አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በአዲሱ የስልጣን እርከን ላይ ሆነው በርከት ላሉ ጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ የመስከርም 24/2006 ዓም የመጀመርያቸው ነው።በእዚህ ቃለመጠይቅ ላይ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተዋል።የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሾች ግን በደንብ ለሚያጤነው ሰው መንግስት አዲስ አይነት አሰራሮች እና ሃሳቦች አሁንም አለማስተዋወቁን እና በአዲሱ 2006 ዓም የህዝቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች እንዳሉ እንደሚቀጥሉ ይገነዘባል።ቃለ ምልልሱ አንገብጋቢ ከሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች ውስጥ ፈፅሞ ያልተመለከታቸው ለምሳሌ-የኑሮ ውድነቱ እየናረ መምጣት፣የስራ አጥ ወጣቶች ችግር ለመቅረፍ መንግስት ስለሚወስደው አፋጣኝ እርምጃዎች፣የትምህርት ጥራት ጉዳይ እና የኢትዮጵያ የውጭ ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ የመናሩ ጉዳይ አልተነሳም። በቃለመጠይቁ ውስጥ ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ የሚከተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሾች ወዴት እየሄድን እና የት ላይ እንዳለን የሚያመላክት ነው።1/ የውሃ እጥረትን በተመለከተ
የአቶ ሃይለማርያም ምላሽ '' በአዲስ አበባ እስከ 90% የሚሸፍን የውሃ አቅም አለ።ችግሩ ስርጭት ላይ ነው።'' በሚል ነው ያለፉት።
እዚህ ላይ እንደተባለው ስርጭት ችግር ከሆነ ችግሩ የመንግስት የሰው ኃይል፣የገንዘብ እና የተክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር ያመላክታል ማለት ነው።ይህም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንግስት አሰራር የሚያሳይ ከመሆን አያልፍም።
2/ ሙስናን በተመለከተ
ሙስናን በተመለከተ አቶ ሃይለማርያም የመለሱት ምላሽ እጅግ አስገራሚ ሆኖብኛል። በመጀመርያ ምላሻቸው እንዲህ አሉ-'' የሙስናው ጉዳይ መጀመርያ ከነበረው እየተወሳሰበ ነው የመጣው አንዱ ክር ስመዘዝ ሌላው እየተነካ ነው ያለው።ቀድሞ ካሰብነው በላይ ትንሽ ውስብስብ ነው የሆነው'' ካሉ በኃላ አንድ የገረመኝን ንግግር አከሉ ''በእኛ (በኢህአዲግ ማለታቸው ነው) እምነት ከእዚህ በፊት ትንሽ ያጠፋ(የሰረቀ) ካለ ከአሁን በኃላ ከተወ ችግር የለውም ዋናው ነገር ከአሁን በኃላ ነው'' የመልሱ መጨረሻ።
ይህ ማለት ከእዚህ በፊት የሰረቁ፣የዘረፉ ሁሉ አሁን ይህንን ተግባር ትተው ቀድሞ የሰረቁትን በመብላት ላይ ብቻ ከተወሰኑ እና እንደ አቶ ሃይለማርያም አገላለፅ ''ዋናው ነገር ከአሁን በኃላ ነው።'' እና መስጋት የለባቸውም ነው።ይህ እስካሁን ድረስ ሙስናን አስመልክተው ከተሰጡት መግለጫዎች ውስጥ ያውም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ሲቀርብ በአለማችን ላይ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም።
3/ ቴሌን በተመለከተ
የስልክ መስመር መቆራረጥ እና ጥራትን በተመለከተ የችግሩ መንስኤ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የሰጡት ምክንያት ''ከጠበቅነው በላይ የተጠቃሚው ቁጥር በመጨመሩ ነው'' የሚል የሚል ነበር።ይህ መልስ ግን አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰጠው ምላሽ ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም የተጠቃሚ ቁጥር እንደጎርፍ የሚመጣ አይደለም።እንበል እንደጎርፍ ጥያቄ ቢመጣ ሲሆን ቀድሞ መስርያቤቱ በአጭር ጊዜ እና በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ ሊቀርቡ የሚችሉ የደንበኞችን ጥያቄ ቀድሞ በገበያ ጥናት ክፍሉ አጥንቶ ከወዲሁ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ያለበት ማን ነው? ድርጅቱ ወይንም መንግስት አይደለም ወይ? አሁንም እንበል እና የደንበኝነቱ ጥያቄ ስለመጣ ብቻ በሌለ የመስመር አቅም መሰጠት አለበት እንዴ? የቁጥር እድገቱ እንዲጨምር ሲባል ብቻ በሌለ የመስመር አቅም የሌላው እየታወከ መሰጠት አለበት ወይንስ ተጨማሪ አቅም ተገንብቶ አቅምን ያገናዘበ ደንበኛ ማፍራት ይገባ ነበር? እንደእውነቱ ከሆነ የእዚህ አይነት መልስ ምን ያህል ስራዎች ምክንያታዊ እና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ እየተሰሩ ለመሆናቸው አመላካች ነው።
4/ የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ
ሰሞኑን ከመንግስት የሚሰጡት በተለይ የኤርትራን ጉዳይ የተመለከቱ መግለጫዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያከበረ ገፅታ የላቸውም።ከእዚህ በፊት በፕሬዝዳንት ደረጃ ያሉት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ''ኤርትራ ድረስ ሄጄ እርቅ እፈጥራለሁ'' አሉን።ቀደም በለው አቶ ኃይለማርያም አስመራ እንደሚሄዱ እና ችግር እንደሌለባቸው አስረዱን።በእዝህኛው ቃለመጠይቃቸው ላይ ደግሞ ''ኳሱ ኤርትራ እጅ ነች'' አሉን። በዲፕሎማሲያዊ ንግግር ''ኳሱ እገሌ ጋር ነው'' ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ምላሹን መስጠት ያለበት ብቻ ሳይሆን ''ተፅኖ የመፍጠር '' አቅሙ (የኃይል ሚዛኑ) ያለው እዚያ ነው።የሚል ትርጉም ይይዛል።ይህ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?
5/ አክራሪነትን በተመለከተ
አክራሪነትን በተመለከተ አቶ ሃይለማርያም ትንሽ ተኮስ ባለ ስሜት ነበር የገለፁት። ''ቀይ መስመሩን ማለፍ አይቻልም'' በሚል ቃል የታጀበ ነበር።ቀይ መስመሩ የሃይማኖት ነፃነትን መጠየቅ? ወይንስ የራስን እምነት አክብሮ መያዝ? ቀይ መስመር ታለፈ የሚባለው ምን ሲታለፍ ነው?በተለይ በአክራሪነት ዙርያ ያነሱት ነጥብ ላይ ስለምድራዊ እና ሰማያዊ ሕይወት ልዩነት ካብራሩ በኃላ ''ከሃይማኖት ተቅዋማት ውስጥ አክራሪዎች እራሳቸውን እንዲለዩ እኔ በግሌ አሳስባለሁ'' ብለዋል። እዚህ ላይ ግን ''እዝያም ቤት እሳት አለ'' የሚለውን አባባል የዘነጉት ይመስላል።ኢትዮጵያ በታሪክ ሕዝቡን ባልመሰሉት ግን ከባህር ማዶ በመጡ ክርስቲያን ነን ባሉ ''ጀሃድስቶች'' አሳር ያየች ምድር መሆኗን የረሷት ይመስላል።የአቶ ሃይለማርያም ቀዩ መስመር የቱ ነው?
አበቃሁ
ጌታቸው
ኦስሎ
No comments:
Post a Comment