ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 18, 2013

ከሰሞኑ ጉዳይ መነሻነት ኢትዮጵያውያን ያላከናወናቸው ሁለት አበይት ተግባራት
ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን በሳውዲ እየደረሰ ያለውን ችግር መፍትሄ እንዲኖረው  በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከተሞች እንዲሁም ትናንት አርብ በአዲስ አበባ (በግፍ በእስር እና በድብደባ እስኪቆም ድረስ) በመሰለፍ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። ከእዚህ ሁሉ ሂደት የነጠሩ እና ወደፊት ሊነጥሩ የሚችሉ ነገሮችን ማውሳት ተገቢ መሰለኝ።

 በቅድምያ ግን ከሂደቱ የተረዳነው ጉዳይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች በተለይ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ መንግስትን ከመደገፍ እና አይዞህ ባይነት ጋር በተያያዘ በቀጥታ እጃቸውን ያስገቡ መንግሥታት መኖራቸው ከምንጊዜውም በላይ ግልፅ ሆኗል።ኢሕአዲግ-ወያኔም ገንዘብ እና ድጋፍ ለሰጡት ሁሉ መታዘዙን እና ከስልጣኑ በላይ ምንም የሚያስቀድመው ነገር እንደሌለ በድጋሚ አስመስክሯል።ለእዚህም የማይካድ ሀቅ ሆኖ የወጣው የሳውዳረብያ መንግስት ምን ያህል በሀገራችን የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ጉዳይ ገብቶ እየፈተፈተ እና እያዘዘ መሆኑ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ በሰልፈኞች ላይ የደረሰው ድብደባ እና እስር ጥሩ ማሳያ ነው።

ከሰሞኑ ሰልፎች ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያውያን ልናከናውናቸው የሚገቡ ሁለት አበይት ተግባራት


1/ በውጭ የሚኖረው ሕብረተሰብ አደረጃጀት ተፅኖ ፈጣሪ ማድረግ 


በውጭ የሚኖረው ሕበረተሰብ አሁን ካለበት አደረጃጀት በተሻለ እና ዓለማቀፋዊ መልክ በያዘ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ በትምህርትም ሆነ በገንዘብ አቅም የደረጁትን ብሎም አዳዲስ ሃሳብ የሚያፈልቁትን በማሰባሰብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ችግርም ሆነ ዘመን ተሻግሮ (ከለውጥ በኃላም) ኢትዮጵያን ለማንሳት ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። በውጭ የሚኖረው ሕብረተሰብ አሁን አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ በተቃውሞ ሰልፍ ከመግለፅ ባለፈ ተፅኖ የመፍጠር አቅሙ በበለጠ መደራጀት አለበት።

ለምሳሌ በየሀገራቱ ያሉት የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች (Communities) ለምን በዓለም አቀፍ ወይንም በአህጉር አቀፍ ደረጃ የመተዳደርያ ደንብ ቀርፀው የጋራ ሃገራዊ ራዕይ ቀርፀው በአጭር ጊዜ አይደራጁም? ይህ መደራጀት በፖለቲካ፣በኢኮኖሚ ማለት በውጭ ባሉ የንግድ ስራዎች እና በማህበራዊው በተለይ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶቻችንን በመጠበቅ እና ለቀሪው ዓለም በማሳወቅ ብሎም ባህሉ ለውጭው ዓለም ባህል እንዲሆን በመጣር ብዙ ተፅኖ የመፍጠርያ መንገዶችን ለመቀየስ ይቻላል። እናም ይህንን ሥራ በአፋጣኝ መስራት ሁሉም በውጭ ያለ ማሕበረሰብ  አባል እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

እዚህ ላይ የፖለቲካ እና የዘር አስተሳሰብ ችግሮች ያደናቅፉታል የሚሉ አስተሳሰቦች እንደሚኖሩ አስባለሁ። እነኝህ ችግሮች ግን በመተዳደርያ ሕጉ ሃገራዊ እና ኢትዮጵያዊ ራዕይ ላይ ከተመሰረተ ብዙ አንድ የሚያደርጉን ነጥቦችን ብቻ ለማጉላት ይረዳል።''ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ወደፊትም አላስብም'' ያለ ወደ ኢትዮጵያዊነት እስኪመጣ ኢትዮጵያውያን ሥራ አይሰሩም ማለት አይቻልም እስከ ዕለተ ምፃትም ድረስ ሁሉ አንድ አይነት አስተሳሰብ እንብድኖረው እና ሃሳብ እንዲያመነጭ አይጠበቅም።ዛሬ ችግሩን የተረዳው ሥራ መስራት ይጀምራል ሌላው ይቀጥላል።

2/ ቀድመው ለሚጠብቁን የተቀነባበሩ የስነ-ልቦና ዘመቻዎች አለመጋለጥ 


ሰሞኑን ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ በማስመልከት ምን ሊደረግ እንደሚችል ቀድሞ መረዳት ተገቢ ነው።እንደ ጣኦት የሚመልኩት የሳውዲ ንጉሳውያን እና ልዑላን ምንም ማለት እንዳልሆኑ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞ ሲናገሩ ማየት ለእራሳቸው ንጉሳውያን ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለሚንቀጠቀጥላቸው  ሕዝብ ማስደንገጡ እና ማናደዱ አይቀርም።ይህ ማለት ሳውዲ አረብያ ባላት መንገድ እና መዋቅር ሁሉ ከወዳጆቿ ጋር ሆና ስሟን ለማደስ ከምትጠቀምበት መንገድ አንዱ ''ኢትዮጵያውያን በየሄዱበት ሕግ አያከብሩም'' ለማስባል እዚህም እዝያም ኢትዮጵያውያንን ስም ለማጉደፍ የሚሰሩ ቀላል የሚመስሉ ግን በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ዘንድ በጊዜ ብዛት ተፅኖ የሚኖራቸው ተግባራት ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠሩ አይከፋም።ለምሳሌ በእየሃገራቱ ጋዜጦች ላይ አርቲክሎች የሚፅፉ ማዘጋጀት፣የቆዩ ቁርሾዎችን ማጉላት፣ኢህአዲግ- ወያኔን ትክክል እንደሆነ ለመሳል መሞከር ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ።

ለእዚህ ተግባር ደግሞ የሚተባበሩ የኢትዮጵያ ስም ሲጎድፍ የእነርሱ የሚተልቅ የሚመስላቸው ከቅርብም ሆነ ከሩቅ አይጠፉም። እዚህ ላይ እራሱ ኢህአዲግ-ወያኔም ተባባሪ እንደሚሆን ማረጋገጥ ይቻላል።በውጭ የሚኖረውን ሕብረተሰብ እንደ ጦር የሚፈራው እና የምጠላው ወያኔ-ኢህአዲግ ለምሳሌ ከሳውዲ መንግስት ጋር ሲነጋገር- ''ይህንን አመፅ የፈጠሩት በመሳርያ ኃይል ያስወገድኩት  የነፍጠኛ፣አክራሪ ክርስትያኖች፣ ፀረ አረብ አመለካከት ያላቸው ናቸው። የእነርሱ ወደ ስልጣን መምጣት ፀረ አረብ ስልጣን ያዘ ማለት ነው'' የሚል የሐሰት ገበያ ሊያደራ ይችላል።

ባጠቃላይ 


በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በያሉበት ያሉትን የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ጨዋነት፣ስነ-ምግባር እና ሌላውን የመረዳት ባህላችንን በጥንቃቄ ከመቸውም በበለጠ መልክ መያዝ ይገባናል።ከእዚህ በበለጠ ደግሞ ወደፊት የሚቀነባበሩልንን የስነ-ልቦና ዘመቻዎች ሰለባ ላለመሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።የስነ-ልቦና ዘመቻዎቹ እንደለመደብን ''ኢትዮጵያዊ በመሆኔ አፈርኩ'' የሚሉ ቃላትን ደጋግመን እንድንናገር ያደርገን እና መጨረሻው አደገኛ ወደ ሆነ  ትንታኔ ይወስደናል።ኢትዮጵያ ዛሬም እጅግ ሃብታም በተፈጥሮ የበለፀገች ሀገር ነች።ይህንን አሁንም ልንጠራጠር አይገባንም።ይህ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ ነው። የቀረን እና መከናወን ያለበት በዘር እና በጎሳ ከፋፍሎ እና ከባዕዳን ጋር ተባብሮ ወደ መጨረሻው ፈተና የሚገፋትን ስርዓት አንስቶ  በአፈራችን ላይ የመኖር መብታችንን ማስከበር ነው።ለእዚህም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ራዕይ ማስቀመጥ እና ከወዲሁ ማዳበር ዛሬ  ጠንካራ የሆነ እንደ ''አለማቀፍ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ'' ሁሉን አቀፍ ድርጅት መመስረት እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅጣጫ በማህበረሰቡ ፍላጎት እና ራዕይ ላይ ተመስርቶ አቅጣጫ መስጠት፣የሚ ታገዙትን ማገዝ አስፈላጊ የሆንበት ወቅት ላይ ነን። ለእዚህ ሁሉ ተግባራት ደግሞ ዘመኑ እራሱ አጋዥ ነው።ተግባሩን ለማከናወንም ሆነ ለማፋጠን የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ብዙ ፋይዳ አላቸው።

ጉዳያችን
ህዳር 7/2006

No comments: