በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ሰጪ ድርጅት እና የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ያዘጋጁት ስብሰባ በከፊል።
ሐምሌ 24/2010 ዓም (ጁላይ 31/2018 ዓም)
ሐምሌ 21፣2010 ዓም የኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ አሁን በኢትዮያ የሚደረገውን የለውጥ ሂደት በመደገፍ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኦስሎ ከተማ ''ኦልፋንገን 3'' በሚገኘው አዳራሽ የፍቅር፣የአንድነት እና የመደመር ቀን በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ እና የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ በጥምረት በጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ አሁን በኢትዮጵያ እየተረገ ያለውን ዲሞክራሲያዊ የለውጥ ሂደት እንደሚደግፉ በጋራ መግለጫ በማውጣት ጭምር ውሳኔ አሳልፈዋል።ከላይ በተጠቀሰው ቀን ከቀትር በኃላ 9 ሰዓት ላይ የተጀመረው ስብሰባ ''በአባይ ሚድያ'' ቀጥታ የቪድዮ ስርጭት ለመላው ዓለም ተከታታዮች እንዲታይ ሽፋን ማግኘቱን ጉዳያችን በስፍራው ተገኝታ ለመረዳት ችላለች።
በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮሚኒቲ) ሰብሳቢ አቶ ፍቅሩ ሁሴን እና ከፖለቲካ ድርጅት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር እና የኖርዌይ ቻፕተር ተጠሪ ዶ/ር ሙሉ ዓለም ተገኝተዋል።የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ሰብሳቢ ኮሚኒቲው አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ለውጥ እንደ ኢትዮያዊ ሲቪክ ድርጅት እንደሚከታተሉ እና በአዎንታዊ መልክ እንደሚመለከቱት ከገለጡ ባኃላ በቅርቡ በኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት የተመለከቱት የሕዝብ ደስተኛ ስሜት ከእዚህ በፊት ያልተመለከቱት መሆኑን ምስክርነታቸውን ከመስጠታቸውም በላይ ወደፊት ከኮምንቲው አመራር ጋር ተመካክረው በጋራ በሚደርሱበት ውሳኔ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማከናወን ዝግጁነታቸውን ለተሰብሳቢዎቹ አረጋግጠዋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር እና የኖርዌይ ቻፕተር ተጠሪ ዶ/ር ሙሉ ዓለም የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ጋር ሁለት ዙር ውይይት እንደተደረገ እና በቅርቡ ድርጅቱ በውይይቱ ውጤት ላይ ተንተርሶ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ቀድም ብሎም የዲሞክራቲካዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጪ ድርጅት ሰብሳቢ አቶ ይበልጣል ጋሹ የድርጅቱን ቀደም ብሎ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ያደረገውን ትግል አብራርተው አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት የዲሞክራቲክ ለውጥ ድጋፍ በኢትዮጵያ እንደሚደግፈው ገልጧል።በመቀጠል የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው በቀለ በአሁኑ ወቅት ለውጥ በኢትዮጵያ አለ ወይንስ የለም? በሚል ርዕስ ለሃያ ደቂቃዎች የፈጀ የለውጡን ሂደት ፣የለውጥ መኖር፣ ሁለተናዊ ተፅኖውን እና የውጭው ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ተግባራት ዙርያ የመነሻ ፅሁፍ አቀርቦ በተሰብሳቢዎች ውይይት ተደርጎበታል።
በእዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አንድ ዶላር ለወገን ጥሪ ላይ ውይይት ከተደረገ በኃላ ወደ ተግባራዊነቱ ለመግባት ኃላፊነቱን ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ (ኮምዩንቲ) ኃላፊነቱ የተሰጠው ሲሆን የጋራ መግለጫም ወጥቷል። በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የወጣው የስብሰባው የጋራ መግለጫ ከእዚህ በታች ይመልከቱ።
በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የመደመርና የፍቅር ቀን በሚል በሀገራችን
ኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ በመደገፍ የተሰጠ የአቋም መግለጫ!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት ለፍትህ፣ለነፃነት፣ለአንድነት የከፈሉት ዋጋ በቃላት ብቻ የሚገለጥ አይደለም። የተከፈለው ዋጋም ፍሬ አፍርቶ አሁን ሀገራችን በለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች። ይህ የለውጥ ተስፍ እንዲመጣ ብዙዎች የህይወት ዋጋ ከፍለውበታል። የአካልና የመንፈስ ስብራት ደርሶባቸዋል።
እኛ በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን አቅማችን በፈቀደው መልኩ አገራችን ኢትዮጵያ ከአረመኔያዊ ዘር ገነን አገዛዝ ነጻ ወጥታ፣ ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተከብረው፣ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር በመገንባት የተረጋጋችና ዲሞክራሲያዊት አገር ትሆን የበኩላችንን አስትዋጾ በድርጅትም በግለሰብ ደረጃ አስትዋጾ ስናበረክት ቆይተናል። ጠቅላይ ሚኔስተር ዶ/ር አብይ አህመድና የለውጡ ቡድን ብዙዎች መስዋዕትነትን የከፈሉበትን ዓላማ ከግብ እንዲደርስና የተጀመረው ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና ስላበረከቱልን በስብሰባው ላይ የተገኘን ኢትዮጵያዊያን በታላቅ ደስታ ልባዊ አክብሮትና ምስጋና አቅርበናል። ስለሆነም በዚህ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጭ ድርጅት በኖርዌይና በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተገኘን እኛ በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የተጀመረው የለውጥ ሂደት ለዓመታት ስንታገልለት የነበረ ፅኑ ዓላማችን በመሆኑ በማነኛውም መልኩ ለውጡን ከዳር ለማድረስና የጠነከረ መሰረት እንዲይዝ ለማድረግ የበኩላችንን አስትዋፅኦ ለማበርከት በአንድ ድምፅ ተስማምተናል።
በዚህም መሰረት የስብሰባው ተሳታፊዎች በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ተስማምተን የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
1ኛ/ አሁን በሀገራችን የተጀመረው የመደመር እና የፍቅር ሂደት በፍትሃዊና ስር ነቀል እርቅ እንዲሆን፤
2ኛ/ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለዘለቄታዊ ለውጥ ለሚደረግ ጥሪ ሁለተናዊ ድጋፍ መስጠት በሚገባን ሁሉ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ከመቼውም በበለጠ ዝግጁዎች ነን፣
3ኛ/ አሁን የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚደረግ ማናቸውንም ሙከራ በጥብቅ እንቃወማለን፣እናወግዛለን፤
4ኛ/ ከዚህ በፊት የነበርን የፖለቲካ፣የአመለካከት፣ የብሄርና ሌሎች ልዩነቶችን በማጥበብ በፍቅርና የጋራ ሀገራችንን ለመገንባት ተስማምተናል፤
5ኛ/ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የለውጥና ሰላም ሐዋርያ ስለሆኑ የኖቬል ተሸላሚ እንዲሆኑ ቅስቀሳ እናደርጋለን፤
6ኛ/ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ላለፉት ሶስት ወራት የወሰዱት የለውጥ እርምጃ የምንደግፍ መሆናችንን እየገለጥን ለወደፊትም ሃገርን የመገንባት ሂደት ላይ ሁሉ መንግስታዊና ማኅበራዊ ተቋማት በሙሉ ነፃነት እንዲሰሩ ለሚደረገው ጥረት የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን፤ 7ኛ/ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀን ከሚያወጡት አንድ ዶላር ለሀገራቸው አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ባደረጉት ጥሪ መሰረት በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያውያንም የበኩላችንን ለማድረግ በዛሬው ስብሰባችን በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማህበር በኩል የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር እንዲከናወን እና እኛም ሃገራዊ ግዳጃችንን በፍቅር፣ በሰላም፣ በመደመርና በይቅርታ ለመወጣት ተስማምተናል፤
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ሐምሌ 28/2018 እኤአ ኦስሎ፣ ኖርዌይ
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment