ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 12, 2013

'ኢሕአዴጎች' ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ሀገር ለማስተዳደር አቅሙም ብቃቱም የላችሁም!ስራችሁን እያየን ጣልያን ለማታውቀው በባህር ሰምጠው ለሞቱት አፍሪካውያን ቀብር ባንዲራ ዝቅ አድርጋ መቅበሯን ማመስገን አለብን እንዴ?
እኛ የሞቱት፣የሚደበደቡት እና የሚደፈሩት እህቶቻችን አያሳዝኑንም?
ኢትዮጵያዊነት በእዚህ ደረጃ መዋረድ አለበት?
ኢቲቪ ከትናንት ጀምሮ ዛሬ ቀን ድረስ ስለጉዳዩ ምንም አላወራም።ስለተገደሉት፣ስለሞቱት እና ስለተደፈሩት ሴቶች የሚጠይቅ መንግስት የለንም።ከእንግዲህ ወዲህም መንግስት አለ ብለን እናወራለን?

ለመሆኑ የትኛው መንግስት ነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ  እስከ ደህነነቱ ድረስ ሌባ ሆኖ ዘብጥያ የወረደው?
የትኛው መንግስት ነው ዜጋው በሲቃ ላይ እያለ ሸራተን ሆቴል  የሚንደላቀቀው?
ድሮም በሙስና የተጨማለቀ መንግስት ሕዝቡን አይደለም እራሱንም ይሸጣል።የተበላ ብር ያሸማቅቀዋል።
ሊባኖስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በር ላይ ከእዚህ በፊት የሞተችው የእህታችን ዓለም ደቻሳን ጉዳይ እንደዋዛ ያለፈ መንግስት ዛሬም በብዛት ኢትዮጵያውያን ደም እንደጎርፍ ሲፈስ ቅንጣት ታህል አልተሰማውም። እኛም ያው ሆነናል።ሁላችንም ማውራት ማውራት አሁንም ማውራት ብቻ ሆኗል ዜማችን።ፓልቶኩ ማውራት ፌስ ቡኩ ማውራት።

ጥያቄው የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ምን አለ አይደለም እኔ ምን አልኩ?፣ እኔ ምን አደረኩ?፣እኔ ምን ላድርግ? ነው ወሳኙ ሥራ።
የእራስን ኃላፊነት መወጣት ነው ቁም ነገሩ።
ይህ ስሜታዊነት አይደለም።የማስተዋል ይልቁንም የእርጋታ ውጤት ነው።

እንደሰው ማሰብ ለቻለ ሰው ሁለት ነገሮች የኢህአዲግ መንግስትን ማንነት በትክክል ይገልጡለታል።
አንዱ ባለፈው ለግራዚያኒ ሊሰራ የነበረውን ዓለም የተቃወመውን የሀውልት ግንባታ በመቃወም ሰልፍ የወጡትን የገታበት ፋሽሽታዊ ቅኔ ሲሆን ሁለተኛው የሳውዲ አረብያውን ጉዳይ የያዘበት ዲፕሎማሲ ነው።ሌላው መንግስት ነኝ ተብዬው በየስርቻው የሚሰራውን ቤት ይቁጠረው።እነኚህ ስራዎች ብቻ በቂ ናቸው።

በአፄ ምኒልክ ዘመን የተሰራ ሐዲድ መስመር በ 21ኛው ክ/ዘመን ባቡር አስገባሁ እያለ የሚመፃደቁ ጉዶችን  ይዘን ድሮስ የት ይደረሳል? የዛሬ 100 ዓመት በፊት እኮ ከ 700 ኪሎ ሜትር በላይ ሐዲድ ኢትዮጵያ የዘረጋችው።ዛሬ እድሜ ለመንግሥታችን ከቆመ ሁለት አስርት አመታትን አስቆጠረ እንጂ።

ያን ጊዜ ሐዲዱ ሲዘረጋ ከአውሬ ጋር እየተጋፉ ሰው እየሞተ፣ውህ ጥም እየተቃጠለ ነው። ዛሬ በካቶ እያንጠለጠሉ ማስቀመጥን ''ጥሩ'' ከሚል ባለፈ ጧት ማታ እንድንዘምር እና የነፃነታችን ልዋጭ ልታደርጉት ትደፋፈራላችሁ።አሳዛኞች ምስኪኖች ናችሁ።ፖለቲካ እና ሰብአዊ አስተሳሰብን ለመለየት ያልታደለ ሰው ድሮስ ምን ሊሰራ ይችላል?

ጣልያን ከሽፍታ መንግስት በምን ይለያል? የሚሻልበትን ማንሳት ይበቃል።ጣልያን ኢትዮጵያን በወረራው ጊዜ ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግሥታት ስር እንዲወክል አልጠብቅም።ግን በአንዲት ነገር እንደሚበልጣችሁ ልንገራችሁ።ምንያህል ስራችሁ  ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ግልፅ አድርጎ ያሳያል።ጣልያን ኢትዮጵያውያንን ከአዲስ አበባ ከፒያሳ አካባቢ ስያፈናቅል መጀመርያ የጭቃ ቤት መርካቶ አካባቢ ገንብቶ ከጨረሰ በኃላ ነበር።እናንተ የአዲስ አበባን ሕዝብ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እየነቀላችሁ ስታባርሩ ለኪራይ ይሁንህ እያላችሁ አልቤርጎ የማያሳድር ገንዘብ እየሰጣችሁ ነው ያባረራችሁት።

እናንተ ሕፃናትን በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ እየተቀበላችሁ ከእናት አባት ሲነጠሉ ፈቃድ ይሰጥ የነበረው አሁንም የሚሰጠው የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።ከካቢኔ አባላችሁ አንዱ ሕፃናትን የሚሸጥ ሌላው ሴት እህቶቻችንን የማለፍያ ቪዛ የሚመታ የተቀረው በሕፃናቱ እና ሴት እህቶቻችን የተሰበሰበ የደም ዋጋ ወደ ካዝና የሚያስገባ ነው።ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ለአረብ ሀገር ስትሸጥ እንደመንግስት ኃላፊነት አልተሰማችሁም።ዛሬ ተሸጠው ካለቁ በኃላ ወደ አረብ ሀገር መሄድ ተከለከል መሰል ዘፈን ሳትዘፍኑ በፊት ግን በአረብ ሀገር ኢምባሲ የሚሰሩ ሰራተኞቻችሁ በኢምባሲው ስልክ የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኢጀንሲ ሥራ ይሰሩ ነበር።

ዛሬ የሳውዲው ጉድ አፍጥጦ የመጣው እና ወገኖቼን የሚደበድበው በእናንተ የስልጣን ዘመን ሀገሬን የሚያውቃት ''ሽባብ'' የተሰኘው ወጣት ነው።ዛሬ እህቶቻችንን በየመንገዱ የሚደፍረው እናንተ ኢምባሲ ብላችሁ በምትጠሩት ቤት ውስጥ የበለጠ ደፋሪ እንዳለ የሚያውቅ ውስጥ አዋቂ ነው።

ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደጋፊ ተብየዎቻችሁ ናቸው።አይናቸውን በጨው ሳይሆን በአሲድ ያጠቡ የዘመኑ ብልጣ ብልጦች 'አባይ ግድብ እና ባቡር ዝርጋታው ፖለቲካ አደለም ልማት ነው' ሲሉ ከርመው በሳውዲው ጉዳይ ላይ ግን የመንግስታቸውን ጉግ ማንጉግ በጨርቃቸው ለመሸፈን ፖለቲካ ነው መንግስትን ለማጥላላት ነው ለማለት  ይራወጣሉ።ቀድሞ ነገር ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ሀገር ለማስተዳደር አቅሙም ብቃቱም የላችሁም።

ጉዳያችን
ህዳር 3/2006 ዓም


No comments: