ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, August 10, 2021

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣ የክህደት ኃይልን ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳቸውን እንዲያሳርፉ መመሪያ ሰጠ፡፡



በቃን ብለን ከተነሣን ከፊታችን የሚቆም ምንም ዓይነት ኃይል እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው። ውጊያው የትግራይን ሕዝብ ምሽግ ካደረገው እኩይ ኃይል ጋር እንጂ ከትግራይ ጋር አይደለም፤ እናም ስንፋለም መጠቀሚያ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ብሎም መላዋ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ለማውጣትና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስከበር ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣ የክህደት ኃይልን ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳቸውን እንዲያሳርፉ መመሪያ ሰጠ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መልዕክትና ሀገራዊ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ኢትዮጵያ ሀገራችን በዘመናት መካከል ያጋጠሟትን ፈተናዎች እና የተጋጠሟትን የክፋት ኃይላት ሁሉ ድል በመንሣት ታፍራና ተከብራ ነጻነቷን አስጠብቃ ኖራለች።
ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን የውጭ ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባንዳዎችን በማንበርከክ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በነፍሳቸው ተወራረደው ለእኛ አቆይተውልናል። በታሪክ አጋጣሚ ዛሬም ኢትዮጵያ የአጠባ ጡቷን፣ የአጎረሰ እጇን የሚነክሱ ከሐዲዎች፣ ሊያዳክሟትና ሊበትኗት ከቅርብና ከሩቅ ከተነሡ ኃይላት ጋር በመመሳጠር አቆብቁበው ተነሥተዋል።
ሀገራችን የድህነትና የጭቆና ቡትቶዋን አሽቀንጥራ በመጣል ወደ አይቀሬው የብልጽግና ጎዳናዋ ለመግባት ታጥቃ በተነሣችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ትንሣኤችን የማያስደስታቸው ታሪካዊ ጠላቶች፣ ከጉዟችን ሊያስቆሙን እየተረባረቡ ይገኛሉ። ‘እኔ ረግጬ ያልገዛሁዋት ሀገር ትውደም’ የሚል የክህደት ቀረርቶ ሲያሰማ የከረመውም ሕወሐት፣ የጠላቶቻችን መጋለቢያ ፈረስ በመሆን፣ ሰላማችንን ለማደፍረስና ሀገራችንን ለማፍረስ የጥፋት ነጋሪቱን እየደለቀ ይገኛል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የነበረበትን ችግር እያወቀ እንኳን ብዙ ዕድሎችንና ሃያ ሰባት የመታረሚያ ዓመታትን ሰጥቶታል። አሸባሪ ቡድኑ ግን በሤራ ተጠንስሶ በጥፋት ያደገ ነውና፣ የሚብስበት እንጂ የሚታረም አልሆነም። ይህ የጥፋት ኃይል በሕዝብ ቁጣ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላም ቢሆን፣ የተሰጠውን ተደጋጋሚ የመታረም ዕድል ለመጠቀም አልፈለገም። ይልቁንም መቀሌ ላይ መሽጎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች ጋር በማሤር ጊዜውንና የዘረፈውን ገንዘብ ሲረጭ ከርሟል።
በዚህም የተነሣ ግጭት፣ መፈናቀልና አሰቃቂ ግድያን በመላ ሀገራችን መለኮስና ማስፋፋት የዕለት ተግባሮቹ አድርጎ ቆይቷል። የትግራይ ሕዝብ በዚህ ለጥፋት ተጸንሶ ለአፍራሽነት በተወለደ አሸባሪ ቡድን የተነሣ እንዳይጎዳ በማለት፣ መንግሥታችን ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያልሞከረው መንገድ አልነበረም። ስድብና መንጓጠጡ ሳያስቆጣው እስከ መጨረሻው ሰዓት መንግሥት ሁሉንም የሰላምና የሽምግልና መንገድ ተግባራዊ አድርጓል።
በተቃራኒው ይኽ የጥፋት ኃይል የፈጸማቸው ልዩ ልዩ ግፎች አልበቃ ብሎት፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው በታሪካችን የማይረሳ አሰቃቂ ጥፋት ነገሩን ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ አደረገው። ጀግናው የመከላከያ ኃይላችንም ከአማራ እና ከአፋር ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ይሄንን የጥፋት ኃይል መትቶ አከርካሪውን በመስበር፣ የቡድኑ አባላት በተንቤን ጉድጓዶች እንዲወሸቁ ተገድደዋል። ከአመራሮቹ ብዙዎቹ ተደመሰሱ፤ ከፊሎቹ ተማረኩ፤ ጥቂቶቹም በየዋሻውና በሰላማዊ ሕዝቡ ጉያ ውስጥ ገብተው ተሸጎጡ።
ሕግን ከማስከበሩ ተግባር ጎን ለጎን፣ መንግሥት የትግራይ ክልልን ከዚህ የጥፋት ኃይል ነጻ ለማድረግ፣ ያፈረሱትን መሠረተ ልማቶች ለመገንባት፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ለማስቻል፣ ሰብአዊ ርዳታ ለሕዝቡ ለማድረስ፣ በሂደቱ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ለማረምና፣ የጤናና የትምህርት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግ ባለፉት ስምንት ወራት በሙሉ ጉልበቱ ተግቷል።በዚህ ሂደት ውስጥ የጁንታው ርዝራዦች በሕዝቡ ውስጥ ተሠግሥገው ሕዝቡን ለጥፋት እየቀሰቀሱ በሚፈጥሩት ቀውስ የትግራይሕዝብ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር አልቻለም።
የርዳታ ሥርጭትን በማስተጓጎል፣ መሠረተ ልማቶች እንደገና ሥራ እንዳይጀመሩ በማደናቀፍ፣የጤናና የትምህርት ተቋማትን በማውደም፣ የአካባቢ አመራሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ ገበሬው ተረጋግቶ እንዳያርስ የእርሻ ሥራውን በማስተጓጎል፣ የመልሶ ግንባታ ተግባራትን ማደናቀፉን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አደረጉት።
ችግሩን ለማባባስ በሚፈልጉ ኃይላት ጆሮውን የተጠመዘዘው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሂደቱን ውስብስብ ጠባይና የአሸባሪውን የጥፋት ባሕርይ ለመገንዘብ ባለመፈለግ፣እውነትን ትቶ የአጥፊውን አካል ጩኸት አስተጋባ። ቡድኑ በረጅም የሥልጣን ዘመኑ የፈጸመውን አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የሚልዮኖችን ህልውና የማጥፋት ሥራ በዝምታ የተመለከቱ ዓለም አቀፍ አካላት፣ ዛሬ አጥፊውን ኃይል ለራሳቸው አጀንዳማስፈጸሚያነት ስለሚፈልጉት፣ እርሱን ለማዳን ሲሉ የመንግሥትን መልካም ጥረት እንዳላዩ ማለፍን መርጠዋል።
እንደሚታወቀው በሰላማዊው ጊዜ እንኳን በትግራይ ክልል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝብ በሴፍቲኔት ድጋፍ የሚደረግለት ነው።ባለፈው የምርት ወቅትም በአንበጣ መንጋና በኮሮና ምክንያት ሕዝቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት እንዳገኘው ይታወቃል። በዚህ መካከል በትግራይ ከተጀመረው ዘመቻ በኋላ ሌላ የክረምት ወቅት መጣ። ዘመቻው ከቀጠለና ሁለት ክረምቶችን ሳይረጋጋ ካሳለፈ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ቀውስ ከፍተኛ ይሆናል በሚል እምነት፣ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ መከላከያ ከትግራይ አካባቢዎች እንዲወጣ ወሰነ። መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁሙን ያደረገው በዋናነት ለገበሬውና ለሕዝቡ ሲል ነበር።
ያም ሆኖ ሕዝቡ ከአሸባሪው ጁንታ እስከ ዘለዓለሙ ካልተለያየ በቀር፣ ገበሬው ተረጋግቶ ማረስ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል። እንኳንስ የትግራይ ገበሬ ወደ እርሻው ሊመለስ ቀርቶ፣ አሸባሪው ጁንታ በአጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎች እንዳያርሱ ማወክ ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊ ርዳታ እንዳይደርስና ሰብአዊ መብቶች እንዳይከበሩ የሀገር መከላከያ ዕንቅፋት ሆኗል እያለ በክስ ጆሯችንን ሲያደነቁረን እንደከረመ ይታወሳል።
አሁን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የተኩስ አቁም አድርጎ ከወጣ በኋላ ግን ሕጻናት ለጦርነት ሲሰለፉ፤ ርዳታ የጦርነት መሣሪያ ሲሆን፣ እናቶችና ወጣት ሴቶች ሲደፈሩ፣ የእምነት ተቋማት የጦር መለማመጃዎችና የጦር መሣሪያ መጋዘን ሲደረጉ፣ የርዳታ እህል የጫኑ መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ በጁንታው የጥፋት ተግባር ሲስተጓጎሉ፣
በአፋር ክልል በአንድ የሕክምና ተቋም የተጠለሉ ከ200 የሚበልጡ ሰዎችን ሲያርድ ፣ ከ300,000 በላይ ዜጋ ሲያፈናቅል፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እውነታው ምን እንደሆነ ለማወቅ ፍላጎት ያለው አካል ሁሉ ለመታዘብ ችሏል።
ከእውነት ይልቅ ሐሰቱን ማድመቅ የሚፈልጉም በዚያው ተግባራቸው ቀጥለዋል። ለመንግሥት ጥረት ተገቢውን ዋጋ መንፈጋቸው ሳያንስ፣ በርዳታ ሰበብ ጁንታውን የሚደግፍ ተግባር ሲፈጽሙም እጅ ከፍንጅ የተያዙ አሉ።
መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁሙን ከማድረጉ በፊት መቀሌ ውስጥ 400ሺ ኩንታል የርዳታ እህል፣ 2.5 ሚልዮን ሊትር የምግብ ዘይት፣ 14 ሚልዮን ሊትር ነዳጅ፣ 536,979 ኩንታል ማዳበሪያና፣ 37,599 ኩንታል ምርጥ ዘር በመንግሥት ገንዘብ ተገዝቶ ለሕዝቡ ደኅንነት ሲባል አስቀምጧል። መታረስ ከሚችለው መሬት 70 በመቶው እንዲታረስ ተደርጓል።
በተጨማሪ 1079 ሜትሪክ ቶን ምግብ፣ 664 ቶን ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ እና 47,740 ሊትር ነዳጅ በአጋር አካላት በኩል መቀሌ ገብቶ ነበር። ከዚያም በኋላ ቢሆን መንገዶችን በማመቻቸት የርዳታ አቅርቦት እንዳይቋረጥ ተሠርቷል። ለሰብአዊ ርዳታ የሚሆን የአውሮፕላን በረራ ተፈቅዷል።የዚህ ሁሉ ምክንያቱ በአሸባሪው ጁንታ ምክንያት በትግራይ ክልል ያለው ሕዝባችን እንዳይቸገር በማሰብ ነው።
ከሐዲው የጁንታ ቡድን ግን ኢትዮጵያን ለመበተን ከተነሳበት የአሸባሪነት ባህሪው ሊላቀቅ አልቻለም። የአማራንና የአፋር ክልሎችአጎራባች ሕዝቦችን መግደልና መዝረፍ ቀጥሏል። ገበሬዎችን እንዳያርሱ አስተጓጉሏል። ገዳማትን ሳይቀር ዘርፏል። የርዳታ መኪኖችንቸ ወደ ትግራይ ከመግባት አግዷል። መንግሥት መቀሌ ውስጥ ያከማቸውን እህልም ጁንታው አይዘምቱልኝም ላላቸው ሰዎች እንዳይታደል ከልክሏል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንና የክልል ልዩ ኃይሎች መንግሥት የወሰነውን የተኩስ አቁም በማክበር ርምጃ ከመውሰድ ቢቆጠቡም፣ አሸባሪው ጁንታ ግን የድፍረት ድፍረት ተሰምቶት የጥፋት ሥራውን ቀጥሎበታል። የሕወሐት ዓላማና ግብ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንደሆነ አመራሮቹ በእብሪት ተናግረዋል። ለዓላማው መሳካትም በብዙ የውጭ ኃይሎች በመታገዝ ለበለጠ ጥፋት ምላጭ መሳብን መርጧል።
ወጣቶችን በእኩይ ፕሮፓጋንዳ በመደለልና ሕጻናትን በሐሽሽ እንዲናውዙ በማድረግ ለጦርነት እየመለመለ፣ በአፈሙዝ የሚነዱ አዛውንቶችን ጭምር እያሰለፈ ይገኛል። የአሸባሪው ጁንታ አካሄድ ሕዝብ አስጨራሽ የሆነ የሽፍትነት አካሄድ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ በተደጋጋሚ ተናግረናል፤ አስጠንቅቀናል።
ጁንታው እየከፈተ ያለው ጥቃት ሕዝባዊ መልክ እንዲይዝ በማድረግ ስለሆነ መመከት የሚገባውም በዚያ አግባብ ነው፤ የመላው ሕዝባችንን የማያዳግም ምላሽ ሊያገኝ ይገባል።
ባለፉት ጊዜያት ሕዝባችን በአራቱም አቅጣጫ አሸባሪውን የሕወሐት ኃይል ከታሪክ ገጽ ለመደምሰስ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። ሕዝባችን በቁርጠኝነቱ እንደሚገፋበት ምንም ጥርጥር የለውም።
የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች፣ ይህንን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣ የክህደት ኃይልና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳችሁን እንድታሳርፉ አቅጣጫ ተቀምጦላችኋል።
ሀገር በመከላከል ዘመቻው ለመሳተፍ እድሜያችሁና ዐቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የሀገር ዘብነታችሁ የምታሳዩበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው።
የጸጥታ ኃይሎችን በቀጥታ ለመቀላቀል ያልተቻለው የኅብረተሰብ ክፍል ከመቼም ጊዜ በላይ ወገቡን አሥሮ በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት። የመንግሥት ሠራተኛውም በሙሉ ዐቅሙ ያለ ቢሮክራሲ ሥራውን ያከናውን።ሁሉም ዜጋ ነቅቶ አካባቢውን ይጠብቅ።
የጁንታው ተላላኪዎች የጥፋት ተልዕኳቸውን እንዳይፈጽሙ ሕዝባችን በዓይነ ቁራኛ ይከታተል። ከዚህ ባለፈ ለሠራዊቱ የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀትና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ብርቱ ደጀን ይሁን።ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ሕዝቡ ከሀገሩ ጎን እንዲቆም የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ ይጠበቃል።
አሸባሪው ጁንታ ሰላማዊ ሰዎች አስመስሎ በየአካባቢው ያሠማራቸው ሰላዮችና የጥፋት ተላላኪዎችን ለመከታተልና ለማጋለጥ እንዲቻል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ዐይንና ጆሮ በመሆን ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሊሠራ ይገባል። የሃይማኖት አባቶች በጸሎት፣ የሐገር ሽማግሌዎች በምክር፣ ሁሉም ዜጋ በችሎታው ኢትዮጵያን ብሎ ይቁም።
ቀደምቶቻችን እንዲህ ሀገር የሚያጠፋ ጠላት ሲገጥማቸው ስንቃቸውን በአህያ፣ አመላቸውን በጉያ አድርገው ዘምተዋል። ሴቶችና ወንዶች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች እንደ አንድ ሠራዊት ተምመዋል። መሥዋዕትነት ከፍለውም ሀገራቸውን አድነዋል። ዛሬ ያ ታሪካዊ አደራ በእኛ ጫንቃ ላይ ወድቋል። በሀገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ እናት ሀገራችሁ ጥሪ ታቀርብላችኋለች።
በቃን ብለን ከተነሣን ከፊታችን የሚቆም ምንም ዓይነት ኃይል እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው። ውጊያው የትግራይን ሕዝብ ምሽግ ካደረገው እኩይ ኃይል ጋር እንጂ ከትግራይ ጋር አይደለም፤ እናም ስንፋለም መጠቀሚያ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ብሎም መላዋ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ለማውጣትና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስከበር ነው።ትግላችን ከአሸባሪው ጁንታ ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው ሀገራችንን ለማፈራረስና የኢትዮጵያን ህልውና ለማጨለም ከተነሡ የቅርብና የሩቅ ኃይላትና ሀገራት ጋር ጭምር ነው።
ስለዚህ ሁሉም ሀገር ወዳድ ሉአላዊነቱን ለማስጠበቅ በሙሉ ልቡ ይሠለፍ፤ እንደ ጥንቱ ዛሬም የሀገሩን ክብር ላለማስደፈር ቆርጦ ይነሳ። የእውነትም ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች፤ የእኛም ስም በታሪክ መዝገብ በጀግንነት ተመዝግቦ ይኖራል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት
ነሐሴ 4፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...