>> በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እውነታውን ለሚኖሩበት ሀገሮች ሚድያዎች በመግለጥ እና በመፃፍ ከምን ጊዜውም በላይ ሊተጉ ይገባል።
>> የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማኅበረሰብም ሆነ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለውጪ መንግሥታት በውጪ ሀገር ሆነው የፅንፍ ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች እኩይ ተግባር ማጋለጥ አለበት።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1992 እስከ 1995 ዓም የቦስንያ ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው የመካከለኛው አውሮፓ እልቂት ከ25 ሺህ እስከ 30 ሺህ ንፁሃን ሕይወት ተቀጥፎበታል።እልቂቱ የታጀበበት አንዱ አሳዛኝ ክስተት ደግሞ ከፍተኛ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ቀድሞ እየተነዛ እውነቱን ለመሸፈን የተደረገው አሳዛኝ ጥረት ነው።
በኢትዮጵያ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ የፅንፈኛ ኃይሎች በአሁኑ ጊዜ እየፈፀሙ ያለው ወንጀልም በአውሮፓ ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ተመሳሳይ ነው።ይሄውም በውጪ የሚኖሩ በኦሮሞ ስም የፅንፍ ኃይሎች በሚያደርጉት ቅስቀሳ ሳቢያ በሀገር ውስጥ የንፁሃን መገደል ምክንያት መሆናቸውን ለመሸፈን በማኅበራዊ ሚድያ እና በሰልፍ ቀድመው በመጮህ እውነታውን ለመሸፈን መሞከር አሁን የያዙት አንዱ ስልት ነው።
የፅንፍ ኃይሉ አሁን በኦሮምያ ባለው የስልጣን ተዋረድ ውስጥም ተሸሽጎ የፅንፍ ኃይሉ በንፁሃን ላይ ያደረሰውን የግድያ እና የንብረት ማውደም ተግባር ለመሽፋፈን የተደረገው ጥረት በግልጥ ታይቷል።ይህንንም ክፍተት በመጠቀም በውጪ ያለው የፅንፍ ኃይል በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመሸፈን የኦሮሞ ማኅበረሰብን እንደ ማኅበረሰብ ለማጥቃት የሚደረግ ተግባር እንዳለ በማስመሰል በሰልፍ፣የተለያዩ ፅሁፎችን በውጪ ሀገር ለሚገኙ ጋዜጦች እና ድረ ገፆች በመፃፍ እና ለፓርላማ አባላት በቀጥታ ትውተር በመፃፍ ሁሉ የተሳሳተ መረጃ እንዲደርስ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ በውጪ የሚኖሩ በከፍተኛ የሙያ እና የአቅም ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የዳር ተመልካች መሆናቸው እና ዝምታቸው በኦሮሞ ስም ለሚነግዱ የፅንፍ ኃይሎች በተሳሳተ መንገዳቸው እንዲቀጥሉ 'ዕድል' ሰጥቷቸዋል።በእርግጥ የፅንፍ ኃይሎችን የተሳሳተ ትርክት እና የሐሰት ዜናዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማጋለጥ ከሰላማዊ ሰልፍ እስከ የተለያዩ ጋዜጦች ላይ በመፃፍ ለኢትዮጵያ ድምፅ የሆኑ መኖራቸው ይታወቃል።ሆኖም ግን በውጭ ሀገሮች ከሚኖረው ከፍተኛ አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ አንፃር የዝምተኞች እና ዳር ተመልካቾች መብዛት ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት ነው።
የፅንፍ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላለው የንፁሃን እልቂት ተጠያቂ እና ምክንያት መሆናቸውን በመሸፈን ያደረጉት መጮህ የአሜሪካን ምክር ቤት አባላትን እስከ ማሳሳት ደርሷል።በእርግጥ የአሜሪካ ምክር ቤት እውነተኛው መረጃ ሳይገባው ቀርቶ ነው ለማለት አይቻልም።የምክር ቤት አባላቱ ከ200 በላይ የሚሆኑ ንፁሃን በግፍ የተገደሉበት አንዱ መነሻ በአሜሪካ ጭምር የሚኖሩ የፅንፍ ኃይሎች ቅስቀሳ መሆኑን ያውቃሉ።ሆኖም ግን ስለ ንፁሃኑ መገደል አንዳች አልተነፈሱም።ይህ ሁኔታም በራሱ የምክር ቤት አባላቱ የሌላ የአሜሪካ የውጪ ፖሊሲ ማስፈፀምያነት የሰሞኑን የኢትዮጵያ ሁኔታ ለመጠቀም የሞከሩ ይመስላል።የምክር ቤቱ አባላት የኢትዮጵያን የአንድነት ጉዳይ ከዲሞክራሲ እና ከሰብዓዊ መብት መርሆዎች አንፃር ብቻ እየተነተኑ ለማቅረብ ከሞከሩ በራሱ አደጋ ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ ግን በመጨረሻ መሰመር ያለበት ጉዳይ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለውጪ መንግሥታት የማስረዳት ታሪካዊ ኃላፊነት ከምንግዜውም በላይ በእነርሱ ላይ መውደቁን ሊረዱት ይገባል።ለእዚህም ያስተማረቻቸውን ሀገር ሳይመሰክሩላት በዝምታ ድባብ የሚኖሩ የዳር ተመልካች ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መነሳት ይገባቸዋል።በእዚህም መሰረት የፅንፍ ኃይሎችን ተግባር እና በውጪ በሀገር ቤት በንፁሃን ላይ የእልቂት ተግባር እንዲፈፀም የሚቀሰቅሱትን ሁሉ ከተግባራቸው እንዲታቀቡ እውነታውን በእየሃገራቱ ለሚገኙ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች፣የድረ ገፅ እና የህትመት ጋዜጦች፣የፓርላማ አባላት እና ፖሊሲ አውጪዎች ሁሉ የማስረዳቱን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው።ከእዚህ በተጨማሪ የማኅበራዊ ድረ-ገፆቻቸውን በመጠቀም ለቀሪው ዓለም እውነታውን ለማሳወቅ መድከም ይገባቸዋል።
ከእዚህ በታች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነሐሴ 21/2020 ዓም የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ በፅንፍ ኃይሎች የሚፈፀመውን የጥፋት ተግባር ባላገናዘበ መልኩ በኢትዮጵያ ባለው የውስጥ ጉዳይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በስልሳ ቀናት ሪፖርት እንዲያቀርብ የጠየቁበት ደብዳቤ ነው።የብዙ ኢትዮጵያውያን ዝምታ እና የዳር ተመልካችነት እንዲህ ኢትዮጵያን እንደሚያስጠቃ መረዳት ይገባል።
===========================//////=====================
No comments:
Post a Comment