ጉዳያችን/Gudayachn
የሸዋው ንጉስ ኃይለመለኮት በ1855 ዓም እአአቆጣጠር ከሞቱ በኃላ የሸዋ ሰራዊት በዳግማዊ ቴዎድሮስ ድል ሲሆን የንጉሥ ኃይለመለኮት ልጅ የ11 ዓመቱ ልዑል ሣህለ ማርያም በመያዣነት ወደ ጎንደር በቤተ መንግስት እንዲያድግ ተወሰደ።ታዳጊው ወጣት ሳህለ ማርያም በቤተ መንግስቱ በሚደረጉ ማናቸውም ውድድሮች ሁሉ የላቀ ወታደራዊ ተሰጥኦ እያሳየ እና ሁሉን እያስደመመ እንደ ቤተሰብ አብሮ አደገ።በመቀጠል አፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን ልዕልት አልጣሽን ዳሩለት።ይህ ሁሉ ሲሆን አፄ ቴዎድሮስ ከልዑሉ ጋር አብረው የመጡትን የሸዋ ጎበዛዝት እንዳይለዩት አድርገው ነበር።
እየቆየ ግን በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የሚሸፍተው በዛ በእዚህ ጊዜ ሸዋም ማጉረምረሙ ተሰማ።አፄ ቴዎድሮስ ስለሰጉ ልዑል ሳህለ ማርያም መቅደላ ላይ የቁም እስረኛ እንዲሆን ተወሰነ።ሆኖም ልዑሉ አብረውት ካሉት የሸዋ ጎበዛዝት ጋር እንዴት እንደሚያመልጥ ሲያሰላስል አፄ ቴዎድሮስ ላይ ያቄመችው የወሎ ገዢዋ ልዕልት ወርቂት ከመቅደላ እንዲያመልጥ ልዑሉን እረዳችው እና አመለጠ።አምልጦም ወደ ሸዋ ገሰገሰ።ወደ ሸዋ ሲሄድ በአፄ ቴዎድሮስ ሸዋ እንዲገዛ የተሾመው በዛብህ ጋዲሎ መንገድ ለመዝጋት ቢሞክርም ልዑሉ ከወሎ ከልዕልት ወርቂት ያገኘው ሸኚ ሰራዊት እና ሸዋ ከገባ በኃላ አልጋ ወራሽነቱን አምኖ የከተተው ሕዝብ ጋር ልዑሉን የምቃወመው አልተገኘም።
ልዑሉ ከድሉ በኃላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1865 ዓም ምኒልክ ንጉሰ ሸዋ ተብለው ነገሱ።ከቴዎድሮስ በኃላ የነገሱት አፄ ዮሐንስ የምንሊክን ንጉሰ ሸዋነት ያፀደቁት በ12ኛው ዓመት በአዋጅ ''ልጅ ምኒልክን የሸዋ ንጉስ አድርጌ አንግሸዋለሁ።እሱንም እንደኔ ልታከብሩት ይገባል'' በሚል ቃል ነበር።
ምንሊክ በሸዋ ላይ ቢነግሱም ሀሳባቸው ሩቅ፣መንገዳቸው ረጅም እንደሆነ አውቀዋል።ምንሊክ ለነገሮች የማይቸኩሉ ነገር ግን ስልት አዋቂ ነበሩ።የአፄ ዮሐንስ መንገስ አላስበረገጋቸውም።ይልቁንም በሰላም ንግስናቸውን ሳይጣሉ እርሳቸው የሩቅ ዓላማቸው የሆነውን ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ግብ ይዘው ተንቀሳቀሱ።ለእዚህ ሃሳብ ከቤተ መንግስት ስርዓት እስከ አውሮፓውያን ጋር የሚደረጉ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች በአፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግስት የተመለከቱት ሁሉ ትምህርት ሆኗቸዋል።ስለሆነም ብዙ ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ሲሞክሩ የማይሆነውን ደግሞ በጦር ይፈቱት ነበር።
ንጉስ ምንሊክ የኢትዮጵያ ንጉስ ከመሆናቸው በፊት ካደረጉት ትልቁ ጦርነት ወደ ሐረር የተደረገው ዘመቻ ነው።ከእዚህ ዘመቻ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ግብፆችን ከሐረር ሲወጡ አብዱላሂ ሐረርን እንዲገዛ አመቻችተውለት ነበር።እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥር 6/1887 ዓም ከእንጦጦ የተነሳው የምንሊክ ጦር ሐረር ግብቶ ከተማዋን አረጋጋት።በመቀጠል ወሎን ካስገበሩ በኃላ የአፄ ዮሐንስ በደርቡሾች መገደል ከተሰማ በኃላ ነው ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሱት።
በአፄ ምንሊክ ንግስና ወቅት የኢትዮጵያ ዙርያ ገባ ምን ይመስላል?
አፄ ምንሊክ ከንግስናቸው በፊትም ሆነ በኃላ የሀገር ውስጥን ብቻ ሳይሆን የውጭውን ፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ መረጃ ይሰበስቡ ነበር።ወቅቱ ጀርመን በርሊን ኮንፍረንስ በመባል የሚታወቀው የቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ውል የተዋዋሉበት፣ፈረንሳይ በጅቡቲ፣እንግሊዝ በሱዳን በኬንያ እና በሱማሌ ላንድ በኩል ጣልያን በሰሜን ኤርትራ በኩል ሰፍረው ኢትዮጵያን ቀለበት ያስገቡበት ወቅት ነበር።ስለሆነም ንጉስ ምንሊክ የፀጥታ ዞናቸውን ማስፋት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነኝህ ቅኝ ገዢዎች እጅ እንዳይወድቅ በዘመነ መሳፍንት የተከፋፈለውን ሀገር ወደ አንድ ንጉሰ ነገስት ግዛት ማምጣት ነበረባቸው።ስለሆነም ከሐረር ዘመቻ ጀምሮ ወደተቀሩት ደቡባዊ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል እየዘመቱ በኢትዮጵያ ስር መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው።
አፄ ምንሊክ ፈድራልዝምን አስተዋውቀዋል።
በኢትዮጵያ ንጉሳዊ አስተዳደር ውስጥ በቀጥታ ከንጉሡ ተሹመው የሚሄዱ ሃገረ ገዢዎች የመኖራቸውን ያህል የሀገሩ ገዢዎች በዓመት ግብር ለንጉሡ እየላኩ የቀረው የውስጥ አስተዳደሩን ግን በራሳቸው ገዢዎች የሚተዳደሩ አያሌ ነበሩ።ከእነኝህ ውስጥ በምሳሌነት የጅማውን አባ ጅፋር ማንሳት ይቻላል።አባ ጅፋር የጅማው ገዢ ሲሆኑ በውስጥ አስተዳደራቸው ውስጥ የአፄ ምንሊክ መንግስት ገብቶ አይፈተፍትም ጥፋት ሲኖር ንጉሡ መልክተኛ ወይንም ደብዳቤ እየላኩ ምክር ይለግሱ ነበር።ለምሳሌ በባርያ ንግድ ላይ አባ ጅፋር መሳተፋቸውን የሰሙት ንጉስ ምንሊክ ይህንን እንዲተዉ የሚመክር ደብዳቤ ልከው ነበር።ከእዚህ ውጭ አባ ጅፋር በዓመት የሚላክ ግብር ከማስገባት እና የንጉሰ ነገሥቱን የኢትዮጵያ ንጉስነት እስካወቁ ድረስ ሌላ አስገዳጅ ተግባር የለባቸውም።ይህንን ወደ ዘመናዊ የፈድራል አስተዳደር ስንመነዝረው ብዙ እርቀት የሄደ አሰራር ሆኖ እናገኘዋለን።
በዳግማዊ ምንሊክ ላይ የተከፈተው የፅንፈኞች ዘመቻ ምስጢር
አሁን ባለንበት ዘመን በዳግማዊ ምንሊክ ላይ የተከፈቱ የማጥላላት ዘመቻዎች በተለይ በሶስት አካላት ማለትም ከኦሮሞ ብሔር እንደወጡ ከሚናገሩ፣ ከፅንፈኛው የእስልምና አራማጆች እና ከጀርባ አቀንቃኞች በኩል ደጋግሞ ይሰማል።ለእዚህ ማጥላላት ምስጢሩ ግልፅ ነው።
1) ከኦሮሞ ብሔር እንደወጡ ከሚናገሩት
ዳግማዊ ምንሊክ በዓማራው ብሔር ከሚታወቁት እና ከታቀፉበት የረጅም ጊዜ የስልጣን ዘመን አንፃር ስናይ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ያላቸው ገናና ስም እና ክብር ይበልጣል።ምናልባት ይህንን በኢህአዴግ ዘመን ለተወለዱ ልጆች አይረዱት ይሆናል።እውነታው ግን ይሄው ነው።አፄ ምንሊክን እምዬ ምንሊክ ብለው ስም ያወጡላቸው የአዲስ ዓለም ኦሮሞዎች ናቸው እንጂ የአማራ ብሔር ተወላጆች አይደሉም።እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በምንሊክ ስም የሚምሉ የኦሮሞ አባቶች ከአምቦ እስከ ሐረር ብትሄዱ ታገኛላችሁ።በሂደት ደርግ ያለፈው ስርዓት በሚል ኢህአዴግ/ህወሓት የነፍጠኛ ስርዓት እያለ በኢትዮጵያ የቅርቦቹ መስራች አባቶች ላይ የከፈቱት ዘመቻ የኢትዮጵያን አባቶች ክብር እና ዝና ለመሸፈን ብዙ ደክሟል።
ከኦሮሞ ብሔር እንደወጡ የሚናገሩት የዘመኑ የኢህአዴግ/ህወሓት ትውልዶች አፄ ምንሊክን ለማጥላላት የሚሞክሩበት ዋናው ምስጢር ዳግማዊ ምንሊክ ቀድሞ የነበረውን በኦሮሞ እና በሌላው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማለትም ከደቡብ፣ከሱማሌ እና ከአማራ ጋር የነበሩ የጠበቁ ማኅበራዊ፣ደማዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት መልሶ እንደብረት የጠነከረ እንዲሆን ያደርጉ በመሆናቸው ነው።ምንሊክ ከጦር ሹማምንቶቻቸው እስከ እንደራሴዎች፣ከአድዋ ዘመቻ እስከ ሐረር ዘመቻ ኦሮሞ ያልተሳተፈበት ትግል አላደረጉም። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ በፍፁም መከባበር፣ኢትዮጵያዊ ስሜት እና አለአንዳች አድልዎ ነበር። ይህ ትስስር በአሁኑ ዘመን ያሉ የብሔር አቀንቃኞች እና ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ለመለየት የሚፈልጉ ፅንፈኞች አልተመቻቸውም።ስለሆነም ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ደግም እንዲዋሃድ ያደረገውን የ19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን ንጉስ ዳግማዊ ምንሊክን ከሕዝቡ ልቦና ለማውጣት እየደከሙ ይገኛሉ።
2) የፅንፈኛ እስልምና አራማጆች ናቸው።
እስልምና በራሱ ፅንፈኛ አይደለም።ነገር ግን በማንኛውም ሃይማኖት ማለትም በክርስትና እና ሌሎች ውስጥ እንዳለው ሁሉ በእስልምና ስም የፅንፍ ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች በኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃም ይንቀሳቀሳሉ። በኢትዮጵያ ያለው ይህ ኃይል የኢትዮጵያ መከፋፈል ለዓላማው እንደምረዳው ያስባል።ስለሆንም በዋናነት የኢትዮጵያ መስራች አባቶችን የማጥላላት እና ኢትዮጵያ አንድ የምትሆንበት ማናቸውንም ሃሳብ ያወግዛል። በመሆኑም አፄ ምንሊክ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን አንድ አድርጎ የሚያየው ኃይል ሁለቱም ላይ ዘመቻ ከፍቷል።
3) የቅኝ ግዛት ህልማቸው የከሸፈባቸው ቂመኛ ሀገሮች እና ኃይሎች
ዳግማዊ ምንሊክ ከመንገሳቸው በፊት ኢትዮጵያን ዙርያዋን የከበቧት ኃይሎችን ቀድመው በመቅረብ እና የኢትዮጵያን የፀጥታ ቀጠና በማስፋት ቀጥሎም በአድዋ ዘመቻ የማያዳግም ቅጣት በመስጠት ቅኝ ግዛትን የቀበሩት አፄ ምንሊክ ዛሬም ድረስ በአንዳንድ የቅኝ ግዛት ስነ ልቦና ውስጥ ባሉ ሀገሮች ቂም ተይዞባቸዋል። በተለይ የአድዋ ድል ንዝረት ዛሬ ድረስ ለመላው ጥቁር ህዝቦች እና በእጅ አዙር አገዛዝ ለሚማቅቁ ሀገሮች ሁሉ ዛሬ ድረስ መሰማቱ እና ኃይል መሆኑ የአፄ ምንሊክ ታሪክ ላይ በመዝመት እና የሚዘምቱትን ከጀርባ በመርዳት ቂማቸውን ለመወጣት የሚያስቡ ሀገሮች እና ኃይሎች አሉ።ከእነኝህ ውስጥ አንዷ ከሐረር ያባረሯት ግብፅ ተጠቃሽ ነች።ግብፅ በአፄ ምንሊክ ላይ የሚደረጉ ዘመቻዎችን ከጀርባ በማገዝ ትታማለች።ከግብፅ በተጨማሪ በምኒሊክ የአፍሪካ የነፃነት ፋና ወጊነት ላይ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍለው ለማዝመት የሚሰሩ አካላትም አሉ።
ባጠቃላይ ዳግማዊ ምንልክን ለማጥላላት የሚሞክሩ ሶስቱ አካላት ምን ያህል ቢደክሙ እውነተኛውን ታሪክ መቼም ሊደብቁት አይችሉም።ንጉሡ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም በማድረጋቸው የሚመሰክሩላቸው ሕያው ምስክሮች ዛሬም አሉ።እውነተኛ ታሪክ ደግሞ እየደመቀ እንጂ እየደበዘዘ አይሄድም።
ምንሊክ ጥቁር ሰው በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን
No comments:
Post a Comment