ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 9, 2013

በኢትዮጵያ ያለፉት አርባ አመታት የፖለቲካ ሂደት ስድስቱ የለውጥ መዘውር ነጥቦች(turning points)-ሰባተኛው የለውጥ መዘውር ነጥብ እየቀረበ ይሆን? (ጉዳያችን አጭር ጥንቅር)


ኢትዮጵያ የዘውድ ስርዓት ከወረደ በኃላ ባልተረጋጋ የለውጥ ማዕበል ውስጥ መናጥ ከጀመረች 40 ዓመታት እየደፈነ ነው።የየካቲት 1966 ዓም አብዮት ዘንድሮ 40 ዓመት ይሞላዋል።ከ 1966 ዓም በፊት በነበሩት ስልሳ አመታት ውስጥ  ሀገራችን ከሁለት መቶ አመታት በላይ በዘመነ መሳፍንት የእርስ በርስ ግጭት ከቀረው ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት በብዙ መልኩ የተለያየ እና ጠንካራ የማይባል ነበር።ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ እስከ አጋምሹ ማለትም 1966 ዓም በነበሩት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ፍፁም ከሆነው የፊውዳል ስርዓት ወደ ዘመናዊነት ለመግባት ብዙ ነገሮች በየዘርፉ የጀመረችባቸው አመታት ነበሩ።ዘመናዊ መንግስት ስርዓት- እንደ ፓርላማ፣ዩንቨርስቲዎች፣የአየር መንገድ አገልግሎት፣የመብራት ኃይል ማስፋፋት፣በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ሆነ በአህጉራዊ እና አካባቢያዊ ፖለቲካ ውስጥ ተፅኖ ፈጣሪነት እና የመሳሰሉት ባጭሩ ሊገለፁ የሚችሉ የዘመናቱ ስራዎች ነበሩ።

ከ1966 ዓም ወዲህ ባሉት አርባ አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የተረጋጋ የመንግስት ስርዓት እና ህዝብን ያማከለ አስተዳደር ቢኖራት ኖሮ ዛሬ ካለአንዳች ማጋነን ደቡብ ኮርያ ከደረሰችበት የስልጣኔ እና የእድገት ደረጃ የመድረስ ዕድል ነበራት።ይህ ግን አልሆነም።

በእነኚህ አመታት ውስጥ በተገቢው ደረጃ እንዳናድግ ያደረጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ።ከእነኝህ ውስጥ በቀን በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የበላ ጦርነት በሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ለአስራ ሰባት አመታት መካሄዱ፣ የነበሩት በእውቀት ክህሎታቸው እና በልምዳቸው ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ያደርጉ የነበሩ ምሁራን የመስራት መብታቸው መታፈኑ፣የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ግንኙነት ብልህነት ያልተሞላበት የነበረ መሆኑ፣ካለፉት 22 አመታት ወዲህ ደግሞ ብሄርን መሰረት ያደረገ የሀገሪቱ የአስተዳደር  መዋቅር ወደባሰ አደገኛ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማምራቱ፣ብሄርን መሰረት ያደረገ አድሏዊ ስርዓት ምጣኔ ሃብቱን በተወሰኑ እና ጥቂት ሰዎች እጅ እንዲገባ ማድረጉ፣የፈጠራ ስሜት እጅጉን እንዲጎዳ መደረጉ፣ሀገሪቱ ያለወደብ ቀርታ ለባሰ የባዕዳን ጥቃት ተጋላጭ መሆኗ ወዘተ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል።

ከላይ በተጠቀሰው 20ኛው ክ/ዘመን (1900 -2000 ዓም) ውስጥ ኢትዮጵያ ስድስት የለውጥ መዘውሮች (turning points) ውስጥ አልፋለች።እነኝህ የለውጥ መዘውሮች (turning points) በሀገራችን የፖለቲካ መረክ ላይ ይከሰቱ እንጂ አብዛኞቹ ብሩህ ተስፋ ይዘው የመጡ የሚመስሉ ግን የከሸፉ ናቸው።የመክሸፋቸውን ምክንያት ለታሪክ ተመራማሪዎች ትቼ ክስተቶቹ ምንነት ላይ ብቻ ላተኩር።

1/ የለውጥ መዘውር ነጥብ (turning point) አንድ  - 

ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ 

ቤ 20ኛው ክ/ዘመን መጀመርያ ላይ የመጀመርያው የለውጥ መዘውር የነበረው የንግሥት ዘውዲቱ ስልጣን ወደ አልጋወራሽ ተፈሪ በኃላም በ 1923 ዓም የንግስና ማዕረግ ያገኙት የቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ወደ ስልጣን መምጣት ነው።በወቅቱ በጥቂት የተማሩ እና ''ተራማጅ'' ተብለው ይጠሩ በነበሩ ወጣቶች ይደገፉ ነበር። ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ገና በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው ሳሉ አውሮፓን መጎብኘታቸው እና የአውሮፓን ስልጣኔ መመልከታቸው በኃላም የጣልያን ኢትዮጵያን መውረር እና በትምህርት እና በስልጣኔ ምን ያህል ወደኃላ እንደቀረን ግልፅ መሆኑ ቁጭት በንጉሱም ሆነ በወቅቱ በነበሩት ወጣቶች ዘንድ በሀገሪቱ ልማት ላይ ለውጥ ለማምጣት ስሜትን ኮርኩሯል።በእዚህም መሰረት ሀገራችን ከምንም ከሚባል ደረጃ በአፍሪካ እና በዓለም ተሰሚ የመሆን ደረጃ ደርሳ ነበር።

2/  የለውጥ መዘውር ነጥብ (turning point) ሁለት 

ብ/ጄ/መንግስቱ  ንዋይ (በንጉሡ ላይ መፈንቅለ መንግስት ከመሩት)

ሁለተኛው የለውጥ መዘውር መነሳሳት የተከሰተው በ 1953 ዓም የተነሳው በብ/ጄ/መንግስቱ ንዋይ  እና ገርማሜ የተመራው በንጉሡ ላይ የተሞከረው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው።ከ 1935 እስከ 1953 ዓም ድረስ የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ ተለወጠ።አዲሱ ትውልድ አዳዲስ አስተሳሰብ ይዞ መጣ።ንጉሡ ምንም ለሀገሪቱ የመስራት ፍላጎታቸው እና ውጤታቸውን ቢያደንቅም መጪውን ግን በእዚህ አይነት አሰራር መቀጠል እንደማይቻል ያሰቡ መኮንኖች የመፈንቅል ሙከራ አደረጉ።ይህ መፈንቅል ተሳክቶ ቢሆን የሀገራችን የፖለቲካ ገፅታ ዛሬ ምን ይሆን ነበር? በርካታ መልሶች ይኖሩታል።

3/ ሶስተኛ የለውጥ መዘውር   ነጥብ (turning point)

1966 ዓም ሕዝባዊ አብዮት 

ሶስተኛው የለውጥ መዘውር ነጥብ አርባኛ አመቱን የሚደፍነው የየካቲቱ 1966 ዓም አብዮት ነው።ይህ አብዮት አሁን እስካለንበት ሁኔታ ድረስ ተፅኖ ፈጣሪ የሆነ እና በአሁኑ ጊዜ ያሉት ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በእዚህ ወቅት ከነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ ባንድም በሌላም ያለፉ ናቸው።

4/  የለውጥ መዘውር (turning point) አራት 

ሜ /ጄነራል ፋንታ በላይ እና ሜ/ጄነራል አምሃ ደስታ በኮ/ል መንግስቱ ላይ መፈንቅለ መንግስቱን ከመሩት መኮንኖች 

አራተኛው የለውጥ መዘውር ነጥብ በ 1981 ዓም በኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ላይ የተሞከረ የመፈንቅለ መንግስት ነው። ይህ መፈንቅለ መንግስት ቢሳካ ኖሮ ለሀገራችን ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣ ነበር? አሁንም ለታሪክ ተመራማሪዎች እተወዋለሁ።የክስተቱ ተፅኖ ግን ብዙም ሳይቆይ በተለይ ከፍተኛ ልምድ የነበራቸው የሀገሪቱ የጦር መኮንኖች በኮ/ል መንግስቱ መገደላቸው የሰራዊቱን አቅም አዳክሞ ለሽምቅ ተዋጊዎች 'ሰርግና ምላሽ' ሁኔታ መፍጠሩን ብዙዎች ይስማማሉ።

5/ አምስተኛው  የለውጥ መዘውር ነጥብ 

አቶ መለስ 1983 ዓም 

አምስተኛው የለውጥ መዘውር ከ 1981 ዓም ብዙም ሳይቆይ በ 1983 ዓም ግንቦት ወር ላይ የኢህአዲግ ሰራዊት አዲስ አበባ መግባት ነው።ይህንን ተከትሎ ሀገራችን በዘመኗ አይታ የማታውቀው የብሔር ፖለቲካ እና መከለል ውስጥ የገባችበት፣ሀገሪቱ ወደብ አልባ የሆነችበት፣በክልሎች ደረጃ የድንበር ቁርሾ የተነሳበት በአስተዳደር ዘይቤ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የምትኖር የዘመነ መሳፍንት ውስጥ ያለች ሀገር የመሰልችበት ክስተት ተከሰተ።ይህ የለውጥ መዘውር እጅግ አደገኛ ያደረገው የህዝቡ ኩራት እና ማንነት ከሆነው ከኢትዮጵያዊነት የተጣላ ስርዓት መሆኑ ነው። ይህ ስርዓት የምጣኔ ሃብቱን፣የጦር ኃይሉን እና ፖለቲካውን እራሱን በጥቂት ሰዎች እና አካባቢ ሰዎች ስር መጣሉ የሀገራችንን መፃኢ ዕድል እጅግ አደገኛ አድርጎታል።

6/ ስድስተኛ የለውጥ መዘውር ነጥብ 

ምርጫ 1997 ዓም 

ስድስተኛው የለውጥ መዘውር ነጥብ  በ 1997 ዓም ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሕዝቧን ያነቃነቀ ነፃ የምርጫ ስርዓት ያየችበት እና  እንደ 1967 ዓም መፈክር ''ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም'' ልንዘመር ነው ተብሎ የተናፈቀበት ወቅት ነበር።ሆኖም ግን ክስተቱ በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሕይወት በኢህአዲግ ሰራዊት አማካይነት አስቀጥፎ እና ብዙዎችን ለእስር እና ለስደት ዳርጎ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ሀገራችንን ላለፉት አርባ አመታት በነበረችበት የአምባገነንነት ስርዓት ውስጥ እንድትቀጥል ተፈረደባት።

7/ ሰባተኛው የለውጥ መዘውር ነጥብ?

ዛሬም በበሬ እያረስን ነው።ሰባተኛው የለውጥ መዘውር ቢያንስ ይህንን መለወጥ የለበትም?

ኢትዮጵያ የመጀምርያውን ሕዝባዊ አብዮት በታሪክ ካደረገች አብዮቱንም በወታደራዊ ደርግ ከተነጠቀች በኃላ፣ሰሜናዊው ህዝቧ እና መሬቷ እንዲነጠል ተደርጎ፣ወደብ አልባ ሆና ለወደብ አገልግሎት በጎረቤት ጂቡቲ ላይ ጥገኛ እንድትሆን ተደርጋ፣ሀገሪቱ በክልል ተከልላ እርስ በርስ የማይተማመን ሕዝብ ለመፍጠር ብዙ ሴራ ተስርቶባት፣በ 1965 ዓም በዓለም ላይ  ሁለት ስደተኞች ብቻ የነበሯት ሀገር ዛሬ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ ስደተኛ በመላው ዓለም በትና እና ብዙ አስር ሺህ ሕፃናቷ በጉድፈቻነት ሸጣ ባጠቃላይ በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆና ነው ሰባተኛውን የለውጥ መዘውር እየቀረበ መሆኑ ይሰማኛል የምለው።ሰባተኛው የለውጥ መዘውር በማን እንዴት መቼ እንደሚመጣ በእርግጠኝነት  መናገር አሁን አይቻል ይሆናል። የህዝብ ፍላጎትን እና በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ግራ መጋባትን ተመልክቶ መረዳት ግን ብዙ አዋቂነትን አይጠይቅም።

ለሰባተኛው የለውጥ መዘውር  ለማምጣት የተነሱ በሰላማዊውም ሆነ በትጥቅ ትግል ውስጥ የገቡ ኃይሎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።እነኝህ ኃይሎች ባብዛኛው ከስድስተኛው የለውጥ መዘውር ሙከራ ማለትም ከ 1997 ዓም ወዲህ የተነሱትንም ማካተቱ ይታወቃል።በሃገርቤት በሰላማዊ ትግል ያለችውን ቀዳዳ እየተጠቀሙ ያሉትን ጨምሮ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉት እንደ ''ግንቦት 7'' አርበኞች ግንባር ወዘተ ያሉት ስርዓቱን በኃይል ለመጣል በሥራ ከተጠመዱት ውስጥ ናቸው።

ከአቶ መለስ ዜናዊ እረፍት ወዲህ በብዙ የውስጥ ቅራኔዎች መዋከቡ የሚነገረው ኢህአዲግ-ወያኔ እራሱን ለመሰረታዊ ለውጥ አለማዘጋጀቱ እራሱን የቻለ ችግር ሆኖ የቀጠለ ክስተት ቢሆንም ለሰባተኛው የለውጥ መዘውር በለውጥ አስፈላጊነት ላይ ከመስማማት ባለፈ የኢትዮጵያን ያለፈውን እና የመጪውን የእድገት ትልሟን የሚያመላክት ጥርት ያለ ፖለቲካዊ ፍልስፍና አሁንም አስፈላጊያችን ነው።እዚህ ላይ ከፖለቲካ ፍልስፍና ይልቅ ነፃነት መቅደም አለበት የሚሉትንም መዘንጋት አይገባም።ለሁሉም ግን እርግጠኛ የምንሆንባቸው ሁለት ነገሮች አሉ።የመጀመርያው የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በሃያኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ጀምሮ የተረጋጋ የመንግስት ስርዓት ከተመለከትን 40ኛው ዓመት ላይ መሆናችንን።ሁለተኛው ደግሞ ጊዜውን አሁን መተንበይ ባንችልም ሰባተኛው የለውጥ መዘውር ምን መምሰል አለበት? ወዴት እንዴት ነው መሄድ የሚገባን?ያለፉት ስህተቶች እንዳይደገሙ ምን ይደረግ? የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሊነሱ የሚገባበት ጊዜ ላይ መሆናችንን አለመርሳት የሚሉት ናቸው።

ጉዳያችን ጡመራ
ጥቅምት 30/2006 ዓም
ኦስሎ

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...