ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, October 29, 2021

የፍትህ ሚኒስቴር በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር እና በአፋር ክልል በህወሃት የሚመራው የትግራይ ወራሪ ቡድን በንጹሃን ላይ የፈጸመው ወንጀል ዛሬ ያቀረበው ሪፖርት

⮚ አንድን ሴት እስከ አስራ አምስት በመሆን እየተፈራረቁ ደፍረዋታል፤
⮚ እናት እና ልጅን በአንድ ላይ ደፍረዋቸዋል፤
⮚ ከተፈጥሮ ተቃራኒ የወሲብ ጥቃቶች ፈጽመዋል፣
⮚ ልጆችን በእናቶቻቸው ፊት ደፍረዋል፤
⮚ አንዲትን ሴት ከደፈሩ በኋላ በጠመንጃ አፈሙዝ ብልቷን በመውጋት የፌስቱላ ተጠቂ እንድትሆን አድርገዋታል፤
⮚ የ8 ወር እመጫትን ጨቅላ ልጇን በፈላ ዉሃ ዉስጥ እንጨምራለን በማለት እናትዋን አስፈራርተው ደፍረዋታል፤
⮚ አንዲት የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሴትን ለሶስት አስገድዶ ደፍረዋታል፤
====================
ሙሉ የሪፖርቱን ይዘት በጽሁፍ እና የቪድዮ ሪፖርት ከስር ያገኛሉ።


በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ስር በተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ወንጀል ምርመራን እና የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን ውጤቱን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
......................................................................
አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አደባባይ ሚድያ)
.......................................................................
መግለጫው በኢ.ፌ.ድ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ እና በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከክልል የምርመራ አካላት ጋር በትብብር በተዋቀረ የዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ የምርመራ ቡድን አማካኝነት የተከናወነ የወንጀል ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ለመግለጽ የተዘጋጀ ነው። ምርመራው የተካሄደው በአፋር እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሚገኙ በአሸባሪው ህወሃት ተይዘው በነበሩ እና ኋላ ላይ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻው ነጻ በወጡ አካባቢዎች ላይ ነው።

የምርመራ ቡድኑ ቀድሞ በተሰጠው እቅድ እና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት ያከናወነው ምርመራ ትኩረቱን ያደረገው ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የህወሃት አሸባሪ ቡድን በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ በማካሄድ የአለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች እና የአለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጽም ከቆየባቸው አካባቢዎች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ፣ የንፋስ መውጪያ ከተማ አስተዳደር፣ የጉና በጌምድር ወረዳ፣ የፋርጣ ወረዳ፣ እስቴ ወረዳ /በከፊል/፣ ደብረታቦር ከተማ አስተዳደር /በከፊል/ ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ በዳባት፤ደባርቅ እና ዛሪማ ንዑስ ወረዳዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እና በፈንቲረሱ ዞን ሥር በሚገኙ እዋ፣ አውራ እና ጉሊና ወረዳዎች ላይ ባልታጠቁ እና ሰላማዊ ህዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ብቻ በመሆኑ ምርመራው በመንግስት በኩል ሕግ ለማስከበር ተሳታፊ የሆኑ ተዋጊ ወታደሮችን እና አጋዥ አካላት ለአብነትም ምርኮኞች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አያካትትም፡፡

ወንጀሉ በአሸባሪው ድርጅት መሪነት ከሐምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢዎቹ በፌዴራል እና በክልል የጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር ተመልሰው እስከ ገቡበት ጊዜ ድረስ ባሉት ጊዜያት የተፈጸሙ ሲሆን ምርመራው ከተጀመረበት ከመስከረም 05 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከአሁን ድረስ የደረሰበትን የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን ለህዝብ ለማሳወቅ ስለሆነ በምርመራው ቀጣይነት የሚገኙ አዳዲስ ውጤቶች በቀጣይ በሚቀርቡ ሪፖርቶች የሚገለጽ ይሆናል፡፡
በዚህ መሰረት በደቡብ ጎንደር ዞን የተሰማራው የምርመራ ቡድን በጠቅላላው ከ790 በላይ ምስክሮችን የምስክርነት ቃል ፣ በሰሜን ጎንደር ዞን የተሰማራው የምርመራ ቡድን ደግሞ 285 የምስክሮች ቃል እንዲሁም በአፋር ክልል የተሰማራው ቡድን 148 ምስክሮች ቃል ተቀብሏል፡፡ ሶስቱም ቡድኖች ከተጠቀሰው የተጎጂዎችና ቀጥታ ምስክሮች የምስክርነት ቃል በተጨማሪ ከምስክርነት ቃል ውጭ ወንጀሎቹን ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ማስረጃዎችን፣ ገላጭ ማስረጃዎችን ፣ኤግዚቢቶችን እንዲሁም የቴክኒክ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ችለዋል፡፡

በውጤት ደረጃም አሸባሪው ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን ለጊዜው በዝርዝር ማስረጃ የተለዩ የ96 ሰዎች ሞት፣ 53 የአካል ጉዳት፣ 29 አስገድዶ መደፈር፣ 11 ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፣ 6 እገታ እንዲሁም የመንግስት፣ የግል እና የሀይማኖት የተለያዩ ተቋማት ንብረቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውደመት መፈጸሙ ተረጋግጧል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች ደግሞ በድምሩ የ129 ሰዎች ሞት፣ የ54 ሰዎች የአካል ጉዳት፣ በንፋስ መውጫ ከተማ ብቻ የ73 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲሁም በርካታ ግለሰቦች ንብረት ላይ ውድመት ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል በአፋር ክልል ነሃሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋሊኮማ ቀበሌ መጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የ240 ሰዎች ሞት፣ 42 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በቀሪዎቹ ሶስት ወረዳዎች ደግሞ የ17 ሰዎች ሞት እና ለ17 ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲሁም 7 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንደተፈጸመባቸው ተረጋግጧል፡፡

በሁለቱም ክልሎች ከሰላማዊ ዜጎች ንብረት በተጨማሪ በመንግስት እና በግል ተቋማት ላይ ማለትም ት/ቤቶች፣ ጤና ኬላዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ የዘረፋ እና ውድመት ድርጊቶች በስፋት መፈጸማቸው ተረጋግጧል፡፡
ድርጊቱ ሲፈጸምም የግለሰብ ቤቶችን እንደ ምሽግ መጠቀም፣ ታሪካዊ እና ሀይማኖታዊ ቦታዎችን እንዲሁም እንደ ዩኤስኤይድ፣ አክሸን ኤይድ እና በመንገድ ስራ ላይ የተሰማራ የቻይና መንገድ ተቋራጭ ድርጅትን ንብረቶችን ኢላማ ያደረገ ጭምር ነበር፡፡ እነዚህን ንብረቶች ለመዝረፍም የባለሙያ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን በመለየት በተጠና እና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በሜካኒክ ፈትቶ እስከመውሰድ የደረሰ የዘረፋ ድርጊቶች ተስተውለዋል፡፡

ወንጀል አድራጊዎቹ ተቆጣጥረውት በነበርዋቸው ቦታዎች ድርጊቱን ሲፈጽሙ ከተናገሩት፣ ቤቶች ላይ በቀለም በተጻፉ ጽሁፎቻቸው እንዲሁም በወቅቱ የወንጀል ድርጊቱን ሲፈጽሙ ሲናገሩ ከነበሩት በመነሳት ለማረጋገጥ እንደሚቻለው አሸባሪው ድርጅት ይህንን መጠነ ሰፊ ጥቃት የፈጸመበት ዋንኛ አላማ ብሄር ተኮር ከሆነ ጥላቻ የመነጨ እና በአሸባሪው ድርጅት የበላይ አመራሮች ውሳኔ እና ትእዛዝ በብሄር የተመሰረተ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ፣ የተወሰነ ብሄርን እንደማህበረሰብ በኢኮኖሚ እና በሞራል የተጎዳ እንዲሆን ለማድረግ ከድርጊት በተጨማሪ ጸያፍ የሆኑ ስድቦችን በመጠቀም እና በመፈረጅ፣ የፌደራል መንግስት ተረጋግቶ ሀገር እንዳይመራ ለማድረግ፣ ህወሃት ከሌለ ሀገር አትመራም በማለት የተዳከመ የፌደራል መንግስት እንዲኖር ለማድረግ፤ ማህበረሰብ ባህሉ እሴቱ እና መሰረታዊ ስሪቱ እንዲጠፋ የማድረግ አላማ አድርጎ የተነሳ መሆኑን በምርመራው ሂደት የታዩ እውነታዎች ያስረዳሉ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ በተገለጸው አግባብ አሸባሪው ቡድን ወንጀሉን ለመፈጸም ከተነሳበት ምክንያት እና ከምርመራው ግኝት ለማሳያነት የሚቀርቡ ዋና ዋና አሰቃቂ ኢሰብአዊ ድርጊቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን በተመለከተ፤-
⮚ አንድን ሴት እስከ አስራ አምስት በመሆን እየተፈራረቁ መድፈር፤
⮚ እናት እና ልጅን በአንድ ላይ መድፈር፤
⮚ ከተፈጥሮ ተቃራኒ የወሲብ ጥቃቶችን መፈፀም፣
⮚ ልጆችን በእናቶቻቸው ፊት መድፈር፤
⮚ አንዲትን ሴት ከደፈሩ በኋላ በጠመንጃ አፈሙዝ ብልቷን በመውጋት የፌስቱላ ተጠቂ እንድትሆን ማድረግ፤
⮚ የ8 ወር እመጫትን ጨቅላ ልጇን በፈላ ዉሃ ዉስጥ እንጨምራለን በማለት እናትዋን በማስፈራራት መድፈር፤
⮚ አንዲት የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሴትን ለሶስት አስገድዶ መድፈር፤
⮚ የመደፈር ወንጀል የደረሰባቸው ሴቶች ለአባላዘር እና ለአእምሮ ጤና መታወክ በሽታዎች ተጋላጭ ማድረግ፤
⮚ የተለየ የስነ ልቦና ጫና ለማድረስ በሚል የማህበረሰቡ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች የሆኑትን የካህናት ሚስቶችን እና ቆራቢ መነኮሳትን ለይቶ አስገድዶ መድፈር፤
⮚ በአፋር ክልል ሴቶችን ለረዥም ጊዜ አግቶ በማቆየት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በተደጋጋሚ በመፈጸም እና የህክምና እርዳታም ሳያገኙ አቆይተው መልቀቀ ናቸው።
የተለየ ጨካኝነትን እና ነውረኝነትን የሚያሳዩ የግድያ እና ተያያዥ ወንጀል ድርጊቶች
⮚ ከ30 ቀን ጨቅላ ህጻን እስከ 70 ዓመት ሽማግሌ ድረስ ተጠቂ የሆኑባቸው ግድያዎች መፈጸማቸው፤
⮚ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 6 ሰዎችን በጅምላ መግደል፤
⮚ በአብያተ ክርስቲያናት እና በመስጊዶች ውስጥ የነበሩ የሃይማኖት አገልጋዮችን መግደል፤
⮚ በዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ሟች ጥላሁን ንጉሴ የተባሉ የ68 ዓመት አዛውንትን ጭንቅላቱን በጥይት በመምታት ገድለው ለአምስት ቀናት በቤት ውስጥ ሳይቀበር ሚስቱን ከአስክሬኑ ጋር በዚያው ቤት በማቆየት ለገዳዮች ምግብ እንድታዘጋጅ ማስገደድ፤
⮚ ደባርቅ ወረዳ አብርሃም ቀበሌ ሟች ዘለቀ አስመራ የተባለ አባትን ከህጻን ልጁ ፊት አንገቱን በማረድ ሶስት ልጆቹ እግሩን እና እጁን እዲይዙ በማድረግ ከአንገቱ እስከ ሆዱ በልጆቹ ፊት በሳንጃ አካሉን መሰንጠቅ፤
⮚ የማህበረሰቡ መኖሪያ ቤቶችን የሞቱ የሽብር ቡድኑ አባላትን ለመቅበሪያነት እና ለመጸዳጃ ቤት ለምግብ ማብሰያነት መጠቀም፣ እንዲሁም ቤቶችን በማፍረስ ፤
⮚ ሰዎችን በማገት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም [በዚህም ብዙ ሰዎች እስከ አሁን የደረሱበት አልታወቀም]፤
⮚ በአፋር ክልል የስድስት ወር ህጻን የእናቱን ጡት እንደያዘ በከባድ መሳሪያ ከእነ እናቱ ተመትቶ ተገድሏል፡
⮚ በአፋር ክልል ሙሉ የስደተኛ ጣቢያ ላይ የተጠለሉ ስደተኞች በተኙበት ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ የጅምላ ከባድ ተኩስ በመክፈት በተኙበት እንዲያልቁ አድርገዋል፤
በንብረት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች
⮚ በመንግስት የጤና ተቋማትን መዝረፍ እና ሙሉ በሙሉ በማውድም ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ በወንጀሉ የአስገድዶ መድፈር እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግ፤
⮚ ማህበራዊ አገልገሎት የሚሰጡ ባንኮችን፣የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ፣ የመብራት ኃይል አውታሮች ላይ ዘረፋ እና ጉዳት ማድረስ፤
⮚ አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የግለሰብ ንብረት የሆኑ እንስሶችን በጥይት መግደል በተለይም ለእርሻ አገልግሎት የሚውሉ በሬዎችን እና የጋማ ከብቶችን፣ ለወተት የሚውሉ ላሞችን መግደል እና በራሳቸውም ለሽያጭ እና ለምግብነት የሚውሉ ዶሮዎችን መዝረፍ እና መግደል በአጠቃላይ ማህበረሰቡን ማደህየትን ዓላማ አድርጎ የተፈጸመ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር በተያያዘም ከማህበረሰቡ እሴት እና ሞራል ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ እርጉዝ ላምን ገድሎ ሽሏን በማውጣት ጠብሶ መብላት፤ ያልደረሱ እና ያልበሰሉ አትክልት እና ጥራጥሬን መመገብ፤ በተቆጣጠሩባቸዉ አካባቢዎች የቤት እንስሳትን እና ከብቶችን መግደል፣ በአጠቃላይ የገበሬው ህልውና መሰረት በሆኑት ነገሮች ላይ ፋት በመፈጸም፤
⮚ የገበሬውን አዝመራ አጭዶ መውሰድ አልያም የአትክልት ምርቶችን መንቀል እንዲሁም ለመሰብሰብ ያልደረሰውን ሰብል ማቃጠል እና ምርት እንዳይሰበሰብ በተሸከርካሪ እና በከባድ መሳሪያዎች መዳመጥ፤
⮚ ከጦርነት ቦታዎች በብዙ ኪሎሜትሮች በሚርቁ አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ /የመድፍ/ ጥቃት መፈጸም፤
አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶችን በተመለከተ
⮚ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውሉ መኪኖችን እና ምግቦችን ለጦርነት አላማ ማዋል፤
⮚ ንብረቶቻቸውን መዝረፍ፤ ለአብነት ያህል በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ ንብረትነቱ ዩኤስኤድ/ ኤፍ ኤች ኢትዮጵያ/ የዋጋ ግምቱ 19 539 918.68 ብር የሚያወጡ ለድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎች የሚውል 482.9569 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል፣ የመጋዘን እቃዎች ሞተር ሳይክ፣ መኪኖች እና ሌሎች ንብረቶች ተዘርዋል፤
የእምነት ተቋማትና አምልኮ ስፍራዎችን በተመለከተ
 አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችን ለወታደራዊ ዓላማ ከመጠቀም በተጨማሪ ማቃጠልና ማውደም ለአብነትም በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኙ 22 አብያተ ክርስቲያናትና 1 መስጊድ በከባድ መሳሪያ በመምታት ማውደም፤ ንብረቶቹንም መዝረፍ
 ከሀይማኖታዊ እሴት ያፈነገጠና ነውነኝነትን በሚያሳይ ሁኔታ ለቁርባን የተዘጋጀን እህል በመዝረፍና በመጠቀም ሀይማኖታዊ ተግባርን የማራከስ ድርጊት መፈፀም
በአጠቃላይ ምርመራው በሂደት ላይ ያለ ከመሆኑ አንጻር እስከ አሁን በተደረሰበት ብቻ በሽብር ድርጅቱ እና በአባላቱ በሁለቱም ክልሎች በተፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች 482 ሞት፣ 165 የአካል ጉዳት እና 109 የአስገድዶ መድፈር ኢሰብዓዊ ድርጊቶች የተፈጸሙ ሲሆን ንብረትን በተመለከተ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ንብረት ውድመት እና እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰላማዊ ዜጋ ከቤት ንብረቱ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ ለአብነትም በአፋር ክልል 112,158 ዜጎች ፣ በሰሜን ጎንደር 135,310 ዜጎች እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ከ 47000 በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡

በሌላ በኩል ምርመራው ያልተጠናቀቀ እንደመሆኑ በቀጣይ በተጠቀሱት ቦታዎች የተሰማራው የምርመራ ቡድን የጀመረውን ስራ በማጠናቀቅ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ ለማቅረብ እንዲቻል ስራዎችን አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን ምርመራው ወዳልደረሰባቸው ቦታዎች ጭምር ሌሎች ቡድኖችን በማዋቀር ሰፊ የምርመራ ስራ ማካሄድ እና በየደረጃው ለህዝብ ማሳወቅ የሚሰራበት መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

የአሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸመው ወንጀል ሪፖርት

ፋና ብሮድካስቲንግ ጥቅምት 19/2014 ዓም (ኦክቶበር 29/2021 ዓም)



No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...