመሪያው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ይሁንታ ውጭ ስሟን መጠቀማቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ሰውነት ያላት የእምነት ተቋም ናት፡፡ ይህ ሕጋዊ ሰውነቷ ደግሞ ስሟንም ይጨምራል፡፡በዚህ መሠረት ያለ እርሷ ይሁንታ ስሟን መጠቀም ወንጀል ነው፡፡ ድርጊቱም ሕጋዊ ሰውነትነቷን በሕገ ወጥነት መጋፋት ነው፡፡ ሁለተኛው ወንጀል መሆኑን እያወቁ አርማዋንና ስሟን በመጠቀም ማኅተም ማስቀረጻቸው ነው፡፡ በሀገራችን ሕግ መሠረት የአንድን ተቋም አርማና ስም ተጠቅሞ ማኀተም ማስቀረጽ ወንጀል ነው፡፡ስብስቡ ይህን ወንጅል ፈጽሟል፡፡ ሦስተኛው የቤተ ክርስቲያንን የማኅተም ቀረጸ አሠራርና ሕግን መተላለፋቸው ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ማኅተም የማስቀረጽ ሥልጣን የተሰጠው ለትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት ብቻ ሲሆን፤ማኅተም የመቅረጽ ሥልጣን ደግሞ የተሰጠው ለትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት ብቻ ነው፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደሚደነግገው በቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉ ተቋማት ሁሉ ማኅተም ለማሰቅረጽ ሲፈልጉ÷የሚቅረጸውን ማኅተም በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት በኩል ለትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ይልኩና ማተሚያ ቤቱም ቀርጾ ማኅተሙን ለአሳተሚ ድርጅቱ ይመልሳል፡፡ እንዲቀረጽላቸው የጠየቁ አካላትም አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽመው ማኅተማቸውን ከማሰተሚያ ድርጅቱ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ከዚህ አኳያ ስብስቡ ይህን የቤተ ክርስቲያናችን የማኅተም አቅራረጽ ሕግ በመተላለፍ ማኅተም አስቀርጾ ተገኘቷል፡፡ ሁለቱም የቤተ ክርስቲያን ተቋማት(አሳታሚ ድርጅቱና ማተሚያ ቤቱ) የስብስቡን ማኅተም እንደማያውቁ ተረጋግጧል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ወንጀል ነው፡፡
ራሱን የኦሮሚያ ‹‹ቤተ ክህነት›› አደራጅ ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው ስብስብ÷ ከቤተ ክርስቲያናችን የማኅተም አቀራረጽ ሕግና አሠራር ውጭ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም ማኅተም አስቀርጾ ተገኘቷል፡፡ማኅተሙም በትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት እንዳልተቀረጸ ተረጋግጧል፡፡ እንዲህ መሆኑ ደግሞ ሌላ ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ ማኅተሙ በምንድ ፈቃድና የት ተቀረጸ ? የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ማኅተም ለማስቀረጽም ሆነ ለመቅረጽ ሕጋዊ ሰውነትን ገንዘብ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ የሕግ ሰውነትን ለማግኘት ደግሞ በዋነኝነት ሁለት አማራጮች አሉ፡፡አንደኛው በሕግ ሥልጣን በተሰጠው መንግሥታዊ ተቋም ተመዝግቦ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ይዞ መገኘት ነው፡፡ ሁለተኛው በሕግ ሰውነት በአለው ሕጋዊ ተቋም ሥር ተደራጅቶ ሕጋዊና መዋቅራዊ ዕውቅና ማግኘት ነው፡፡ ይህ ስብስብ ደግሞ ሁለቱንም የሕጋዊ ሰውነት አማራጮችን አሟልቶ አይገኝም፡፡ ወይም ራሱን የቻለ ሕጋዊ ተቋም ሆኖ በመንግሥት አልተመዘገበም፡፡ አሊያም ደግሞ ሕጋዊ ሰውነት ካላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊና መዋቅራዊ ዕውቅና አለገኘም፡፡ከዚህ አንጻር ስብስቡ በሕግ ፊት ሕገ ወጥ ከመሆኑም በላይ÷ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ወንጅል እየፈጸም ሰለሚገኘ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል፡፡
በዚህ መሠረት ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚተዳደረው በኦሮሞ ባሕል ማዕከል÷ ምንም ዐይነት ሕጋዊ ሰውነት የሌለው ስብስብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም መርሐ ግብር ለማካሔድ ሕጋዊ መሠረት የለውም፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ የኦሮሞ ባሕል ማዕከል አስተዳደር ያለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታ ለሕገ ውጡ ስብስብ መርሐ ግብር ማካሔጃ አዳራሽ የመፍቀድ ሕጋዊ ሥልጣን የለውም፡፡ ‹‹ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤›› የሚለውን ሕገ መንግስታዊ ጥሰትንም ያስከትላል፡፡ በብሔር ተዛምዶነት የሚፈጽም አድሏዊነትም ይሆናል፡፡ ስብስቡም በሌላ ስም መስብሰብ መብቱ ነው፡፡በዚሁ አግባብ ማዕከሉም አዳራሽ መስጠት መብቱ ነው፡፡ ያለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታ÷ በስሟ መርሐ ግብር ለማካሔድ መጠየቅም ሆነ መፍቀድ ግን ወንጀል ነው፡፡'' የመምህር ቀሲስ ታደሰ ወርቁ ፅሁፍ መጨረሻ።
ከላይ በመምህር ቀሲስ ታደሰ ወርቁ እንደተገልጠው ጉዳዩ ህገወጥ የሆነው በቡድኑ ብቻ ሳይሆን የቡድኑ ተባባሪ የሆኑ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሁሉ ለመሆናቸው የኦሮምያ የባህል ማዕከልን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሁኔታ ወዴት ያመራል? ባጭሩ ካለምንም ማጋነን ኢትዮጵያን ወደ አጭር ጊዜ ጦርነት ይመራታል።ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ለሚሆነው ባጭሩ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ አሰላለፍ ያሃይል ሚዛኖች እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ታላቅ ማኅበራዊ መሰረት መመልከት በቂ ነው።
የኢትዮጵያ የወቅቱ ፖለቲካ በተለያዩ የብሔር ኃይሎች ውጥረት የሚታይበት ብቻ ሳይሆን ፈጣን ግጭት የሚፈልጉ ኃይሎች በከፍተኛ ደረጃ በውስጥም ሆነ በውጭ አሰፍስፈው የሚፈልጉበት አደገኛ ወቅት ነው። በውስጥ የዓማራ ብሔር ገንግኖ እንዲወጣ ከታች ገበሬው እስከ ምሁሩ ድረስ አሁን ያለው መንግስት  ''ፀረ ኦርቶዶክስ፣በፅንፈኛ የእስልምና እና የኦሮሞ አክራሪዎች የሚመራ'' የሚለው አባባል በከፍተኛ ደረጃ  ከመሰራጨቱ የተነሳ ባብዛኛው የታጠቀው የእዚህ አካባቢ ሕዝብ ይህንን አባባል የሚያረጋግጥለት የበለጠ መረጃ ማለትም እንደ እዚህ ሳምንቱ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የመክፈል ተግባር በመንግስታዊ አካላት ጭምር እየተሰራ መሆኑ እንደተሰማ በቀጥታ ጦርነት ይከፍታል።በየቦታው አለመረጋጋት እንደ ሰደድ እሳት ይነሳል።
በሌላ በኩል በለውጡ ያልተደሰተው የህወሓት አመራር ይህንን የኦርቶዶክስ የመከፈል ሂደት የሚያቀጣጥል አዝማምያ እየታየበት ነው።በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ልማት ማኅበር ሰብሳቢ እና የህወሓት አክቲቪስት  አሉላ ሰለሞን በማኅበራዊ ድረ ገፅ ላይ በአለፈው ሳምንት በለቀቀው ፅሁፍ የኦሮምያ ቤተ ክህነት መመስረት ጥያቄ ላይ  መልካም ምኞቱን ገልጦ፣ትግራይም ተመሳሳይ መስመር በቅርቡ ትከተላለች ብሏል። እዚህ ላይ የስልጣን ጥመኞች እና ጎጠኛ ፖለቲካ አራማጆች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የፅንፍ ፖለቲካ አራማጆች ከስልጣናቸው በላይ ስለማይታያቸው አይሳካላቸውም እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብትወድም ጉዳያቸው አይደለም።
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ዋናው ቁምነገር በኦሮምያ ስም የተነሳው ቡድን የኦሮምያን ሕዝብ የማይወክል ነገር ግን ዓላማው በክልሉ ያሉትን ምዕመናን እና አብያተ ክርስቲያናት ለማገት የሚንቀሳቀስ አካል መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በራሱ በኦሮምያ ውስጥም ከፍተኛ ጦርነት መቀስቀሱ የማይቀር ነው።ምክንያቱም በኦሮምያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በኦዴፓ በራሱ ውስጥም የፅንፍ ኃይሉ የፖለቲካ ሥልጣንንም ሆነ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲቆጣጠር  የማይፈልጉ ከ90% በላይ ሲሆኑ ጥቂቶች ፅንፈኞች በመደራጀታቸው እና የመንግስት ቢሮክራሲን በመቆጣጠራቸው ብቻ ድምፃቸው ስሰማ ይታያል። ቀሲስ በላይ በ2002 በተጭበረበረ የፓርላማ ምርጫ የፓርላማ ተወካይ የሆኑበት እና በፕሮፌሰር መርጋ የሚመራው አንድም ተአማኒ ሥራ ያልሰራው የምርጫ ቦርድ አባል የሆኑበት የስራ ሂደት ሁሉ በአግባቡ እንዲመረመር ወቅቱ የግድ ይላል
የኢትዮጵያ ኦርቶድክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰራው ደባ በቀጥታ የዶ/ር ዓብይን መንግስት ወደ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀ መንግስት እንደሚያደርገው፣የጦርነቱ አቅጣጫም ከሁሉም አቅጣጫ እንደሚሆን፣ከሀምሳ ሚልዮን በላይ ተከታይ ያላት፣በርካታ የስራ አጥ የሆነ እና በመንፈሳዊ ልዕልና ስሜቱን ገትቶ ለመንግስት  ታዞ እንዲኖር ያገዘችው ቤተ ክርስቲያን በእዚህ አይነት ደረጃ ለመከፋፈል እየተሞከረ ለመሆኑ ማረጋገጫ ከካህናቱ ስሰማ በቀጥታ የየትኛውም ኃይል መሳርያ የመሆን ዕድል አለው። በእዚህ ላይ መንግስት የፅንፈኛ ኃይሎችን የመግታት ሥራ ላይ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ብሔራዊ ህልውና ማስጠበቅ ሲያቅተው የፅንፍ ኃይሎችም የለመዱትን የኃይል ተግባር በቤተ ክርስቲያን ላይ አጠናክረው ይቀጥላሉ። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ የሃይማኖት አክራሪ ኃይሎች ጋር ከሱማሌ እስከ አርሲ  እና የባሌ ቆላማ ቦታዎች ሁሉ ውጥረት ያለባት ሀገር ነች።እነኝህ ሁሉ ኃይሎች የመጀመርያ ኢላማቸው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነች። ለእዚህ ነው ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ እና መብቷን የማክበር አቅም የሌለው መንግስት በጊዜ ስልጣኑን መልቀቁ አዋጪ የሚሆነው።
በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚነሱ የመከፋፈል ተግባሮች ጦርነት የማስነሳት አቅማቸው ከገበሬው ብቻ አይደለም። ከምሁሩ እና ከጦር ሰራዊቱ ጋር ሁሉ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት  ውስጥ ብቻ ከመቶ ሺህ በላይ ከዩንቨርስቲ የተመረቁ ወጣቶቿን በሚገባ በሥርዓቷ  እና በሀገር ፍቅር ስሜት እና ሃገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ተረድተው እንዲያድጉ አድርጋለች። ይህ ሥራ በእያንዳንዱ ዩንቨርስቲ ውስጥ የተማሩ ምሑራን ላይ የተሰራ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅ የክፍለ ዘመኑ ገድል ተብሎ ሊጠራ የሚችል እና ዛሬ ማንም ሊቀለብሰው በማይችለው ደረጃ የሚገኝ ነው። ዛሬ ቤተ ክርስቲያኒቱን ህንፃዋን ማቃጠል ትችል ይሆናል እንጂ በመቶ ሺህ ምሑራን ልቦና ውስጥ እና በሚልዮን የሚቆጠሩ በቤተ ክርስቲያናቸው ፍቅር በነደዱ ምዕመናን ውስጥ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ልታነዳት አትችልም። እነኝህ ልቦች በብሮክራሲው ውስጥ እስከ ጦር ሰራዊቱ ውስጥ አሉ። የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና ስትፈታተን  የጦርነቱ አድማስ በእዚህ ደረጃ እያሰፋህ እየሄድክ መሆኑን አለመረዳት በራሱ ሌላው የአስተሳሰብ ድክመት ነው። ይህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ማለት ኢትዮጵያ ማለት ለመሆኑ ከበቂ ማስረጃ በላይ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመንካት ስትሞክር ፀቡ ከህዝብ ጋር ነው።ፀቡ ቀላል ፀብ ቢሆን ጥሩ ነበር።ግን አይሆንም።መንግስት በተደጋጋሚ ሊያስብበት የሚገባው እና ለፅንፈኛ ኃይሎች መንበርከኩን ከቀጠለ በመንግስት መዋቅር ላይ ያለው እምነት የተሟጠጠበት ሕዝብ መብት እንዴት እንደሚከበር እና ፅንፈኛ እንዴት እንደሚንበረከክ በትክክል ለማሳየት ወደ ተግባር ይገባል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ቋንቋ መቀደስ፣ማስተማር ትከለክላለች? 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው ከሰባ ሁለት በላይ ቋንቋ የወረደላቸውን ቀን የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ብላ የምታከብር እና ሕዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር፣መቀደስ እና ማምለክ እንዳለበት ታምናለች።የግድ ይህ የተለየ መለኮታዊ ቋንቋ ነው ብላ የምታስተምረው እና ሕዝብ የምታስገድድበት ተግባር የላትም።ስለሆነም የሰው ኃይል እና የገንዘብ አቅም ውሱንነት ካልሆነ በቀር በአፋን ኦሮሞ እና ሌሎች ቋንቋዎች ማስተማር ብቻ ሳይሆን ጳጳሳት እና ካህናት የተለያዩ የቋንቋ ችሎታ እያየች ነው ወደ አህጉረ ስብከት የምታሰማራው።የኦሮምኛ ቅዳሴ መፅሐፍ ጨምሮ የፀሎት መፃህፍትን ከማዘጋጀት አልፋ ከወለጋ እስከ ሐረር ባሉ አጥብያዎች በኦሮምኛ ቅዳሴ ሕዝቡን ማገልገል ከጀመረች ቆይታለች። የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በአዲስ አበባ ዙርያ ቡራዩ ፀደንያ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በኦሮምኛ ቅዳሴ ሲሰጥ በአንድ ንግሥ በዓል ላይ ተገኝቶ ምስክር ከሆነ ብቻ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ሆኖታል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በአፋን ኦሮሞ አሳትማ ለምዕመናን አሰራጭታ ከሃያ አመታት በላይ ከምትገለገልባቸው ውስጥ የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው። እነርሱም - ውዳሴ ማርያም፣ቅዳሴ እግዚእ፣ቅዳሴ ማርያም፣ቅዳሴ ሐዋርያት እና ሌሎች፣ሌሎች የሥርዓት መጻሕፍት፣በርካታ የነገረ ሃይማኖት መጻሕፍት፣በርካታ መንፈሳዊ መዝሙራት ሲኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል የሆነው የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን መደበኛ የመንፈሳዊ መርሃ ግብር በአፋን ኦሮሞ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።ከመስከረም ወር ጀምሮ ማኅበሩ ከሚጀምረው አዲስ የሃያ አራት ሰዓታት ስርጭትም የአፋን ኦሮሞ መርሃግብር አንዱ እና ዋናው ነው።ስለሆነም አሁን የተነሱት ቡድኖች ዓላማ ሌላ መሆኑን በእዚሁ አንፃር መረዳት ይቻላል።

ይህንኑ የቡድኑ ተግባር ቤተ ክርስቲያን የማፍረስ ተግባር መሆኑን የተረዱት እና የወለጋ ፍሬ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ፣ የሰሞኑን የቀሲስ በላይ እና ግብረ አበሮቹ እንቅስቃሴ በመቃወም ሲናገሩ -


" እኔ መጀመሪያ ስሾም የቀደስኩት በኦሮሚኛ ነበር። ብዙ አገልግሎቶችን በኦሮምኛ ነው የምናከናውነው። የነዚህ ሰዎች አላማ ምንድነው ?!! ቅዱስ ሲኖዶስን ማክበር ያስፈልጋል። ከዛ ያፈነገጠ አካሄድ ከባድ መለኮታዊ ቅጣት አለው። እኔ በአንዲት ቤተክርስቲያን ፥ በአንድ ቤተክህነት አምናለው። ከዚህ ውጭ የሚደረግን እንቅስቃሴ ነፍሴን አስይዤ እፋለመዋለው !!! የአባቶቼ አደራ አለብኝና።" ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል 
መፍትሄው  
መፍትሄው የችግሩ ግልባጭ ነው።አሁን በምንኖርበት ዓለም ማንም የማንንም መብት ጨፍልቆ እንዲኖር ሊፈቀድለት አይገባም።ልዩነትን ማክበር እና ሀገር የጋራ ሃይማኖት የግል የሚለው አባባል ሁሉንም የሚያስታርቅ ነው። ሃይማኖት ምድራዊ ስርዓትን ብቻ የያዘ አይደለም።ሰማያዊ ሕግ እና ስርዓት መሠረትነት ነው የምድር ሕጎቹን የሚመሰርተው። ስለሆነም በሃይማኖት ውስጥ ፍርሃት ፈፅሞ አይታወቅም።በሃይማኖት የመጣ ማናቸውም ምድራዊ ኃይል በእምነቱ ውስጥ ላለው ሁሉ ኢምንት ነው።የአድዋ ጦርነት በወቅቱ ለነበሩ አባቶቻችን የፀረ ቅኝ ግዛት ብቻ አይደለም።ከሞት በኃላ የመኮነን እና የመፅደቅ ጉዳይም ነበረበት። የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦተ ሕግ ይዘው ሲዘምቱ እና ካህናቱን ፍቱን ብለው ወደ ጦርነቱ አውድማ ዘለው ሲገቡ ተዋህዶ እምነታቸውን በካቶሊክ የሚያስቀይር ወታደር እንደመጣ ሁሉ ስላወቁ ነው። በአፄ ሱሱንዮስ ዘመን በአንድ ቀን እስከ ስምንት ሺህ ገበሬ መስዋዕትነት አያምልጥህ! እየተባባለ እየተጠራራ የተሰዋው የእምነት ጉዳይ ስለሆነ ነው።ሃይማኖት የህዝብ ስስ ብልት ነው።ከሰውነት ውስጥ ስስ የሆነው ብልታችን በትንሽ መርፌ ቢነካ ግዙፉን ሰውነት እንደሚያንዘፈዝፈው ሁሉ፣ሃይማኖትም እንዲሁ መላ ሀገር ያንቀጠቅታል። ስለሆነም በመፍትሄነት መንግስት ከሌሎች ስራዎቹ ቀድሞ የሚከተሉትን ቢያደርግ ኢትዮጵያን ከጦርነት መታደግ ይቻላል።
ይሄውም -  
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ሰውነት ማክበር እና ማናቸውም ተግባር የቤተ ክርስቲያኒቱ ደንብ፣ሕግ እና ስርዓት ከሚያዘው ውጭ በውጫዊ አካል ምንም ነገር እንዳይፈፀም መንግስት ዋስትና መስጠት፣ሕጋዊ እና የፀጥታ ሥራ መስራት ይህንንም በተግባር ለሕዝቡ ማሳየት፣
  • ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተሳሳተ የፅንፍ አመለካከት ያላቸው ባለስልጣናት ሚዛናዊ አስተያየት እንዲኖራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ አስተዋፅኦ እንዲረዱ የማድረግ ሥራ በመንግስትም ሆነ በሁሉም አካላት መስራት፣
  • ኢትዮጵያን ለማሳደግ አሁንም ካሉት እድሎች ውስጥ አንዱ እና ዋናው የቤተ ክርስቲያንን ሚና ማጎልበት መሆኑን በልማት አካላት ሁሉ ተገቢው ግንዛቤ መስጠት እና ለቤተ ክርስቲያኒቱም ዕድል መስጠት፣
  • ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መሻሻል ሲኖዶሳዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዲፈፀም፣ይህ እንዲሆን መንግስት በበጎ ጎኑ ግፊት ማድረግ አለበት።ከእዚህ በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ መሻሻል ሲከናወኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ ጥቅም ሲያገኙ የነበሩ የትንኮሳ ሥራ እንዳይሰሩ መንግስት በቂ ጥበቃ እና የሕግ ከለላ መስጠት፣
  • የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ከተሻሻለ በኃላ ቤተ ክርስቲያንን አንዷ እና ዋናዋ የልማት አጋር አድርጎ በሀገሪቱ ሕግ፣ፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንድትሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት። ይህ ጉዳይ በሃይማኖት የለሹ የደርግ ዘመን ሳይቀር የቤተ ክርስቲያኒቱን ሚና ተረድቶ በወቅቱ በነበረው ሸንጎ (ፓርላማ) ቅዱስ ፓትርያሪኩ እንዲገኙ ያደርግ ነበር።ይህ ጉዳይ አሁንም በብዙ ሀገሮች የሚደረግ ነው። ዋናው የልማት አጋር ትቶ ኢትዮጵያን አለማለሁ ማለት ከንቱ ልፋት ነው። ለምሳሌ በመንገድ ላይ የሚለምኑ ዜጎችን ጉዳይ እፈታለሁ ብሎ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሲነሳ ለዘመናት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ድሆችን አስጠልላ መግባ የምታሳድረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ያማከረ የለም።ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን የማኅበራዊ ዋስትና  በሺህ ለሚቆጠሩ ነዳያን በመስጠቷ ምክንያት ከተሞች ከከፍተኛ የፀጥታ ችግር መዳናቸውን መንግስት ራሱ ረስቶታል። ቤተ ክርስቲያን ግን ኃላፊነቷን እየተወጣች ነው።አስተዳደራዊ መዋቅሯ ቢስተካከል ደግሞ ለበርካታ የመንግስት ችግሮች መፍትሄው አላት።
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች እና የሉላዊነት አቀንቃኝ ሀገሮች ጭምር እንደ ስጋት ስለምትታይ በከፍተኛ በጀት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ዓለም አቀፋዊ ሴራ መኖሩን መንግስት መረዳት አለበት።ይህ ጉዳይ በተለይ አሁን ካለንበት የሱማሌ እና በኤርትራ ቆላማ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ የአክራሪ እስልምና ኃይሎች አንፃር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሱ የማናጋት ስራዎች ስረ መሰረታቸው የት ድረስ እንደሆነ መንግስት ሊያጠናው ይገባል።የቀሲስ በላይ እና አጃቢ ፅንፈኞች ግብ ምንድነው? እውን ለኦሮሞ ሕዝብ የታሰበ ነው? ወይንስ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ማናጋት፣በመቀጠል በኢትዮጵያ ውስጥ ግርግር መፍጠር እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለአክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ አጋልጦ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ላይ አዲስ የመከራ ቀንበር ለመጫን? ከአስር ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ በደህንነት መስርያቤቱ የሚታወቅ አንድ ወንጀል አለ። ይሄውም ፅንፈኛ የሙስሊም እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ የአብነት መምህራንን የመግደል ፕሮጀክት ነበር።በእዚህ ፕሮጀክት መሰረት ጎንደር ውስጥ የሚገደሉ የአብነት መምህራን ስም እና አገዳደሉን የያዘ መረጃ በደህንነት ቢሮ ተይዞ ግለሰቦቹም ከውጭ ሀገር ፅንፈኞች ጋር ሁሉ ግንኙነት እንዳላቸው የተደረሰበት መረጃ (ለሕዝብ አልተገለጠም እንጂ) እንደነበር ይታወቃል።ስለሆነም መንግስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሀገር ጉዳይ መሆኑን ማወቅ አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይም ''ኦርቶዶክስ ሀገር ነች።አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን የኦርቶዶክስ ጉዳይ የእነርሱ ብቻ ይመስላቸዋል። የሀገር ጉዳይ ስለሆነ ሁላችንም ይመለከተናል'' ማለታቸው ይታወሳል። ይህንን ሲሉ ጉዳዩ በደንብ ገብቷቸዋል ብዬ አስቤ ነበር።አሁን ግን በሰሞኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ አንፃር መውሰድ የሚገባቸውን ርምጃ እና ኃላፊነት በደንብ ያጤኑት አይመስልም።ስለሆነም አሁንም ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ የለውጥ ዕድል እንዳይታጠፍ  መንግስት ከፅንፈኛ ኃይሎች በቶሎ ራሱን መለየት አለበት።
በመጨረሻም ለማጠቃለል፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከአክሱም ስልጣኔ እስከ ኮምፕዩተር ዘመን ስትኖር፣በምድራዊ ጥበብ አይደለም።ልዩ መንፈሳዊ ኃይል ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አለ። ከህገ ልቦና እስከ ህገ ኦሪት፣ከሕገ ኦሪት እስከ ህገ ወንጌል ኢትዮጵያ በእምነት ውስጥ የኖረች ሀገር ነች። አርዮስ ሲነሳ ነበረች፣ንስጥሮስ ሲነሳ ነበረች፣ሉተር ስነሳ ነበረች፣ሉላዊነት ሲነግስ አለች።ወደፊትም እርሷን እና የዕምነት ፍልስፍናዋን የሚረታ ምድራዊ ኃይል የለም።ምንም ማድረግ አይቻልም።አለማመን መብትህ ነው። በፈለከው እምነት ውስጥ መኖር እግዚአብሔርም የሰጠው መብት ነው።ሰው እጁን ከፈለፈው ውስጥ የመክተት መብት አለው።ቢፈልግ ውሃ ውስጥ ካሻው እሳት ውስጥ ካልፈለገ አጣምሮ መቀመጥ። ይህ ሁሉ መብት ነው።እግዚአብሔር በእዚህ ሁሉ እርሱ መልካም ነው ወዳለው እስክትመጣ እድሜ እየሰጠ ይታገስሃል።እራስህን ችለህ መቀመጥ አቅቶህ እርሱ ከሕገ ልቦና እስከ ህገ ወንጌል ያሻገራትን የኢትዮጵያውያንን ሃይማኖት ስትነካ ግን ግለሰብ ሆንክ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ሃብታም ሆንክ ድሃ፣ ሃያል ሆንክ ደካማ መንግስት አይታገስህም።ይህንን የምለው በተረት ተረት ወሬ አይደለም።ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፋሺሽት ጣልያን እስከ ግራኝ መሐመድ፣ከጋዳፊ እስከ መካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ የፅንፍ መንግሥታት ተገዳድረዋታል፣ቤተ ክርስቲያን ዛሬም አለች።እነርሱ ግን አይሆኑ ሆነው የሉም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ''ሰይጣን ቀስቱን ወረወረ ፣ ዝናሩን ጨረሰ ቤተ ክርስቲያንን ግን አላጠፋትም''  እንዳለ፣ቤተ ክርስቲያን ፈፅሞ ልትጠፋ አትችልም።ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሰይጣን ማደርያ መሆን ደግሞ ሌላው የጥፋት ጥፋት ነው።
ሰላም ለኢትዮጵያ ያድልልን።  
ጉዳያችን/Gudayachn 


No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...