ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, October 18, 2021

ኢትዮጵያን ሊያፈርሷት እያደሟት ነው።አሁን ታሪክ የመስርያ ጊዜ ነው።በውጭም በውስጥም ያለው ሕዝብ እና መንግስት ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ ሰባቱ ቁልፍ ተግባራት።

ትግራይ ከሰሞኑ 
 ፎቶ= ቪኦኤ አማርኛ  ኤዲቶርያል ገፅ የተወሰደ 

==============
ጉዳያችን/Gudayachn
==============
የአረብ ሊግ ዝቶብናል፣ግብፅ ሌት ከቀን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሰማይ እና ምድር እየቧጠጠች ነው።የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያ አፍሪካን ይዛ ትነሳለች ብሎ ለመኮርኮም ከቡድን 7 ስብሰባ እስከ የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ሕብረት ስብሰባ ዶልተዋል፣የባዕዳን ተላላኪዎች እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱት በደም የተነከሩት የህወሓት ጀሌዎች ፋሽሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ያልሰሩትን  ወንጀል በኢትዮጵያ ላይ እየፈፀሙባት ነው።አሁን ታሪክ የመስርያ ጊዜ ነው።

በውጭም በውስጥም ያለው  ሕዝብ እና መንግስት ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ ሰባቱ ቁልፍ ተግባራት።

1) መንግስት 

መንግስት ከእዚህ በፊት ይሄድበት የነበረውን የሕግ ማስከበር መንገድ መቀየር አለበት።የማስታመምያ ጊዜው ይበቃል።በውስጡ ያሉትን ለሽብርተኛው ህወሓት የሚሰሩትን በኦሮምያ እና በአማራ ክልል ውስጥ ያሉትንም በልዩ ዘመቻ ወደ ሕግ የማቅረብያ ጊዜው ነው።በትግራይ የተጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጊዜ አሁን ነው።በተጨማሪ በትክክል ለሀገራቸው የቆሙትን  ካለምንም ይሉኝታ ወደፊት ማምጣት አለበት።

2) ድምፃውያን እና የኪነጥበብ ሰዎች ከግብር ይውጣ ሥራ መውጣት እና ውስጣቸው የፈነቀላቸውን ሥራ በቶሎ ይዘው መውጣት  

ለጥፋት የዋሉ የሽብርተኛው ህወሓት ጀሌ እንዴት የድምፃውያኑን ዜማ ለመቀስቀስ እየተጠቀመበት እንደሆነ እያየን ነው።በሀገር ቤት ያሉ የኪነ ጥበብ ሰዎች በተለይ የሙዚቃ ሰዎች ሕዝብ ለሀገሩ እንዲቆም የሚቀሰቅሱ፣ከሀዲዎችን የሚያሸማቅቅ የቅስቀሳ እና የሀገር ፍቅር ዜማዎች በቀናት ውስጥ ምናልባት በያዝነው ሳምንት ሳይቀር ማድረስ አለባቸው።የኪነጥበብ ሰዎች ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ላይ  መሽኮርመም  ትዝብት ነው።አሁን የኪነጥበብ ሰው ማን እንደሆነ የሚታይበት ጊዜ ነው።ይህ ከውስጥ ለሀገር ከመነጨ ፍቅር እና አሁን ያለው ሃገራዊ አስጊ ጉዳይ ዕድል ቢያገኝ ኢትዮያን ምን ሊያደርጋት እንደሚችል በሚገባ ከመረዳት የመነጨ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።

3) ከቤት ጀምሮ መንቃት  

ለህወሓት እና ጀሌው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ  የሚሰራ እና የቤተሰብህ አካል ሆኖ ሁሉ የስነ ልቦና ጦርነት ሊያደርግ የሚሞክር ማንኛውም አካል ማስታገስ። በተለይ ለአማራ የተቆረቆሩ መስለው ወይንም ለኦሮሞ የተቆረቆሩ መስለው ማናቸውም ፀረ ኢትዮጵያዊ ዘመቻ የሚያደርጉ ሁሉ  ላይ ምንም ዓይነት ትዕግስት አለማሳየት።ይህ ወዳጅ፣ቤተሰብ ወይንም ጎረቤት ብሎ አይሰራም።በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የሚፈታተን ማናቸውም ዓይነት ተግባር የሚሰራ ወይንም የምትሰራን ነቅቶ መግታት።ይህ ደግሞ ከቤት ጀምሮ በሰፈር እና በሥራ ቦታ ያለውን ሁኔታ ሁሉ በሚገባ መፈተሽ።ሽብረተኛው ቡድን የምቀናቀነውን ሰው ከቤተሰብ እስከ የቤት ሰራተኛ፣ከቅርብ ወዳጅ እስከ ጎረቤት አጥምዶ የጥፋት ስራውን እንደሚሰራ መንቃት።

4) ሲበርድ በእጅ፣ስፋጅ በማንክያ የሚሉ ሀገር ችግር ላይ ስትሆን ግን ዝም ባዮችን ማስተካከል። 

ስለኢትዮጵያ ጊዜያቸውን፣ጎልበታቸውን እና ገንዘባቸውን የሚሰጡት ምንም ከማያደርጉት አንፃር ሲታይ ዝም ብሎ ሌላው ለፍቶ በሚያመጣው ነፃነት ለመኖር የሚሞክሩ ብልጣብልጦች በዝተዋል። ይህ ሁኔታ ከአሁን በኃላ ሊቀጥል አይችልም።ኢትዮጵያ ድሮም የተጎዳቸው በባንዳ እና ዝም ብለው ኑሯቸውን በመኖር እና ለሁሉ አድር ባይ ሆነው በወንድማቸው እና እህታቸው ደም የሚቀልዱ ናቸው። ከአሁን በኃላ ዝም ባዮች እና የሌላውን ሞት እንደተውኔት የሚያዩ መልሰው አሳልፈው ለመስጠት የማያፍሩ ናቸው።ስለሆነም ሕዝብም፣መንግስትም የኪነጥበብ ሰዎችም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዝም ባዮችን ወቅሶም ሆነ ቀስቅሶ ማስነሳት ያስፈልጋል።

5) በቤተ ዕምነት ውስጥ የመሸገው ዕምነት የለሽ የህወሓት ጁንታ ጀሌ መመንጠር 

የኢትዮጵያ አጥፊዎች የመጨረሻ ምሽግ የዕምነት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ የህዝቡን ስነ ልቦና ከመስለብ ጀምሮ ሕዝብ በሚደርስበት ፈተናዎች የዕምነት ፅናት እንዳይኖረው አገልግሎቶች እንዲዳከሙ እና ሕዝብ ስነ ልቦናው እንዲጎዳ በየመዋቅሩ ያሉ የሽብርተኛው ጁንታ ጀሌ ወኪሎች እና የአስተሳሰብ በሽታ ተሸካሚዎች መመንጠር አለባቸው።ይህ ዘርን የሚወክል አይደለም።ሀገርንም የሚያገለግሉትን የዕምነት ሥራ በተቃራኒው እንዲሆን የሚያደርጉ ስለሆኑ ሰውንም ፈጣሪንም ለመግፋት የቆሙ ስለሆኑ አይጠቅሙም። ኢትዮጵያ እየተሞከረባት ያለው የምዕራብ እቀባ ወደፊት ቢቀጥል ሕዝብ የሚፀናበት አንዱ መንገድ እምነቱ ነው። ይህ እምነቱ የተጎዳበት ሕዝብ እና በሴራ የተተበተበበት ሕዝብ መራመድ አይችልም።ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ ሕዝብ በዕምነት የሚኖርባት ሀገር ነች።ይህ ክፍል የህዝቡ ወሳኝ የሞራል እና መንፈሳዊ ኃይሉ መነሻ እና መድረሻ ነው።ጠላት የሚያጠቃው ስስ  ብልት ይህ ክፍል ነው።ቸልታ አያስፈልገውም።ኢትዮጵያ ለ40 ዓመታት የተጎዳባትን የዕምነት እና የኃይማኖት አካሏን በሚገባ መልሳ በሥርዓት ማሰናዳት ጊዜ ልትሰጠው አይገባም።

6) ሁሉ ዓይን እንዲሆን ማብቃት 

ሀገር የሚጠበቀው ሁሉም ሕዝብ ለሀገሩ ዓይን መሆን ሲችል ነው።በአውሮፓ አንዱ የህዝቡ ብቃት ሁሉም ሰው መንገድ ላይ የተመለተውን ስህተት፣ወንጀል ወይንም አስጊ የመሰለው ጉዳይ በሙሉ ለፖሊስ ወድያው ደውሎ ያሳውቃል እንጂ እኔን እስካልነካኝ ምን አገባኝ አይልም።ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ወጣቶች፣ወንዶች፣ሴቶች እና አዛውንቶች ሁሉ ለሀገራቸው ዓይን መሆን አለባቸው። በየትኛውም ቦታ እና ሰዓት የሚሰሙትን በጥንቃቄ የሚሰሙ፣የሚያዩትን ነቅተው የሚያዩ እና ማገዝ ያለባቸው ሥራ ላይ ሁሉ ማገዝ የሚችል ስብዕና  እንዲያዳብሩ በቶሎ ማንቃት ያስፈልጋል።ይህ በትምህርት ካሪኩለም የሚገባ ቢሆንም አሁን ግን በመገናኛ ብዙሃን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እንዲከታተል ጥርጣሬ ሲመለከት ወድያው ለሚመለከተው እንዲጠቁም እራሱ መፍታት ያለበትን ደግሞ መፍትሄ ሰጥቶ እንዲያልፍ የማብቃት ሥራ ያስፈልጋል።
በእዚህም ማናቸውም እና በየትኛውም ስፍራ ሃገሩን የሚጠብቅ ሕዝብ እንዲኖር ያደርጋል።

7) ገንዘብ፣ጉልበት ወይንም ጊዜ ለሀገር 

ከገንዘቡ ወይንም ከጉልበቱ ወይንም ከጊዜው ለሀገሩ የማይሰጥ ሰው ፈፅሞ መኖር የለበትም።በውጭ የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በወር ለሀገሩ የሚከፍለው ገንዘብ ማውጣት ዛሬውኑ መጀመር አለበት።ቡና እና ቢራ እየጠጡ ስለሀገር የሞቀ የቁጭት ወሬ በማውራት ሀገር አይድንም።ለሀገር ካለምንም ማቆም በቀጣይ ከሚያገኙት ገቢ መክፈል ትናንት እንደሀገር ከታወቀችው ኤርትራ ጀምሮ የናይጀርያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በአስገዳጅ ሕግነት አፅድቀው ሀገራቸውን እየጠቀሙበት ነው።ወደፊት ወደ ሀገር ቤት የሚገባ ሁሉ ይህንን ማድረግ አለማድረጉ መጣራት አለበት።በሀገር ውስጥ ቀረጥ ከፍሎ ከሚኖረውም  በሰላም ወጥቶ ለሚገባባት ሃገሩ የአቅሙን ከሽራፍ ሳንቲም ጀምሮ መስጠት አለበት።ገንዘቡን የማይችል ጉልበቱን ወይንም ጊዜውን መስጠት አለብት።

አሁን ኢትዮጵያ ለህልውናዋ ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር የምታደርገው ፍልምያ ከህወሓት ጀሌ ጋር ብቻ የሚደረግ አይደለም።ከሱዳን እስከ ግብፅ ያሉ የወታደራዊ አማካሪዎች ሁሉ የተሳተፉበት ነው።ተሳትፎው ከጦር መሳርያ እስከ ማማከር ይዘልቃል።ስለሆነም ጦርነቱ ከተራ ሽፍቶች ጋር ብቻ አይደለም።ከኢትዮጵያ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ጋር ነው።በፍልምያው ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።ይህ ምንም ጥርጥር የለውም።ማሸነፉዋ ግን በጥቂቶች ትከሻ እና እንቅልፍ ማጣት ከሆነ መስዋዕቱን ያበዛዋል ጊዜውን ያረዝመዋል።ሁሉም ወደ መሃል መጥቶ ሃገሬን ብሎ ከሰራ ግን ጊዜው ያጥራል፣መስዋዕትነቱም ይቀንሳል።

=========///===========
 

No comments: