ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, July 7, 2018

በክቡር ጠ/ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ እና ኢትዮጵያዊነት አንፃር የቆመው እሳቤ።

ጉዳያችን/Gudayachn
ሐምሌ 1/2010 ዓም (ጁላይ 8/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ 
- በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያሉት ሁለቱ ሃሳቦች እና ኃይሎች፣
የኢትዮያ መጪ የፖለቲካ መንገድ ዋስትናው እና መፍትሄው በሚል ርዕስ ፅሁፎች እና 
የአዲስ ሙላት አዲስ ነጠላ ዜማ(ቪድዮ) ያገኛሉ።

ኢትዮጵያ የክፍለ ዘመኑ አንዱ እና አይነተኛ የለውጥ ሂደት ላይ ነች።ለውጡ አንድ እየሞተ ያለ ሐሳብ እየሸኘ አዲስ ሀሳብ እያስተዋወቀ የሚሄድ የለውጥ ሂደት ነው።እየሞተ ያለው ሐሳብ ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን  ኢትዮጵያን ሲያምስ የኖረው '' ከእኔ ሃሳብ ጋር የማይስማማ ሁሉ ጠላቴ ነው እና ደምስሰው'' የሚለውን ሃሳብ ሲሆን እያስተዋወቀ ያለው ሃሳብ ደግሞ ''የእኔን ሃሳብ የማይቀበል ሁሉ ጠላት አይደለም።ችግሩን በውይይት መፍታት ይቻላል'' የሚለው ሃሳብ ነው። አዲሱ ሃሳብ በእራሱ በቂ ቦታ ለማግኘት በቀደመው ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ፅንሰ ሃሳቦች አራማጆች አሁንም መኖራቸው እና ወራሾችም ከአዲሱ ትውልድ ውስጥ መኖራቸው የለውጥ ሂደቱ በጥንቃቄ እንዲራመድ እና ጥንቁቅ አራማጅም የሚፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ነው። አንዲት ሀገር በእዚህ አይነት የለውጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ስትሆን የተለያዩ ሃሳቦች ሰፊውን ምህዳር ለመያዝ የተለያዩ ስልቶች ከመቀየስ እስከ አላስፈላጊ መንገድ ውስጥ የመግባት አደጋዎች እንዳይኖሩ የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን የመወጣቱ ፋይዳ እጅግ ወሳኝ ነው።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያሉት ሁለቱ ሃሳቦች እና ኃይሎች

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያሉት ሃሳቦችን በሁለት ኃይሎች ከፍሎ በማየት መጠቅለል ይቻላል። የመጀመርያው ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን የሚያቀነቅነው እና በኢትዮጵያዊነት የወል ስም ሃሳብ ስር ያለው እና  ብሔርተኝነትን ዋስትናዬ የሚለው ሃሳብ እና ኃይል ነው። 

ሕብረ ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያዊነት

የመጀመርያው ሕብረ ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነው ኃይል ካለምንም ማጋነን በስፋቱ፣በርካታውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማቀፉ እና እሳቤው በራሱ ያለው የኃላ እና የወደፊት መሰረት ጥልቀት አለው። ይህ ማለት ወደ ኃላ ስንመለከት ኢትዮጵያ በኖረችበት የመንግስትነት ስሪት ታሪክ ውስጥ የፖለቲካው መሪ ተዋናይ እሳቤ ኢትዮጵያዊ እሳቤ መሆኑ ነው።የወደፊቱንም ስንመለከት እንደሀገር በጋራ ለመኖር ሌላ አማራጭ እሳቤ ለጊዜው ከኢትዮጵያዊ እሳቤ የተሻለ እንዳልተሰማ ብዙ ማስረጃ ማምጣት አይሻም።የህብረ ብሔራዊ እና ኢትዮጵያዊ እሳቤ ያለፈ እና የመጪው እሳቤ አካል ብቻ አይደለም የዘመናዊነት እሳቤ አካልም ነው።በዘመናዊው ዓለም በፈጣን ቴክኖሎጂ ምርት አሳድጎ ሰፊ ገበያ የመፍጠር እሳቤ የሚጋራው አሁንም ሰፊ የሕዝብ አንድነት እና ስምምነት ፈጥሮ የገበያ አድማስን ማስፋት ከሚለው ዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣም ነው።

ይህ የህብረ ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያዊነት እሳቤ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያህል እንዲጎሳቆል ያልተደረገበት ሙከራ አልነበረም።

እሳቤውን በራሱ ያለፈ እና ያረጀ ስርዓት እሳቤ ነው ብሎ ከማጥላላት እስከ የሃሳቡ ተጋሪዎችን ማሰር እና መግደል ድረስ ያልተፈፀመ የግፍ አይነት በህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት  አቀንቃኞች ሁሉ ሲፈፀምበት ኖሯል።ይህም ሆኖ ግን ሃሳቡ ገዢ ሃሳብ ሆኖ መኖሩን የሚገታው ኃይል አልተገኘም።ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ ነው። ምክንያቱም በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሃብቱ መስክ ሁሉ ለሚገጥሙ ችግሮች መፍትሄው ምንድነው? ለሚለው ፈታኝ ጥያቄ መልሱ ሁሉ የሚያመራው ወደ አንድ ነጥብ ብቻ መሆኑ ነው። ይሄውም ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያ የሚለው መልስ ነው። ይህ በእንዲህ እያለ ነው እንግዲህ በኢህአዴግ የውስጥ ቅራኔ አይሎ የዶ/ር አብይ ቡድን ነጥሮ እንዲወጣ ዕድል የሰጠው።ይህ ቡድን ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያን ችግር በሚገባ ለማየት የቻለ አካል ነበር እና የሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት እሳቤን በአማራጭ የፖለቲካ መሪ ሃሳብ ይዞ መውጣቱ ሳይንሳዊ እና ተሞክራዊ እንጂ ድንገት ደራሽ ሃሳብ አይደለም። ዶ/ር አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር በተረከቡበት ቀን መጋቢት 24/2010 ዓም ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር በሕዝብ ውስጥ የነበረውን የህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት እሳቤ መግነጢሳዊ በሆነ መልክ በሕዝብ ውስጥ የነበረውን ስሜት አንፀባረቁት።በደቂቃዎች ውስጥም ሚልዮኖች ከጎናቸው አሰለፉ።ይህ ማለት ለሕዝብ የነገሩት አዲስ እሳቤ ስለሆነ አይደለም።ይህ ቢሆን ኖሮ ሀሳባቸው ሕዝብ ዘንድ ደርሶ ድጋፍ ለማግኘት አመታትን በጠበቀ ነበር።ሆኖም ግን ሕዝብ ውስጥ ሲንተከተክ የነበረው የህብረብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የመተንፈሻ ቀዳዳ ሲያገኝ ፈንቅሎ ወጣ እንጂ ስሜቱ ቢቆይ ኖሮ በአብዮት ወይንም በሌላ መልኩ ገንፍሎ መውጣቱ የማይቀር እንደነበር መረዳት ይገባል።

 ብሔርተኝነትን ዋስትናዬ የሚለው ሃሳብ እና ኃይል 
ሁለተኛው እሳቤ እና ኃይል ብሔርተኝነት ዋስትናዬ የሚለው እሳቤ ነው።የእዚህ እሳቤ ዋነኛ መነሻ እና ምክንያት ስጋት እና ስጋት ነው።ስጋቱ የሚነሳው ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በህወሓት እና አጋሩ ኢህአዴግ እንዲሁም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ግን ብሄርተኝነትን የሙጭኝ ያሉ ኃይሎች ተከታታይ የፕሮፓጋንዳ ሥራ በአንድ ትውልድ ላይ የፈጠረው ያለመተማመን እና  የስጋት ውጤት ነው። የእዚህ እሳቤ አቀንቃኞች ሁል ጊዜ የሚሰጉት ኢትዮጵያዊነት እና ሕብረ ብሔራዊነት የእነሱን የብሔር እይታ የሚጋርድ ብቻ ሳይሆን ሊያጠፋን ይችላል በሚል ስጋት የተሞላ ነው።ይህንን ስጋት ደግሞ ከሃምሳ እና መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ የታሪክ ትርክቶችን የተለያየ ቀለም በመቀባት በአይነት በአይነት እየመተረ የልዩነቱን ጎራ ብቻ እያጎላ ስለኖረ ከስጋት ሊወጣ ፈፅሞ አልቻለም። ሆኖም ግን አስከፊው ጉዳይ ከስጋት ለመውጣት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ስጋቱ የሚርቀው የራሱ የብሔር ኃይል የስልጣን እርከኑን ሲቆጣጠር ብቻ መሆኑን ያስባል።እዚህ ላይ ግን የስልጣን እርከን ተቆጣጠረ የሚባለው የቱን የፖለቲካ ኃይል ሲይዝ መሆኑን እራሱም ጥርት አድርጎ ማስቀመጥ አይችልም።ምክንያቱም የእዚህ አይነቱ የስልጣን አላማ እሳቤ በራሱ መለክያ የለውም።ሁሉንም የስልጣን እርከን ቢቆጣጠርም ተቆጣጠርኩ ብሎ እንደማይረካ ግልጥ ነው።ይህ የስጋት ፖለቲካ ዋና ጠባይ ይህ ነው።ስልጣን ላይ ሆኖም እንዳልሆነ ቆጥሮ ሌላ ግንባር ይከፍታል።በብሄርተኝነት እሳቤ ውስጥ ያሉት የህወሓት፣የኦሮሞ እና የአማራ ብሔርተኝነቶች ተጠቃሽ ናቸው።እዚህ ላይ ግን የህወሓት የብሄርተኝነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ እና የስልጣን ጥማት ያላቸው እና በልዩ ልዩ ወንጀል ውስጥ የገቡ ብሔርተኝነትን እና የትግራይን ሕዝብ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ለመጠቀም የሚያስበው አካል ፍፁም ብሔርተኘነት ስሜት ያለው ነው ለማለት የሚያስቸግርበት ደረጃ ደርሷል።ይህ ደግሞ ከብሄርተኝነት አልፎ ወደለየለት የፋሽሽት ኃይል ለመቀየር በማኮብኮብ ላይ ያለ ምናልባትም የተቀየረበት ደረጃ እንደሆነ በጥልቀት አጥንቶ በማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።ከእዚህ በተለየ ግን የኦሮሞ፣አማራ እና ትግራይ ብሄርተኛ እሳቤዎች ብቸኛ ችግር መጪውን ዋስትና የማግኘት ጥማት ነው።በእዚህ ውስጥ ግን ሁሉም ውስጥ የስልጣን እና የግል ''ኤጎ'' ስሜቶች የሉም ማለት አይቻልም።ይህንን በሚገባ ለመመርመር ግን  እንደ እየቡድኖቹ አመራሮች ጠባይ በዝርዝር መመልከትን ይፈልጋል።

የኢትዮያ መጪ የፖለቲካ መንገድ ዋስትናው እና መፍትሄው

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአሁኗ ኢትዮጵያ ያሉት የፖለቲካ እሳቤዎች በሁለቱ ማለትም በሕብረ ብሔራዊ እና የብሔርተኝነት እሳቤዎች ስር መሆኑን መረዳት ይቻላል።አሁን ጥያቄው የኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ መንገድ ዋስትናው እና መፍትሄው ምንድነው? የሚል ነው።

ከመጋቢት 24/2010 ዓም ዶ/ር ዓብይ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ እና ከሁሉም በላይ ያነሱት የህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት እሳቤ የኢትዮጵያ እጅግ ውድ የሆነ መልካም ዕድል ነው።ይህ ማለት መጪው የለውጥ ሂደት ሕዝብ ከህዝብ ሳይጣላ፣ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ሂደት ሳይቆም እና የመንግስት ስሪቷ ሳይበጠስ ስለለውጥ እና አዲስ የፖለቲካ ሂደት ለመወያየት እና ወደ ውጤት ለመድረስ ፋታ አገኘን ማለት ነው።ይህንን ዕድል የህብረ ብሔራዊውም ሆነ የብሄርተኛ አቀንቃኙ በሚገባ ሊጠቀሙበት ይገባል።ስለሆነም ለመጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ዋስትናው እና መፍትሄዎቹ የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም

  • የህብረ ብሔራውውም ሆነ የብሔረሰብ አቀንቃኞች ዋስትናቸው የሕግ የበላይነት እና ከሴራ ፖለቲካ የራቀ የዲሞክራሲያዊ ሂደት ውጤት መሆኑን ማመን፣
  • ለሕግ የበላይነት እና የዲሞክራሲያዊ ሂደት ውጤት ስኬት ሃሳብን በጨዋነት የመግለጥ እና ሃሳብን ለሕዝብ ግምገማ በመግለጥ ማመን፣ለእዚህም እንዲረዳ የሚድያው ሚዛናዊ ሂደት ሁሉም እኩል መግባባት እና መጠበቅ መቻል፣
  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጦር ሰራዊት፣የደህንነት መዋቅር እና የፍትህ ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ተፅኖ አለመፍጠር። ምክንያቱም ሶስቱም አካላት ለሁሉም እኩል የሚያገለግሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ በእራሱ አንዱ የዋስትና ምንጭ ስለሆነ፣
  • ካልሰለጠነ እና ኃላ ቀር አስተሳሰብ እና ተራ ንትርክ እንዲሁም ብሽሽቅ ወጥቶ በሰለጠነ ሃሳብን የማንሸራሸር፣የመግለጥ እና የላቀ የሃሳብ ማመንጨት ልዕልና መሸጋገር፣ 
  • በህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትም ሆነ በብሄርተኝነት ስም የተደራጁ ሁሉ በእየቦታው በሃሳብ የሚመሳሰሉ ግን በቁጥር የተለያዩ ድርጅቶች ከማብዛት ሁሉም በሃሳብ ወደሚመስላቸው ስብስብ በመጠቃለል ሁለት ግዙፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም መድረኮች ፈጥረው ለምርጫ የመቅረብ ዝግጅት ማድረግ እና  
  • ለኢትዮጵያ እኩል የመጠንቀቅ፣የመቆርቆር እና ህልውና መቆምን በተግባር ሁሉም ወገን ማሳየት እንዲህም ለጋራ የሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ልዩነት ሳይኖራቸው የሚቆሙበት የጋራ ሃገራዊ ህገ መንግስት ላይ ማሻሻል አድርጎ ፍፁም ታዛዥነትን ከግደታ ማስገባት የሚሉ ናቸው።
ባጠቃላይ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ ተስፋ ሰጪ፣የትውልድ ሽግግር የሚታይበት እና ኢትዮያ ተስፈንጥራ ለመነሳት ኃይል የመስጠት አቅም ያለው ነው።በእዚህ ሁሉ ሂደት ላይ ግን በብልጣብልጥነት አንዱ ጠቅልሎ ለመያዝ የሚደረጉ ሙከራዎች እጅግ አደገኛ ብቻ ሳይሆን መልሶ ወደ አልተፈለገ  ግጭት ውስጥ የሚቀት ነው።ለእዚህ ደግሞ አደጋው ያለው በአጉል ጀብደኘንት የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ሂደቱን ለማሰናከል ከሚመኘው ከህወሓት በኩል ያለው የመጀመርያው አደጋ ሲሆን በመቀጠል ከአንዳንድ የብሄርተኛ አካላት ዘንድ ተመሳሳይ ምልክቶች አሉ።የእዚህ አይነቱ ሙከራ ለመጭዋ ኢትዮጵያ የማይመጥን ጊዜው ያለፈበት አንዲት ስንዝር የማያስኬድ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።በእዚህ አይነት የተሳሳተ መንገድ ለሚያልሙ ደግሞ ሁለት አይነት መንገዶች መጠቀም ይቻላል።የመጀመርያው በተቻለ መጠን የተሳሳተ ሕልም ለሚያልሙ የሴራ ፖለቲከኞች በሙሉ በግልጥ ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል።ማስጠንቀቁን አልፎ ሂደቱን ለማደናቀፍ ለሚሞክር ደግሞ የሚመጥን ምላሽ አስፈላጊ ነው።ከእዚህ ውጭ ግን በህብረ ብሔራዊውም ሆነ በበሄርተኛ እሳቤ ባለቤቶች በካከል የሚደረጉ የሃሳብ ልውውጦች አንዳንዴም  ከሰንደቅ አላማ ጀምሮ እስከ ዜግነት ድረስ የሚነሱ የሃሳብ ክርክሮች አንዳንዴም መወራረፎች ጨዋነትን ባለፈ መልኩ እስካልተቀየሩ ድረስ አደጋዎች አይደሉም።በእርግጥ ለእኛ ሀገር ፖለቲካ የእዚህ አይነት የሃሳብ ክርክሮች ካለማዳበራችን አንፃር የዓለም የመደናገጥ፣ተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች አንዳንዶች ቢያሳዩ አይገርምም።እአየቆየ ግን ልምዱን እያዳበርን በሃሳብ ልዩነቶች መካከል መኖር አደጋ ሳይሆን እውነታውን ማየት ግን በሃሳብ የማሸነፍ አስፈላጊነትን ብቻ እንደሚያሳይ ስንረዳ ሁሉም ቀላል ይሆናል።አዎን ሁሉም ቀላል ይሆናል።መልካም መንገድ ላይ ነን።የበለጠ ደግሞ የላቀው የፍቅር፣በልዩነት አንድነት እና የመተሳሰብ ፖለቲካችን ያድጋል።ዋናው ቁምነገር እያንዳንዱ የዳር ተመልካች ከመሆን የእኔ ሚና በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሃብቱ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ሁሉ ምን ለስራ ብለን ወደ ተግባር መግባት አስፈላጊ እና ጊዜ የማይሰጠው ነው።

የአዲስ ሙላት አዲስ ነጠላ ዜማ(ቪድዮ) 
======================
አብይ አብይ ሲሉ ያው ፆሙን ነው ብዬ፣
ሰውም አብይ አለው አረ እናንተ ሆዬ።
 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...