አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጥይቄ የህወሓት ከስልጣን የመውረድ ብቻ አይደለም።የኢትዮጵያ የግዛት እና የሕዝብ አንድነት ጥያቄም ጭምር ነው።ስለ አቶ ኃይለማርያም ቀደም ብሎ የወጣውን ፅሁፍ ከፃፍኩ ከተኛሁ በኃላ ስለ ኢትዮጵያ ተጋድሜ ማሰላሰል ጀመርኩ።እንቅልፍ በአይኔ አልዞረም።ሰዓቱ ሌሊቱ አልቆ ሊነጋ ነው።ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ነች።ስለ ህወሓት ከስልጣን አለመልቀቅ ስላስከተለው ምስቅልቅል ሁኔታ ብዙ ተፅፏል።ህወሓት የሰራው ስህተት እዚህ አድርሶናል።አሁን ጥያቄው ግን የአንድነት አደጋም ጭምር ነው።
ስለሆነም እንደ ሀገር የተደቀነውን አደጋ ለማስወገድ ለጊዜው ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ስልጣኑ በህወሓት ስር እስካለ ድረስ ህወሓት የብዙሃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ አዎንታ ያስገኘ ለውጥ ለመጀመር የሚችለው በመጀመርያ ያለፈ የጎሳ ፖለቲካው ስህተት መሆኑን በግልጥ አምኖ የሚከተሉትን አስራ ስድስት ነጥቦች በድፍረት መተግበር ከቻለ ነው።
1/ በጎሳ ስም የፖለቲካ ድርጅት መመስረት በመላ ሀገሪቱ መከልከል አለበት፣
2/ ከእዚህ በፊት በጎሳ ስም የተደረጁ ጥምረት ፈጥረው ወይንም ለብቻቸው ሃገራዊ ስም ወይንም የቃላት ሐረግ መርጠው እንዲሰየሙ መታዘዝ አለባቸው ፣
3/ ህወሓት ስሙን በፍጥነት ሃገራዊ ስም መስጠት አለበት ማንም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ትግሪኛ ተናገረም አልተናገረ አባል መሆን መቻል አለበት፣
4/ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት መመስረት እና ህገ መንግስቱን ማሽሻል፣
5/ የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ከሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች እና ሴቶች የተውጣጣ ካለ ምንም የፖለቲካ ተፅኖ መመስረት እና ሥራ ማስጀመር፣
6/ ለዲሞክራሲ ሂደቱ ዋስትና የሚሆኑትን ሚድያ በነፃ እንዲዘግቡ ማድረግ፣
7/ የፍትህ ስርዓቱን በገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ
8/ የሃማኖት አካላት በሙሉ ነፃነት እንዲሰሩ መፍቀድ በውስጣቸው ያለውን ንቅዘት እንዲነቀል ከሕዝቡ ጋር በቅንነት መስራት፣
9/ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወደ ሀገር በነፃነት የመግባት ፍቃድ መስጠት።ከእዚህ በፊት በፖለቲካ የተከሰሱት ሁሉ ነፃነት ማወጅ
10/ የጦር ኃይሉን እና የደህንነት መዋቅሩን ሁሉን አቀፍ ማድረግ ይህንንም የሚያረጋግጥ ልዩ የህዝብ ኮሚሽን መሰየም፣
11/በሙስና ያጠፉ፣በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና በልዩ ልዩ ወንጀል የሚጠየቁ አካላትን በሙሉ ለፍትህ ማ1ቅረብ ህዝብን እና ትውልድን አስተማሪ በሆነ መልኩ ይያለፈ ስህተትን ማረም፣
12/ የሰማዕታት ሃውልት በማለት የተሰሩት ሐውልቶች ሙሉ በሙሉ የቅርፅም ሆነ የይዘት ለውጥ ተደርጎባቸው በሃያኛው ክፍለ ዘመን በደርግም ሆነ በህወሓት ወይንም በኢህአፓም ሆነ በኢድዩ ወይንም በኦነግ ስር ሆነው ለሞቱት የሃውልቱ ሁሉ የጋራ መታሰቢያ እንዲሁን አዲስ ስያሜ ለምሳሌ በእርስ በርስ ጦርነት ህይወታቸውን ላጡ ወይንም ሌላ የወል ስም ተፈልጎ እንዲሰየም ፣
13/ ኢትዮጵያ አንድ የብሔራዊ ክብር ቀን እንዲኖራት በእዚህም ቀን ያለፈ የእርስ በርስ ጦርነት ምዕራፍ መዝጊያ መታሰቢያ ቀን ሆኖ ቀኑ የዕርቅ እና የአንድነት ቀን ሆኖ እንዲታስብ እንዲታወጅ ፣
14/ ህወሓት በስሩ ያሉትን የኤፈርት ንብረቶች ወደ ሕዝብ ንብረትነት እንዲቀየሩ እንዲያደርግ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሀብት በሕግ እንዲወሰን
15/ ኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ የሆነ እንዲሆን እና ኢትዮጵያ የፕረዝዳንታዊ ሀገር እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር የምትመራ ሀገር መሆኗ እንዲቆም ቢደረግ እና
16/ አሁን ያለው የጎሳ አከላለል ስርዓት ጎሳን ሳይሆን በጅኦግራፍ፣ታሪክ እና ባህልን መሰረት ያደረገ የፌድራል አከላል ስርዓት እንዲዘረጋ እንዲያደርግ የሚሉት ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለመከወን ህወሓት አሁን ባለው የሰው ኃይል ወይንም ሕዝቡን ደጋግመው ሲዋሹ በተያዙ ባለስልጣናቱ ማከናወን አይችልም።ስለሆነም አዲሱ ትውልድ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት።ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ህወሓት እራሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንደሚጥላት ሳይታለም የተፈታ ነው።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment