ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, August 5, 2020

የሻሸመኔ፣አርሲ፣ዝዋይ፣ሐረር እና ባሌ የሰሞኑ ጭፍጨፋ እና የንብረት ማውደም ወንጀል ምንጩ፣ዓላማው፣የመንግስት ምላሽ እና በመፍትሄነት ወደፊት መደረግ ያለበት።

በሻሸመኔ ከደረሰው ውድመት በከፊል 

ጉዳያችን ልዩ ወቅታዊ 

ሰሞኑን የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ሰኔ 23 እና 24/2012 ዓም በሻሸመኔ፣አርሲ፣ዝዋይ፣ሐረር እና ባሌ በተለየ መልኩ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የግፍ ግድያ እና የንብረት ማቃጠል ወንጀል ተፈፅሟል።ወንጀሉ  የተፈፀመባቸው በምእራብ አርሲ ዞን በአርሲ ነገሌ እና ዶዶላ ከተማና ወረዳ፣ በሻሻመኔ፣ ኮፈሌ፣ አዳባ ፣ ዶዶላ፣ ሻላ፣ ቆሬ እና አሳሳ ወረዳዎች፣በዝዋይ እና በባሌ አጋርፋ  እና ሐረር ነው።በእዚህም መሰረት እስካሁን ከ200 በላይ ንፁሃን ሲገደሉ በሚልዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል።ወንጀለኞቹ በመንጋ እየከበቡ ንፁሃንን የገደሉበት አገዳደል ህሊና የሚፈትን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ መሆን በራሱ ወንጀል ነው የሚል መልዕክት የያዘ እና በቀጥታ ከውጭ የተቀዳ ይመስላል።በተለይ የንብረት አወዳደሙ በራሱ ልዩ ስልጠና የታከለበት እንጂ ተራ የብስጭት ውድመት እንዳልሆነ የዓይን ምስክሮች እማኘንታቸውን እየገለጡ ነው።

የወንጀሉ ምንጭ ምንድነው?

ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች የተፈፀሙት ወንጀሎች ፈጣን ምክንያቱ የሃጫሉን መገደል ያስመስል እንጂ ቀደም ብሎ በሁለት ኃይሎች የታሰበበት ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም።እነኝህ ሁለት ኃይሎች በፈጠሩት ጥምረት እና የመረጃ ልውውጥ መንጋውን ለማንቀሳቀስ ችለዋል። እዚህ ላይ ጥያቄው መንጋው ማን ነው? የመንጋው አንቀሳቃሾች እነማን ናቸው? የሚለው ነው።መንጋው በድምር የሚጠራው አመራሩ እና ቅርፁ በመንጋ መልክ ብቻ እንዲገለጥ የተደረገው ቄሮ በሚል ስም ቢጠራም በመንጋ የሚያንቀሳቅሱት እና የሚመታውን ኢላማ የሚመርጡለት ግን እነኝህ ሁለት ኃይሎች ናቸው።

የመጀመርያው አንቀሳቃሽ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ቅርፁን እና መልኩን ሲቀይር የኖረው የፅንፈኛ የአክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ ነው።ይህ እንቅስቃሴ በብሄር ፖለቲካ ውስጥ ተሸጉጦ በኢህአዴግ/ህወሓት ውስጥ ነበር።ይህ እንቅስቃሴ በተቃዋሚ የብሔር ድርጅቶች ውስጥም ነበር። አክራሪው ኃይል በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮምያ የፖሊስ እና ቢሮክራሲ ውስጥ መግባቱ ጉልበት ሰጥቶታል።ይህንን ቡድን የህወሓት/ኢህአዴግ ደህንነት በሚገባ ያውቀዋል።ከአስር ዓመት በፊት ይህ ቡድን በአሰላ እና በአዲስ አበባ  ከተማ ውስጥ በግለሰቦች መኖርያ ግቢ  ውስጥ  በሺህ የሚቆጠር ገጀራ ተይዞ ነበር።ተመሳሳይ ድርጊቱ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ተገኝቷል።ምናልባት አሁን ደግሞ በጦር መሳርያ ንግድ ላይም ተሰማርቶ ይሆናል።

ቡድኑ በተለያዩ ጊዜዎች ቦግ እልም እያለ አመቺ የቀውስ ጊዜዎችን ሲጠብቅ የኖረ ነው። ከአስር ዓመት በፊት በበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ሲታረዱ፣በአሰቦት ገዳም ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀም ሁሉ ህወሓት/ኢህአዴግ ደህንነት የጉዳዩ ፈፃሚዎች ዋና ሽፋናቸው የኢህአዴግ ባለስልትናንነት እንደነበር ይታወቃል።ለምሳሌ በበሻሻ ወንጀሉ ከተፈፀመ በኃላ የሚድያ ሽፋን እንዳያገኝ ብቻ ሳይሆን  ድርጊቱን በቪድዮ ለምን ተሰራጨ? እያሉ ሲያስሩ የነበሩት የድርጊቱ በተዘዋዋሪ ተባባሪ እንደሆኑ የተጠረጠሩት የአካባቢው ባለስልጣናት ግን የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አባላት ነበሩ።

ከእዚህ የፅንፍ ቡድን ጋር ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለች በሁለት መልኩ አጋርነት ነበራት።እነርሱም የመጀመርያው የክልል የመከፋፈል ፖሊሲ ላይ ጥሩ አስፈፃሚ በመሆናቸው እና በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አንድነት ትሰብካለች፣መለያየት ትቃወማለች በሚል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መጨቆን ላይ ስለሚያግዙ ነው።ስለሆነም የህወሓት/ኢህአዴግ አመራር እነኝህ የፅንፍ ኃይሎች በኢህአዴግ አባልነትም ሆነ በአጋርነት ሲደራጁ እና ሃገሩን ሲያምሱ ህወሓት/ኢህአዴግ ታበረታታ ነበር።ደህንነቱ በስልጣን እርከን ላይ እጅግ አደገኛ የሆኑ የፅንፍ እና የሽብር ቡድኖች ከሱማሌ ክልል እስከ ኮፈሌ፣ከቤንሻንጉል እስከ መቱ ሲደራጁ እያወቀ ዝም አለ።ለምሳሌ በሱማሌ ክልል ጅጅጋ የፅንፉ ኃይል ልዩ ኃይሎች ከአዲስ አበባ የመጣ ሰውን መንገድ ላይ አስቁመው መታወቂያ እየጠየቁ ካለምንም ወንጀል ያስሩ ነበር።የህወሓት ሙሰኛ ባለስልጣኖችን እስካልነኩ ድረስ የሌላው ስቃይ ለህወሓት/ኢህአዴግ ደንታ አልሰጣትም።ይልቁንም ህወሓት ጠቅልላ ወደ መቀሌ ስትገባ ይህንን የፅንፍ ኃይል እንደ መቅጫ ዱላ እንደምትጠቀምበት ተማምናበት ነበር።የቀድሞው የደህንነት ሹም አቶ ጌታቸው ሙሉ መረጃው በተለይ በፅንፍ ኃይሉ የሚጠቁ ስስ አካባቢዎችን ያውቃሉ።ስለሆነም ለሀገር ማተራመሻነት ከእነማን ጋር መስራት እንዳለባቸው ሳይወስኑ አልቀሩም።

ካለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ይህ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው የፅንፍ ኃይል የኢህአዴግን መንገዳገድ ከተመለከተ በኃላ ራሱን ይበልጥ ወደውጭ ያሉ የተቃዋሚ ኃይሎች ማስጠጋት ጀመረ።ከተቃዋሚ ኃይሎች ውስጥ የመረጠው ደግሞ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑትን ሳይሆን አሁንም በጎሳ ላይ የተመሰረተ ዓላማ ያላቸውን መረጠ።ከብሔርም የመረጠው በልዩ ልዩ ውስጣዊ ውጥረቶች የታወከውን የኦሮሞ የብሔር ዘውግ እንቅስቃሴን ነበር።በእዚህ መሰረት እንደ ተኩስ ማስጀመርያ የጀዋር መሐመድ የዛሬ ሰባት ዓመት በአሜሪካ ያደረገው ''ክርስቲያኖችን በሜጫ በሏቸው'' የሚለውን ንግግር እንደ መክፈቻ ስነ ስርዓት ተጠቀመበት።ጀዋር ይህንን ንግግር ሲያደርግ በአዳራሹ የተሰበሰቡ በፅንፍ ፖለቲካ አራማጅነት የሚታወቁ እና በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች እያደነቁ ራሳቸውን ከላይ ወደታች ሲነቀንቁለት ይታይ ነበር።

የፅንፍ አክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ ኢህአዴግ/ሕወሃት እየደከመ መሆኑን ሲያውቅ ወደ ተቃዋሚው ጎራ በድንገት የገባ አይደለም።ቀድም ብሎ ወደ ኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን ሲጠጋ መውጫውን አዘጋጅቶ ነበር።ጀዋር የኦህዴድ አባል ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ ሀገር ለትምህርት ሲሄድ የድጋፍ ደብዳቤ ሁሉ ያገኘው ከኢህአዴጉ አባል ድርጅት ኦህዴድ ነው።ጀዋር ከኢትዮጵያ እንደወጣ ወደ ሩቅ ምስራቅ መሄዱን ቢነግረንም በእርግጥ ለስልጠና በወቅቱ የት ሀገር እንደነበረ የሚያውቀው እርሱ ነው።

የፅንፍ ኃይሉ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ መሸጎጡ በተለይ የኦርቶዶክስን እና የኢትዮጵያ ሕብረትን በልዩነት የሚደግፈውን ሕዝብ ለመምታት ይመቻል በሚል እንደ ለም የዓላማ ማስፈፀሚያ የተመረጠው በተለያዩ ቡድኖች የተከፋፈለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሆኖ ተገኘ።ይህ የፅንፍ ቡድን የሚያሽከረክረው በቄሮ ስም የተሰበሰበው ወጣት ይህንን ሁሉ ጉድ አያውቅም።የሚገርመው የቄሮ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው ቦታዎች ሁሉ ብዙ መንጋ ለማሰባሰብ የፅንፍ ቡድኑ እራሱን ደብቆ በቄሮ ውስጥ እንዳለ ሁሉ በኢህአዴግ/ህወሓት የፀጥታ አካልም ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ እልቂት እንዲፈፀም ይሰራ ነበር።

እዚህ ላይ ከአምስት ዓመት በፊት በእዚህ በጉዳያችን ላይ እንደተገለጠው የቄሮ ኃይል በስለጠነ መልክ እንዳይደራጅ የሚፈልገው ይሄው የፅንፍ ኃይል ነው። ጀዋር በተደጋጋሚ የቄሮን አደረጃጀች ላይ ሲጠየቅ አድበስብሶ የሚያልፈው ቄሮ እንዲደራጅ እና ወደ የዜግነት ኃላፊነት የሚወስድ ኃይል እንዳያድግ ስለማይፈልግ እና ስውሩ የፅንፍ እና የጀሃድ ኃይል እየመራው እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው።ለእዚህ አብነት መጥቀስ ይቻላል።በኦሮምያ ሚድያ ኔት ዎርክ ውስጥ የተፈጠረው ሹክቻ እና ጀዋር የፈታበት መንገድ ነው። ከለውጡ በፊትም ሆነ በኃላ በኦኤምኤን ውስጥ የተፈጠረው ሹክቻ የፅንፍ ጀሃዲስት አስተሳሰብ የሚያራምዱ እና የኦሮሞ ብሔር ዘውግ በሚያራምዱ መሃል የተፈጠረ ነበር።ከለውጡ በፊት ኦኤምኤን ጥለው የሄዱት ጋዜጠኞች እና የቦርድ አባላት መሃል እና በጀዋር የአርሲ የፅንፍ ቡድን መሃል የነበረው ልዩነት ምን እንደነበር በወቅቱ የወጡት የፃፉትን ማገላበጥ በቂ መረጃ ነው።ከለውጡ በኃላም ዋናው የፅንፈኛው ቡድን በውጭ እንዲቆይ አድርጎ ወደ ሀገር ቤት የገባው ከፊት የዘውግ አክራሪ መስሎ በውስጥ ግን የሚዘወረው በፅንፍ የጀሃዲስቶች ቡድኖች ነበር።

ሰሞኑን በአርሲ፣ባሌ፣ሻሸመኔ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈፀሙት የጭካኔ ግድያዎች እና የንብረት ማውደም ተግባር ዋና ምንጭ የእዚህ የፅንፍ ኃይል አሁንም በኦሮሞ ብሔር የዘውግ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሸሽጎ እና እግሮቹን በመንግስት ቢሮክራሲ እና የፀጥታ መዋቅር እንዲሁም በተቃዋሚዎች ላይ አንሰራፍቶ የፈፀመው ተግባር ነው።ይህ ቡድን ከእዚህ በፊት ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለ የኢህአዴግ/ህወሃትን ስልጣን እስካልተጋፋ ድረስ በስውር እና በግልጥ ሲደገፍ የነበረ ሲሆን በሰሞኑ ግን የፅንፍ ኃይሉ እና ህወሓት በግልጥ የጋራ ስልት ቀይሰው በሰው ኃይል፣በገንዘብ እና በፕሮፓጋንዳ ጭምር እየተጋገዙ የሄዱበት የወንጀል ድርጊት ነው።

እዚህ ላይ የህወሓት በቀጥታ በጉዳዩ ላይ ለመግባት አሳማኝ ጉዳዮች ለማንሳት ሁለት ነጥቦችን ማንሳት ይገባል።የመጀመርያው የህዋሃት ፕሮፓጋንዳም ሆነ የውስጥ መልዕክቶች በተለይ በሻሸመኔ እና በዝዋይ የሚኖሩ የድርጅቱ አባላት ሆኑ ባለሀብቶች ለቀው እንዲወጡ ሲወተውቱ ነበር የከረሙት።ጀዋር እና በቀለ ገርባም ከድርጊቱ ሁለት ሳምንታት በፊት በተደጋጋሚ ወደ ስፍራው መሄዳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያውቁት ነው።በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት በኢትዮጵያ ትልቅ ጥፋት ይፈጠራል በማለት በሚድያዋ ብቻ አይደለም የለቀቀችው ከእዚህ ባለፈ ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ ለበርካታ መንግሥታት ደብዳቤ ልካለች።በደብዳቤው ከሰሞኑ ''እኔ ያልኩት ካልሆነ ታዩታላችሁ'' መሰል መልዕክት የያዘ ነበር።ወንጀሉ በተፈፀመ ቀንም ሆነ በኃላ የህወሓት ሚድያዎች ሰፊ ሽፋን የሰጡት ለእዚሁ የፅንፍ ኃይል ከመሆኑ በላይ የኦሮምያ ሚድያ ኔት ዎርክ የሚያስተላልፈውን የመንግስት ንብረት አውድሙ መልዕክት በቀጥታ የስርጭት ሽፋን ጭምር በማስተላለፍ የወንጀሉ ተባባሪ ሆናለች።

ስለሆነም የችግሩ ዋና ምንጭ በኦሮሞ የብሔር ዘውግ ፖለቲካ ውስጥ የተደበቀው የቆየው የፅንፍ ጀሃዲስት ቡድን ሲሆን አጃቢዎቹ የዘውግ አራማጆቹ እና ህውሓት እራሷም ነች።ይህ በእንዲህ እያለ ግን የቅርቡ መልካም ክስተት የቄሮ እንቅስቃሴ እራሱን ከህወሓት ተንኮልም ሆነ ከጀሃድስት ቡድኑ እራሱን እያገለለ እና እየተሰራ የነበረውን ተንኮል እያወቀ መምጣቱ ነው።ለእዚህ ምስክሩ ደግሞ በቅርቡ የጀሃድስት ቡድኑ እንደለመደው በኦሮሞ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ተሸሽጎ የጠራው የአመፅ ጥሪ ከአንዴም ሶስቴ መክሸፉ ነው። በእዚህም የጀሃድስት ቡድኑ ለብቻው እየቀረ መሆኑን እንመለከታለን።አሁን የጀሃድስት ቡድኑ ዋና የትግል ግንባር ያደረገው የውጭ ሀገሮችን ሲሆን በውጭ ሀገሮች ''ኢትዮጵያ ትውደም'' የሚል መፈክር ከዱባይ እስከ ጀርመን ጀለዎቹን እያሰለፈ በመጮህ ላይ ይገኛል።ለእዚህ ዓይነቱ ድርጊት ደግሞ የውጭ መንግሥታትም ዝም አላሉም።በዱባይ ኢትዮጵያን ያጥላሉት የተባበሩት አረብ መንግሥታት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልካቸው መወሰኑ በቅርቡ ተሰምቷል።

የወንጀሉ ዓላማ ምንድነው?

የወንጀሉ ዓላማ ሶስት ናቸው። እነርሱም 
1) ክርስቲያኖችን ምጣኔ ሀብታቸውን ማውደም እና ማደህየት በእዚህም በተፅኖ ስር እንዲወድቁ ማድረግ፣

2) ሁለተኛው ደግሞ ክርስቲያኖችን በመግደል እና የስነ ልቦና ተፅኖ በመፍጠር እንዲሰደዱ በማድረግ  አካባቢውን በፅንፍ ጀሃዲስቶች ቁጥጥር ስር ማዋል እና 

3) በሶስተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን መልክ፣ታሪክ እና ማንነት ደምስሶ በአዲስ የጀሃዳዊ ታሪክ እና መንግስት መቀየር ናቸው።

እነኝህን ሁሉ ለማስፈፀም ግን ጀሃዲስቱ ቡድን በብሄር ፖለቲካ ስር ይሸጎጣል።ነገ ሌላ ዓይነት ፖለቲካ ቢመጣም በእዛ ስር ሆኖ ዓላማውን ለማሳካት የማያፍር እንደ እስስት እራሱን የሚቀያይር ለመሆኑ ያለፉ ታሪኮቹ ያሳያሉ።

የመንግስት ምላሽ 

ወንጀሉን ተከትሎ መንግስት የወሰደው እርምጃ እንደ ሻሸመኔ ያሉ ከተሞች ሙሉ የካቢኔውን እና ከንቲባውን ከማሰር ጀምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ጀዋር እና በቀለ ገርባን ጨምሮ አስሯል። ለምሳሌ እንደ ፋና ዘገባ በ10 ወረዳዎች በደረሰ የሰው ህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ወንጀል የተጠረጠሩ 1 ሺህ 168 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።70 ተጠርጣሪዎች ሃምሌ 13 ቀን በወረዳ ፍርድ ቤቶች ቀርበው የጠየቁት ዋስትና ለጊዜው ወድቅ ተደርጎ ለመርማሪ ፖሊስ የወደመና ጉዳት የደረሰ ንብረትን በባለሙያ ለማስገመት እና በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት የህክምና እንዲሁም ህይወታቸው ያለፉትን የአስከሬን ምርመራ እና የምስክሮችን ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ፍርድ ቤቶቹ ለፖሊስ 14 ቀን ፈቅደዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ኃይል እና የፌድራል ፖሊስ የፀጥታ ሥራ በመስራት ላይ ናቸው።ለምሳሌ ከእዚህ በፊት መንገድ ይዘጉ የነበሩ ወጣቶች አሁን ካለምንም ይቅርታ የፀጥታው ኃይል እርምጃ ይወስዳል።ለምሳሌ በያዝነው ሳምንት በዶሎ መና ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈፅሙ የሞከሩት ላይ ሰራዊቱ ወዲያው ደርሶ እርምጃ ወስዷል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም በፓርላማም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሲያነጋግሩ የሕግ ማስከበር ሂደቱ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።በአቃቢ ሕግ በኩልም ተከታታይ ሕግ የማስከበር ተግባር እንደሚቀጥል መግለጫዎች ተሰጥተዋል።በእዚህ እርምጃ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ወደ ሕግ የማስከበር ተግባር በቁርጠኝነት መግባቱን ማሳየቱ ሊበረታታ የሚገባ እና ሁሉም አብሮት ሊቆም የሚገባ ጉዳይ ነው።

እነኝህ እርምጃዎች ሁሉ ግን አንድ ነገር ይጎድላቸዋል።ይሄውም በደረሰው ሰቆቃ በሚመጥን ልክ መንግስት በፌድራልም ሆነ በክልል ደረጃ ሃዛኑን አልገለጠም።እርግጥ ነው በክልልም ሆነ በፌድራል ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች የወንጀሉ አሰቃቂነት ሳይሰማቸው ቀርቶ ነው ለማለት ያስቸግራል። ግን ሕዝብ አሁን እየጠየቀ ያለው በተለይ ጥቃቱ ኦርቶዶክሳውያንን ዓላማ አድርጎ ከመፈፀሙ አንፃር የክልሉ ፕሬዝዳንትም ሆኑ በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት የሃጫሉ ሞት ተከትሎ የገለጡበት ድምፀት ልክ ከሁለት መቶ በላይ ክርስቲያኖች የተገደሉበትን አረመኔያዊ ድርጊት በሚመጥን ደረጃ አለማውገዛቸው የህዝቡ መነጋገርያ አጀንዳ ነው።በእዚህም አሁንም የፅንፍ የጀሃድስቱ አካል ከወረዳ ባለስልጣን እና ፖሊስ ኃይል ባለፈ በመንግስት መዋቅር ውስጥ አለ ወይ? የሚል ግዙፍ ጥያቄ ጭሯል።ለእዚህም አሁንም መንግስት ውስጡን እስከ ወረዳ ድረስ የማጥራት ስራውን እንደጀመረው መቀጠል አለበት። ጉዳዩ የሀገር ህልውና ጉዳይም ነው።

ወደፊት ምን ይደረግ? መፍትሄውስ?

የችግሮች ሁሉ መፍትሄ መነሻ በመጀመርያ የችግሩን ምንጭ እና መነሻ ማወቅ ነው። ጉዳያችን የኦሮሞ የብሄርተኝነት የዘውግ ፖለቲካ በፅንፍ ኃይሎች መጠለፉን ከአምስት ዓመት በፊት አውስታለች።አንዳንዶች የችግሩ ዋና መሰረት የጎሳ ፖለቲካው ብቻ እንደሆነ ያስባሉ።የጎሳ ፖለቲካው በርግጥ ለስላሳ መሬት ለጀሃድስቱ ከፍቶለታል።ለእዚህም ነው የጎሳ ፖለቲካን እየኮተኮተ ለማሳደግ የጀሃድስቱ ቡድን ላይ እና ታች የሚለው።በተከፋፈለ ሀገር ላይ ጀሃድ ማካሄድ ስለሚቀለው።

በኢትዮጵያ የተከሰተው የፅንፍ ጀሃዲስቶች እንቅስቃሴ በሌሎች ሀገሮች ውስጥ ሲከሰት በነበረው የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ተደብቆ የመሄዱ ባህሪ የተለመደ ነው።በግብፅ ሙባርክን ከስልጣን ለማውረድ የእስላማዊ ወንድማማቾች ቡድን አብሮ የትግሉ አካል ከሆነ በኃላ ውደ ስልጣን ለመምጣት የሞከረው ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በመሰለ የምርጫ መንገድ ነበር።ይህ ሂደት ግን ዋና ፊቱን ለመደበቅ አልረዳውም።በኢትዮጵያም በቄሮ እና በኦሮሞ የዘውግ ፖለቲካ ውስጥ ተደብቆ ኢትዮጵያን ለማመስ የተነሳው የጀሃድስት ቡድን አሁን ከምንጊዜውም በበለጠ ተጋልጧል። 

በአምቦ መቀመጫቸውን ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ እንዳይገቡ ችግር ሊፈጥር በሞከረው ቡድን ዙርያ አምቦ ላይ ወጣቶች ተሰብስበው ሲመክሩ የሄዱበት መንገድ አስተማሪ ነው።አምቦ ከአምስት ወራት በፊት በነበረ ስብሰባ ላይ ማን ነው አቡኑ እንዳይመጡ ያገደ? የሚል አውጣጭኝ ላይ የተነሳው እና እርሱን ተከትሎ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቄሮ የላትም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ነበሩ።በስብሰባው ላይ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ግን በቄሮ ትግል ውስጥ የተሰለፉ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ነን ደሞ ቄሮ ነን።ነገር ግን ይህንን አባታችንን እንዳይመጡ የሚከለክል ማን እንደሆነ አናውቅም! በማለት መለሱ። በመቀጠል ከውስጣቸው የጀሃድስቶች ሥራ መሆኑን ተማምነው እና ይህንን ለመዋጋት ወስነው ጳጳሱ በክብር በወጣቶቹ ታጅበው አምቦ ገብተዋል።

በመጨረሻም ወደፊት ሊደረግ ስለሚገባው ወደ የመፍትሄው ሃሳብ ስንሄድ የሚከተሉት ወሳኝ ተግባራት ሊተኮርባቸው ይገባል። እነርሱም -

1) ሕዝብ ሙሉ በሙሉ እራሱን የመከላከል መብት እንዳለው እና እራሱን ለእዚህ ተግባር በህብረት በመቆም እራሱን ማስከበር አለበት።ከአሁን በኃላ የለቅሶ እና የሃዘን እንጉርጉሮ ማንንም አይጠቅምም።ኢትዮጵያ የእኔም ነች ማንም ከሕግ ውጪ እንዲገፋኝ አልፈቅድለትም የሚል ጠንካራ ስነ ልቦናዊም ሆነ የጋራ ዝግጅት ያስፈልጋል።

2) መንግስት የፀጥታ አካላት፣የወረዳ እና የቀበሌ ኃላፊዎች ጭምር ከጀሃድስት እና የጎሳ ፅንፍ የፀዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና የአካባቢ ሚሊሻ በአዲስ መልክ የሁሉንም ነዋሪ ተዋፅኦ በትክክል ባሳተፈ መልኩ ማደራጀት አለበት።

3) ሕይወታቸው ለጠፋ እና ንብረታቸው ለወደመው ሁሉ መንግስት ከህዝብ ሀብት አሰባስቦም ቢሆን ሁሉንም መልሶ የመርዳት እና ወደነበረ ኑሯቸው መመለስ መቻል አለበት።

4) የወንጀሉ አፈፃፀም፣እነማን እንደፈፀሙ  እና ከጀርባ ያሉ ኃይሎች ሁሉ የያዘ የተሟላ ሪፖርት መንግስት  ለሕዝብ ግልጥ ማድረግ አለበት። ይህ ለወደፊቱ ሕዝብ ጠላቱን ለይቶ እንዲያውቅ ይረዳል።

5) በከፍተኛ ባለሙያዎች የታገዘ ህዝብን የሚያቀራርቡ የአካባቢ ችግሮች ላይ ያተኮሩ አዳዲስ የመገናኛ ብዙሃን ያስፈልጋሉ።ለምሳሌ ለአርሲ፣ለባሌ፣ለሻሸመኔ፣ሐረር ወዘተ ቦታዎቹን በልዩ ሁኔታ ያተኮሩ ዜናዎቹ በጣም የአካባቢውን የዕለት ከእለት  ተግባራት ላይ ያተኮሩ እና የአካባቢውን ሕዝብ ጆሮ የሚስቡ ነገር ግን በማዕከል በብሮድካስት ኮርፖሬሽን ቁጥጥር ሚድያዎች ያስፈልጋሉ።ምድያዎቹ ኤፍኤም ራድዮኖች ቢሆኑ በተለይ ለአካባቢው ገጠር ስለሚዳረሱ በከተሞቹ እና በአካባቢ ገጠሮች መሃል ያሉ ልዩነቶችን  ያጠባሉ፣ማኅበራዊ ትስስሮችን ያጠነክራሉ።

የእዚህ ዓይነት ሚድያዎች በተለይ በሰለጠኑ ሀገሮች በጣም ይጠቀሙበታል።የአካባቢ ሚድያ እና ጋዜጦች በዝርዝር በመንደሩ የዕለት ከእለት ጉዳይ ላይ ስለሚያተኩሩ ያላቸው ማኅበራዊ መስተጋብር እና እርቅ የመፍጠር አቅማቸው ሁሉ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።በተለይ እነኝህ ሚድያዎች በአካባቢው የሚኖሩ  መልካም ግለሰቦች ሃይማኖት እና ብሔር ሳይለዩ ስለሚያስተዋውቁ መከባበሩ ይጠነክራል።ሰሞኑን እንደተገደሉ የምንሰማው መልካም ሰዎች ቀደም ብሎ በነበሩ የአካባቢ ሚድያ ለገጠሩም ሆነ ለከተሜው ቢነገር ኖሮ መተዋወቁ በተፈጠረ ጀሃድስቶቹም ለመግደል ባልቻሉ ነበር። 
 
6) ሕዝብ አካባቢውን በደንብ የመቃኘት አቅሙን ማሳደግ።በአካባቢው የሚኖሩ ከመስመር የወጣ አካሄድ ያለባቸው ላይ ትኩረት የማድረግ እና የማረቅ አቅሙን ማሳደግ።

7) የተበጠሱ እና የላሉ ማኅበራዊ ዕሴቶች መቃኘት፣ማጠናከር እና ማዳበር 

8) የወጣት ማኅበራት ኃላፊነት እንዲወስዱ ማድረግ።ከስነ ምግባር ውጪ የሆኑትን በህጋዊ ቅጣትም ሆነ በምክር ማረቅ።

9) የማክሮ ኢኮኖሚው በዋናነት በሥራ ዕድል ላይ እና በገቢ ልዩነት ማጥበብ ላይ መስራት እና 

10) የትምህርት ካርኩለሙ ለጀሃድስቶች እና ለፅንፍ ብሄርተኞች እንዳይመች አድርጎ መከለስ፣መምህራን በክፍል ውስጥ የሚሉት ሁሉ  ከፅንፍ መስመሮች የወጣ መሆኑን ማረጋገጥ እና ተማሪዎች አካባቢያቸውን የምጎበኙበት መርሃ ግብር እንዲኖር ትምህርት ቤቶች ከማስተማር ሂደቱ ውስጥ እንዲያስገቡ ማድረግ የሚሉት ለአጭር እና ለረጅም ጊዜ የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦች ናቸው። 
=======================////=================

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...