===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============
ኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ መስከረም 24/2021 ዓም አዲስ የተመረጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመጀመርያ ስብሰባቸውን ያደርጋሉ።ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሰይማሉ።በምክር ቤቱ የቀደመ አከፋፈት ስነስርዓት መሰረት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጪው ዓመት የመንግስት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ያተኮረ ንግግር ያደርጋሉ።ምክርቤቱን ይከፍታሉ።ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ እንደሚሆን የሚነገርለት የአዲስ መንግስት ይፋ የማድረግ ሂደት ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ስትከተለው የነበረው የጎሳ ፖለቲካ የሚያገነግን የፖለቲካ መስመርን በኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ አሰራር እንደሚቀይር ይጠበቃል።
የመስከረም 24ቱ የምክር ቤቱ የአከፋፈት ስነ ስርዓት የኢትዮጵያን ደረጃ የጠበቀ እና ፍፁም ኢትዮጵያዊ መልክ የሚያንፀባርቅ እንዲሆን ያስፈልጋል።ኢትዮጵያ የራሷ አሻራ የሚያሳዩ ዕሴቶች ከብዙ ቦታ እንዲፋቁ ሲደረጉ ስለኖሩ አሁን እነኝህን ዕሴቶች መልሶ ማምጣት ያስፈልጋል።
ሰኞ የሚከፈተው አዲሱ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አከፋፈት እና የአዲስ መንግስት ይፋ አደራረግ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው የሚከተሉት የአከፋፈት ስነ ስርዓቶች እንዲኖሩት መሻቱ ጥሩ ነው።ይህ የአከፋፈት ስነ ስርዓት በእየዓመቱ የሚከናወን ቢሆን ደግሞ የበለጠ ይሆን ነበር።እነርሱም -
1) ከዘንድሮው መክፈቻ ጀምሮ ምክር ቤቱ በሃይማኖት አባቶች ጸሎት መክፈቱ ተገቢ ነው።ይህ ማለት
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ማዕጠንት እያጠኑ፣ምስባክ ተሰምቶ በመባረክ።
- በኢትዮጵያ እስልምና አባቶች የጸሎት ስነ ስርዓት፣
2) የኢትዮጵያ የጥንቱ እምቢልታ በማሰማት እና ነጋሪት በመጎሰም
3) የኢትዮጵያ የፖሊስ ማርሽ አዳራሹ ገብቶ በሚያሰማው ማርሽ
4) እያንዳንዱ ተመራጭ ስሙን እና የሚወክለውን አካባቢ ስም ብቻ እየጠራ ማስተዋወቅ ቢችል፣
5) ከታዳጊ ወጣቶች አጭር ንግግር በማድረግ ምን እንዲሆን እንደሚፈልጉ እንዲገልጡ ማድረግ የሚሉት በዋናነት የሚወሰዱ ቢሆኑ ያለፈውን እና መጪውን የምናይበት ይሆናል።
በመጨረሻም በዋናነት ከዘጠና በመቶ በላይ የሆነ ህዝቧ በአንድም ሆነ በሌላ በእምነት ውስጥ ያለ ሕዝብ ሀገር ምክር ቤት በፀሎት መጀመሩ ስነ ልቦናዊ ሰላምን ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም የሚሰጥ የራሱ በረከት ያስገኛል።ምክር ቤቱም ዓመቱን ሙሉ በሚያደርገው ስብሰባ የኢትዮጵያን ዕጣ ላይ የሚወስኑ ብዙ ተግባራት ስለሚኖሩ በጸሎት የመክፈት ፋይዳው በቀላል የሚተው አይደለም።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለዓለም የምትተርፍ ያድርግልን።
No comments:
Post a Comment