ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, September 16, 2019

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካዊ ዕሳቤ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት እና ሚናውን በማስፋት የኢትዮጵያ ህልውናን በትክክል ማረጋገጥ ይቻላል። (ጉዳያችን ሃሳብ)

በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚመከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ - 

  • የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በፖለቲካ አደረጃጀት ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ ይገባል፣
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካዊ  ዕሳቤ ምንድነው?
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተችውና አሁን ያለችበት ፈተና፣
  • ''ኢትዮጵያን ለመምታት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ምታ!'

================================
ጉዳያችን / Gudayachn
መስከረም 5/2012 ዓም (መስከረም 16/2019 ዓም)
=================================

ወቅታዊው ሃገራዊ ሁኔታ

የኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ዓይነተኛ አያያዥ ኃይል ካላገኘ ከኢሕአዴግ መሰነጣጠቅ ተከትሎ የሀገሪቱ ፖለቲካ ማባርያ ወደ ሌለው የእርስ በርስ እልቂት እንዳይመራ ያሰጋል።ክልሎች በራሳቸው የታጠቀ ኃይል በማደራጀት ላይ ተጠምደዋል።ሌላው ቀርቶ ክልሎች ያላቸውን የሚሊሻ ብዛት ራሱ ማዕከላዊ መንግስት የሚያውቀው አይመስልም።ይህ ደግሞ አደገኛ መንገድ ነው።ዛሬ መስከረም 5/2012 ዓም የኬንያው ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ በኢትዮጵያ እና ኬንያ በኩል ያለው መንገድ መዘጋቱን መዘገቡን ጠቅሶ ዋዜማ ራድዮ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ገልጧል።በሌላ በኩል ሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ  በምሽት የዜና እወጃው ላይ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር  አምባሳደር መለስ ዓለምን ደውሎ ባናገራቸው መሰረት ጉዳዩ ውሸት ነው በሚል በደፈናው ለአዲስ ዓመት ለማክበር ሞምባሳ ነበርኩ የእኛ እና የኬንያ ግንኙነት ጥሩ ነው።በሚሉ ንግግሮች አልፈውታል። እንደ ዘስታንዳርድ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ኬንያ ድንበሩን ለመዝጋቷ ምክንያቷ ሕገ ወጥ ንግድ በመበራከቱ መሆኑን እና በየቀኑ ከ30 እስከ 50 የሚደርሱ ካሚዮኖች ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሕገ ወጥ ሸቀጦችን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያግዙ እና ብዙዎቹ መጋቢ መንገዶችን ስለሚጠቀሙ ታከስ ሳይከፍሉ የሚገቡ መሆናቸውን በመጥቀስ ነው።እነኝህ መሣርያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባው ማን ነው? ለምን ተግባር? መንግስት በአግባቡ ድንበር እየጠበቀ ነው? መንግስት መዋቅር ውስጥ  በተለይ በኦዴፓ ውስጥ የገቡ የመንግስት ኃላፊዎች ድንበር ጠባቂዎች፣የግምሩክ ባለስልጣናት ከፅንፍ ኃይሎች ጋር ተባብረው  የጦር መሳርያ እንዲገባ እያደረጉ ላለመሆናቸው ዋስትናው ምንድነው? 

ይህ በጣም ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ለማሳየት የቀረበ ማሳያ ነው እንጂ በመንግስታዊው መዋቅር ውስጥ የሚታየው ወጥ ያልሆነ እና የልዩ ልዩ ኃይሎች መጠቀምያ የሆነው ቢሮክራሲ ኢትዮጵያ ወደ አደገኛ ሁኔታ እየሄደች ለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ጠቅላይ ምንስትር ዓቢይ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ መስከረም 3/2012 ዓም ለሸገር ''ጨዋታ'' በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ሲናገሩ ''የመንጋ ሂደት በአዲሱ ዓመት የሚቀጥል አይሆንም'' ሲሉ ተደምጠዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእዚህ ቃለ መጠየቃቸው ላይ  ባብዛኛው የሚነበብባቸው የየዋህ ፖለቲከኛ እሳቤዎች እንጂ መረር ያለ የኢትዮጵያን አድነት በሚያቅፍ መልኩ የማዕከላዊው መንግስትን ሚና የሚያጎላ ሆኖ አልታየም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያነሱት የመደመር ዕሳቤ  በትክክልም የሚያማልል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ መልካም መንገድ የሚያስዝ ሊሆን ይችላል።ይህ ግን ከጠንካራ የማዕከላዊ መንግስት የማስፈፀም አቅም ጋር ካልሄደ ተግባራዊነቱን አሳሳቢ ያደርገዋል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተችውና አሁን ያለችበት ፈተና 


ኢትዮጵያ በዘመናት ጉዞዋ እንደ ጅማት እና ክር ሆኖ ታሪክ ማንነቷን ካቆዩት ውስጥ ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነች።ከክርስቶስ ልደት በፊት በሕገ እግዚአብሔር እና በኦሪት ስርዓት የፀኑ ነገስታቶቿ በአራተኛው ክ/ዘመን በብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ በቤተ መንግስት የታወጀው ክርስትና እስከ 20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ የራሷን አሻራ ከማቆየቷ በላይ ኢትዮጵያ በነፃነት እንድትዘልቅ መንፈሳዊ እና ሞራላዊ ልዕልና በማጎናፀፍ የመሪነት ሚና ተጫውታለች።ከእዚህ በተጨማሪ ቤተክርስቲያኒቱ ከፊደል ገበታ እስከ ከፍተኛ የፍልስፍና እሳቤዎች እንዲሁም መሪ ነገሥታቱን ከልጅነታቸው በሞራል፣በመንፈሳዊ ሕይወትና በፍትሃዊ አሰራሮች ሁሉ አሰልጥና ለመሪነት በማብቃት የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ብቸኛ እና መተኪያ የሌለው ሆኖ ከሁለት ሺህ ዘመናት በላይ  የዘለቀ አንፀባራቂ ታሪክ ነው።ይህ በእንዲህ እያለ ግን ላለፈው ግማሽ ክፍለዘመን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የደረሰው ፈተና በርካታ ጥፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከማድረሱም በላይ በውጤቱ ኢትዮጵያ አንድ በሞራል እና በመንፈሳዊ ሕይወት የበለፀገ ትውልድ በማጣቷ ምክንያት  በጎሳ የሚያምን፣ሙሰኛ እና በገዛ ወገኑ ላይ ገጀራ የሚያነሳ ትውልድ በኢትዮጵያ ምድር  እንዲበቅል ምክንያት ሆኗል።


ከእዚህ በባሰ ሁኔታ ደግሞ በቅርብ በኢሕአዴግ ውስጥ በመጣው የጥገናዊ ለውጥ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንቷ በባሰ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቃለች።ይሄውም ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር የገቡት  የጎሳ እና አክራሪ የፅንፍ ኃይሎች ጋር ኢሕአዴግ በገጠመው ግንባር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ  ቀጥተኛ ዘመቻ ከፍቷል።ለእዚህም ማሳያው የኦሮምያ ቤተ ክህነት ለመመስረት የተደረገው ሙከራ ላይ የመንግስት ስውር ድጋፍ፣ ብፁዓን ጳጳሳት መንግስትን ባናገሩበት ሂደት ያገኙት አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ እና ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መንግስት  ለሚደርሰው ጥፋት ለማስቆም እርምጃ ይውሰድ የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በጎንደር፣ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ደብረ ታቦር እና ሌሎች ከተሞች ያደረጉት ሰልፍ በኢትዮጵያ የመንግስት ዜና ማሰራጫዎች አለመዘገቡ ትልቅ ቁጣ በመላው ሀገሪቱ ፈጥሯል።ከእዚህ በተጨማሪ ሰሚ ያጣው የቤተ ክርስቲያኒቱን ህንፃዎች የማቃጠል እና ምመናኗን የማሰደድ ተግባር ሁሉ የሚመሩት የቤተ ክርስቲያኒቱን  እሳቤዎች የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ መሆኑን ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካዊ  ዕሳቤ ምንድነው?


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ዘመናት አሻግሯል።

  • አቃፊው ፖለቲካ የእስልምና መስራች መሐመድ ቤተሰቦችን ተቀብሎ ያስተናገደ ፖለቲካ ነው።
  • አቃፊው ፖለቲካ የይሁዲ  እምነት ተከታዮችን ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ አስጠልሎ ወደ ሀገራቸው የሸኘ አቃፊ ፖለቲካ ነው። 
  • አቃፊው ፖለቲካ ከምፅዋ እስከ ሞያሌ፣ከፈርፈር እስከ አኮቦ ከእስልምና አማኞች ጋር ጎን ለጎን በአንድነት እና በመከባበር የዘለቀ፣ኢትዮጵያን እንደ ደም ስር እና ጅማት ያስተሳሰረ አቃፊ ፖለቲካ ነው። 
  • አቃፊ ፖለቲካው ኢትዮጵያ በፋሺሽት ጣልያን ስትወረር ከደቡብ እስከ ሰሜን ሕዝብ አስተባብሯል።
  • አቃፊ ፖለቲካው በየትኛውም ዓለም ያልታየ መከባበርን፣እምነት ያልለያቸው ኢትዮጵያውያን በአንድ እድር፣እቁብ፣ሰርግ እና ሃዘን ሁሉ እንዴት እንደሚኖሩ አስተምሮ በፍቅር አስተሳስሯል።
ይህ አቃፊ ፖለቲካዊ እሳቤን ለመናድ መሞከር ኢትዮጵያን ለመናድ የመሞከር የእብደት ሥራ አሁን በኢትዮጵያ እየተሰራ ነው። የእብደት ስራውን እየሰሩ ያሉት የፅንፍ የጎሳ ድርጅቶች እና ኦዴፓ ውስጥ የተሰገሰጉ አደገኛ  ግለሰቦች እና የውጭ ተባባሪዎቻቸው ቅንጅት ሁሉ ነው።

''ኢትዮጵያን ለመምታት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ምታ!''

ኢትዮጵያ በዘመኗ ሁሉ የመጡባት ጠላቶቿ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ኃይል አለበት ብለው የደመደሙት እና ቀድመው የሚያጠቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ነው።በዘጠነኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ የተነሳችው እና የአክሱም ስርወ መንግስት የናደችው ዮዲት ጉዲት ተብላ በታሪክ የምትጠራው ሴት እና ሰራዊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቀናጀ ዘመቻ በማድረግ፣በማቃጠል እና እና ምዕመናንን በመፍጀት  ኢትዮጵያን ለማዳከም ሞክራለች፣ከክልበኃላ 1500 ዓም በኃላ የተነሳው እና በቱርክ የታገዘው ግራኝ መሐመድ የመጀመርያ ኢላማው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ቱርካዊ አማካርዎቹም ሆኑ ግራኝ መሐመድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በመበተን ኢትዮጵያን ገልብጦ እንደፈለገ ሊሰራት ሞክሮ አልተሳካለትም።ግራኝ መሐመድ ይህንን ያድርግ እንጂ ሁሉን አቃፊዋ ቤተ ክርስቲያን ግን የግራኝ መሐመድን ካባ ሳይቀር በቅርስነት ይዛ መርጦለ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሙዚየሟ  በመስታወት አስቀምጣ ለጎብኚዎች አሁን ድረስ ታሳያለች።


በ1928 ዓም ኢትዮጵያን የወረረው ፋሺሽት ጣልያን  ዋና ኢላማው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች።ፋሺሽት ጣልያን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጳጳሳት አቡነ ጴጥሮስን ጭምር በአደባባይ በጥይት ከመደብደብ እስከ በአንድ ቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳትን ገደል በመጨመር ሁሉ  ጥፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አድርሳለች።ዛሬም  የባዕዳን ተልኮ አስፈፃሚዎች የፅንፍ ጎሰኘንት አራማጆች እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አስፈፃሚዎች በመንግሥትነት ተከስተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ግልጥ ዘመቻ ላይ ናቸው።ይህ የጥፋት እና የጥላቻ ስሜታቸውን መታገስ አቅቷቸው ምእመናኑ በአደባባይ ያሰሙትን ድምፅ ግብር ከፍሎ ለሚያስተዳድራቸው ሕዝብ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይዘግቡ በማገድ እኩይ ተግባር ተገልጧል።ይህ ብቻ አይደለም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከጅጅጋ እስከ ሲዳማ፣ከከፋ እስከ ጅማ በቃጠሎ ስትጠቃ እና ምዕመናኗ ሲሰደዱ የሚከላከል መንግስታዊ አካል አለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመልካም እሳቤዎቿ ላይ ተመስርታ ልጆቿን በፖለቲካ አደረጃጀት መደራጀት የወቅቱ ቀዳሚ እና ዋነኛ ጥያቄ አድርጎታል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በፖለቲካ አደረጃጀት ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ ይገባል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን የቻለች የኢትዮጵያ የደም ስር እና የጀርባ አጥንት አያያዥ ነች።በኢትዮጵያ የተነሱ ቅራኔዎች ሁሉ ለመፍታት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚና የግድ አስፈላጊ ነው።ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ 1966 ዓም ድረስ መንግስታዊ ጥበቃ ስለነበራት የሀገር አንድነትም ሆነ ሰላም ተጠብቆ ለመቆየት ችሏል።በአሁኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርስ፣ማንነት፣የጋራ እና አቃፊ ዕሴት ሁሉ ጠባቂ አጥቶ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው። አሁን ይህንን የሚጠብቅ ንጉሰ ነገስት መንግስት የለም።ይህንን ክፍተት በዘመናዊው የፖለቲካ መንገድ ማለትም የተደራጀ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም አደረጃጀት ኢትዮጵያ ከሌላት ለሀገሪቱ እንደ ሀገር ለመቀጠል እጅግ አደኛ ነው። 

ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ በፖለቲካ አደረጃጀት ትደራጅ ማለት አይደለም።የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ  ሂደት ሁሉ የነበረ ወደፊትም የሚኖር እና ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊ ሕይወትን መሰረት ያደረገ ነው። ሆኖም ግን ''የቄሳርን ለቄሳር'' ካለ መፅሐፉ የእግዚአብሔርን ጉዳይ ስናወራ የቄሳርን ሥራ ግን ረስተነዋል።በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀድሞ በነገሥታቱ ሕጋዊ ከለላ የነበራት ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊው የፖለቲካ አደረጃጀት የተደራጁ ልጆች  ባለመነሳታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ ክፍተት ተፈጥሮባታል።ክፍተቱ ደግሞ በቀጥታ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ አንድነት መፍረስ ላይ በትክክል እየተንፀባረቀ ነው።ለእዚህ ነው የኦርቶዶክሳውያን ፖአለቲካዊ አደረጃጀት ክፍተቱን የመሙላቱ ፋይዳ አንገብጋቢ የሚያደረገው።

ይህንን ክፍተት ይህ ትውልድ መሙላት ካልቻለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ለአደጋ የሚያጋልጣት ትውልድ እንዳይሆን ያሰጋል።ይህ ጉዳይ የሃይማኖት ልዩነት የሚፈጥር የሚመስላቸው አሉ።አንዳንዶች  ሌሎችም በሃይማኖት እንዲደራጁ በር የሚከፍት ነው የሚሉም አሉ።ሆኖም ግን አሁን የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት የእስልምናም ሆነ የሌሎች እምነቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በተስፋ እንደሚጠብቁ መረዳት ያስፈልጋል።አሁን ያለው የኢትዮጵያን የነበረ ዕሴት መናድ ላይ ማንኛውም  ኢትዮጵያዊ የዕምነት ድርጅት አይስማማም።ምክንያቱም ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ ነው።የመጥፋት እድሉ ሁሉም ላይ የመጣ ነው። ስለሆነም የጋራ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ጎልብቶ በፖለቲካ ኃይልነት መውጣት እና  የኢትዮጵያን እሴቶች ከበታኝ ኃይሎች መታደግ ወቅታዊ እና አንገብጋቢው ጉዳይ መሆኑን የማይረዳ የማንኛውም የእምነት ድርጅት  የለም። በእርግጥ ኢትዮጵያን ለመበተን የሚያልሙ ኃይሎች ይህ ጉዳይ አይዋጥላቸውም። ኢትዮጵያን ለመበተን እንደሚያስቡት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መበተን ፈፅሞ በቅርብ የማይሳካላቸው ግን ጊዜ የሚወስድ ድምፅ አጥፍቶ ውስጥ ውስጡን በመሄድ ብቻ ሊሳካ እንደሚችል ያስባሉ።

ለማጠቃለል የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ የሚገባበት ወሳኝ እና ታሪካዊ ጊዜ ላይ ነን።መልፈስፈስ እና መዘግየት በራሱ አደጋ አለው። አንዳንድ የዋሃን ዛሬም ፖለቲካ ከእምነት ጋር ይጣረሳል፣ እያሉ ስሌት ውስጥ የሚገቡ ይኖራሉ።እነኝህኞቹ ንጉስ ዳዊት ንግስናው፣ንጉስ ሰለሞን ሀገር ማስተዳደሩ፣ንጉስ  ቆስጠንጢኖስ በእናቱ ንግስት ዕሌኒ አማካይነት የክርስቶስን መስቀል ማግኘቷ ሁሉ ፖለቲካ ብለው ይተዉት እያሉ ነው። ነገሥታቱ አብርሃ ወአፅብሃ  ለሀገር መትረፋቸው፣ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ መስመር መምራታቸው ሁሉ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ይዘው መሆናቸውን የመዘንጋት ያህል ነው። አሁንም ወቅቱ ኢትዮጵያ እራሷን በአግባቡ የምታይበት ወሳኝ ጊዜ ነው። በድጋሚም  የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ ይገባል።ጉዳዩ ከተራ ሰላማዊ ሰልፍ እና ድርድር በላይ ከፍ ያለ አደገኛ ሁኔታ ነው የሚታየው።

አለን ሁሉን በእግዚአብሔር አልፈን (ቪድዮ)


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...