ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 20, 2020

እስክንድር ነጋ 'የመልክዓ' እስክንድር ደጋሚዎችን አያደንቅም

 እስክንድር ነጋ 
  
ለአስራ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ከአስተዳደረው የደርግ ስርዓት በኃላ በኢትዮጵያ የሕትመት ገበያ ውስጥ የአራት ኪሎን ቤተመንግስት የሚያንቀጠቅጥ የኅትመት ውጤቶች ውስጥ  የእስክንድር ነጋ  ኢትዮጲስ ጋዜጣ አንዷ ነበረች።በእየሳምንቱ ጋዜጣዋ ይዛ የምትወጣው ዜና ለሕወሃት/ኢህአዴግ መንግስት አዳዲስ አጀንዳ መፍጠር ችላ ነበር።የጋዜጣዋ የመጀመርያ አዘጋጆች የነበሩት ተፈራ አስማረና ጋዜጠኛ ወርቁ አለማየሁ ነበሩ።በተለይ የተፈራ አስማረ በአንድ ወቅት ''ጎንደር ጦርነት አለ'' የሚለው ከፊት ገፅ የወጣው ዜና ህወሓትን የማበድ ያህል ወሰድ አድርጎ የመለሳት ርዕስ ነበር።ጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ጎንደር በወቅቱ የነበረውን ጦርነት የሚያሳይ ማስረጃ ይዞ ፍርድ ቤት ቢቀርብም ማዕከላዊ ከመውረድ ግን አላዳነውም።በቀጣይ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም በሚፅፋቸው ቱባ ቱባ አራት ኪሎ አንቀጥቅጥ ፅሁፎች ህወሓት/ኢህአዴግንም ሆነ አቶ መለስን እረፍት አሳጣቸው። ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የጋዜጠኛ እስክንድር አጀንዳ ለቤተ መንግስቱ የመስጠት አቅሙን አቶ መለስም ሆኑ አቶ በረከት ስላልቻሉት ነበር። 

እስክንድር ከሁለት ዓመት ወዲህ በመጣው ለውጥ በተለይ ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዞ የፅንፍ ኃይሎች እንቅስቃሴ በመሞገት፣በመቃወም እና ባላሰቡት መንገድ አጀንዳ በመስጠት  አሁንም ባለው የፖለቲካ መንደር ውስጥ የሚፈሩት አይደለም ማለት አይቻልም።እስክንድር አጅንዳ መስጠት ከፈለገ የትም ቦታ በመሄድ አጀንዳ መስጠት ይችላል።ድንገት ተነስቶ ስታድዮም መግባት ብቻ ፖሊስ እንዲሰጋ እና የሚያደርገው እንዲያጣ ማድረግ ይችላል። ስታድዮም በሩ ላይ ሲደርስ ፖሊሶች አናስገባው እናስገባው እያሉ ሲወዛገቡ እርሱ በሩን አልፎ ሊገባ ወደፊት እየተራመደ ነበር። ሲያስቡት ስታድዮም ገብቶ በመቀመጡ ብቻ ትልቅ አጀንዳ እንደሚሆን ፈሩ እና ከለከሉት።እስክንድር  የካራማራ ድል ድንገት ብቅ ብሎ አበባ በማስቀመጥ ሊያስጨቅ ይችላል።በእነኝህ  ሁሉ ሒደቶች፣ እስክንድር አጀንዳ በመፍጠር ወደ የሚፈልገው የፖለቲካ ግብ መድረስ የሚችል ነው። በፖለቲካ ውስጥ አጀንዳ ተቀባይ ከሆንክ ምንም አቅም የለህም።አጀንዳ ሰጪ ከሆንክ ግን እያጠቃህ ነው ማለት ነው። እስክንድር በዘመነ ህወሓት/ ኢህአዴግ በእስር ቤት በመግባቱ ብቻ ለስርዓቱ ቢያንስ በየስድስት ወሩ አጀንዳ ሰጥቶ እረፍት ነስቷል።ዓለም አቀፍ የሽልማት መዥጎድጎድ  እና እስክንድር የበለጠ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱ በራሱ የማይጋፉት እና የማይመልሱት አጀንዳ ነበር።

እስክንድር እውቅና ያልሰጣቸው የመልክዓ እስክንድር ነጋ ደጋሚዎች

እስክንድር የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ አይደለም።እስክንድር ኢትዮጵያ 'ፓትርዮት' የምትለው ሰው ነው።ከሀገረ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በሀገር ፍቅር ስሜት እንጂ በጎሳዊ ፖለቲካዊ ቅኝት አይደለም።በተለያየ ጊዜ በሰጣቸው መግለጫዎች እና ዓለም አቀፍ ሽልማቶቹ ሁሉ በጎሳዊ ፖለቲካ አራማጅነት አይደለም።አዲስ አበባን በተመለከተ የሚያንፀባርቀው የፖለቲካ መንገድ በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ በሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆች ላይ የፅንፍ አስተሳሰብ የሚያራምዱ አካሎች ግፊት ውጤት ነው።በእዚህ ግፊት ላይ እስክንድር የበለጠ አዲስ አበቤያዊ ስሜቱን አንሮት ህዝቡ እራሱን ለአከላከል መውሰድ ያለበት እርምጃ ያላቸውን አንፀባርቆ ይሆናል። ስለ አዲስ አበባ መቆም ለብሄር ፖለቲካ መቆም አይደለም።አዲስ አበባ አንድ ወጥ ጎሳ የላትም።ለአዲስ አበባ ስትቆም ለሽሮ ሜዳ ሰፈር የወላይታ እና ዶርዜን፣ተክለሃይማኖት ሰፈር ያሉ የአክሱም ተወላጆችን፣መርካቶ የሚወጡ የሚወርዱ የጉራጌ ማኅበርሰብ አባላትን  እና ሌሎችንም የመወከል ሁሉ ሂደት ነው።አዲስ አበባ የሁሉም ብሔር ሀገር መሆኗን አምኖ እስክንድር የአዲስ አበባን ጉዳይ አደባባይ ይዞ ብቅ እንዳለ መጠራጠር አይገባም።

እስክንድር በቅርቡ የድምፃዊ ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ ተመልሶ ለእስር መዳረጉን መንግስት መግለጡ ይታወቃል።እስሩ በተለይ የፅንፍ ኃይሎች በአዲስ አበባ ላይ የድምፃዊ ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ ሊከሰት የነበረው ጥቃት አንፃር እስክንድር እንደግጭት ፈጣሪ ሆኖ የቀረበበት  ጉዳይ ነው።ዝርዝር ጉዳዩን ለሕግ ባለሙያዎች እንተወው እና ሕጉ ሌሎችን ሊያጠቁ በመንቀሳቀስ እና ስፍራን ሳይለቁ ከተማን ለመከላከል መንቀሳቀስ መሃል በሚለው ልዩነት መሃል የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት እንዳለው ማወቅ ቀላል ነው።

የእስክንድር ጉዳይ ከአዲስ አበባ በላይ  የፖለቲካ ንግድ  ማጧጧፍያ እና መተዳደርያ የሆነው ግን በሀገረ አሜሪካ ነው።እዝያ እራሱ እስክንድር የማይቀበለው ብቻ ሳይሆን  አንገብጋቢው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ የፅንፈኞች እንቅስቃሴ መግታት ነው ወይንስ እስክንድር በተመለከተ ከጧት እስከ ማታ አጀንዳ ማድረግ የቱን ታስቀድማለህ? ተብሎ እስክንድር ቢጠየቅ የሚሰጠው መልስ  የኢትዮጵያ ጉዳይ ቅድምያ ማግኘት አለበት ነው።ይህ የእስክንድርን ስብዕናም ሆነ ልዕልና ዝቅ የሚያደርግ አይደለም። ይልቁንም አስተዋይነት የሚለካበት ነው።እስክንድር ከእርሱ አስተሳሰብ እና ፍላጎት በላይ የእስክንድር መልክዓ  በመድገም የራሳቸውን ዝና ለመገንባት የሚፈልጉትን ይፀየፋቸዋል።እስክንድር አንገታቸውን በካራ ከተቆረጡት ጋር እኩል አድርጉኝ አላለም።እስክንድር ቤታቸው ከጋየባቸው እና መድረሻ ካጡ ወገኖች እኩል ተንከባከቡኝ አላለም። እስክንድርም የሚፀየፈው  የዲሞክራሲን የበላይነት ትቶ የመልክዓ እስክንድር ነጋ ደጋሚዎችን ነው።

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)