አቶ ኢሳያስ እና አልሲሲ በካይሮ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ
በእዚህ ፅሁፍ ስር -
>> በምዕራባውያንም ሆነ በግብፅ ትንተና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሸንፈው ወጥተዋል።
>> አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ባሳለፍነው ሳምንት በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ምንነት።
>> ነፍሰ ጡር በምጧ ጊዜ እንድትጨነቅ ሁሉ ኢትዮጵያም የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥራ ለመጣል የመጨረሻ የመገላገያ ጊዜዋ
ላይ ነች የሚሉ ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ።
ከልክ ያለፈው ትዕግስት
ከ1983 ዓም በፊትም ሆነ በኃላ ብዙዎቹ የጮሁለት፣የተሰደዱለት እና የሞቱለት ኢትዮጵያን ከከፋፋይ እና የእልቂት የጎሳ ፖለቲካ የማላቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ትግል ተጀምሯል።ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ሁሉን አቃፊ ሆኖ ሰንብቷል።የኦነግ ዓርማ በአዲስ አበባ ሲውለበለብ እና የጎሳ ፖለቲካ ሲሰበክ እንዲሁም ሚድያዎች በአዲስ አበባ ቢሮ ከፍተው በግልጥ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ሲሳደቡ በትግስት ታልፏል።በቦሌ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው አዲስ አበባ እና ሐዋሳ ላይ መከፋፈልን በአደባባይ የሰበኩ፣በሕዝቡ ላይ የዛቱ ለወራት ዝም ተብለው ሰንብተዋል።
ይህ ሁሉ የፈለጉትን የመሆን መብት ግን በራሱ ገደብ አለፈ።ጀዋር መሐመድ ከበቀለ ገርባ ጋር እንዲሁም ልደቱ አያሌው ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በዓደባባይ መንግስት ከመስከረም 30 በኃላ አይኖርም ማለት ጀመሩ።ይህ አባባል ቀደም ተብሎ ''ሁለት መንግስት ነው እዚህ ሀገር ያለው'' በማለት ጀዋር ደጋግሞ ከተናገረ በኃላ መሆኑ ነው።ቀደም ብሎ ብዙ ነገሮችን ሲያስታምም እና ሕግ ባለማስከበሩ በከፍተኛ ደረጃ የተወቀሰው መንግስት ከመስከረም 30 በኃላ አናውቀውም የሚል ንግግር ሲነገር፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መንግስት ትዕግስቱ እያለቀ መሆኑን በመግለጥ ማስጠንቀቅያ ሰጡ።ሆኖም ከቃላት ዝልፍያ የተጀመረው መንግስትን አናውቅም ስድብ ወደ መሬት የወረደ የሴራ ፖለቲካ ተሸጋግሮ አንድ አመፅ ለማቀጣጠል የሚረዳ አንዳች ምክንያት (Immediate Cause) መፈለግ ተያዘ።ለእዚህም ጉዳይ የድምፃዊ ሃጫሉ ሞት ተመረጠ።ስለሆነም የዛሬ ሳምንት ሰኞ ሰኔ 22/2012 ዓም አዲስ አበባ ላይ ተገደለ።በደቂቃዎች ውስጥ ኦኤምኤን እና የህወሓት ሚድያዎች የጎሳ ግጭት የሚያስነሱ የቅስቀሳ ዘገባዎች ጀመሩ።
በምዕራባውያንም ሆነ በግብፅ ትንተና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሸንፈው ወጥተዋል
የለውጡ ሂደትን በአንክሮ የሚከታተሉ የምዕራባውያንም ሆኑ የኢትዮጵያ ባላንጣ ግብፅ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ልደናቀፍ የሚችልባቸው ሶስት ምክንያቶች ይኖራሉ ብለው ያስቡ ነበር።እነርሱም -
የመጀመርያው ምክንያት፣ የጦር ኃይሉ በዋናነት በህወሓት አፍቃሪ መኮንኖች የተሞላ ስለሆነ በቀላሉ የጦር ኃይሉን ሊቆጣጠሩ አይችሉም የሚል ግምት ነበር።ሆኖም ግን ይህ ግምት ስህተት መሆኑ ለመጀመርያ ጊዜ ምልክት በማሳየት የታወቀው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ጋር በቤተ መንግስት የጦሩን ኤታማጆር ጀነራል ሳሞራን በክብር ጠርተው እና ሸልመው ሲያሰናብቱ እና በደህንነት መስርያ ቤቱ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ እየመጣ መሆኑ ሲነገር ነበር።
በሁለተኛ ደረጃ የምዕራባውያንም ሆነ የግብፅ የለውጡ ሂደት ድልድዩን አይሻገርም የሚለው ግምት እና ጥርጣሬ የራሱ የኢሕአዴግ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚል ሲሆን በአጭር ጊዜ ግንባሩ ሊከስም ስለማይችል ኢትዮጵያ ትከፋፈላለች የሚል ዕሳቤ ነበር።በእርግጥም በወቅቱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት ለሚከታተል ሰው ትልቅ ፈተና እና መውጭያ መንገዱም ድቅድቅ ጨለማ ይመስል ነበር።ለእዚህ መንገድ ግን ቀድመው አቅደው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በለውጡ ሰሞን በሐዋሳ በተደረገው የኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ እንደዋዛ ወደ ጉባኤው ማብቅያ ላይ አንዲት ነገር ጣል አደረጉ።ይሄውም ጉባኤው ኢህአዴግ ወደ አንድ የፖለቲካ ኃይል የሚቀየርበትን ሂደት (ከእዚህ በፊትም ተነስቶ ስለነበር) አጥንቶ ለማቅረብ ስልጣን እንዲሰጠው የሚጠይቅ ነበር።እንደዋዛ ቀለል አድርገው ያነሱትን ነገር ጉባኤው በጭብጨባ ተቀበለ። በእዚህ መሰረት ኢህአዴግ ከስሞ ብልፅግና ተመስርቶ ቀድሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሂደት ላይ ፖሊሲ የማውጣት ዕድል ያልነበራቸው ክልሎች እንደ አፋር፣ቤንሻንጉል፣ሱማሌ እና ጋምቤላ በብልፅግና ፓርቲ በአንድ ግንባር ተሰባሰቡ።ይህ ለኢትዮጵያ አንድነት ከሰላሳ ዓመታት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ አንዱ እና ዓይነተኛ መሰረት የጣለ ሂደት ሆኗል።በእዚህም የምዕራባውያንም ሆነ የግብፅ ግምት ትክክል አለመሆኑን አመኑ።
ሶስተኛው እና የመጨረሻው ጉዳይ በኦሮሞ የፅንፍ ኃይሎች በተለይ በጀዋር እና መሰሎቹ ዙርያ ያለው የኃይል ሚዛን መንግስትን የሚገዳደር ባይሆን አመፅ የመፍጠር እና ወደ አደገኛ መስመር ኢትዮጵያን የመምራት አደጋ አለው።በእዚህ ሳብያ የለውጡ ሂደት ይደናቀፋል የሚል ግምት ነበር።ይህንን ሃሳብ ብዙዎች በስጋት የሚመለከቱት እና ኢትዮጵያን ወደ አላስፈላጊ ኪሳራ እንዳይከት በማለት መንግስት በቶሎ ነገሮችን ማስተካከል እንዳለበት ሲወተውቱ ነበር።ይህ ጉዳይ ግን የድምፃዊ ሃጫሉን የግፍ ግድያ ተከትሎ በተነሳ ግጭት መንግስት ሕግ ለማስከበር በአዲስ መንፈስ እንዲነሳ እና ለሕዝቡም ቃል እንዲገባ ምክንያት ሆነ።በእዚህም መሰረት ጀዋር እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካቶች በአመፅ ሂደት እና ሴራ ውስጥ ገብተው አግኝቻቸዋለሁ ያላቸውን በቁጥጥር ስር አዋላቸው።እስሩን ተከትሎ በበርካታ የኦሮምያ ክልሎች የኦሮሞ የፅንፍ ፖለቲካ አራማጆች በንፁሃን ላይ የግፍ ጥፋት ቢያደርሱም መንግስት እንደመንግስት ግን ሁኔታዎችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ እየወሰደ ያለው እርምጃ በራሱ በጣም አበረታች ነው።በእዚህም የምዕራባውያን እና የግብፅ የኢትዮጵያ ለውጥ ሊደናቀፍ ይችላል ያሉት ጉዳይ በመንግስት የበላይነት ቁጥጥር ስር መዋሉ የለውጡ ሂደት በሚገባ እየሄደ ለመሆኑ የማረጋገጫ ማሕተም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ቀደም ብሎ በሱዳን ባሳለፍነው ሳምንት በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ምንነት።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ ከሳምንት በፊት ሱዳንን፣ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ ግብፅን ጎብኝተዋል።የአቶ ኢሳያስ ጉብኝት በኤርትራ ዜና ማሰራጫዎች እንደተገለጠው በሁለቱ ማለትም ኤርትራ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር ያላት ግንኙነት ዙርያ ተወያዩ ከማለት በቀር ዝርዝር ጉዳይ ያወሩት የለም።በኤርትራ የሚድያ ነፃነት ካለመኖሩ አንፃር ከእዚህ የበለጠ ሊያወሩ አይችሉም።ሚድያዎቹ አይደሉም በአቶ ኢሳያስ የስልጣን ወንበር ላይ ያሉም ዝርዝሩን የማወቅ እድሉ አይኖራቸውም።አቶ ኢሳያስ በሚያደርጉት ጉብኝት ረዳታቸውን አቶ የማነን አስከትለው እንጂ ሌሎች ሚኒስትሮችን አስከትለው አይሄዱም።ሌሎቹን ጉዳዮች አቶ ኢሳያስ ከጉብኝት ወደ አስመራ ሲመጡ መጥነው እስክነግሯቸው መጠበቅ አለባቸው።
የአቶ ኢሳያስ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ግብፅ ያደረጉት ጉብኝት በኤርትራ በኩል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳለህ፣ አቶ የማነ ገብረአብ እና አምባሳደር ፋሲል ገብረስላሴ የተገኙ ሲሆን በግብፅ በኩል ደግሞ የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሽኩሪ፣ የደህንነት ሚኒስትሩ አባስ ከማል እና የእርሻ ሚኒስትሩ መሐመድ ማርዙቅ ተገኝተዋል።የአቶ ኢሳያስ በሱዳንም ሆነ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ዓላማዎች ሁለት ናቸው።
የመጀመርያው ዓላማ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ወገን ወግና በግብፅ እና በሱዳን ላይ እያሴረች አለመሆኗን እና እንደ ገለልተኛ ሀገር እንድትታይ ለማድረግ ነው። አቶ ኢሳያስ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት መቀራረብ በግብፅ እና በሱዳን ዘንድ የተገለሉ እንዳይሆኑ ይፈልጋሉ።ስለሆነም አንድ ዓይነት የዲፕሎማሲ ሥራ ማድረግ ነበረባቸው።
ሁለተኛው ዓላማ፣ የግድቡ ጉዳይ የአካባቢው ሀገሮችን የትብብር ዕቅድ እንዳያሰናክል ጉዳዩን ማለሳለስ ነው።እዚህ ላይ አቶ ኢሳያስ አሳማኝ ነጥቦችን ይዘው ካልሄዱ በግድቡ ጉዳይ ያለውን ውጥረት ማለሳለስ አይችሉም።ስለሆነም ሁለት ነጥቦችን ይዘው ነው ወደ ሱዳን እና ግብፅ የሄዱት።አንዱ ለአካባቢው ዋና ስጋት የህወሓት የታጠቀ ኃይል መኖሩ መሆኑን ማስረዳት ሲሆን ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን በሚገባ አልተረዳችሁትም፣እርሱ ፈፅሞ ግብፅን እና ሱዳንን የሚጎዳ ሥራ አይሰራም።ይልቁንም እርሱ እስካለ ድረስ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ማተኮሩ የተሻለ ነው የሚሉ ሃሳቦች ናቸው።እነኝህ ሃሳቦች ከኤርትራ መምጣታቸው ግብፅን በተወሰነ ደረጃ አያሳምንም ማለት አይቻልም።ባያሳምናትም አሁን ባለችበት ደረጃ ምንም ልታደርግ አትችልም። ሆኖም አቶ ኢሳያስን ''አንተ ካልክ'' በሚል ከኤርትራ ጋር ወዳጅነቷን ለማቆየት ትጠቀምበታለች።አቶ ኢሳያስ ግብፅን ከአልሲስ በላይ ያውቃሉ።የሻብያ እንቅስቃሴ ዋና መነሻ ካፒታል የተፈጠረባት ሃገርን ሊረሱ አይችሉም።በመሆኑም የግብፁን ፕሬዝዳንት በአካባቢው ለረጅም ጊዜ እንደቆየ ሽማግሌ መሪ ፕሬዝዳንት አልሲስን ቆጣ እያሉ እንዴት ነው ዓብይን የማትረዳው? ቢሉ ላያንስባቸው ይችላል።
ይህ በእንዲህ እያለ ግብፅ የኢትዮጵያን የመልማት እና የመብራት የማግኘት መብት በማይቃረን መልኩ አዲስ የስምምነት ፕሮፖዛል አለኝ ማለት መሰማቱ ቀድሞም በውስጥ ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ ከመሞከር በላይ ምንም ልታደርግ ያልቻለችው ግብፅ የአቶ ኢሳያስ ጉብኝትን እንደ አንድ ምክንያት ልትጠቀምበት ትችላለች።ግብፅ ከሰሞኑ በዓባይ ጉዳይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ልትለሳለስ ትችላለች።የምትለሳለሰው ግን በአቶ ኢሳያስ ጉብኝት አይደለም።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እና የለውጥ ኃይሉ ለለውጥ ሂደቱ ስጋት የነበረውን የመጨረሻውን የኃይል ሚዛን በአሸናፊነት ስለተወጣው ነው።
ነፍሰ ጡር በምጧ ጊዜ እንድትጨነቅ ሁሉ ኢትዮጵያም የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥራ ለመጣል የመጨረሻ የመገላገያ ጊዜ ላይ ደርሳለች
ባጠቃላይ አሁን በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ወደ የከፋ መስመር የሄደ ቢመስላቸውም ዕውነታው ግን ተቃራኒ ነው። በእርግጥ ነው ብዙዎች በፅንፈኛ የኦሮሞ አክራሪዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣የንግድ ቤታቸው እና መኖርያቸው ወድሟል።ሆኖም ግን ነፍሰ ጡር በምጧ ጊዜ እንድትጨነቅ ሁሉ ኢትዮጵያም የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥራ ለመጣል የመጨረሻ የመገላገያ ጊዜዋ ላይ ነች። ስለሆነም ህመም አለው።ህመሙ ግን የአጭር ጊዜ ህመም ነው።ተመልሳ ወደ የጎሳ ፖለቲካ የማትገባበትን የጋራ ቃል ኪዳን የምታፀናበት ብሩህ ጊዜም እየመጣ ነው።መታመማችን ለበጎ ነው።ጎሰኘነትን መልሶ የሚጭን የፖለቲካ ስርዓት ፈፅሞ የማይሸከም ሀገር እና ሕዝብ ከእዚህ ሁሉ ፈተና መሃል ጠንክሮ ይወጣል።
ጉዳያችን
No comments:
Post a Comment