ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, August 14, 2021

ማዋከብ እና ማቀዝቀዝ ሁለቱ የሽብርተኛው ህወሓት ወቅታዊ ዘዴዎች ናቸው።ከገጠር እስከ ወረዳ ከተሞች፣ከሀገር ቤት እስከ ዲያስፖራ ልናውቀው የሚገባ ነው።  • ኢትዮጵያ የህልውና ትንቅንቅ ላይ ነች።ትንቅንቁ ከተወካዩ የሽብር ቡድኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዋሽንግተን እስከ ካርቱም፣ ከካይሮ እስከ የአረብ ሊግ ሀገሮች ሴራ ትብተባ ድረስ ይዘቃል።


ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በተጠና መልኩ ሲሴርባት  የነበረው ሀገሪቱን የማፍረስ ዕቅድ ለማስፈፀም ጠላቶቿ ተነስተውባታል።የኢትዮጵያ ጠላቶች የረጅም ጊዜ እቅድ ለማስፈፀም እጅግ የተመቸ ሆኖ የተገኘው ደግሞ  ሽብርተኛው ህወሓት ነው።ህወሓት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሙሉ ውክልና ወስዷል።ለውክልናው ምላሽ ደግሞ የጦር መሳርያ እና የሎጀስቲክ ድጋፍ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ያገኛል።ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ከገጠማት የባዕዳን ከበባ የከፋ ደረጃ ነው።በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ኢትዮጵያን አንድ ካልሆነች ዙርያዋን በከበቧት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የመወረሯን አደጋ የተረዱት አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት የተነሱትን የአካባቢ ገዢዎች ወደ አንድ ለማምጣት ደክመዋል ብቻ ሳይሆን መሰረትም ጥለዋል።


ኢትዮጵያ በ19ኛው ክ/ዘመን ከትግራይ የገጠማት ፈተና ለኤርትራ በጣልያን መወረር ምክንያት ነበር።


የአፄ ቴዎድሮስ ፍፃሜን ከወቅቱ የብሪታንያ ወራሪ ጋር አብረው  የእንግሊዝን ሰራዊት እየመሩ እስከ መቅደላ ድረስ ያስመጡ፣አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ከሰዉ (መስዋዕትነት ከተቀበሉ) በኃላ እንግሊዞች የአፄ ቴዎድሮስ ንብረቶች እና ልጃቸውን ይዘው እንዲሄዱ እያጫፈሩ  ኢትዮጵያን የከዱ የትግራይ ደጃች በዝብዝ ነበሩ።ደጃች በዝብዝ ከእዚህ በላይ መቅደላ ተሰብስበው የነበሩ የኢትዮጵያ የብራና መፃህፍት እና ቅርሶች በግመሎች እና በዝሆኖች ተጭነው እንዲሄዱ ያስደረጉ ቅርሶቹ ከሀገር ሲወጡ አጅበው እስከ ወደብ ያደረሱ የወቅቱ የትግራዩ ገዢ ደጃች በዝብዝ ነበሩ።

ደጃች በዝብዝ አሁንም ይህንን ሁሉ ያደረጉት ከእንግሊዝ አሮጌ መሳርያ ለማግኘት እና ንግስና ለመጫን ነበር።ደጃች በዝብዝ ከንግስናቸው በኃላ ደርቡሽ ሲመጣ ለኢትዮጵያ በመሞታቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለፈ ጥፋትን የመተው ባሕሉ መኖሩ ነው እንጂ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ከትግራይ የተነሱት ደጃች በዝብዝ ኢትዮጵያን በእዚህ ደረጃ አደጋ እንዳደረሱባት መካድ አይቻልም።በደጃች በዝብዝ እየተመሩ መቅደላ የደረሱት እንግሊዞች የኢትዮጵያን መልክዐ ምድር አስቸጋሪነት እና የህዝቡን ተዋጊነት ተረድቶ በአፄ ቴዎድሮስ የታሰሩበትን ዜጎቹን ብቻ አስፈትቶ ባይመለስ ኖሮ እና በቅኝ ግዛት ኢትዮጵያን ለመያዝ ቢሞክር ኖሮ ደጃች በዝብዝ ኢትዮጵያን አሳልፈው ሰጥተዋት ነበር ማለት ነው።እዚህ ላይ ደጃች በዝብዝ የኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ይዞታ ለማስጠበቅ ዋጋ የከፈሉት ራስ አሉላ ከዶጋሊ በኃላ ተመልሶ የመጣውን ጣልያንን እንዳይዋጉ በምን ያህል ደረጃ እንቅፋት እንደፈጠሩባቸው እና ኤርትራ በጣልያን እጅ እንድትወድቅ ከአድዋ በፊት ምን ዓይነት ስሕተት እንደሰሩም መዘንጋትም አይገባም።

ጣልያን ኤርትራን እንዲቆጣጠር የቀድሞው ደጃች በዝብዝ የኃላው አፄ ዮሐንስ ራስ አሉላን ከጦር ኃይል አዛዥነት አንስተው ስልጣኑን ለታላቅ ወንድማቸው ልጅ ራስ ኃይለማርያም በመስጠት የጣልያን እግር እሳት የነበሩትን ራስ አሉላን በሐማሴን ብቻ እንዲወሰኑ ማድረጋቸው ጣልያንን አስፈንድቆ፣ራስ አሉላን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን አሳዝነው በውጤቱም ኤርትራን ለጣልያን እንድትጋለጥ አድርገው አልፈዋል። ይህንን ታሪክ ማወቅ በተለይ በእዚህ ጊዜ አስፈላጊ ነው።በተለይ ይህንን እውነታ እየደበቀች ህወሓት አዲስ አበባ ስትገባ የኤርትራን በጣልያን መቆየት በአድዋ ጦርነት ተከትሎ የመጣ ለማስመሰል ሲተረክ ቆይቷል።እውነታው ግን የቀድሞው ደጃች በዝብዝ የኃላው አፄ ዮሐንስ ራስ አሉላን በሀማሴን ወስነው ለታላቅ ወንድማቸው ስልጣኑን መስጠታቸው መሆኑን እና ራስ አሉላንም በሚገባ አለማበረጣታቸው ነው። ራስ አሉላ ግን ይህ ሁሉ ደርሶባቸውም ለኢትዮጵያ የቆሙ ናቸው እና ጣልያን ተመልሶ በአድዋ ዘመቻ ሲመጣ አዲስ አበባ ድረስ መጥተው አፄ ምንሊክ ጋር ህብረት ፈጥረው ኢትዮጵያን ለመከላከል ተዋግተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም  የራስ አሉላ መገፋት አዳፍኔ በተሰኘ መፃህፋቸው ላይ ሲገልጡ 

 ''ከዶጋሊው ጦርነት ወዲህ የጦር ጠቅላይ አዛዥነቱን ንጉሰ ነገስቱ ከራስ አሉላ አንስተው ለታላቅ ወንድማቸው ልጅ ለራስ ኃይለ ማርያም ሰጥተው አሉላን በሃማሴን ግዛት ስለወሰኗቸው (ራስ አሉላ) ቅሬታ ነበራቸው ይባላል።" (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አዳፍኔ፣ገፅ 13) 

ማዋከብ እና ማቀዝቀዝ  ሁለቱ የሽብርተኛው ህወሓት ወቅታዊ ዘዴዎች

''ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖልም ቢሆን እንወርዳለን'' እያለ የሚያቅራራው ሽብርተኛው ህወሓት አሁን ከገጠር እስከ ከተማ እና ዲያስፖራ ድረስ ሊጠቀምባቸው የሚሞክራቸው ሁለቱ መንገዶች ማዋከብ እና ማቀዝቀዝ ናቸው።

ማዋከብ 

ህወሓት ጀሌዎቹን ወደ አማራ እና አፋር ክልል ሲገቡ የተጠቀሙበት አንዱ መንገድ በከተሞች እና በገጠር የሚኖረው ሕዝብ መሃል  የሐሰት ወሬ በመንዛት ማዋከብ፣አዋክቦም ሕዝብ የሚኖርበትን ቀዬ ለቆ እንዲወጣ፣እንዲቅበዘበዝ እና  በቀላሉ የጠላቶቹ ዒላማ እንዲሆን ማድረግ ነው።የማዋከብ ተልዕኮ የሚወስዱት ደግሞ በተለያየ ደረጃ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ አካላት ናቸው።እነኝህ አካላት በቁጥር ጥቂት ሲሆኑ አብዛኛው ያልገባው ግን በማያውቀው ጉዳይ እየተዋከበ የሚገባ ነው።የማዋከብ ስራው በዋናነት ሕዝቡ ውስጥ የሚፈፅሙት የሽብርተኛው ቡድን ከተማ ወይንም የገጠር ወረዳ ሳይገባ እንደገባ በማስመሰል ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሆነ በማውራት ሕዝብ ከተማ ወይንም ገጠር ይዞታውን ለቆ እንዲወጣ ያደርጉታል።

የማዋከብ ስራው ሌላው የሚከናወነው ሕዝቡን በሚመሩ የከተማ እና የገጠር የመንግስት አስተዳደር ኃላፊዎች ቢሮዎች ውስጥ ነው። በእነኝህ ቢሮዎች ውስጥ የሚሰሩ ለሽብር ቡድኑ በዘር ሐረግ ወይንም በገንዘብ ጥቅም የተያዙት የመንግስት የአስተዳደር ኃላፊዎችን ወሬ የሰሙ በማስመሰል ያዋክቧቸዋል።በውክብያውም ተረጋግተው ሕዝብ እንዳይመሩ እና ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ብቻ ሳይሆን በሕዝብ እና በሃላፊዎቹ መሃል ክፍተት እንዲፈጠር ኃላፊዎቹ ቀድመው እንደሄዱ አድርገው ስብሰባ ላይ ያሉትን ኃላፊዎች ሁሉ ስም የማጥፋት ስራ በመስራት ለሽብር ቡድኑ በር የሚከፍቱ አሉ። እነኝህ የማዋከብ ስራዎች በሀገር ውስጥ የጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ብቻ የሚታይ አይደለም።በውጭ ሀገርም ስልክ እየደወሉ ወይንም በአካል ሲያገኙ ሁሉ ግለሰቦችን እየመረጡ የሚያዋክቡ እና የሐሰት ወሬ በመንዛት የሰውን ስነ ልቦና ለመስለብ የሚሞክሩ አሉ። እነኝህኞቹ በውጭ ያለውን ማኅበረሰብ በማወክ በቀላሉ የተሸናፊነት ስሜት ለማሳደር እና ይህንን ስሜት ሀገር ቤት ለሚያውቁት እንዲያጋቡላቸው የታለመ ነው።

ስለሆነም በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ማኅበረሰብ የሽብር ቡድኑ በዋናነት በማዋከብ ግርግር ፈጥሮ ከፍተኛ ጥፋት ለማድረስ እና ሕዝቡን ከመኖርያው አፈናቅሎ ማኅበራዊ ቀውስ መፍጠር እንዲሁም በመግደል እና በመዝረፍ ትርምስ ለመፍጠር የሚጠቀምበት ዋነኛ መንገድ መሆኑን በማወቅ ሕዝብ ቀየውን ሳይለቅ እራሱን ማደራጀት እና መጠበቅ እንዳለበት ሊገነዘብ ይገባል።

ማቀዝቀዝ 

ሌላው የሽብር ቡድኑ ተግባር ማቀዝቀዝ ነው።ይሄውም የሕዝብ በሽብር ቡድኑ ላይ ያለው የቁጣ እና የመደምሰስ ስሜት፣ወደ የጦር ማሰልጠኛ ካምፖች የመግባት ተነሳሽነት፣የእርስ በርስ ማኅበራዊ ትስስሩ መጠንከር ላይ ቀዝቃዛ ስሜት ማፍሰስ ነው። ይህንንም በተለያየ መንገዶች ይፈፅሙታል።ከእነኝህ ውስጥ ወጣቱ ወደ ፈንጠዝያ የሚሄድባቸው መርሃግብሮች በከተሞች እንዲበዙ ማድረግ፣ማኅበራዊ ሚድያዎች በዘፈን እና አልባሌ ጉዳዮች ትኩረት ማስቀየር፣ በሕዝቡ መሃል ወሬ በመንዛት በመንግስት እና በሕዝብ መሃል መተማመን እንዳይፈጠር በማድረግ የህዝብ ስሜት ማቀዝቀዝ እና ሕዝቡን ለማስተባበር የነቁትን እና የተጉትን እንዲሁም የአመራርነት ሚና የወሰዱትን ከወረዳ ጀምሮ ሕዝብ የመምራት እና የማስተባበር ስሜታቸው እንዲቀዘቅዝ የግል ማኅበራዊ ጉዳያቸውን ሁሉ በሚያውቁት ሰው እንዲረበሽ ከማድረግ ሙከራ እስከ የአካል ጥቃት በማድረስ የመምራት እና የማስተባበር ስሜታቸውን አቀዝቅዞ ለማስወጣት መሞከር የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።

ስለሆነም በእዚህ ወቅት ግለሰብ እንደ ግለሰብ፣ሕዝብ እንደ ሕዝብ እና አመራሮች እንደአመራሮች ኃላፊነት እንዳለባቸው መረዳት አለባቸው። ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ጠላት የሽብርተኛው ጁንታው ኃይሎች ብቻ አይደሉም።ከዋሽንግተን እስከ ካርቱም፣ ከካይሮ እስከ የአረብ ሊግ ሀገሮች ሴራ እየተጠነሰሰባት ነው።ይህ ሴራ ደግሞ ዋና ኢላማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ የሚመስለው ካለ ተታሏል።ጉዳዩ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አንገቷን ቀና እንዳታደርግ ለማዳከም እና በተዳከመች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደልባቸው ገብተው የተፈጥሮ ሃብቷል ለመቀራመት የሚፈልጉ ኃይሎች እሩጫ ነው።ይህ ግን ፈፅሞ እንደማይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሞኑ ያሳየው እጅግ ፈጣን እና አስደማሚ  ሕብረት፣ውሳኔ እና ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እያደረገ ያለው መትመም ሁሉ ለወገን ደስታ ለቅርብም ሆኑ ለሩቅ የኢትዮጵያ ጠላቶች ታላቅ ድንጋጤ አትርፏል። አሁን የሽብር ኃይሉ ህወሓት ሙሉ በሙሉ እንደሚመታ ምንም የሚያጠራጥር አይደልም።ይህ ማለት ግን እየተበጣጠሰ ሾልኮ እየገባ ሕዝብ አያወናብድም ማለት አይደለም።ሕዝብ ግን ለመወናበድ እራሱን ሳያጋልጥ የማዋከብ እና የማቀዝቀዝ የሽብር ቡድኑን መንገዶች ከመንደሩ ጀምሮ እየመረመረ እና እራሱን አንቅቶ እስከ ቆመ ድረስ ብቻ ነው።ኢትዮጵያ ተሸንፋ አታውቅም። 

 ==========================
ማስታወቂያ /Advertisement 
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...