ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, July 26, 2018

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶስ አንድነት የዕርቅ ጉባኤ ዝርዝር ውሳኔ እና የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የቪድዮ ንግግር።

ጉዳያችን/Gudayachn
ሐምሌ 19/2010 ዓም (ጁላይ 26/2018 ዓም)
በሁለቱም ሲኖዶስ ለዑካን በተፈጸመው እርቅ የተደረስበትን ስምምነት ቃል በቃል እንደሚከተለው ይቀርባል።
1. ስለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ
በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ የተነሣ አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት ተከፍላ በሁለት ፓትርያርኮች የሚመሩ አንድ ሲኖዶስ ለሁለት ሲኖዶሶች መፈጠራቸው ግልጽ ነው። በዚህም የተነሣ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በስደት ዓለም መቆየታቸው ይታወቃል። ስለሆነም የሁለቱን ቅዱሳን ፓትርያርኮች ቀጣይ ሁኔታ በተመለከተ በሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶሶች የተወከሉት የሰላም ልዑካን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም በአደረጉት የጋራ ስብሰባ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ እንደሚከተለው በአንድ ድምጽ ወስነዋል።
ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፓትያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ /እንዲገቡ፤
ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ኢትዮጵያ ሲመለሱ በክብር የሚያርፉበትን የመኖሪያ ቦታ በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ ቦታ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤
ሐ/ የሥራ አፈጻጽምን በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
1.1/ ስለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤
ሀ/ በሕገ ቤተ ክርቲያን መሠረት የአስተዳድር ሥራውን በመሥራት ቅድስት ቤተ ክርስቲንን እንዲመሩ፤
ለ/ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
1.2/ የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ አባቶቻችን ስም በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ፤
1.3/ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወተ ሥጋ እስከ አሉ ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንድትይዝ፤
1.4/ይህ ስምምነት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ የአገር ቤትና የውጭ አገር ሲኖዶስ የሚለው ስም ቀርቶ አንዲት ቤተ ክርስቲያንና አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲሆን፤
2. ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት
ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ በልዑካኑ ታምኖብታል። ስለሆነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ሆነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋር አብሮ በመሄዱ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ሆነ ዛሬ ላይ ያሉትን በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልዑካኑ ጉባዔ በአንድ ድምጽ ተስማምቶ ወስኖአል።
ስለሆነም ከሁለቱም ሲኖዶስ ውህደት በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስህተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ እንዲዘጋጅ የልዑካኑ ጉባዔ በአንድ ድምጽ ተስማምቶ ወስኖአል።
3. ስለነባር ሊቃነ ጳጳሳት
ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተፈቶ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ጉባኤው በአንድ ድምጽ ተስማምቶአል።
4. ከልዩነት በኋላ ስለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት
ከልዩነት በኋላ በሁለቱም ወገኖች የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስቆጶሳትን በተመለከተ ፦ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭ ዓለምም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ጉባዔው በአንድ ድምጽ ተስማምቶአል። ስም አጠራራቸውንም አስመልክቶ እንደ ሹመት ቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፤ካልዓይ፤ሣልሳይ... ወዘተ እየተባሉ እንዲጠሩ ጉባዔው በአንድ ድምጽ ወስኖአል።
5. ስለቃለ ውግዘት
በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሁለቱም ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት እንደ ተላለፈ ይታወቃል። ስለሆነም ከዚህ ስምምነት በኋላ ቃለ ውግዘቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ የሰላም ልዑካኑ በአንድ ድምጽ ወስኖአል።

6. በውጭ ዓለም በስደት የምትገኘውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ያገናዘበ መዋቅራዊ አስተዳድርን ስለማዘጋጀት
እንደሚታወቀው በዘመናችን በየትኛውም ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በአሉበት ሁሉ ተስፋፍታ ትገኛለች። ይሁን እንጂ በውጭ ዓለም የምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድነቷን፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ክብሯን ጠብቃ መኖር እንዳለባት ጉባዔው አምኖበታል።
ስለሆነም የየሀገሩን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ የቃለ አዋዲውና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ገዥነት የሚረጋገጥበት መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያዘጋጅ ልዑካኑ በአንድ ድምጽ ወስኗል። እንዲሁም በውጭ ዓለም የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በመዋቅራዊ አስተዳድር መሠረት ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በመቀበል በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንድትመራም ወስኖአል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና የሁለቱንም ሲኖዶስ ውሕደት ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም በስደት የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው፥ የቀደመውን ሰላምና አንድነት አጽንተው፥ ሁሉም በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ሁኔታ የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልዑካን እንዲያዘጋጁና እንዲከታተሉ የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልዑክ በአንድ ድምጽ ወስኗል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከስኖዶሳዊ ዕርቅ ውሳኔ በኃላ ያደረጉት ንግግር

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments: