ቅንጡዎቹ ሶስት ቦታዎች ሆነው ወጣንበት የሚሉትን ብሔር ድረስልን እያሉ ነው።አንድኛው መቀሌ የሚገኘው የትህነግ የአዛውንቶች አመራር ነው።ይህ ቡድን በግንብ በታጠረ ምቹ ቤት ውስጥ ተቀምጠው የተቀሩት ደግሞ በመቀሌ እና አድዋ ሆቴሎች ውስጥ ውሎ እና አዳራቸውን አድርገው ነው ምስኪኑን የትግራይ ሕዝብ ከቀረው ወገኑ ጋር እንዲጋጭ የሚወተውቱት።እነርሱ እና ልጆቻቸው በጣታቸው ሊነኩት የማይፈልጉትን ጦርነት ወጣቱ የነገ ተስፋው ጨልሞ፣ ምክንያቱ እና ግቡ በማይታወቅ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብቶ እንዲያልቅ መወትወቱን ይዘውታል።የተቀሩት የአዛውንቶቹ ፍርፋሪ የለመዱት እና ከዘረፋ እስከ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ውስጥ የተነከሩት ደግሞ በአውሮፓ እና አሜሪካ ተቀምጠው በማኅበራዊ ሚድያ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚሰራውን ወንጀል ለመሸፈን ሲሞክሩ እና እነርሱም ለአዛውንቶቹ ስልጣን ሙቱላቸው እያሉ መማፀኑን ተያይዘውታል።
ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ የትግራይ ሕዝብ እስከ ታች ወረዳ ድረስ ጦርነት የመጣበት በማስመሰል ሲያምሱት ነው የከረሙት።በአስተዳደር በደል የመጣውን የኑሮ ውድነት የጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ ስለሆነ የመጣ በማስመሰል ሲያታልሉት ሰንብተዋል።ትናንት ሐምሌ 26/2012 ዓም ደግሞ የትግራይ ልዩ ኃይል በመቀሌ ስታድዮም በማሰለፍ እና ሕዝብ በግድ ወደ ስታድዮሙ እንዲመጣ እና ለወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ በማጋለጥ ሽብር ሲነዙበት ውለዋል።
በሌላ በኩል በኦሮሞ ሕዝብ የሚነግዱት ፅንፈኛ ቅንጡዎች በአሜሪካ፣አውስትራሊያ እና አውሮፓ ተቀምጠው መንገድ ዝጉ፣የመንግስት መስርያቤቶች አቃጥሉ፣ጎማ አተንፍሱ፣ከእገሌ ብሔር ብቻ እንጀራ ግዙ፣ከቻላችሁ እንጀራ አትብሉ እያሉ እነርሱ በቅምጥል ከሚኖሩበት አውሮፓ፣አሜሪካ እና አውስትራሊያ ተቀምጠው ድሃውን የኦሮሞ ትውልድ ሕልሙን ለማጨለም እና እነርሱ ወደ ፅንፍ አስተሳሰብ በተመራ መንገድ ለስልጣን እንዲበቁ ተንበርክከው የመለመን ያህል እየተማጠኑ ነው።
ሁለቱም በኦሮሞ እና የትግራይ ሕዝብ የሚነግዱ ቅንጡዎች ግንባር መፍጠር ደግሞ አስገራሚው የወቅቱ ድራማ ነው።ድራማውን የሚጫወቱት ደግሞ ሁለቱም የተመቸ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ደግሞ በውጭ ሃገራት ልከው እያስተማሩ ነው። መቀሌ ውሃ ለመቅዳት ጀርካል ኮልኩሎ የሚጠብቀው ሕዝብ፣ሽሬ ላይ አንድ እንጀራ ለማግኘት የምትዋትተው እናት፣ኦሮምያ ያለው የስራ አጡ ከተሜ ወጣት እራሱን ለማውጣት የሚያደርገው መፍጨርጨር ሁሉ ለቅንጡዎቹ አይሰማቸውም። እነርሱ በድሃው ደም እና በአዲሱ ትውልድ ተስፋ ላይ ተረማምደው የስልጣን ጥማቸውን ማርካት ብቻ ነው ግባቸው።
ባጠቃላይ የትሕነግም ሆነ በኦሮሞ ስም የሚነግዱት የፅንፍ ኃይሎች በጋራ ያገናኛቸው የፖለቲካ ፕሮግራም አይደለም።የጋራ መገናኛ ነጥባቸው የስልጣን ጥማት እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸው ከንቱ ሕልም ብቻ ነው።የቅንጡዎቹ እባካችሁ ለልስጣናችን ሙቱልን ልፈፋ የሚሰማ ወጣት የለም።የትግራይም ሆነ የኦሮምያ ወጣት በጋራ በምትገነባ ሀገር ውስጥ ያለ ዘለቄታነት ያለው የጋራ ጥቅም የበለጠ እንደሆነ ያውቃል።ስለሆነም በመጀመርያ ለጥርያችሁ ምላሽ ባለመስጠት ተቃውሞውን ይገልጣል።በመቀጠል ጭቅጨቃቹ አላቆም ካለው በእናንተው በቅምጥሎቹ ላይ ይነሳል።ይህ መሆኑ አይቀርም የጊዜ ጉዳይ ነው።
============================
No comments:
Post a Comment