ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 12, 2013

መንግስት በሳውዲ አረብያ ጉዳይ ''የግብር ይውጣ'' በሚመስል መልክ ለመያዙ ማሳያ የሆኑት አምስት ነጥቦች፣ምን ይደረግ?....በአዲስ አበባ ያለው የሳውዲ አምባሳደር መልስ እስካሁን አልሰጡም




በሳውዲ አረቢያ ያሉ ወገኖቻችን ላይ የሳውዲ ፖሊስ እና ''ሸባብ'' የተሰኙ ወጣቶች እያደረሱ ያሉት ግፍ ካለፈው አርብ ወዲህም መሻሻል አላሳየም። ኢቲቪ በሰኞ 02/03/2006 ዓም ምሽት  የዜና እወጃው ላይ ስለ ሳውዲ ጉዳይ ምንም አለማለቱ እውነት ይህንን ያህል ታፍነናል እንዴ? የሚያስብል ነው።ዓለም የሚያወራውን ጉዳይ ጉዳይ የሀገራችን ብሔራዊ ቴሌቭዥን አንድ ምሽት ዘግቶት አለፈ ማለት ምን ትርጉም ይሰጥ ይሆን?

በአንፃሩ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ እጅግ አስገራሚ፣አሳዛኝ እና ''የግብር ይውጣ'' ያህል በሚባል ደረጃ  ነው።።ለእዚህ ማስረጃ የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነጥቦች ብቻ ማንሳቱ ይበቃል።


1/ አምባሳደሩ የፅሁፍም ሆነ የቃል መልስ እስካሁን አልሰጡም 

 መንግስት እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ ያለውን የሳውዲ ምክትል አምባሳደር በፅሁፍ እና በቃል ማብራርያ እንዲሰጡን ጠይቀናል ይበል እንጂ አምባሳደሩም ሆኑ ኢምባሲው እስከ ሰኞ ማታ ድረስ ምላሽ አለመስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል።ስለ ጉዳዩ ሸገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጠይቆ እንደተረዳው እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ መልስ አልሰጡም።ይህ በዲፕሎማሲ አነጋገር ንቀት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ እርምጃ መንግስት መውሰድ እንደሚገባው የፖለቲካ ሳይንሱ እራሱ ያዘዋል።እርምጃው አምባሳደሩን ከሀገር እስከማስወጣት ድረስ ያደርሳል።በእዚህ ምክንያት ሳውድ ያሉ ወገኖችን ጉዳይ ወደ አለማቀፍ መድረክ ማምጣት ይቻላል።ይህ ማለት ሌሎች አካላትም ሆኑ አለማቀፍ ድርጅቶች በጉዳዩ እንዲገቡ ይጋብዛል።መንግስት ግን ይህንን ያህሉን ውርደት ተሸክሞ  ሀገርንም አሸክሞ ተቀምጧል።

 2/ መንግስት መግለጫውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ደረጃ ዝቅ አድርጎታል።

 እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ስለጉዳዩ  መግለጫ እየተሰጠ ያለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ብቻ ነው።የእዚህ አይነቱ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በምድር ላይ ምናልባት በናዚ ዘመን የተፈፀመ ግፍ ጋር የተስተካከለ ግፍ ተሰርቶ፣ጉዳዩ በቀጥታ ከብሄራዊ ሉዓላዊነት አደጋ ጋር የተያያዘ ትልቅ ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳች መግለጫ አልሰጡም። ይህ ህዝብን መናቅ ነው። አቶ ሃይለማርያም እና ዶ/ር ቴዎድሮስ ከማን ይበልጣሉ? አሜሪካ ሕፃናት መዋያ ላይ ለተፈፀሙ 3 እና 4 ሰው ለሞተበት አደጋ ፕሬዝዳንቷ ለመላው ሕዝብ መግለጫ ይሰጣሉ።እኛ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን የዜግነት መብታቸው ተገፎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማብራርያ መሰል ነገር ይወረወርልናል።

3/ ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች  እና አካላት ጉዳዩን እንዲመለከቱ አላደረግም 

መንግስት ጉዳዩን ጉዳዬ ብሎ ይዞት ቢሆን ኖሮ ቢያንስ የሳውዲ አረብያን መንግስትን ከፍተኛ ባለሥልጣጥናት ማነጋገር በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ያደርግ ነበር።ይህ ባይሳካ በአፍሪካ ህብረት፣በአረብ ሊግ በኩል ባሉት ወዳጆቹ ለምሳሌ በኩዌት በኩል ሌሎች አካላት ጣልቃ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ አልተርሰራም።ይህ ደግሞ የሕይወት አድን ጉዳይ ስለሆነ ከማጣደፍ ጋር ቢሆንም ለሀገራቱ እንግዳ ሥራ ሊሆን አይችልም ነበር። የአፍሪካ ህብረት ለዓለም አቀፉ ፍርድቤትን ለመወንጀል ያንን ያክል የመሪዎች ስብሰባ የጠራ መንግስት በዜጎቹ ጉዳይ ምነው ዳተኛ ሆነ?

በተለይ ኩዌት የኢትዮጵያ የእረጅም ጊዜ ወዳጅ  ነች።በባህረ ሰላጤው ውግያ (በኢራቅ ወረራ ጊዜ) ኢትዮጵያ ከጎኗ በመቆሟ የተገነባ ጥሩ ግንኙነት መኖሩ ይታወቃል።የቦሌ አየርመንገድን በአዲስ መልክ የመስራት ሥራ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገችም ኩዌት መሆኗ ይታወቃል።ይህንን ግንኙነት ዛሬ ኢህአዲግ ጠብቆታል ወይስ አበላሽቶታል? እራሱን የቻለ ጥያቄ ነው።የሆነው ሆኖ መንግስት በሳውዲ አረብያ መንግስት ላይ ዜጎች ከእነ ክብራቸው ወደሀገራቸው እንዲገቡ ተፅኖ ለመፍጠር አልሞከረም።

4/ አረብኛ የማይችሉ ሰራተኞች በአረባዊቷ ሀገር መመደብ 

 ሳውዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በራሱ ብዙ ችግር ያለበት መሆኑ እየተወሳ ነው።ከችግሮቹ አንዱ በፓርቲ አባልነት የተመደቡት ሰራተኞች አረብኛ መናገር ቀርቶ አማርኛ በአግባቡ የማይናገሩ መሆናቸውን በሳውዲ የሚኖሩ ዜጎች እየተናገሩ ነው።የዲፕሎማሲ  የመጀመርያው መሳርያ የተመደበበትን ሀገር  ቋንቋ የሚናገር የሰው ኃይል መመደብ ነው። ሳውድ አረብያ ያለው ኢምባሲ ግን ይህንን ያሟላ አይደለም።ስለዚህ ከሀገሪቱ መንግሥታት የተለያዩ ቢሮዎች ጋር ተነጋግረው የሚያሳምኑ ሰራተኞች አለመኖር በራሱ የመንግስትን ፓርቲ-ተኮር የስራ ምደባ የሚያመጣውን ክስረት የሚያመላክት ነው።ይህ ደግሞ ዛሬ በይድረስ ይድረስ የሚመደብ ሳይሆን በሀገሩ ቆይተው ወዳጅነት ሊያጠነክር የሚችል የሰው ኃይል ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር።

5/  የኢጀንሲ ድርጅት ባለቤቶች የኢምባሲ ሰራተኞች? 

የመጨረሻው አሁንም ውጭ ጉዳይም ሆነ መንግስት ከእዚህ በፊት'' የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እየሰራሁ ነው'' ሲል የነበረውን ሁሉ የሚያፈርስ ጉዳይ ሰሞኑን ለማወቅ ተችሏል።ይሄውም በሳውዲ አረብያ  የኢትዮጵያ ኢምባሲ እና የኮምኒት  አንዳንድ ሰራተኞች ከኢትዮጵያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ወጣቶችን በቅጥር መልክ የሚደልሉ ኤጀንሲ ድርጅቶች ባለቤት መሆናቸው እና ብሮአቸውም በሳውዲ አረብያ መኖሩ መገለጡ ጉዳዩን አጀብ የሚያሰኝ ነው።በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ሕግ አንድ ሰው ከሚሰራበት መስርያቤትን ሥራ የሚቃረን ሥራ መስራት በራሱ እንደሚያስቀጣ ይገልፃል።በኢምባሲ ደረጃ የተመደበ ሰራተኛ በእንደዚህ አይነት እርካሽ ሥራ ተሰማርቷል መባሉ በራሱ ትልቅ የሀገር ውድቀት ነው።

ምን ይደረግ?

ባጠቃላይ ይህንን ሁሉ ጉድ የያዘው የመንግስት ድርጅት ምን እንዲሰራ ይጠበቃል? የችግራችን ስሩ እረጅም ነው።መንግስት እንደትልቅ ሥራ አድርጎ ሊያሳየን የሚሞክረው እስካሁን መልስ ያልሰጡት ምክትል አምባሳደርን አናገርኩ እና ልዑክ ልክያለሁ ብቻ ነው።ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ይህ ፌዝ እና ቀልድ ብሎም ''የግብር ይውጣ''  ሥራ ነው።

እዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን በእዚህ ደረጃ መከራ ሲደርስባቸው ለምን የውጭ አካላት አይናገሩም? የሚሉ አሉ።ሆኖም ግን የውጭ ኃይሎች በራሳቸው የተደመሙበት ጉዳይ የመንግስት የዲፕሎማሲ አካሂያድ ነው።ከመንግስት ሳይጠየቁ ምንም ለማለት አይችሉም።ቢያንስ ለአንዲት ቃል መነሻ ቃል ያስፈልጋል። ያንን መነሻ ቃል ሊሰጥ የሚችለው መንግስት ነበር። ግን አልሆነም።

አሁን በውጭ የሚኖሩም  ሆኑ በሀገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያን ብቻ ናቸው መፍትሄውን ማምጣት ያለባቸው።የሳውዲው ጉዳይ አስተማሪ ሆኖ በተገቢ መልኩ ካልታረመ ሌሎች አካባቢ ያሉ ወገኖቻችን ላይ ተመሳሳይ ችግር ወደፊት የመፈጠር እድሉን ያሰፋዋል።በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ሃገራት ያለን ሁሉ  አስተማሪ የሆነ ሥራ መስራት ይገባል።ለእራሳችን መቆም ያለብን እራሳችን ብቻ ነን።በውጭ ያለው ሕብረተሰብ ትልቅ የ አድቭኬት ሥራ መስራት ይጠበቅበታል።

ለእዚህም እንዲረዳ በሳውድ ያሉ ወገኖች ጋር ግንኙነት ያላችሁ ወገኖች ከአሳዛኝ ፎቶ ባለፈ ወጥ የሆነ በተለይ በህፃናት እና በሴቶች ላይ የደረሰውን ግፍ ባለታርኮቹ ሲናገሩት የሚያሳዩ ደረጃቸውን የጠበቁ ፊልሞች በእየሃገራቱ ቋንቋ እየተርጎሙ ለየሀገራቱ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መስጠት እና በጋዜጦች ላይ እንዲወጣ አርቲክሎችን መፃፍ ያስፈልጋል።በተለይ በህፃናት እና በሴቶች ላይ የተሰሩ ፊልሞችን ደረጃውን በጠበቀ መልክ ማዘጋጀት የምዕራቡን ዓለም በእጅጉ የሚስብ እና ጉዳዩን ለዓለም ሕዝብ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ ጉዱን እያወቀ ጥቅም ላወረው ዓለም ምክንያት ይሆነዋል።የሲ ኤን ኤን ''የነፃነት ዘመቻ'' የተሰኘውን ፕሮጀክት ፕሮግራሞች ይዘት መረዳቱ ብቻ ከላይ ለተቀስኩት ሕፃናት እና ሴቶች ላይ ያተኮሩ ፊልሞችን ውጤታማነት አመላካች ነው።

ከእዚህ ሁሉ ባለፈ ደግሞ በውጭ የሚገኙ የእስልምና ማኅበረሰብ መሪዎች በኢትዮጵያዊነት የሳውዲ አረብያን መንግስት እና  አረብ ሊግ ዙርያ የሚሰሩ ስራዎችን እንዲሰሩ ማድረግ በተጨማሪም  በአረብ ሃገራት እና በእራሷ በሳውድ አረብያ ያሉ ጋዜጦች ላይ ጉዳዩን ማሳወቅ እና ትኩረት መሳብ በአጭር ጊዜ የሚሰሩ ስራዎች መሆን ይገባቸዋል። ከእዚህ ሁሉ በፊት ግን የሳውዲ ኢምባሲን ከአዲስ አበባ እስከ ውጭ ሀገር ባሉት ሁሉ ላይ ተቃውሞ ማሰማት ይገባል።ለእዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች ሊያንቀሳቅሱት የሚገባ አፋጣኝ ሥራ ነው።

ጉዳያችን
ጥቅምት/2006 ዓም

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...