ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, October 17, 2013

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለእምነታቸው ዘብ ቆመው ዋሉ! ምንጭ - ሐራ ዘተዋህዶ

ከጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘውና ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው ፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ የተለየ ክሥተት አስተናግዷል፡፡ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚል ርእስ በ፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ በተካሄደው ውይይት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋራ በተለይም በመቻቻልና በኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ዙሪያ ሲከራከሩና በአንዳንድ ኹኔታዎችም ኤክስፐርቶቹን ሲገሥጹ ውለዋል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ÷ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ እንድርያስ÷ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተጨባጭ ኹኔታና ከቀረበው ጽሑፍ እየተነሡ በመረጃ፣ በጥያቄና በትችት ስለ መቻቻል ጽሑፍ ያቀረቡ የሚኒስቴሩን ባለሥልጣናት ፈተና ላይ ጥለዋቸው አምሽተዋል፡፡ የሊቃነ ጳጳሳቱ ምስክርነት ‹‹የባዕድ እምነት አራማጆች በቤተ ክርስቲያንና በካህናት ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉና ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ታላቅ ድፍረት እንደሚፈጽሙ›› ቀደም ሲል ለአጠቃላይ ጉባኤው የቀረቡ ሪፖርቶችን በገሃድ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

የሚኒስቴሩ አማካሪዎችና ባለሞያዎች በበኩላቸው፣ ቅሬታዎቹ በተጨባጭ ማስረጃዎች ተደግፈው በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩል ቢቀርቡላቸው መፍትሔ እንደሚሰጧቸው፣ በሊቃነ ጳጳሳቱ ከተገለጹት በላይ ያልተነገሩ ቅሬታዎች ስለመኖራቸው በየወረዳው ተዘዋውረው መረጃዎችን አሰባስበው ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ በ‹‹ሕግ የተያዙት ጉዳዮች በሕግ እንደተያዙ ጠብቀው እንዲቀጥሉ›› ለዚህም የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጥንካሬ አስፈላጊ መኾኑን አሳስበዋል፡፡

የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጥያቄ፣ አስተያየትና ትችት በከፍተኛ ጥሞና የተከታተለው የአጠቃላይ ጉባኤው ተሳታፊ የሞቀ ድጋፉን ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የውይይት አጀንዳ አጋጣሚውን እንደ ምቹ ኹኔታ ለመጠቀም ያሰቡ የሚመስሉትና ልዩ ፍላጎት የነበራቸው የሚመስሉት አቡነ ሳዊሮስ ውይይቱን ሳይጨርሱ አቋርጠው ሲወጡ ታይተዋል፡፡

‹‹አክራሪነት/ጽንፈኝነት የሚለው ቋንቋ እናንተ ናችኹ ያሰማችኁን፤ ከዚህ በፊት አይታወቅም፤ ዕድሜ ሰጥታችኁም ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችኹ፡፡ አባቶቻችን የእረኛ ሰነፍ ከሩቅ ይመልሳል ይላሉ፤ በሩቅ መቅጨት ሲገባ ታሪካቸው እየተተረከ ብዙ አተራመሱት፤ [የአክራሪነት]መረባቸውን ከላይ ዘርግተዋል፤ መሬት አልነኩም ተባለ፤ መረባቸውን መሬት ዘርግተው፣ ሕዝብ እያተራመሱ ሙስሊሙ ራሱ እኛ አናውቃቸውም እያለ እየጮኸ እንዴት መሬት አልነኩም ይባላል? በእናንተ አነጋገር መሬት ሲነኩ እንዴት ሊያደርጉነጅ ኖሯል? . . .ተቻቻሉ? እስከ ምን ድረስ ነው መቻቻል? ምንድን ነው መቻቻል? አሁን በወለጋ ያለው ኹኔታ መንግሥት በአገሩ ያለ ያስመስላል? ሰው እግሩን እሳት እየበላው ቻል ይባላል? እንድንቻቻል አድርጉን፤ እንችላለን!!›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት በሦስት ወረዳዎች – ነጆ፣ ባቦ ገምቤል፣ ቤጊ – በፖሊቲካና የመናፍቃን አባላት የኾኑ ባለሥልጣናት በሥነ ልቡና ጦርነት ምእመኖቻችንን እየነጠቁን በደል አድርሰውብናል፡፡ አገሩ ለፕሮቴስታንት የተፈቀደና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አታስፈልግም የተባለ ነው የሚመስለው፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/
 
‹‹ከዚህ በፊት በዚህ መድረክ ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም መጥተው ብዙ ነገር አስጨብጫቸው ነበር፤ ምላሽ አላገኘኹም፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ነገር በጋሞጎፋ ሀ/ስብከት ተፈጥሯል፡፡ የደመራ በዓል በሚከበርበት ቦታ ላይ ምትክ ሳይሰጥ ተወስዶ ሱቅ በመከፈቱ ዘንድሮ በመቶ ወረዳ የደመራ በዓል ሳይከበር ሕዝቡ እያዘነ፣ እያለቀሰ ቤቱ ውሏል፡፡ በሴቻ ከተማ ባልተፈቀደ ቦታ ለስምንት ቀን ጉባኤ አዘጋጅተው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ጽላት፣ ቅዱሳን መላእክት እያነሡ ሲቃወሙ ነበር፡፡ ይህ ነዳጅ የተረከፈከፈበት ክብሪት ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ሰልፍ እንውጣ ሲለን ሰላማችንን፣ ልማታችንን እንወደዋለን፤ መብታችንን በሕግ ነው የምንጠይቀው ብለን ከልክለናል፡፡ ጉባኤ ማካሄዳቸውን አንቃወምም፤ ግን ስማችንን ማንሣት ምን ማለት ነው? ይሄ ነው መቻቻል? እኛ ሌላውን አንነካም፤ ስንነካ ግን መብታችንን እንጠይቃለን፤ ቤተ ክርስቲያኗ መሬት መያዟን የወረዳው ባለሥልጣናት መሬቷን ቆርሳችኹ ጉባኤ አድርጉ ይላሉ፤ ይህን እንደ በቀል ነው የሚያዩት›› /ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፤ የጋሞጎፋና ደቡብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹በሶማሌ ክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ የመንግሥት መሥ/ቤቶች ብዙ ሠራተኞች ምእመናን አሉ፡፡ ያሉን አብያተ ክርስቲያናት ግን አምስት ብቻ ናቸው፡፡ በየወረዳው ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ ምእመናን ይጠይቃሉ፡፡ እስከ ክልሉ መስተዳድር ድረስ ለምእመናን የምንጮኸበት፣ መብታችንን የምናስከበርበት ኹኔታ ግን የለም፡፡. . .ምእመናን እምነታቸውን በካሴትና በዘመናዊ መሣርያ ካልኾነ እኛ ተንቀሳቅሰን ለማገልገል የምንችልበት ኹኔታ የለም፡፡ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የምእመናኑን ብዛት ዐውቀንና አጥንተን ያዘጋጀነው ስላለ የሚመለከተው ክፍል መፍትሔ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ የሶማሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹ታሪክ ክፉ ይኹን ደግ እንደ ታሪኩ ነው የሚተረክ፤ ወንድማችን [ከዕለቱ የሚኒስቴሩ ሦስት ተናጋሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ገዛኽኝ ጥላሁን] ይህን ታሪክ ስታቀርብ ምን ያህል ላይሰንስ አለኽ? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ፤. . .ክርስትና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው የሚለው ሌላ ጊዜ እንዳይደገም፣ ዛሬ ግራጁዌት አድርጉት፤ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ክርስቶስ ካረገ ዓመት አልሞላውም፤ ገና ከኢየሩሳሌም አልተወጣም፤ ከሰው አይደለም ደግሞ ከእግዚአብሔር ነው የተቀበለችው፡፡ (የሐዋ.8÷26) ባለሥልጣን ሁሉ አገር የሚጠላ ምንድን ነው? በዓለም በትልቁ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፤ በእግዚአብሔር ማመንንም የተቀበልን ከአይሁድ በፊት ነው፡፡ ታሪኩን አታዛቡ፤ ከዚህም ስትመጡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሠለጠነ፣ ቢቻል ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ የኾነ፣ በጳጳሳቱ ፊት ለመናገር የሚገባው መኾን አለበት፤ አታስቆጡን!. . .ቤተ ክርስቲያን እንግዳ ሲመጣ ሃይማኖትኸ ምንድን ነው አትልም፡፡ እግር አጥባ፣ አብልታ ነው፤ ግን ልታስተምሩን ስትመጡ ሳብጀክቱን ግራጁዌት አድርጋችኹ ኑ!›› /ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

‹‹. . .ችግሮቹ መፍትሔ አጥተው ቀርተዋል፡፡ ስድስት አድባራት ተቃጥለዋል፤ ሦስቱ በአንድ አካባቢ፣ ሦስቱ በተራራቀ ኹኔታ፡፡ ቢጮኽ የክልሉ መንግሥት አይሰማም፤ መልስም አይሰጠም፤ እንዲያውም ያስተባብላል፤ የተበደለ ሲናገር ፖሊቲካ ነው እያሉ ያተራምሱናል፤ ሐቅ ሲነገር ድብቅ የለውም፤ ሌትም ቀንም ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለ፣ የሚጮኽበት እየታጣ ነው፡፡. . .የመንግሥት ሥልጣን የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት? ለሌላው ብቻ ነው የቆሙት? ይህ የሰላም መደፍረስ አይደለም? መቻቻል የሚባለው አማርኛ ምንድን ነው? አማርኛ ነው እንዴ የምታመርቱት? በየቢሯቸው ሄጃለኹ፣ አንዱ እንደውም ተቆጣኝ፤ ይኸው ዘመን ተቆጥሯል፤ ዐርባ ዓመት ኾኗል፤ ለሕዝቡም ለመንግሥትም የምንኖረው እኛ ብቻ ነን፡፡ ለምንድን ነው በሽፋንነት የምትጠቀሙብን? ሁሉም ሲያጭበረብረን፣ ሲያታኩሰን፣ ሲያቃጥለን የሚኖረው መንግሥትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡ ይቅርታ አድርጉልን፡፡›› /ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/
ምንጭ - ሐራ ዘተዋህዶ
http://haratewahido.wordpress.com/2013/10/16/ብፁዓን-ሊቃነ-ጳጳሳቱ-ለእምነታቸው-ዘብ-ቆ/#more-2160 

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...