ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 19, 2021

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ - ትግራይ ክልል፣የአማራ ክልል፣ወቅታዊው የምጣኔ ሀብት እና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ዲፕሎማሲ ሁኔታ

አዲስ አበባ Addis Ababa
Photo Getty images

  • ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ላይ ብትሆንም ይህ ፈታኝ ሁኔታ ይዞላት የመጣው ዕድል ደግሞ አለ።

ጉዳያችን ምጥን ዳሰሳ 

መነሻ 

የኢትዮጵያ ወቅታዊ  ሁኔታ በተመለከተ የተለያየ ሰው ካለው መረጃ እና የቀደመ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር እንዲሁም ወደፊት እየሄደችበት ካለው ሁኔታ አንፃር የየራሱን ዕይታ ይሰጣል።በተለይ የእኛ ማኅበረሰብ የመረጃ ምንጩም ቡና ሲጠጣ በሚ ወያየው፣ወይንም ከሚኖርበት መንደር ውስጥ የተሻለ ግንዛቤ አለው ብሎ የሚያስበው ሰው የሚሰጠው አስተያየት፣ ከእዚህ ባለፈ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ለምሳሌ እንደ የአሜሪካ ድምፅ እና የጀርመን ራድዮ በሃገርኛ መግባብያ የሚያዘጋጁት  የምዕራቡን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች ናቸው።ከእዚህ በተለየ ግን አሁን ባለው ሁኔታ የማኅበራዊ ሚድያ እንደፈለገ የሚነዛው የሐሰት ወሬ ሌላው የአብዛኛው ህዝባችን የመረጃ ምንጮች ናቸው።

እዚህ ላይ የመንግስት እና የግል መገናኛ ብዙሃን የመረጃ ምንጭነትን መዘንጋት አይገባም።ከእነኝህ የመረጃ ምንጮች በተለየ ግን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ሕዝብ እንዲረዳው ትክክለኛ የመግለጥ እና የማስረዳት ሥራ ያስፈልጋል።መረጃዎች በድፍን ለሁሉም ሕዝብ መረጃ አይሆኑም።ያልተቆረጠ ብርቱካን ብርቱካኑን ቆርጦ  እንዴት እንደሚበላ ለማያውቅ ልጅ መጫወቻ እንጂ የሚበላ መሆኑን አያውቅም።በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም እንዲሁ ለሕዝቡ እንዴት ጉዳዮችን ማየት እንዳለበት በቅጡ ዕይታን ማቅረብ ያስፈልጋል እንጂ ድፍን መረጃዎች እና ዜናዎች ብዥጎደጎድ ዜናውን እና መረጃውን እንዴት እንደሚረዳው ለማያውቅ ሕዝብ የፈለገው በፈለገው መንገድ እየትነተነ የሚያሳስት እና ሽብር የሚነዛ ሞልቷል። በመሆኑም አሁን ያለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ በተመለከተ ጉዳያችን ምጥን ዳሰሳ እንደሚከተለው ታቀርባለች።

ትግራይ ክልል

ትግራይ ክልል አሁን ህዝቡ ያለበት ሁኔታ ከተለያዩ በእርዳታ ድርጅቶች ሰራተኝነት በክልሉ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሰራተኞች የሚሰማው በጣም አሳዛኝ ነው።ክልሉ ትምህርት ቤቶችን ወደ የማሰልጠኛነት ቀይሮ የትምህርት ቤት መቀመጫ ሳይቀር እየተፈለጠ ለማገዶ መጠቀም ተጀምሯል።መብራት የለም፣የጤና ጣብያዎች ፕላስተር ብርቃቸው ሆኗል።የምግብ ዋጋ ይህን ያህል ነው ለማለት መጀመርያ ባንክ ኖሮ ገንዘቡ ሲገኝ ነው።ባጭሩ ክልሉ የሚገኙ ከተሞች ወደ ድንጋይ ዘመን እየተምዘገዘጉ ነው። ቀድሞ የነበሩ ፋብሪካዎች እነሞሰበ ሲብንቶ ፋብሪካ መኪናዎች ከአማራ ክልል ለመዝረፍ እንደወጡ ሲመለሱ የአስከሬን ክምር እየጫኑ ያውም እድለኛ የሆኑት ወደ ትግራይ ሲመለሱ የቀሩት በሰቆጣ፣አላማጣ የቆረጠው መከላከያ እና ልዩ ኃይል መመለሻ አጥተው እዚሁ ወሎ እና ደቡብ ጎንደር ቆላዎች እየታከኩ ከቦታ ቦታ እየተንከራተቱ ነው።

ሽብርተኛው ህወሓት ወደ አማራ ክልል እና አፋር ጀሌውን የላከው በሳምንት ውስጥ የጅቡቲ አዲስ አበባን መንገድ እዘጋለሁ፣ወደ ሱዳን የሚወስደውን መንገድ አስከፍታለሁ፣ የቆመውን የመብራት እና የበጀት ገንዘብ በእዚህ አስገድጄ አስለቅቃለሁ የሚሉ ነበሩ። ሆኖም ግን በአፋር ክልል ለቁጥር የሚያታክት ሰራዊቱ ከአፋር አሸዋ ጋር ተደባለቀ።አስከሬን ለመቅበር ሳምንታት አልበቃ አለ።ይህ በእንዲህ እያለ ትግራይ ልጆቻቸውን ፈልገውም ሳይፈልጉም የላኩት ልጆቻቸው ማለቃቸውን ህወሓት ባይነግራቸው የእናት ስድስተኛ የስሜት ህዋሳቷ ይነግራታል።ለእናቶች መልስት መስጠት ያልቻለው የጌ ታቸው ረዳ ቡድን ያለው አማራጭ ድል እያደረግን ነው እያለ መዋሸት ነው።የትግራይ ክልልን ሁኔታ የሚገልጠው አባባል ህወሓት ወደ የድንጋይ ዘመን እየቀየራት ነው።ይህ በእዚሁ ከቀጠለ ደግሞ ለመጪዎቹ 30 ዓመታትም ተመልሳ ለመነሳት የምትችልበት ሁኔታ አይሆንም።እውነታው ይሄው ነው።እነጌታቸው እና ደብረ ፅዮን አይናቸው እያየ አንድ ብርጭቆ ውሃ እና የአንዲት አንፖል መብራት አገልግሎት ለሕዝቡ የማያቀርቡ ከመቀሌ አድዋ የሚመላለሱ በጭንቀት የተወጠሩ ሆነው ነው የቀሩት።ይህንን ተመልክቶ ለለውጥ ህዝቡ እንዳይነሳባቸው ደግሞ በጦርነት መወጠር ስላለባቸው እየሰበሰቡ ወደ አማራ ክልል ዘርፈህ ብላ ብለው ይልኩታል። 

የአማራ ክልል

የአማራ ክልል በጎጠኛው ህወሓት ግልጥ እና ስውር ተግባሮች አማካይነት በርካታ የማዳከም እና ሕዝቡን እንደህዝብ የማደህየት ሥራ ሲሰራ ኖሯል። በአሁኑ ጊዜ ክልሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በተለይ በህወሓት ዘረፋ እና ወረራ ምክንያት ይዟል።ይህ በራሱ የሚፈጥረው ጫና ቢኖርም ክልሉ ግን በአሁኑ ጊዜ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚባል ደረጃ ሽብርተኛ ህወሓትን ለመመከት ተነስቷል።በእዚህም  ሺዎች ወደ ስልጠና ገብተዋል።ሌሎች ሺዎች ደግሞ ታጥቀው ፍልምያ ገብተዋል።አሁን በአማራ ክልል ሰርጎ የገባው የህወሓት ጀሌ  በተበታተነ መልኩ በዘረፋ እና አንዳንድ ቦታ ሸሽተው የተበተኑት እንደገና ለመሰባሰብ እየሞከሩ መንደሮች ላይ ጥቃት ይፈፅማሉ። በገጠር ነክ የወረዳ ከተሞች ቀድሞም ከወረዳው ያለፈ የፖሊስ ኃይል  ስለሌለ እየተደበቁ እየገቡ ፎቶ መነሳት እና ሽብር ፈፅሞ መውጣት ከእዚህ ባለፈ ደግሞ ሴቶችን መድፈር፣ንብረት መዝረፍ እና ከተሞች ላይ ለምሳሌ ወልድያ እና ደብረታቦር ከተማ ላይ ከባድ መሳርያ በመተኮስ አለን ለማለት ይሞክራሉ።እዚህ ላይ በአማራ ክልል አንዳንድ በወንጀል የተገለሉ እና ከወረዳ ስልጣን የወረዱ ከሽብርተኛው ቡድን ጋር እየተመሳጠሩ በሕዝቡ ላይ ደባ ለመስራት የሞከሩትን ህዝቡ በአደባባይ እርምጃ መውሰዱ ነው እየተሰማ ያለው። 

የአማራ ክልል ሕዝብ አሁን ምናልባትም በቅርብ ታሪኩ በእዚህ ደረጃ ታጥቆ አያውቅም።በርካታ ጀግኖች በየቀኑ እየወጡ ነው።ታንክ ላይ ዘለው ገብተው ተዋጊውን በስለት የሚያወርዱ፣ምግብ ቤት ገብተው ሊመገቡ ያሉትን አስራ አንዱ ላይ አንዱ ብቻውን እርምጃ የሚወስድበት እና መትረጌስ ከሚተኩሰው ሰው ጀርባ ድንገት ደርሰው በዱላ የሚማርኩ ብዙ ያልተነገረላቸው ጀግኖች ወጥተዋል።የህወሓት ጀሌ አሁን በየትም ከተሞች ታየ ቢባል እውነታው አንድ ነው። ይሄውም በገባበት የሰሜን ወሎ መስመር መውጣት እንደማይችል ግልጥ ሆኗል ስለሆነም ሰተት ብሎ የገባበት ወጥመድ ለመውጣት መንከራተቱ ሒደ ላይ ነው አሁን እዚህ ከተማ ታዩ እስህ ከተማ ከባድ መሳርያ ጣሉ እየተባለ የሚወራው።ብዙዎቹ ገባንባቸው የሚሉት ከተሞች ደግሞ የፎቶ ከተሞች ናቸው።የአማራ ክልል ይህንን የህወሓት ወረራ ከመቀልበስ አልፎ የትግራይን ሕዝብ ከህወሓት የማላቀቅ አቅም አለው።ይህንን አቅም ደግሞ በቁጭት እንዲሰራ የሚያደርገው የራሱ የህወሓት የጭካኔ ተግባር ነው።የአማራ ክልል ይህንን ወረራ በሕዝብ ደረጃ እንዲመቀት ያደረገው ዘግይቶ ነው።ህወሓት ግን ሕዝቡን በግድም በውድም ያለውን እንጥፍጣፊ የሰው ኃይል ሳይቀር ወደ አማራ ክልል የላከው ዘርፋችሁ ብሉ ብሎ ነው እንጂ እንደማያሸንፍ ያውቀዋል።ሌላው ቀርቶ ዛሬ በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ሶስት የከባድ መሳርያ የተኮሱት ሶስቱ ጀሌዎች ውስጥ ሁለቱ ወዲያው እርምጃ ሲወሰድባቸው አንዱ መማረኩ ለማወቅ ተችሏል።የአማራ ክልል በተመለከተ ጠንካራ የደህንነት ሥራ፣የቁሳቁስ እና የገንዘብ እርዳታ እና በወረዳ እና ታች ቀበሌ ደረጃ ያሉ አመራሮች አቅም በጊዝያውነትም ቢሆን ህዝቡ ጣልቃ እየገባ የአስተዳደር ስራዎቹን ማገዝ አስፈላጊ ነው 

 ወቅታዊው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት

ጦርነት የምጣኔ ሀብት ይበላል።በተለይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሽብርተኛው ህወሓት እጅ ዛሬም የሚ ዘወርበት መንገድ በመኖሩ በምጣኔ ሃብቱ ላይ ከባድ ሴራ እየተበተበ ነው።በመሆኑም የዋጋ ንረቱ ቀላል አይደለም።ይህ ብዙ ጊዜ የተባለ ነው።አሁን መንግስት እና የግሉ ዘርፍ ይህንን የምጣኔ ሀብት ችግር በተመለከተ መውሰድ የሚገባቸው ሶስት እርምጃዎች አሉ። እነርሱም -
1) በተመረጡ ትልልቅ ከተሞች መንግስት መሰረታዊ ፍጆታዎች ከገበያው በተሻለ ዋጋ መንግስት ማቅረብ አለበት።ይህ ከመንግስት ሰራተኞች ጀምሮ እስከ የከተማ ድሆች ድረስ ለመጪዎቹ ጥቂት ወራት መዝለቅ ይችላል።የቀድሞው ወታደራዊ መንግስት በጦርነት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ለከተማ ነዋሪ በቀበሌ ኅብረት ሱቅ አማካይነት በማቅረቡ ሕዝቡ በቅናሽ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ፍጆታዎች ያገኝ ነበር።

2) በተወሰኑ የምግብ ሸቀጦች እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ ቀረጥ በግዚያዊነት ማንሳት ወይንም በጣም መቀነስ የዋጋ ቁጥጥር ማጠናከር እና 

3) ከመስከረም ጀምሮ የሚሰበሰበው የእህል ምርት በቁጠባ መጠቀም እንዲቻል መንግስት በባንኮች ካለው ገንዘብ በብድርም ቢሆን በመውሰድ ወይንም እራሳቸው ባንኮቹ በስራው እንዲገቡበት እና በሚያገኙት መጠነኛ ትርፍ ዋናቸውን እንዲመልሱ በማድረግ ከገበሬው ላይ እህል መንግስት በብዛት መግዛት እና መልሶ በተመጣጣኝ ዋጋ የመሸጥ ሥራ ማከናወን።በእዚህ ከልክ የለሽ አትራፊ ምርቱን ከማዳን ጀምሮ ተጠቃሚውም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ይረዳዋል።


የኢትዮጵያ ወቅታዊ ዲፕሎማሲ ሁኔታ

ኢትዮጵያ የራሷን መብት ስታስከብር እና በምዕራባውያን ጫማ ልክ ማሰብ ማቆሟን የተረዱት ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የቻሉትን ያህል ዘመቱባት።በሽብርተኛው ህወሓት ጎን ሆነው አዋከቧት።ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ተመላለሱ።መመላለሳቸው ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ጉዞ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን እነርሱ ባሉት መንገድ ለማስገደድ እና እጅ ለመጠምዘዝ ተነሱ። ይህ ሁኔታ ላለፉት ወራት ቀጥሎ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ጉዳይ ዘንድሮ ከጂ 7 ስብሰባ እስከ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ድረስ ተነሳ።ኢትዮጵያ በእዚህ ዓይነት ደረጃ ርዕስ የሆነችው ምናልባት በ1977 ዓም በደረሰው የድርቅ አደጋ ሊሆን ይችላል። 

ይህ የተበላሸ የዲፕሎማሲ ሂደት አንዱ ዓላማ ለምዕራቡ ፍላጎት የታዘዘ አመራር በአራት ኪሎ ለማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ይህ ካልሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን መበተን እና እንደ ሶርያ፣የመን እና ሊብያ እርስ በርሷ የምትጋደል ሀገር መፍጠር ነው።ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ በትናንትናው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የቱርክ ጉብኝት ነፋሱን ቀይሮታል። በእዚህም ኢትዮጵያ በይፋ የዲፕሎማቲክ ማጥቃት ጀምራለች። የምስራቅ አፍሪካ አራት ሀገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ጅቡቲ፣ኤርትራ እና ሱማልያ ለማስተባበር ኢትዮጵያ በዶ/ር ዓብይ  አነሳሽነት የተጀመረው ሥራ ፍሬ የማግኘት እድሉ እያደገ ነው።በእዚህም ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር የዋይት ሃውስ ባለስልጣናትን አስደንግጧል።በእዚህም ኢትዮጵያ ለምዕራቡ ዓለም ምላሽ '' መፈንቅለ ዲፕሎማሲ  '' (Diplomatic coup d'etat  ) አድርጋለች ማለት ይቻላል።በእዚህም ኢትዮጵያ የነበረውን የዲፕሎማሲ ከባቢያዊ ሁኔታ ቀይሮታል።በቀጣይ የሚታዩት ውጤቶች የምናየው ነው።ሆኖም ግን ከግብፅ እና ሱዳን አንፃር ራሱን የቻለ ማስጠንቀቅያ ያዘለ ነው።አሜሪካም በቀጣይ የአካሄድ ለውጥ ማድረግ እንዳለባት ከማመን ውጭ በያዘችው የደረቀ አካሄድ ልሂድ ብትል የፖሊሲ መሰበር እንደሚገትማት ግልጥ በሆነ መልዕክት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እንዳገኘች መረዳት ይቻላል።የቱርክ ወዳጅነት ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ አይደለም ዛሬ ምሽት የሱማልያው ፕሬዝዳንት ፈርማጆ ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ ከቱርክ ከተመለሱ በኃላ በትውተር ገፃቸው ላይ በቱርክ እና በሱማልያ መካከል ያለው ግንኙነት የጠነከረ መሆኑን በማመስገን ፅፈዋል።



ይህ ማለት ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው የዲፕሎማሲ አፀፋዊ ምላሽ የአካባቢ ሃገራት ማለትም በሱማልያ እና ኤርትራ አንፃርም የተናበበ መሆኑ ለምዕራቡ ዓለም በቀላሉ ለመሰርሰር እንደሚያስቸግረው አመላካች ነው።ለእዚህ ነው ያላቸው አማራጭ በደረቀ ፖሊሲ ቀጥሎ ፖሊሲው ሲሰባበር ማየት ወይንም ነገሮችን አለሳልሶ መደራደር እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሮ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጥቅም ላይ መደራደር።በህደቱም የህወሓት ሽብርተኛ ጋር የሚኖር ግንኙነት እና ድጋፍ ማቆም ያላቸው አማራጭ ነው።

ባጠቅላይ ኢትዮጵያ በምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ላይ ብትሆንም ይህ ፈታኝ ሁኔታ ይዞላት የመጣው ዕድል ደግሞ አለ። የመጀመርያው ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ውትድርና ብዙ ሕዝብ አይመለመልም የሚል ማሳሰብያ በተወካዮች ምክርቤት ስብሰባ ተናግረው ነበር።ን ይህ ተቀይሯል።የህወሓት ወረራ ኢትዮጵያ የብዙ መቶ ሺዎች ሰራዊት ባለቤት ያደርጋታል።ይህም በአካባቢው ካሉ ሀገሮች በተሻለ ብቻ ሳይሆን በአሸናፊነት እንድትወጣ ብቻ ሳይሆን ለመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ ሀገሮች ዛቻም የማትቀመስ  አድርጎ ያወጣታል። በሌላ በኩል በምዕራብ ወጥ የትብተባ አዙሪት የምትወጣበት እና በራሷ የምትራመድበት ወርቃማ ጊዜ ይፈጥራል። ይህ ብዙ ማለት ነው።ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ባሕል እና ስልጣኔ ያላት ሀገር በመሆኗ ከተፈጠሩ ሁለት መቶ ዓመታት ገደማ የሆናቸው በቀላሉ የምያጠፏት አድርጎ የማየት አባዜ ይቀበራል ወይንም ሽባ ይሆናል።ስለሆነም የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ተስፈንትራ ለመውጣት የምችልበት  እጅግ ወርቃማ ጊዜ ነው። ይህ ግን የሚሆነው ኢትዮጵያን ከሽብርተኛ ህወሓት እጅ አስጥሎ በመረጠችው መንገድ የመሄድ እና ከድህነት የመውጣት እድሏን ከፍ ያደርገዋል።ስለሆነም የኢትዮጵያ መንገድ አዋጭ ብቻ ሳይሆን አፍሪቃንም ይዛ እንድትነሳ የሚያደርግ ሂደት ነው። ይህንንም የሚያውቁት ምዕራባውያን  ኢትዮጵያ የህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ተጭኖባት ስትራኮት እንድትኖር ሽብርተኛውን ቡድን ሲደግፉ ይታያሉ። ይህ ግን አዋጭ እንዳልሆነ እራሳቸውም ገምግመው አይረዱም ማለት አይቻልም።ግራ መጋባት እና የተሳሳተ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጥቅማቸውን በእዚህ የሚያስጠብቁ መስሏቸው ይለፋሉ።

====================  
================
 ማስታወቂያ / Advertisment
====================
የጓደኞችዎን ወይም የቤተሰብዎን የሞባይል አየር ጊዜ ለማሳደግ ከዚህ በታች ያለውን አገናኝ ጠቅ ያድርጉ።
በአንድ ሁኔታ ውስጥ በሚመገብ ቤት የሚኖር የቤተሰብ እውነተኛ የወዳጅነት ስልክዎ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን የሚመለከት ከስር ሊ መረጃን ይጫኑ - 
Open the link to mobile top up at home


No comments: