ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, July 10, 2020

የንፁሃን ደም እና እንባ ይጣራል!ፍጅት የፈፀሙት እና ያስፈፀሙት በሙሉ በልዩ ችሎት ለፍርድ ቀርበው ቅጣታቸውን ሲቀበሉ ሕዝብ መመልከት አለበት።


>> በውጭ ሀገር ኦነግ ሸኔ እና ህወሓትን ደግፎ የሚሰለፍ እጆቹን  በንፁሃን ደም እንደነከረ ሊያውቀው ይገባል።

>> የእዚህ ዓይነት ወንጀል ላይ የሚሰጠው ፍትሕ ትውልድ አስተማሪ መሆን አለበት።ወደፊት የወንጀሉ ታሪክ ሲዘከር፣የተሰጠው ፍርድ ከወንጀሉ ካነሰ የዘላለም ጠባሳ ነው።
=================
በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የአርቲስት ሃጫሉ ግድያ ተከትሎ በኦሮምያ ክልል የደረሰው የዘር ፍጅት እና የንብረት መውደም እጅግ አሰቃቂ ነው።ጥቃቱ ለምሳሌ በአርሲ አምስቱ ዞኖች፣በሻሸመኔ፣አምቦ ጥቃቱን ለመፈፀም የተደረጉ ዝግጅቶች የታዩት ገና ሰኞ ምሽት 3:30 ላይ ሃጫሉ ከመገደሉ በፊት መሆኑ የጉዳዩን ተያያዥነት ያሳያል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።በሰሞኑ በኦሮምያ ብቻ ከ200 በላይ ንፁሃን ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው።

በአርሲ አምስቱ ዞኖች ውስጥ ከተፈፀሙት ወንጀሎች ውስጥ የሁለቱን ማለትም በቀርሳ እና ዴራ ወረዳ የደረሰው ዘርን እና ሃይማኖትን የለየ የዘር ማጥፋት ተግባር በሌሎች ቦታዎች ለተፈፀሙት ማሳያ ነው።የቢቢሲ ዘገባ እንደሚከተለው ይነበባል።

''የቀርሳ ነዋሪ ሦስት የቤተሰቦቻቸውን አባላት ደረሰባቸው ባሉት ጥቃት አጥተዋል። "የአክስቴን ልጅ፣ ልጁንና አማቹ ተገድለዋል" የከፋ ችግር የነበረው በአርሲ ዞን በቀርሳ ሙኔሳ ወረዳ ነበር ያሉት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰብ የደረሰውን ሲገልፁም፤ ሙኔሳ ዳሞት ቅምቢባ የሚባል ገበሬ ማኅበር የጥቃቱ እምብርት ነው ይላሉ።በአካባቢው የሚገኝ ወደ 40 ገበሬ ማኅበር ላይ ጥቃቱ እንደደረሰ መረጃ አለን የሚሉት እኚህ ግለሰብ ግድያና ዘረፋ የተካሄደው ዳሞት ቅምቢባ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው ብለዋል።ጥቃቱ የደረሰው ድምጻዊ ሃጫሉ መገደሉ በተሰማበት ሰኞ ሌሊት መሆኑን የሚገልፁት እኚህ ግለሰብ ጥቃት አድራሾቹ የታጠቁ እንደነበሩ ይናገራሉ።"ፊታቸውን ሸፍነው ነበር፤ የሚፈልጉትን ሰው በስም እየጠሩ በሩን እያንኳኩ ነበር የሚያስወጡት" በማለትም ገጀራ፣ ስለት ያላቸው ነገሮችና ጦር መሳሪያ መያዛቸውን ያስረዳሉ።በዚህ አካባቢ ሰባት ሰዎች በገጀራና በጥይት መገደላቸውን በመግለጽ ሁለት ሰዎች ከባድ መቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው በአሰላ ሆስፒታል እንደሚገኙ ነግረውናል።"ሁለት ሰዎች (ስማቸውን ጠቅሰዋል) ሞተዋል ብለው ጥለዋቸው ሄደው ነው በህይወት የተገኙት" በማለት በአሁኑ ሰአት በአሰላ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል።

በማግስቱ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ፖሊስ መምጣቱንና የሞቱና የቆሰሉትን ሰብስቦና ማኅበረሰቡን አረጋግቶ መሄዱን ያስታውሳሉ። ነገር ግን በስፍራው የፖሊስ ኃይል አለመኖሩን በመገንዘባቸው ጥቃት አድራሾቹ በድጋሚ መምጣታቸውን የሚናገሩት እኚህ ግለሰቡ የአካባቢው ሰው ሸሽቶ ሙኔሳ ገብርኤል ወደሚባል አካባቢ ሄዶ ማደሩን ገልፀዋል።''

በአርሲ ዴራ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ልጃቸውን ያጡት ግለሰብ ልጃቸው ከአዳማ ሊጠይቃቸው የመጣው ሰኞ ዕለት ማታ እንደሆነ ይናገራሉ። ለማክሰኞ አጥብያ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በአካባቢያቸው ረብሻ መከሰቱን ተናግረዋል። ልጃቸው በአጥር ዘሎ ወደ ጎረቤት ጊቢ ሲያመልጥ ከዚያ ጎትተው በማውጣት መንገድ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።400 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤታቸው፣ እስከነ ሰርቪሱ፣ ሱቃቸው እስከነ ሙሉ እቃው መዘረፍ መቃጠሉን እንዲሁም ከብቶቻቸውን መንዳታቸውን ይናገራሉ።ሌላኛው ልጃቸው መፈንከትና ስብራት እንደደረሰበት ገልጸዋል።ግለሰቡ የሚሉት በከተማዋ ላይ በደረሰው የቤት ቃጠሎ ወደ 300 የሚደርሱ ቤቶች መውደማቸውን ገልፀው። በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ይናገራሉ።በከተማዋ የጸጥታ ኃይል ቢኖርም፣ ከአሰተዳደሩ ምንም ዓይነት መፍትሄ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።''

ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ጥቃት መሰረት ያደረገው ከዓማራ እና ጉራጌ ተወላጅ ናችሁ የሚል እና ከኦሮሞም ቢወለዱ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ተከታዮች ናችሁ በሚል ነው።በተመሳሳይ መንገድ በሻሸመኔ፣ባቱ፣አምቦ፣ሐረር እና ሌሎች የኦሮምያ ክልል ቦታዎች ሰሞኑን ጥቃት ተፈፅሞ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል።

በሻሸመኔ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት እና የሽብር ተግባር በተመለከተ ከእዚህ በታች ያለው በጀርመን ድምፅ ራድዮ የተዘገበው እና በአደባባይ ሚድያ የተዘጋጀው ማጠቃለያ የጥፋቱን መጠን ያሳያል። 


የፍትህ ሂደቱ በቶሎ መጀመር፣ በግልጥ ለሕዝብ መታየት እና አስተማሪ መሆን አለበት።

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ከሰሞኑ እየወሰደ ያላቸው ዕርምጃዎች አበረታች እና ሊደገፍ የሚገባው ነው።ክስተቶቹ በሀገር ላይ ሊያመጡ የነበሩት አደጋዎችን ተጋፍጦ የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ በሙሉ ሊያስመሰግነው ይገባል።በእስር ሂደቱ ላይ ከጉዳዩ ጋር ሊገናኙ አይችሉም የተባሉትን ሁሉ ጨምሯል መባሉ መጣራት ያለበት ሁኔታ ነው።በሌላ በኩል ግን  አሁን በሚታየው የኦሮምያ ክልል የመንግስት መዋቅር ውስጥ የፍትህ አካሉም ሆነ ፖሊሱ እምነት የሚጣልበት አይደለም።ከላይ በዘገባው ላይ እንደተገለጠው ፖሊሶች የድርጊቱ ተባባሪ ከመሆን አልፎ ሕዝቡን ለጥቃት ያጋለጡ ሆነዋል።ስለሆነም አሁን ተያዙ የተባሉትም በአካባቢያቸው በቂ የፍትህ ውሳኔ ላያገኙ እና የማድበስበስ ተግባር ሊፈፀም ይችላል።ስለሆነም በወንጀሉ የተሳተፉትን የፍትህ ሂደት በልዩ ሁኔታ በተመሰረተ ችሎት ፍርድ መስጠት ያስፈልጋል።ለድርጊቱ ተባባሪ የሆኑትም ላይ እንዲሁ።

ሕዝብ በማንነቱ ሲገደል፣ንብረቱ ሲወድም እና ሲሰደድ ከደረሰበት በደል በላይ የፍትህ ሂደቱ ኢፍትሓዊ ከሆነ ሌላ በደል ነው።ስለሆነም በመጀመርያ በድርጊቱ የተጠረጠሩት ከተያዙ በኃላ እንዳይለቀቁ በቂ ቁጥጥር ማድረግ፣ በመቀጠል የፍትህ ሂደቱ ግልጥ እና አስተማሪ የሆነ (በወንጀሉ መተባበራቸው ለተረጋገጠባቸው እስከ የሞት ቅጣት የሚደርስ ፍርድ) ከፍትሕ ሰጪው አካል ሕዝብ ይጠብቃል።የእዚህ ዓይነት ወንጀል ላይ የሚሰጠው ፍትሕ ትውልድ አስተማሪ መሆን አለበት።ወደፊት የወንጀሉ ታሪክ ሲዘከር፣የተሰጠው ፍርድ ከወንጀሉ ካነሰ የዘላለም ጠባሳ ነው።

ለማጠቃለል የሰሞኑ የግፍ ተግባሮችም ሆኑ የቀደሙት ግድያዎች ሁሉ የአንድ ሰሞን ሥራ አይደሉም።ህወሓት/ኢሕአዴግ የዘራው የጥላቻ ዘር፣አክራሪ ኃይሎችን ወደ ስልጣን የማምጣት ደካማ አሰራር፣የፀጥታ ኃይሉን በሚገባ በአካባቢ ደረጃ አለማደራጀት፣ወደ መቀሌ የሸሸው ህወሓት ስውር እጅ ከኦነግ ሸኔ ጋር እና ከፅንፍ አክትቪስቶች ጋር በጥምረት የቀሰቀሱት ቅስቀሳ ሁሉ ውጤት ነው። በመሆኑም የፍትሕ ሂደቱ ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ሀገር በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በሙሉ የሚመለከት መሆን አለበት። በውጭ ሀገር ኦነግ ሸኔ እና ህወሓትን ደግፎ የሚሰለፍ እጆቹን  በንፁሃን ደም እንደነከረ ሊያውቀው ይገባል።

========/////===========


No comments: