አቶ ሽመልስ አብዲሳ
የሰው ልጅ አንገት በካራ ተቀነጠሰ፣እርጉዝ በስለት ሆዷ ተቀደደ እየተባሉ የአስተዳደር ድክመታቸውን በላም እና ጊደር ተረት ለመሸፈን ይሞክራሉ።በያዝነው ሳምንት አጋማሽ በኦቢኤን ቴሌቭዥን ቀርበው መግለጫ የሰጡት የኦሮምያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በቃለ መጠየቃቸው ላይ አሁንም በጎሳ ፖለቲካ የኦሮሞ ህዝብን ስሜት በመኮርኮር ቅጥ የለሽ የክልል አስተዳደር ሥርዓታቸውን ሊሸፋፍኑ እየሞከሩ ነው።በእዚሁ ቃለ መጠየቅ ላይ እስካሁን ምን ሰሩ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከአንድ ዓመት በፊት በኮሚቴ የተሰራውን ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉትን መመለስ ከጠቀሱ በኃላ በድፍኑ በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል በማለት አልፈውታል።በእርግጥ በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው የሰላም እጦት ከክልሉ አልፎ ለኢትዮጵያም አደገኛ ሁኔታ መጋረጡን በራሱ እንደ አንድ የኦሮሞ መኩርያ ነጥብ አድርገው ሊያጎሉትም ሞክረዋል።
በኦሮምያ የተነሳው የፀጥታ ችግር ምክንያቶቹ እንደርሳቸው አገላለጥ ላለፉት ክ/ዘመናት ኦሮምያን የበዘበዙ ናቸው ካሉ በኃላ ችግሩ 'ድንበሩን እንዲያልፍ' ያደረጉት አሁንም ለ150 ዓመታት የተበተቡት ናቸው ብለዋል።በመቀጠል የኦሮሞ ሕዝብ ስልጣኑን አግኝቷል፣ባገኘው ስልጣን መጠቀም አለበት ብለዋል።ላለፉት 150 ዓመታት ኦሮሞ የተሸነፈው ከውስጣችን ተላላኪ ፈረስ ስላለ ነው ብለዋል።በመቀጠልም ላሚቷ፣ጊደሯም፣ወተቷም፣አሬራውም አሁን በእጃችን ነው ሲሉ በእዚሁ ቃለ መጠየቃቸው ላይ ተደምጠዋል።
አቶ ሽመልስ በእዚህ ቃለ መጠየቃቸው ትውልድ ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቅ ጉዳይ ላይ ማተኮራቸው አሳፋሪ የመንግስት ባለስልጣን ያደርጋቸዋል።ኢትዮጵያ ላለፉት 150 ዓመታት ውስጥ የነበረችበትን የፊውዳል፣የፊውዶ-ቡርዣ እና የደርግ ዘመን (የሶሻሊስት ርዕዮት) አስተዳደር ሁሉ በአንድ ከረጢት ውስጥ ከትተው የኦሮሞ ሕዝብ ለ150 ዓመታት ሲበዘበዝ ነበር የሚለው ትርክታቸው ፈፅሞ ውሸት ነው።ይህ ተራ የስሜት መኮርኮር ሙከራ ከመሆን አያልፍም።
በእዚህም አቶ ሽመልስ ምን ያህል የታሪክ ዕውቀታቸው ብዙ የሚቀረው መሆኑን ያሳያል። እዚህ ላይ አፄ ሃይለስላሴም ሆኑ ኮለኔል መንግስቱ እነማን እንደሆኑ አለማወቃቸውን ያሳብቅባቸዋል።ከ150 ዓመቱ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የመሩት እነርሱ ናቸው።ሁለቱም ደግሞ ከኦሮሞ ቤተሰብ የሚወለዱ ናቸው።አቶ ሽመልስ በምናብ የፈጠሩት ብዝበዛ ተራ የብሔር ስሜት ኮርኩረው ነገሮችን ለማድበስበስ ነው የሞከሩበት መንገድ ከመሆን አሁንም አያልፍም።ላለፉት 150 ዓመታት ለምሳሌ በፊውዳል ስርዓት ውስጥ ጭሰኛ ወሎ ውስጥ እንደነበረ ሁሉ ወለጋም ውስጥ ነበር።የወለጋው ባላባት ከወለጋ የወጡ ደጃዝማች እና ፊታውራሪዎች እንደሁኑ ሁሉ በወሎ እና ጎንደርም ተመሳሳይ ነበሩ።በ1967 ዓም የካቲት 25 የወጣው መሬት ላራሹ አዋጅ ደግሞ ይህንን የፊውዳል ስርዓት ስያንኮታኩት ወለጋ ያለው ገበሬም መሬት እንደተመራ ሁሉ ለጎንደሩም ተመርቷል።ኦሮሞ በተለየ የተበዘበዘበት የቱ ጋር ነው?
የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ተከትሎ በአርሲ፣ሐረር፣ባሌ፣ዝዋይ እና ሻሸመኔ በንፁሃን ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ እና የንብረት ዘረፋ የክልሉ የፀጥታ አጠባበቅ፣የልዩ ኃይል ከፅንፈኞች ጋር መተባበሩን በምስክርነት የሚያነሱ ተጠቂዎች እየተናገሩ፣ሰው በአደባባይ በስለት መታረዱ እርጉዝ ሴት በስለት መገደሏ ባጠቃላይ ከ200 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን በተለይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮችን እንዳጠቃ እያወቁ ዛሬም የሰለቸ የ150 ዓመት ትርክት ውስጥ ለማብራራት መሞከራቸው የሚመሩትን ሕዝብ አለማወቃቸውን ያመለክታል።
የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮምያ አመራር በክልሉ የሚያስተዳድረውን ሕዝብ እኩል የማስተዳደር እና በአንድ ዓይን የማየት ከፍተኛ ችግር እንዳለበት በክልሉ የሚኖሩ አሁን ድረስ የሚያማርሩት ጉዳይ ነው።በእዚህም ሳቢያ በርካቶች መጤ እየተባሉ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚኖሩባት ክልል የሆነችው የኦሮምያ ክልል በአሁኑ ጊዜ ኢንቨስተሩ እየለቀቀ ወደ ሐዋሳ፣ባህርዳር እና ደብረብርሃን እየሸሸ እና ከፍተኛ የካፒታል ሽሽት እየታየ አቶ ሽመልስ ግን ብዙ ፕሮጀክት ገንብተናል እያሉ ነው።
የአቶ ሽመልስ ሌላው የአስተዳደር ድክመታቸው ማሳያ ደግሞ ሰሞኑን በአርሲ፣ሐረር፣ባሌ፣ዝዋይ እና ሻሸመኔ በንፁሃን ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ እና የንብረት ማቃጠል እና ዘረፋ ተከትሎ ለደረሰው ጥፋት የሃዘን መግለጫም ሆነ በቦታው ሄደው ያላፅናኑት አቶ ሽመልስ ከሰብዓዊነት ስሜት በራቀ መልኩ ለችግሩ መቀረፍ ያደረጉት የጎላ እንቅስቃሴ አለመታየቱ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።ባድምፃዊ ሃጫሉ ሞት ተከትሎ እንባቸው እየወረደ መግለጫ የሰጡት አቶ ሽመልስ የ200 ሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ማለቁ እንዴት አልተሰማቸውም? ይህንን ያህል ንፁሃን ሕይወት ከጠፋ ገና በአንድ ወር ውስጥ የሰጡት መግለጫ ላይ የተበላሸ እና በአድሎ እና በፅንፈኞች የተበላሸውን አስተዳደራቸውን ለመሸፈን ያልሰሩትን እንደሰሩ ማቅረባቸው እና አሁንም ሕዝብ ከህዝብ የሚለያያ የውሸት የታሪክ ትርክት በመተረክ ለመሸፈን መሞከር ከተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ሙከራ ከመሆን አያልፍም።
=================/////================
No comments:
Post a Comment