ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, August 29, 2020

የትምህርት ሚኒስቴር ላለፉት 27 ዓመታት በተሳሳተ ሥርዓተ ትምህርት ኢትዮጵያን እንደከፋፈለ ዳግም እንዲከፋፍል ሊፈቀድለት አይገባም።

የትምህርት ሚኒስቴር ዋና መስርያ ቤት በቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ዘመን (1950ዎቹ መጨረሻ) አዲስ አበባ ልዩ ስሙ አራት ኪሎ ግንባታ ላይ ሳለ 

ኢትዮጵያ የኅብረብሔር ሀገር ነች።በዘመናት ሂደት ህዝቧ ከሰሜን ደቡብ፣ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በንግድ፣በጦርነት፣በስደት፣በተፈጥሮ አደጋ እና በሌሎች ምክንያቶችም እየተንቀሳቀሱ እርስ በርስ ተዛምደዋል፣ተዋልደዋል።ይህ በታሪካችን የነበረ ዕውነታ ነው።በምሳሌነት የዝዋይ ደሴት ነዋሪዎችን ብንመለከት ከላይ የተጠቀሰው የህዝብ የአኗኗር ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው።በዘጠነኛው ክ/ዘመን የተነሳችው እና አያሌ አብያተ ክርስቲያናትን ያቃጠለችው ዮዲት ጉዲትን ሸሽተው ታቦተ ፅዮንን ይዘው የተሰደዱት ካህናት እና አብሯቸው ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የመጣው ሕዝብ በዝዋይ ደሴት ሰፍሮ ነበር።ታቦተ ፅዮን ስትመለስም ከመላው ኢትዮጵያ የመጣው ሕዝብ ግማሹ ስመለስ ሌላው እስካሁን ዝዋይ ደሴት ቀርቷል።በእዚህም መሰረት በዝዋይ ደሴት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጡ ቃላት በአንድነት የፈጠሩት ዘዬ የተሰኘ መግባብያ ፈጥረው ይኖራሉ።በመሆኑም የዘዬ ሰዎች ዛሬም ሲናገሩ ከጉራግኛ፣ከአማርኛ፣ከትግርኛ እና ከሌሎችም የተቀየጡ ቃላት መስማት የተለመደ ነው።

ኢትዮጵያ እንዲህ ነች።እርስ በርሷ የተጋመደች፣የተዛመደች እና የተጣመረች ነች።ይህ ሁኔታ የአንዱ ስልጣኔ የተለየ፣የሌላው ዝቅ ያለ ብሎ መውሰድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም።በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለፈው የህዝቡ ታሪክ የራሱ የሆነ በዘመናችን የሚጠራው የዲሞክራሲም እንበለው የመንግስት ስርዓት ወይንም የአካባቢ አስተዳደር ዘይቤ አለው።ለሺህ ዓመታት የነበረው የነገሥታቱ የንግስና ስርዓትም ሆነ የኦሮሞ ገዳ ስርዓት፣ፍትሐ ነገሥትም ሆነ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ሁሉም በኢትዮጵያ ምድር ያለፉ ናቸው እና በሚገባ መጠናት፣በቂ ምርምር ማድረግ እና መመርመር ይፈልጋሉ።

ይህንን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በግብታዊነት የተወሰነ ውሳኔ በሚመስል መልክ የትምህርት ሚኒስቴር የገዳ ስርዓት በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ ክልል ከ2013 ዓም የትምህርት ዘመን ጀምሮ እንዲሰጥ መወሰኑን ነሐሴ 23/2012 ዓም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በምሽት ዜና እወጃው ላይ  ማስታወቁን ለማወቅ ተችሏል። 

ይህ ውሳኔ ግን በራሱ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል።በመጀመርያ ደረጃ የገዳ ስርዓት የኢትዮጵያ ተማሪዎች መማር የለባቸውም የሚል ተቃውሞ በደረቁ ያነሳ የለም።በእዚህ ፅሁፍም ላይ ይህ አይደለም የሚንፀባረቀው። የትምህርት ሚኒስቴር የወሰነበት ሂደት እና አፈፃፀሙ ግን በራሱ ብዙ ጥያቄ ያጭራል።የትምህርት ሚኒስቴር በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የሚሰጡ ትምህርቶችን ወጥነት ባለው መልክ እንዲሰጡ የማድረግ ግዴታ አለበት።በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት እና ሶስት አይነት ትምህርት እየሰጠ ትውልድ የሚነጣጥል ተግባር መስራት በራሱ ወንጀል ነው።እዚህ ላይ አንድ መርሳት የሌለብን ጉዳይ የገዳ ስርዓት ታሪክ በኢትዮጵያ ሁሉም ትምህርት ቤቶች እና ዩንቨርስቲዎች በዘመነ ደርግም ሆነ በቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ዘመን  በታሪክ ትምህርት ውስጥ  ራሱን በቻለ ምዕራፍ ተሰጥቶት ተማሪዎች ይማሩት ነበር።ይህ አሁን ያልነበረ የሚመስላቸው ካሉ ተሳስተዋል።ኢህአዴግ ስለ ገዳ ማውራት የጀመረ የሚመስላቸው አይጠፉም።ደርግ በኢትዮያ የብሔር ብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ አስጠንቶታል። ሆኖም ግን ደርግም ሆነ በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን በታሪክ ትምህርት ውስጥ ገብቶ ተማሪዎች እንዲማሩት የተደረገው ሀገር በሚከፋፍል አንዱ የእናት ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ በሚመስል እና በሚነጣጥል መልኩ አልነበረም። በወቅቱ ትምህርቱ ትምህርቱ የሚሰጠው  የኢትዮጵያ ታሪክ ትምህርት የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ከአክሱም እስከ ሞያሌ፣ከጅጅጋ እስከ ጎንደር በታሪክ ትምህርት ውስጥ የሌላውን የኢትዮጵያ ታሪክ ሲማሩ ራሱን በቻለ ምዕራፍ የገዳ ስርዓትን  በዝርዝር በሚያስረዳ መልኩ ከሌላው የኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በአንድነት ነበር። 

የሰሞኑ የትምህርት ሚኒስቴር በተናጥል አስተምራለሁ ያለው ትምህርት ግን የገዳ ስርዓት የሚባል ትምህርት ለብቻው ለአዲስ አበባ እና ለኦሮምያ ክልል እሰጣለሁ የሚል ነው። እዚህ ላይ ጥያቄው የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲህ እየነጠለ የእየብሄረሰቡን ትምህርት በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በማስገባት እና ለየብቻው እየሰጠ ይዘልቀዋል? ወይንስ ለገዳ ስርዓት ብቻ ነው የተፈቀደው? ለምንስ ነው የኢትዮጵያ የተለያዩ የዲሞክራሲ ባህሎች በአንድነት ተሰብስበው በእዚሁ ስር የገዳ ስርዓትም ገብቶ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲማሩ የማይደረገው? ኢትዮጵያ ለዘመናት የተዳደረችበት ለዓለም አቀፍ ሕግም ያበረከተችው ፍትሐ ነገስት የሚባል ስርዓት እንዳላት የትምህርት ሚኒስቴር አልሰማም? ከገዳ ስርዓት ጋር ለምንድነው ኢትዮጵያውያን የማይማሩት? መማር አይጎዳም።ተማሪዎች ዛሬ የሀገራቸውን የነበረ እና የዳበረ የማሕበራዊ እሴቶች ታሪክ ማወቃቸው ነገ የተሻለውን አውጣጥተው ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለሀገራቸው አዲስ ሃሳብ እንዲያፈልቁ ይረዳል።

የትምህርት ሚኒስቴር ዋና መስርያ ቤት አዲስ አበባ (አራት ኪሎ) 

በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር የገዳ ትምህርትን ለብቻው ለአንዱ ክልል እሰጣለሁ ከማለት ይልቅ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድ ማዕድ የገዳ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ እሴቶች ለምሳሌ ፍትሐ ነገስት፣የኮንሶ ባህላዊ እሴቶች፣የአክሱም ጥንታዊ ስርዓቶች፣የሐረር እና የጅማ የንግድ ባህሎች ሁሉ ያካተተ ስርዓተ ትምህርት ቀርፆ ሁሉንም ኢትዮጵያን እንዲያስተምር ሕዝብ ግፊት ሊያደርግበት ይገባል። የትምህርት ሚኒስቴር ላለፉት 27 ዓመታት በተሳሳተ እና በከፋፋይ የትምህርት ፖሊሲ ኢትዮጵያን እንደከፋፈለ ዳግም እንዲከፋፍል ሊፈቀድለት አይገባም።የትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠውን ርዕይ፣ተልዕኮ እና እሴቶች ብሎ ላስቀመጣቸው ገዢ ሃሳቦች ተገዢ እንዲሆን ደግመን ልንነግረው ይገባል።

ከእዚህ በታች የትምህርት ሚኒስቴር ርዕይ፣ተልዕኮ እና እሴቶችን እንመልከት እና አሁን እየነጠለ እና እየከፋፈለ ለመስጠት የምሞክረው ትምህርት ምን ያህል ከራሱ ጋር እንደሚጣላ መመልከቱ በቂ ነው። ፍትሃዊ የትምህርት አሰጣጥ ማለት የሁሉንም ያቀፈ ትምህርት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መስጠት እንጂ እየነጠሉ ብሔሮች የራሳቸውን ታሪክ ብቻ እንዲያጠኑ መወሰን አይደለም።ትምህርት ድንበር የለውም።በትምህርት የአሜሪካንን ታሪክ እያጠናን የአክሱምን የመንግስት ስሪት ወይንም የጎንደርን የቤተ መንግስት ስርዓት ለጅማ እንዳያውቅ ማድረግ ወይንም የአባ ጅፋርን የቤተ መንግስት ስርዓት እና የገዳ ስርዓትን ለወሎ እና ለጎጃም ተማሪ እንዳያውቅ ማድረግ በርሱ የትምህርትን መሰረታዊ መርህ የሚፃረር ተግባር ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር  የተቀመጠለት ርዕይ

ብቁ ዜጋ የሚያፈራ፣ ጥራትና ፍትሃዊነት ያረጋገጠ የትምህርትና ስልጠና ስርአት በቀጣይነት መገንባት ነው!

የትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠው ተልእኮ

የትምህርት ዘርፉን የማስፈጸም አቅም በመገንባት፣ የብቃት መለኪያዎችን በማውጣትና በማስጠበቅ፣ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትን በማስፋፋት፣ እንዲሁም ተግባሮቻችንን በህዝብ ግንኙነት ስራ በማገዝ ጥራት ያለው ውጤታማና ፍትሃዊ የትምህርትና ስልጠና ስርአትን ማረጋገጥ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር እሴቶች

- ውጤታማነት
- ጥራት
- ፍትሃዊነት
 -አሳታፊነት
 - አርአያነት
 -የአላማ ጽናት
 - ልቆ መገኝት

================////===========================

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...