ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, October 25, 2013

በኢትዮጵያ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ የቆየ ማንዴላን የተመለከተ የደህንነት ሚስጥር ዛሬ ይፋ ሆነ።ሚስጥሩን ማንዴላም እስካሁን ድረስ አይውቁትም።

ለኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ስልጠና የሰጡት አፄ ኃይለሰላሴ  ከከዮርዳኖሱ ንጉሥ ሐሰን ጋር


ምንጭ- ሸገር ራድዮ 
ቅንብር- ጉዳያችን ጡመራ 
ቀን ዓርብ ጥቅምት 15/2006 ዓም

ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ የፀረ-አፓርታይድ (የዘር-መድሎ) ተዋጊ አርበኛ መሆናቸው ይታወቃል።በደቡብ አፍሪካ ዘረኛ መንግስት ለእስር የተዳረጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና ወስደው እንደተመለሱ ነበር። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 1962 ዓም ማንዴላ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ኢትዮጵያ ፓስፖርት በመስጠት አጋርነቷን የገለፀች ብቸኛ ሀገር ነበረች።

ከዘመናት በኃላ ማንዴላ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት  የግድያ ሙከራ ሴራ ተደርጎ እንደነበር ሚስጥሩን ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ይዘው የቆዩ በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ፖሊስ መኮንን ዛሬ ጥቅምት 15/2006 ዓም ለመጀመርያ ጊዜ በሸገር ራድዮ የዜና እወጃ ላይ ገልፀዋል።

ኔልሰን ማንዴላ እና ጄኔራል ታደሰ(የማንዴላ አሰልጣኝ በወቅቱ ኮ/ል የነበሩ)ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ

ሻምበል ጉታ ዲንቃ በንጉሡ ዘመን የፖሊስ መኮንን ነበሩ። ማንዴላን በከፍተኛ ሚስጥር እንዲጠብቁ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ጄኔራል ታደሰ(የማንዴላ አሰልጣኝ በወቅቱ ኮ/ል የነበሩ)፣ኮ/ል ፍቃደ እና ሻምበል ፈቃደ ውስጥ ነበሩ።ዛሬ የ76 አምቱ የእድሜ ባለፀጋ  ሻምበል ጉታ ዲንቃ ለሸገር ሲናገሩ እንዲህ አሉ።

'' ማንዴላን እንድጠብቅ ኃላፊነት የተሰጠኝ እኔ ነበርኩ።ማንዴላ የሚያድሩበት እና ወታደራዊ ስልጠና የሚወስዱበት የኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ቦታ ነበር ።በተለይ እርሳቸው የሚገኙበት ቦታ 'የፈንጅ ወረዳ' ነበር የሚባለው።ከአራታችን በቀር ማንም ወደ እርሳቸው ቦታ ዝር ማለት አይችልም። ሲተኙ መስኮት ከፍተው ነው የሚተኙት።...አንድ ቀን ታድያ አብሮኝ ከሚሰራው የፖሊስ ባልደረባዬ በጥብቅ እንደሚፈልገኝ ነገረኝ።ጣይቱ ሆቴል ተቀጣጠርን እና ሃሳቡን ገለፀልኝ።'' ካሉ በኃላ  አሁን አዲስ አበባ ላፍቶ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ሻምበል ጉታ በመቀጠል እንዲህ ብለዋል-

''ጣይቱ ሆቴል የወሰደኝ ሰው ለጊዜው 2000 ፓውንድ በወቅቱ አስቡት 2000 ፓውንድን እና  ሰጥቶ እንዲህ አለኝ- 'ሁለት ዕድል ከፊታችን ተቀምጧል።ሊያመልጠን አይገባም።ከፍተኛ ገንዘብ እናገኛለን።ቀጥሎም ወደ ውጭ ሀገር የመሄድ ዕድል አለን።ከአንተ የሚጠበቀው ማንዴላ በተኛበት ዛሬ ሌሊት በመስኮት ገብተህ በገመድ አንቀህ ግደል እና ውጣ እንደወጣህ መኪና ተዘጋጅቶ ይጠብቅሃል ከእዚህ የውትድርና ሕይወት እንገላገላለን' አለኝ። እኔም ጉዳዩን ከሰማሁ በኃላ በጉዳዩ የተስማማሁ መስዬ ቀጥታ  ለጀኔራል ታደሰ ነገርኩኝ። ጉዳዩ በሚስጥር ተይዞ ይህንን ያደረጉት ሰዎች ተደረሰባቸው እና ከሀገር እንዲወጡ(እንዲባረሩ) ተደረጉ ይህ ሚስጥር ለዘመናት ከእኔ ጋር የኖረ ነው።ጉዳዩን ማንዴላም አያውቁትም።'' ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለኔልሰን ማንዴላ የሰጠቻቸው ፓስፖርት 

ኔልሰን ማንዴላ በወቅቱ እንደ ሻምበል ጉታ ዲንቃ አይነት ታማኝ የኢትዮጵያ የፖሊስ መኮንን ባይገጥማቸው ኖሮ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታሪክ ሂደትም ሆነ የነፃነት ትግሉ ታሪክ ሌላ መልክ በያዘ ነበር።ይህ ጉዳይ እጅግ ትልቅ ጉዳይ ነው።የኢትዮጵያ ፖሊስ ለአፍሪካ ያደረገው አስተዋፆ የሚያጎላ በመሆኑ በኢትዮጵያ የዜና አገልግሎቶች ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶት የዓለም አቀፍ የዜና ሽፋን እንዲያገኝ ጥረት ማድረግ ለኢትዮጵያ ፋይዳው ብዙ ይመስለኛል።እስካሁን ድረስ ማንዴላ በኢትዮጵያ ምን ያህል ድጋፍ ተደርጎላቸው እንደነበር የማያውቅ አፍሪካዊም ሆነ ደቡብ አፍሪካዊ እንዲሁም የዓለም ሕዝብ አለ።በመሆኑም ይህ ጉዳዩን ለማጮህ የሚረዳ ወርቃማ አጋጣሚ ነው።

በመሆኑም ቢያንስ ለሻምበል ጉታ ዲንቃ የኢትዮጵያ ፖሊስ ጠርቶ ማዕረግ እና ሽልማት ከእዚህ ባለፈም ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት እና  ማንዴላ  በሕይወት ዘመናቸው ሳሉ ሻምበል ጉታ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ሄደው እንዲያገኙዋቸው ማድረግተገቢ ይመስለኛል።።ጉዳዩ የደህንነት ሚስጥር የነበረ በመሆኑ በወቅቱ ግድያውን ሊፈፅም የሞከረው አካል ወይንም ሀገር (ማንነቱን ሻምበል ጉታ የተባረሩት ዜጎች የየት ሀገር እንደነበሩ አልገለፁም) ዛሬ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ላይ ጥላ እንዳያጠላ ስጋት ስለሚሆን ዜናው በተፈለገው ደረጃ ለዓለም ሕዝብ እንዳይደርስ የሚደረጉ ስውር ስራዎች እንደማይጠፋ ማጤን ሌላው ሥራ ሊሆን ይችላል።
በመጨረሻም ሻምበል ጉታ ዲንቃ ለሕዝብ ወጥተው ዛሬ ላይ ምንም ምስጢርነት የሌለውን ጉዳይ ለሕዝብ በመንገራቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
ማንዴላ ከእስር እስኪፈቱ ድረስ በኢትዮጵያ ፓስፖርት ነበሩ።ይህ የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት ከእስር በተፈቱ በ 8ኛ ቀን ያገኙት ነው።




1 comment:

Fitsum said...

good to know ......but i m not surprised....Ethiopian's before are known for there responsibility, iron strength and integrity.....and hope We are still the same

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።