ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, October 19, 2013

በቤተ ክርስቲያን ላይ የአስተዳደር፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት የሚፈጽሟቸው በደሎችና ተጽዕኖዎች – የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ትችት፣ ጥያቄና ምስክርነት ሙሉ ቃል


ምንጭ - ሐራ ዘተዋህዶ
http://haratewahido.wordpress.com/2013/10/18/በቤተ-ክርስቲያን-ላይ-የአስተ/#more-2179
የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴፪ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚለው መርሐ ግብር ‹‹የብዝኃነት አያያዝ፣ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርእስ አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን፣ አቶ ታዴዎስ ሲሳይ እና አቶ ጣሰው ገጆ በተባሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሦስት ከፍተኛ አማካሪዎችና ባለሞያዎች ጽሑፍ መቅረቡና ውይይት መካሄዱ ተዘግቧል፡፡

በውይይቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተጨባጭ ኹኔታ በመነሣትና ጽሑፉ በቀረበበት ይዘቱ በመገምገም በተለይ በመቻቻል፣ በመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነትና በኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ዙሪያ ጥያቄ አንሥተዋል፤ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ቃል በተነገረበት አኳኋን ወደ ጽሑፍ ተመልሶ ቢቀርብ በተለይ በስፍራው ላልነበሩና በሌሎችም መንገዶች ለመከታተል ዕድል ላላገኙ ወገኖች ይጠቅማል በሚል በጡመራ መድረኩ ተስተናግዷል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በጉዳዩ ላይ የሰነዘሩት ትችት፣ ያቀረቡት ጥያቄና የሰጡት ምስክርነት በሁሉም የዓመታዊ ስብሰባው ተሳታፊዎች ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን የመንግሥትን ተቋማት በሚመሩ ዓላውያንና መናፍቃን ጫናዎች መማረሯን ከመግለጽ ባሻገር በደሎችና ተጽዕኖዎች እስካልተወገዱ ድረስ መጪውን የከፋ አደጋ የጠቆመችበት፣ የመንግሥቱንም ተወካዮች በብርቱ የመከረችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ስለመኾኑ ከፍተኛ መግባባት ተደርሶበታል፡፡

ይልቁንም የውይይቱ ቁም ነገሮች፣ መንግሥት የፀረ አክራሪነት እንቅስቃሴዎቹን በሚያብራራባቸው ሰነዶቹ እንደሚያትተው፣ በፕሮቴስታንት ሃይማኖት ሽፋን የጠባብነት አመለካከት ፖሊቲካ ከሚያራምዱ አካላት ጋራ ትስስር መፍጠሩና ሽፋን መስጠቱ፣ ‹‹ከማቆጥቆጥና አዝማሚያነት›› አልፎ በገሃድ መገለጹን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ‹‹የመልካም አስተዳደርና ሴኩላሪዝም ጥያቄን እንደ መንሥኤ ወስዶ ሕዝብን የጽንፈኝነት አመለካከት በማስያዝ›› ሰላማዊ መስተጋብሩን የማናጋት ሙከራው ለማቃናት አዳጋች ወደሚኾንበት ዳርቻ እየነጎደ መኾኑን ነው፡፡ ስለዚህም ‹‹ለመንግሥት መዋቅር የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከአድሏዊ አሠራር በጸዳ መልኩ እንዲሰጡና ፍትሐዊ ጥያቄዎች አለምንም ማጉላላት እንዲፈጸሙ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ›› በቃል የሰፈረው በተግባር ተተርጉሞ መታየት ይኖርበታል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ስላስተማሩን እናመሰግናለን፡፡ እንግዲህ ቤተ ክርስቲያኗ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምትነፍገው ነገር የለም፤ ያላትን ሁሉ ታበረክታለች፤ ታገለግላለች፡፡ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነት የሚለውን ቋንቋ እናንተ ናችኹ ያስተዋወቃችኹን፤ እናንተው ናችኹ ያሰማችኹን፤ ከዚያ በፊትም አይታወቅም፤ በደርግም ይኹን በሌላ፡፡ እንደገና ደግሞ ብዙ ጊዜ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እያላችኹ ዕድሜ ሰጥታችኹ ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችኹ፡፡

አባቶቻችን፣ የእረኛ ሰነፍ ከቅርብ ሲሉት ከሩቅ ይላሉ፡፡ ወዲያው በአጭሩ መቅጨት ሲገባ ታሪካቸው እየተተረከ፣ እየተተረከ፣ እየተተረከ ብዙ ሕዝብ አተራመሱ፡፡ አዎ፣ ጥያቄዬ÷ ‹‹መረባቸውን በላይ ዘርግተዋል፤ መሬት ግን አልነኩም፤›› አሉ፡፡ እንዴ፣ ነክተው አይደለም ይህ ሁሉ የሚተራመሰው! መረባቸውንማ መሬት ዘርግተው ሕዝብ መካከል ገብተው፣ ሙስሊሙ ሕዝብ እንኳ ‹‹እኛ አናውቃቸውም፤ የእኛ አይደሉም›› እያለ እየጮኸ፣ እየጮኸ መረባቸውንማ መሬት አስነክተው ወጣቱን ትውልድ የመረዙት እነርሱ ናቸው፡፡ እንዴት መሬት አልነኩም፤ መረባቸው ወደ ላይ ነው ይላሉ? እንደ እናንተ መረባቸው መሬት ሲነካ እንዴት ሊያረጉን ይኾን?

ሁለተኛ ጥያቄዬ፣ ‹‹መሬትም ሕዝብም የነገሥታቱ ነበር›› ብለዋል፡፡ አሁንስ የማን ነው? ይልቁንም ከአንድ ቤት ‹ግድግዳው የቤቱ ባለቤት ነው፤ ሳሎኑ የመንግሥት ነው› የሚለው ዐዋጅ የአሁን አይደለም እንዴ? ለኢትዮጵያዊነቱ ዋስትና የለውም፤ ይኼ የእኔ ነው የሚለው ከሌለ ምንድን ነው? ይህች የእኔ የኢትዮጵያዊነቴ መገለጫ ናት ካላለ ምንድን ነው ኢትዮጵያዊነት? አሁንም መሬቱም ሕዝቡም የእናንተው ኹኖ ሳለ ለፊቱ፣ ለነገሥታቱ መስጠታችኹ በምን ተመልክተውት ነው?

ሌላው፣ ተቻቻሉ፣ ተቻቻሉ. . .እንዴት ነው መቻቻል? እስከ ምን ድረስ ነው መቻቻል? መቻቻል ጥሩ ነው፡፡ እንደውም ከዚያ በላይ ነው የእኛም የሚያውጀው፡፡ ይህን ጉንጭኽን ቢመታኽ ይህን ስጠው፤ ይህም ለማንም ወንበዴ ሳይኾን የቤተሰብ ግጭት እንዲያልፍ ነው፤ ከወንድምኽ ጋራ ያልፋል ጠቡ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ÷ ‹‹ማንም ሰው እኔን መላጣ ብሎ መሳደብ ይችላል፤ መላጣውን ግን መንካት አይችልም፤›› ነው ያሉት፡፡

እንዴ! በእውነቱ ለምሳሌ፣ አንድ ሙስሊም ሙተዋል በደቡብ ወሎ፡፡ በጠቅላላ፣ ሴቱም ወንዱም በሰላማዊ ሰልፍም በሁሉም ነገር ጩኸቱን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ግን ብዙ ሰዎች ታርደዋል፤ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ነገር ግን በማስ ሚዲያ እንኳ እንዳይነገር ነው የተደረገው፡፡ እዚያው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ ቤተ ክርስቲያኑም ተቃጥሎ ሰዎቹም በቢላዎ ታርደው በማስ ሚዲያ እንኳ እንዳይሰማ ተደርጓል፡፡ አሁን ወለጋ ያለው አካሄድ፣ ሂደት መንግሥት በአገሩ ያለበት ይመስላል እንዴ! በእውነቱ፣ እንችላለን፤ ነገር ግን አንድ ሰው እግሩን እሳት እየበላው ቻል ይባላል? እሳት እያቃጠለው? እንድንቻቻል አድርጉን፤ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ይስጠልኝ፡፡



ብፁዕ አቡነ ኄኖክ

የምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የዚህ ታላቅ ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች በሙሉ፣ ስለተፈቀደልኝ አመሰግናለኹ፤
በዛሬው ዕለት በዚህ ታላቅ ጉባኤ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ትምህርት ለመስጠት የመጣችኹ እንግዶቻችን እናመሰግናለን፡፡

በምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት በሦስት ወረዳዎች የደረሱብን ተጽዕኖዎችና በደሎች እናንተን ስለሚመለከት ማስታወሻ ይዛችኹ ለሚመለከተው የበላይ አካል እንድታሳውቁልን ለማሳሰብ ነው፡፡ ጉዳዩ በትላትናው ዕለት ለአጠቃላይ ጉባኤው ባቀረብነው የሀ/ስብከታችን ሪፖርት በሰፊው ተነሥቷል፤ ሰዓት እንዳልሻማ በአጭሩ ለመግለጽ እሞክራለኹ፡፡

በምዕራብ ወለጋ ነጆ ወረዳ ከዐሥር በላይ የፕሮቴስታንት ጸሎት ቤቶች አሉ፡፡ የሙስሊም አምስት መስጊዶች አሉ፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ብቻ ነው ያለው፡፡ ሦስተኛ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ለማዘጋጃ ቤት ወረዳ ቤተ ክህነቱ ጠይቆ ተፈቅዶላቸው፣ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው፣ ጉልላት አስቀምጠው ከጨረሱ በኋላ አፍርሱ የሚል ጥያቄ ተነሣ፡፡ ወደ ስድሳ የሚኾኑ ምእመናን አናፈርስም ብለው በመቃወማቸው ግብግብ ተፈጠረ፤ ስድሳዎቹንም አሰሯቸው፡፡ ከስድሳዎቹ ምእመናን ሁለቱ የመንግሥት አካላት ነበሩና ‹‹ባለሥልጣናትን ደፍሯችኋል፤ ሰድባችኋል›› በሚል በዐቃቤ ሕግ ተመስክሮባቸው ወደ ሦስት ዓመት እንዲታሰሩ ተወስኖባቸው ነበር፡፡ በአካል ወደሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቀርበን ከጠዋቱ 4፡00 – 11፡00 በመጨቃጨቅ ሁሉም እንዲፈቱ አድርገናል፡፡

ይኹንና ከዚህም በኋላ ‹‹ቤተ ክርስቲያኑ መፍረስ አለበት›› የሚለው አቋም ቀጠለ፡፡ እኛም እየተከራከርን ጉዳዩ በፍ/ቤት ተይዞ ነው ያለው፡፡ ምንድን ነው ለማሳሰብ የምፈልገው÷ እዚያ ያሉቱ ባለሥልጣናት፣ ከቀበሌ እስከ ወረዳ ያሉ ባለሥልጣናት ተባብረው ‹‹ካቢኔ አልወሰነም›› በማለት ነው ቤተ ክርስቲያኑ እንዲፈርስ ውሳኔ ያስተላለፉት፡፡ በዚህ ተጽዕኖ በሕዝባችን ላይ የሥነ ልቡና ጫና እየደረሰ ነው፡፡ የመንግሥት አካላት ኾነው ይህን በማድረጋቸው አዝነናል፡፡ ገዳዩ በፍ/ቤት ተይዞ ስላለ ይህን ለሚመለከተው ክፍል እንድታሳውቁልን ነው፡፡

ሁለተኛ፣ ባቦ በተባለው ወረዳ በቤተ ክርስቲያን ዕጣን አዙር መሬት ላይ አንድ ካህን እርሻ እያረሱ፣ ለእርሻ የሚገባውን ሥራ እየሠሩ እያለ የወረዳውን የጸጥታ ዘርፍ ሓላፊና ፖሊሶችን ይዞ ካህኑን በሰደፍና በዱላ ከመደብደብም አልፎ፣ ‹‹ይህን አገር ጠዋት ለቀኸ ውጣ! ይህች አገር የነፍጠኛ አገር አይደለችም፤ ይህ የኦሮሚያ ክልል ነው›› በሚል ደብድበዋቸው፣ በቤተ ክርስቲያኑ አካባቢ ያሉትን ምእመናንንም ‹‹ቤተ ክርስቲያን ልትሠሩ ያሰባችኁበት ቦታ የቱ ነው? ይህን ዐውጡ›› ብለው ወደ ሦስት የሚደርሱ ምእመናንን ይደበድቧቸዋል፡፡ ሁለቱ ሮጠው አመለጡ፤ አንዱ ሽማግሌ ነበሩና ይዘው አንበርክከው፣ ‹‹ፀሐይን ትክ ብለኽ ተመልከት›› ብለው ለ15 ደቂቃ ያህል አሠቃዩዋቸው፡፡ በዚህ የተነሣ ባለቤታቸው ደንግጠው ወድቀው በሦስተኛው ቀን ዐረፉ፡፡ ይኼ ቤተ ክርስቲያን ለምን ትሠራላችኹ በሚል በምእመኖቻችን ላይ የደረሰባቸው በደል ነው፡፡

ሌላው በሰንበት ቀን፣ ‹‹ካህኑ ቀዳሹ ብቻ ይቅር፤ እናንተ ውጡ፤ ሥሩ!›› ብለው በሰንበት ቀን እርሻ እንዲያርሱ ያደርጓቸዋል፡፡ በቅዱስ ሚካኤል ቀን፣ በሰንበታት ቀን በቤተ ክርስቲያን በጸሎት ላይ ያሉ ምእመናን እንዲወጡ እየተገደዱ ብዙ ተጽዕኖ እየደረሰብን ነው ያለው፡፡ ይህን የሚያደርጉ የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ በሃይማኖት ተጽዕኖ በሕዝባችን ላይ የሥነ ልቡና ጫና እያደረሱ ነው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ እንጂ በዚህ ወረዳ ላይ አያሌ ግፍ ነው የተሠራው፡፡ በ፳፻፭ ግንቦት/ሰኔ እቦታው ድረስ ከዞኑ ባለሥልጣናት ጋራ ሄደን፣ የማጣራት ሥራ ሠርተን አሁን ጉዳዩ በፍ/ቤት ተይዞ ነው ያለው፡፡ ሰዎቹ ለፍርድ ቀርበዋል፤ መቼ እንደሚፈረድ ባናውቅም፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፣ ቤጊ የሚባል ወረዳ አለ፡፡ ቤጊ ወረዳ ከምዕራብ ወለጋ ወደ 250 ኪ.ሜ ነው ርቀቱ፡፡ እዚያ አካባቢ ሙስሊሞች ናቸው የሚበዙት፡፡ ያሉት ምእመናን ጥቂቶች ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ በቅርብ ርቀት፣ 70 ሜትር ርቀት ላይ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ፈቅደናል›› በሚል ለመካነ ኢየሱስ ቸርቻቸውን እንዲሠሩ ፈቀዱላቸው፡፡ ሕዝቡ አይሠራም ብሎ ለተቃውሞ ወጣ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አንድ ዲያቆን ተደብድቦ በሦስተኛ ቀኑ ነው ያረፈው፤ የዛሬ ሁለት ዓመት፡፡ ‹‹በወባ በሽታ ነው የሞተ›› ተብሎ በፍርድ ቤቱ የሐሰት ማስረጃ ከዶክተሩ ታዘዘ፡፡

የዞኑን የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ሓላፊ ሀ/ስብከቱ፣ እኔም ባለኹበት ሔደን እንዲጣራ ተደርጎ በገደሉት ሰዎች ላይ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነገሩ ሥር እየሰደደ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በ፳፻፭ ዓ.ም ለሰውዬው ብር ሰጥተውት ‹‹መሬቱን ከግለሰብ ገዝተናል፤ የእኛ መሬት ነው፤ እዚህ ላይ ቸርች መሥራት አለብን›› ብለው ሁለተኛ ቅሰቀሳ ጀመሩ፡፡ ሕዝቡ፣ ‹‹በሕግ አምላክ! የዛሬ ሁለት ዓመት ልጃችን ሞቷል፤ አሁንም ደም መፋሰስ ይመጣል፤ እዚህ አትሠሩም›› ብለው ሲከላከሉ እዚያ ያሉት የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ሐላፊ ‹‹መሠራት አለበት›› እያለ ሕዝቡን አስፈራርቶ፣ ከ70 ምእመናን በላይ ለኻያ አራት ሰዓት አስሯቸዋል፤ በበዓል ቀን ተይዘው ወደ ዞኑ ማረሚያ ቤት ወርደው አድረዋል፡፡ የሚመለከታቸውን አካላት፣ ይህ ነገር ትክክል አይደለም ብለን አስፈትተናቸው ቦታው ለእኛ ተወስኖ፣ ለእነርሱ ሌላ ቦታ ተሰጥቶ ሰላሙ ወርዷል፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

ሌላው ግምቢ እና መንዲ ላይ በትምህርት ቤት ከልጆቻችን አንገት ላይ ማዕተባቸውን፣ መስቀላቸውን እየበጠሱባቸው ነው፡፡ ይህን የሚፈጽሙት መምህራን ናቸው፡፡ ወደ ዞን ሄደን ከሠናል፡፡ ስንከሥ ‹‹ከላይ መምሪያ ተላልፎ ነው፤ በሸሪዓ ሕግ ሴቶች ራሳቸውን እንዳይከናነቡ፣ ክርስቲያኖች ደግሞ በአንገታቸው ማዕተብ፣ መስቀል እንዳያስሩ ከላይ መንግሥት መመሪያ አስተላልፎልናል፤ ስለዚህ መስቀል ማሰር አይቻልም›› እያሉ ከአንገታቸው በጣጥሰውባቸዋል፡፡ ፖሊሶች ሳይቀሩ ከአምስት ልጆች ጋራ ከአንገታቸው ማዕተብ ከመበጠስ አልፎ ደብድበዋቸው የማጣራት ሥራ ስንሠራ ከሁለቱ ሳጅኖች አንዱ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ ኾኖ ነው የተገኘው፡፡

እንዲህ፣ እንዲህ ያለ በደልና ተጽዕኖ እየደረሰብን ነው፡፡ ‹አገሩ የፕሮቴስታንት አገር ነው፤ ለእነርሱ ብቻ ነው የሚፈቀደው የተባለ ነው፤› የሚመስለው፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አታስፈልግም የተባለ ስለሚመስል አፋጣኝ መፍትሔ እንፈልጋለን፡፡

ከተሰጠው ትምህርት ያልገባኝ፣ ክርስትና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ገባ የሚል ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ግን በ፴፬ ዓ.ም. በጃንደረባው አማካይነት ክርስትናን እንደተቀበለች ነው የምታምነው፤ የምታስተምረው፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን አባ ሰላማ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ክርስትናን ያስፋፋበት ነው እንጂ የገባው በ፴፬ ዓ.ም. ነው፡፡ የተናገሩት ነገር ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ጋራ ይጣረሳል፡፡ ከምን አንጻር ነው የተናገሩት?



ብፁዕ አቡነ ኤልያስ

የጋሞጎፋና ደቡብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ በዕለቱ ከመንግሥት ለውይይት ተወክላችኹ የመጣችኹ፤
ርእሳችን መቻቻል ነው የሚለው፡፡ ከዚህ በፊት ክቡር ዶ/ር ሽፈራው በቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ መጥተው ብዙ ነገሮችን አስጨብጫቸው ነበር፡፡ ምላሹን ግን እስከ አሁን አላገኘንም፡፡ ያን ደግሜ ለማንሣት እገደዳለኹ፡፡ ጉዳዩን እናንተ እንድትሰሙት ለማለትና ሐዘናችንን ጉባኤው መስማቱ አስፈላጊ ስለኾነ እንጂ የጋሞጎፋ ዞን መስተዳድር ባለሥልጣናቱ በሙሉ ከእኛ ጋራ እየረዱን ነው ያሉት፡፡ ችግሩ ወረዳዎች ላይ ነው ያለው፡፡ ዞኖቹ አያዝዙንም እስከ ማለት የደረሱ የመንግሥት ወረዳ ባለሥልጣናት ስላሉና ይህም በብዙ ቦታ የሚያጋጥም ችግር በመኾኑ እንዲታይ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ፣ በዚህ በመስከረም ወር በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተደርጎ የማይታወቅ በሀገረ ስብከታችን የተፈጸመ በጣም አሠቃቂ ጉዳይ ገጥሞናል፡፡ በበቶ ወረዳ በዑባ ደብረ ፀሐይ ለብዙ ዓመታት ሕዝቡ ሲያከብርበት በኖረው ቦታ ላይ ምትክ ቦታ ሳይሰጥ ቦታው ለመናኸርያ ተሰጥቶ፣ ሱቆች ተሠርተውበት ሌላ አገልግሎት ተጀምሮበታል፡፡ ቦታው እንኳ አስፈላጊ ኾኖ ቢገኝ ለልማት እንደሚያስፈልግ ሕዝቡን አወያይቶ በመግባባት፣ ትክ ቦታ ሰጥቶ በመኾን ሲገባው ኻያና ሠላሳ ዓመት ከዚያም በላይ ደመራ ሲለኮስበት የነበረበትን ቦታ ለሌላ ሰጥተው፣ አምናም በጭቅጭቅ ነበር የተከበረው፣ ዘንድሮም በበቶ ወረዳ ዑባ ደብረ ፀሐይ ሕዝቡ የደመራን በዓል ሳያከብር ነው የዋለው፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ከባድ ሐዘን ነው፡፡

በሀገራችን ታሪክ ስናነብ ጦርነትም ቢኾን የደመራ በዓል ሳይከበር እንደዋለ ያጋጠመን ርእስ የለም፡፡ ይህ የተፈጸመው በወረዳው ባለሥልጣናት በውይይት ያልተደገፈ አላስፈላጊ ጥናት፣ ዞኑ በደብዳቤ መመሪያ ቢሰጥ ሊቀበሉ ባለመቻላቸው ሕዝቡ የደመራን በዓል ሳያከብር በቤቱ እያለቀሰ፣ እያዘነ ነው የዋለው፡፡ ይህ እንዴት ይታያል? መቻቻል የሚለውን መንግሥት ይሰብካል፤ መንግሥት የመደባቸው ሰዎች ደግሞ መቻቻልን እያበላሹ፣ እያጠፉ ይገኛሉና ሊጠና የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ፣ ለክቡር ዶ/ር ሽፈራው የነገርኋቸው፣ ዋጂፎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቦታን አስቀድሞ የእኛ እምነት ተከታይ የነበሩ ሰዎች የቤተ ክርስቲያኑን መሬት ይዘው ያገለግሉ፣ ይሠሩ ነበር – ሰበካ ጉባኤ በመኾን፣ ኮንትራት አርሰን እናስገባለን በማለት ቦታው ይዘው ሲያበቁ በመጨረሻ ሃይማኖታቸውን ወደ ሌላ ቀይረው ቦታውን እንዳለ ወስደውታል፡፡ እነኚህ ግለሰቦች በየግላቸው ከአንድ ሰው በቀር በከተማው ውስጥ የየራሳቸው ቦታ አላቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታ በተጨማሪ በመውሰድ ክሥም ቢከሠሥ ፍ/ቤቱ ለእነርሱ ነው የፈረደው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ መሬቱ ይዞታ ባለቤትነቷን በሕግ ያረጋገጠችበት ደብዳቤ እያላት ፍርድ ቤቱ ለእነርሱ ነው የፈረደው፡፡ እንደገና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለክልሉ ደብዳቤ ጽፈን ትእዛዝ ደርሶ ቦታው ተጠንቶ እንዲመለስልን ቢወሰንልንም እስከ አሁን አልተመለሰም፡፡ ይኼ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትፈርስ ነው፤ የእኛኑ ቦታ ከልክለውን፣ ሌላ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታም አጥተን እየተገፋን ከባድ ችግር ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህ ሊጠና ይገባዋል፡፡

በተጨማሪ መቻቻል የሚለውን ቤተ ክርስቲያናችን ጌታ ባስተማረው ወንጌሉ መሠረት ጠንቅቃ ታውቀዋለች፡፡ ዛሬ አይደለም መቻቻልን የምታውቀው፡፡ ጌታ በወንጌሉ÷ ስንዴ ተዘርቶ ነበር፤ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ተገኘ፤ መላእክቱ ወረዱና እንክርዳዱን እንንቀለው አሉ፤ ኅቡረ ይልሐቊ፤ እኔ በአዝመራ ሰዓት ስንዴውን ለብቻ እንክርዳዱን ለብቻ እለየዋለኹ ነው ያለው ጌታ፡፡ ቤተ ክርስቲያን መቻቻልን የምታውቀው በዚህ ነው፡፡ የመቻቻል መሥመራችን ይኼ ነው፡፡

ዘንድሮ በአርባ ምንጭ ሴቻ ከተማ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ስምንት ቀን የሚፈጅ ጉባኤ ተዘጋጅቶ÷ ጉባኤው ያድርጉ እኛ አንቃወምም፤ ግን በጉባኤው ላይ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብሎ ማንሣት፣ ጽላቱን፣ መላእክቱን፣ ቅዱሳኑን እያነሡ መቃወም ይኼ ሌላ ክብሪት ነው፤ ነዳጅ የተርከፈከፈበት ክብሪት ማለት ነው፡፡ እንዴት ነው መቻቻል የሚባለው ነገር? ሕዝባችን የተቃውሞ ሰልፍ እንድንወጣ ጠየቀን፡፡ አንወጣም፤ በሕግ ነው የምንጠይቀው፤ አገራችንን እንወዳለን፤ ልማታችንን እንወዳለን፤ ሰላምችንን እንወደዋለን በማለት ሕዝቡን ከልክለነዋል፡፡ አሁንም በሕግ ለመጠየቅ ተዘጋጅተናል፡፡ እኛ ጉባኤውን አይደለም የምንቃወመው፤ ሺሕ ጊዜ ይደረግ አንቃወምም፡፡ የእኛን ስም ማንሣት ምን ማለት ነው? ‹‹ከኦርቶዶክስ ይህን ያህል ሺሕ ሰው የዛሬ ዓመት ይመጣል›› አሉ፡፡ መቻቻል ማለት ይኼ ነው እንዴ? ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ እኛ የማንንም መብት አንነካም፤ ስንነካ ግን አቤቱታችንን እናቀርባለን፤ አትንኩንም እንላለን!!

ብዙ ፈተና ነው ያለው፤ ‹‹የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሁሉ ቦታ ይዛ. . .›› እያሉ እንደውም የወረዳ ተሿሚዎቹ እንዴት መሰላችኁ የሚያዩት÷ እንደ መበቀል፣ ቤተ ክርስቲያኗ ፊውዳል ኾና ሕዝቡን፣ አገሩን ስትበድል እንደቆየች አድርገው የሚያዩ ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ መሬት ለኦርቶዶክስ ማን ነው የሰጠው? ሂዱ ቁረሱና በኦርቶዶክስ ቦታ ላይ ጉባኤ አድርጉ!›› እያሉ ሕዝቡ እርስ በርሱ እንዲጋጭ፣ እንዲጣላ ይገፋፋሉ፡፡ የጋሞጎፋ ዞን ግን በብልህ አስተዳደር ስለሚመራ ብዙ ችግሮቻችንን ፈተውልናል፤ ይህንንም እናንተ እንድትሰሙት ነው፡፡ ተዉ እንድትሏቸው፣ መሥመር ይዘው እንዲኖሩ፡፡

እኛ ማንንም አልነካንም፤ ሲነኩን ግን አቤቱታችንን እናቀርባለን፤ አትንኩንም እንላለን፡፡ ሰላማችንን፣ ልማታችንን፣ አገራችንን እንወዳለን፡፡ ይህ በጥንቃቄ እንዲታይ ነው፡፡ እንግዲህ እናንተንም እጠብቃለኹ፡፡ ይህን ጥያቄ ይዛችኹ ሄዳችኹ የተነጠቀው የቤተ ክርስቲያኗ ቦታ በቀጣዮች ዐሥር፣ ዐሥራ አምስት ቀናት እንድንረከብ ታደርጉ ይኾናል፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡



ብፁዕ አቡነ ያሬድ

የሶማሌ(ጅግጅጋ) ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጉባኤው ተሳታፊ አባላት በሙሉ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ

ቅድም ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሲብራራ እንደነበረው፣ ከአራቱ ክልሎች አንዱ የሶማሌ ክልል ነው፡፡ ክልሉ ዘጠኝ ዞን ያለው፣ ብዙ ወረዳዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ ከዞን ጀምሮ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ የመንግሥት ት/ቤቶች፣ ሆስፒታል፣ ቴሌ፣ መብራት ኃይል፣ ባንክ የመሳሰሉት በሙሉ የሚሠሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ምእመናን አሉ፡፡ ለእኒህ ምእመናን ሁሉ በክልሉ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት አምስት ብቻ ናቸው፡፡ የምንጮኸበትም ቦታ የለም፡፡ መንግሥትም ያን አገር ያዝበታል ወይ ለማለት፣ ጥያቄው መልስ ቢያገኝም ባያገኝም እኔ የምጠይቀው፣ ምእመኖቻችን በየዞኑ ላይ፣ በየወረዳው ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከል ጥያቄ አለ፡፡ ከወረዳ ጀምረን እስከ ክልሉ መስተዳድር ድረስ ብንከሥም ብንጮኸም፣ የመጨረሻ ውሳኔ ዐጣንም አገኝንም ፌዴራል ሠበር ላይ ነው፡፡ እስከ ክልሉ መስተዳድር ድረስ መዋቅሩ የእነርሱ ነው፡፡ አቤት የምንልበት፣ ቦታ የምንመራበት፣ ያለንን ይዞታ የምናስከበርበት፣ የምእመኖቻችንን ጩኸት የምናሰማበት ቦታ የለም፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ በኦጋዴን ዞን አንድ በጎ አድራጊ ምእመን ‹‹ቤተ ክርስቲያንን ትረዳለኽ›› ፖሊሱ የመኪና አገልግሎት ስጠኝ ብሎት አሳፍሮት ይዞት ሔዶ ከመሥሪያ ቤቱ ካደረሰው በኋላ ‹‹ገጭተኸኛል›› በሚል ሰበብ ወዲያውኑ ወደ ዞኑ ፍ/ቤት አቅርቦት ብር 280,000 አስፈረደበት፡፡ አገልግሎት ስለ ሰጠው ብቻ፣ ያለ ምንም ማስረጃ ገጭተኸኛል በማለት ብቻ!! በአካባቢው አቤት የምንለው፣ የምንጮኸው ወደ መከላከያ እንጂ ሌላ አካል ፍጹም የለም፡፡ ወደ መከላከያ ጮኸን አንድ ጄኔራል መኰንን ነገሩ በሽምግልና የሚፈታበት መንገድ ቀይሰው ከብር 280,000 ወደ ብር 15,000 ወርዶ ክፍያው እንዲፈጸም ተስማማ፤ በጎ አድራጊው ሰውዬ ይግባኝ ቢጠይቅ እስር ቤት አስገቡት፡፡ በፌዴራል በኩል አቤቱታ አቅርበን በሁለተኛው ቀን ክፍያው ተፈጽሞ ሰውዬው ነጻ ወጡ፡፡

አሁንም በብዙ ቦታዎች ምእመኖቻችን ክርስትና የሚነሡበት፣ ቅዱስ ሥጋውን ክብር ደሙን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ዞን ወደ ሌላው በጣም ረጅም ርቀት ስላለው ፍጹም አዳጋች ነው፡፡ ምእመኖቻችን እምነታቸውን እየጠበቁ ያሉት በዚሁ በካሴት፣ በዘመናዊ መሣርያ ካልኾነ በቀር በእኛ በካህናት በኩል ተንቀሳቅሰን አገልግሎት የምንሰጥበት መንገድ ፍጹም የለም፡፡ በሶማሌ ክልል በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ላይ ያለው ተጽዕኖ ከሳዑዲ ዐረቢያ የሚበልጥ እንጂ ያላነሰ ኾኖብናል፡፡

በዘጠኙ ዞኖችና ወረዳዎች ላይ ያጠናናቸው ቦታዎች አሉ፤ የምእመናኑን ብዛት፣ የሚያስፈልገውን የጸሎትና የመካነ መቃብር ቦታ ለይተን አጥንተናል፡፡ ይህ በክልሉ መንግሥት በፍጹም መፍትሔ አያገኙምና ይህ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል እንዴት ይታይልናል? ጥያቄዬ ይህ ነው፤ የሚመለከተው ክፍል መልስ እንዲሰጠን አሳስባለኹ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡


ብፁዕ አቡነ ማርቆስ

የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መላው የጉባኤው ታዳሚዎች፣ ለውይይቱ ምክንያት የኾናችኁ የመንግሥት ልኡካን

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ

እኔ የምጠይቀው ዋና ጥያቄ ነበረኝ፤ ታሪክ ላይ፣ ዓመተ ምሕረት ላይ ነበር፤ ተመልሷል፡፡ የኾነው ኾኖ ለሌላው ቀንም መቼም ታሪክ ክፉ ይኹን ደግ እንደዚያው እንደ ታሪኩ ነው የሚተረክ፡፡ እና በመጀመሪያ ለዚህ ታሪክ ወንድማችን [ከዕለቱ የሚኒስቴሩ ተናጋሪዎች አንዱ አቶ ገዛኸኝ ጥላሁን] ይህን ታሪክ ስታቀርብ በዚህ ታሪክ ምን ያህል ላይሰንስ አለኸ? አዎ፣ እውነቴን ነው፤ ነገሮች የሚበላሹ መቼም ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!!

ታሪኩ ሲነገር፣ እንዴ! ኢትዮጵያ ስንልኮ አብራ እዚኹ ናት፤ የሃይማኖቱ መሥራቾች ናቸውኮ፤ ይህን ስንል ሌላ ሰው አይኑር፣ መቻቻል የለም እያልን አይደለም፡፡ ግን አንዳንዴ ስትተርኩ እንዴ፣ መንግሥቱንስ ከምን ተረከባችኹት ያሰኛል፡፡ አገሪቱንስ ከማን ተረከባችኹ? የተሳሳተውን ማስተካከል ዛሬም ነገም ተገቢ ነው፤ ዕድገት ነው፡፡ ግን ልጁ ሁልጊዜ አባቱን እየኮነነ፣ ‹እኔ ከአባቴ በፊት ነበርኹ› የሚለው ታሪክ ምንድን ነው? እንደ ሃይማኖቱ ነው፣ እንደ ሌላው አይደለም፡፡ ስለዚህ ይኼ ክርስትና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገባ የሚለው በእውነቱ እንዳይደገም፤ ዛሬ ግራጁዌት አድርጉት፡፡

ብዙ ቦታ ሰምቻለኹ፡፡ ክርስቶስ ዐርጎ ዓመትም አልሞላ፣ ሐዋርያት እዚያው በመዲናው ኢየሩሳሌም እያሉ የብሉይ ኪዳን እምነት ተከታይ ስለነበረች በዓል(የፋሲካን) ልታከብር ሔዳ ያውም ደግሞ ከሰው አይደለም፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እንደሌላው አገር የሰባኪ ደም አፍስሳ፣ መምህር ገድላ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ያውም በባለሥልጣኑ በጃንደረባው ነው፡፡ እኔ እንደው አሁን አሁን እየቀፈፈኝ የሄደ ባለሥልጣን አገሩን የሚጠላ ምንድን ነው! በጣም የሚቀፍ ነገር፤ እንዴ! እኛ እኮ ዛሬ ነው የተወለድን፡፡ ስለዚህ ጃንደረባው በዓል አክብሮ ሲመለስ እግዚአብሔር መልአኩን ‹‹ሂድ፣ ተከተለው›› ብሎ መልአኩ ለፊልጶስ. . .በዓለም አቀፉ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ ምዕ. ፰÷፳፮ ጀምሮ ተጽፏል፡፡ ይህ ዓለሙ፣ ሳይንቲስቱ ሁሉ ይቀበለዋል፡፡ እናንተስ ለምንድን ነው?

ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እንደው ራስ ወዳድ ያስመስላል እንጂ ከአይሁድ በፊት ነው፡፡ አይሁድነቱን ከአብርሃም በግዝረት ነው የተቀበሉት፡፡ እኛ ከኖኅ ነው፤ የኖኅ የልጅ ልጆች፤ ኖኅ መምለኬ እግዚአብሔር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይኼ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪኩን አታዛቡ ነው! ሲያስፈልግ በእውነቱ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሠለጠነ፣ ቢቻል የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የኾነ፣ ስለ ኦርቶዶክስ እምነት የሚያስተምር፣ በጳጳሳቱ ፊት ለመናገር ዕውቀት ያለው መኾን አለበት፡፡ ዐሥር ጊዜ በዲግሪ ቢመረቅ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አይኾንም፡፡ ያልኾነ ታሪክ አምጥታችኁ ስትደፉት እንዴት ዝም እንበል? አታስቆጡን!

በተጨማሪ ቱሪዝምን በተመለከተ፣ ይህች ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሕዝብ ባለቤት ናት፡፡ ነፍጠኛ ምናምን ስለምትሉት አይደለም፡፡ እርሱ ይሙትም ይኑርም ፈልጉት፡፡ እኛ እያወራን ያለነው ስለ እውነተኛው ነገር ነው፤ እና ቱሪስቱ ዋልድባን ሊጎበኝ ሲሄድ ሙስሊሙ ዋልድባ ሄዶ ስለ ዋልድባ ያወራል፡፡ እንዴ! ምን ጉድ ነው! እንዴት ተደርጎ ይኾናል፤ ለእርሱስ ክብረ ነክ አይኾንም ወይ? መልእክቶች ስለኾናችኁ ይህን ይዛችኁት ሒዱ፡፡ እንዴት አድርጎ ሙስሊሙ ስለ ኢትዮጵያ ገዳማት ይተርካል? ምኑን ያውቀዋል እስኪ? አኹን እኔ ሔጄ ስለ መስጊዱ ተርክ ብባል ውርደት ነው፤ አይገባም፡፡ ቅ/ሲኖዶስ በእውነቱ እዚህ ላይ ደክሟል፡፡ የእኛ ገዳማት በቪዲዮ እየተቀረጹ ገቢው ለሌላ ነው፡፡

በስተቀር መንግሥት ስለ ሰላም፣ ስለ ልማት፣ አንድ ኹኑ የሚለው ምን ችግር አለው፤ እኛ ባለቤቶች ነን፤ ምን ችግር አለ፤ ምንስ አድርጋ? ከእርሷ በኋላ የመጡትን በክብር ተቀብላ ነው ያስተናገደች፡፡ አትጋፋ፣ እንግዳ ተቀብላ፣ እግር አጥባ፣ ሃይማኖትኸ ምንድን ነው አትልም፡፡ ተቀብላ፣ እግር አጥባ፣ ምሳ ራት አብልታ የምትሸኝ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ነገር ግን ልታስተምሩን ስትመጡ ሳብጀክቱን ግራጁዌት እያደረጋችኹ ኑ፡፡



ብፁዕ አቡነ እንድርያስ

የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤


ብፁዕ አቡነ እንድርያስ

በቤተ መንግሥት የወርቅ የብር አገልግሎት የሚሰጥ ዕቃ ብቻ አይኖርም፤ ከዕንጨትም፣ ከጭቃም የተሠራ አገልግሎት ሰጭ ሀብት አለ፤ ይላል ሐዋርያው ሲናገር፡፡ ምን ማለት ነው፣ በቤተ ወንጌል ምእመናን፣ ጻድቃን ብቻ አይኖሩም፤ ወንጀለኞችም አሉ፡፡ በስም የሚጠቀሙ፣ ነግደው የሚያድሩ፣ ቅድም ወንድሜ ተናጋሪው በሃይማኖት ሽፋን እያለ ብዙ ምሳሌዎችን እየሰጠ ቆይቷል፡፡ ይቆይ እንጂ በወሬ ማመን በደል ነው፤ በተግባር ማመን ደግሞ እውነትነት ነው፡፡ ወሬው ያለቦታው እየተወራ አስቸግሮናል፡፡ መንግሥት የራሱ አካሄድ አለው፤ ሲነገር እንደዋለውም ሥልጣኑን ከማን እንደተረከበውም ራሱ ያውቃል፡፡

መንግሥት የሚኖረው በእግዚአብሔር ርዳታ፣ በእግዚአብሔር ሰጭነት ነው እንጂ በራሱ ሥልጣን የለውም፡፡ ይኹን እንጂ ወሬ ያደራጃል፤ ያስጠነቅቃል እንጂ አካልነት የለውም፡፡ ምሁራኑ ይመስክሩ፡፡ ወሬ ያደራጃል፤ ጠላት ወዳጅ ያስለያል፤ ምንነቱን ይገልጣል፡፡ ታማኝነት ያለው፣ በትምህርት ያደገ ሰው አይዋሽም፤ አይዘርፍም፤ አያዘርፍም፤ ሕይወትም አያጠፋም፤ ራሱን ግን ይጠብቃል፤ ሌላውም ራሱን እንዲጠብቅ ይጋብዛል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ መርሖ ይኸው ነው፡፡ ዘሰ ይትኤገሥ እስከ ተፍጻሜ ውእቱ ዘይድኅን ይላል በሀገሪቱ ቋንቋ፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚታገሥ የሚድን እርሱ ነው፤ ይላል፡፡

ይህን ሁሉ በማለት የተነሣኹት፣ ባለኹበት ሀ/ስብከት ብዙ ችግሮች ተፈጥረው፣ ችግሮቹ መፍትሔ አጥተው ቀርተዋል፡፡ ስድስት አድባራት ተቃጥለዋል፡፡ ያቃጠላቸው አይታወቅም፡፡ ሦስቱ በአንድ አካባቢ፣ ሦስቱ በተራራቀ ኹኔታ በቆላ፣ በደጋ፣ በከተማ አቅራቢያ ተቃጥለዋል፡፡ የዞኑ መንግሥት፣ ክልሉ መንግሥት ቢጮኸለትም አይሰማም፤ መልስም አይሰጥም፤ እንዲያውም ያስተባብላል፡፡

ቅድም ከተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳት ሲነገር የነበረው አትንኩን የሚል ነው፡፡ የተበደለ ሰው ሲናገር ፖሊቲካ ተናገረ እየተባለ የውሸት ውሸት ሲያተራምሱን የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሐቅ ሲወጣ ስውር ነገር የለውም፡፡ አካል ነው፡፡ ቀድሞ የብራና መጻሕፍት፣ የመስቀል ስርቆት ሲያጥለቀልቀው ቆየ፡፡ ዛሬ ደግሞ ወደ ቃጠሎ ተመልሶ ሌትም ቀንም ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለ፣ ምእመናን እያለቀሱ፣ የሚጮኹበት አካል ጠፍቶ፣ የተበሳጨና የነደደው በሃይማኖት ሽፋን እንደተባለው፣ ብዙ መናገር ይቻል ነበር ግን ነፋስ ስለሚወስደው፡፡ ያለው ኹሉ አንድ ቤት ነው፤ በአንድ አቋም ያለ ነው፡፡ ይህ ዘመቻና ቃጠሎ በየኹሉ ይደርሰዋል ብዬ ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ ወረዳዎች ስድስት አድባራት ተቃጥለዋል፡፡ ለስድስቱም የሚያጽናናቸው ሰው የለም! መንግሥትም አልጠየቀንም፤ መረጃ ብንሰበስብም እገሌ አቃጠለው የሚል ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ጨለማ ለብሶ ነው የሚያቃጥለው፡፡ ሰዓት ጠብቆ ነው የሚያቃጥለው፡፡ ለአቤቱታ ከብዶናል፡፡ ምእመናን እያለቀሱ ይገኛሉ፡፡

እንዴ! የመንግሥት ሥልጣን የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አፍ፣ የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት? ለሌሎቹ ሞራል ይሰጣሉ ማለት ነው? ጽላቱ ሲሰረቅ፣ መስቀሉ ሲሰረቅ፣ ብራናው ሲሸጥ፣ ሙስሊሞች ሲከብሩበት፣ ቤተ ክርስቲያኑ ተቃጥሎ ዐመድ ሲለብስ፣ የክርስትናው ጥምቀት ሲቀር ምን ይሰማችኋል? ይኼ የሰላም መደፍረስ አይደለም? መቻቻል፣ መቻቻል ትላላችኹ፤ መቻቻል የሚለው አማርኛ ከየት ዘር ነው የወጣው? አማርኛ ነው እንዴ የምታመርቱት? ሐቅ መናገርኮ ኮሶ መቆርጠም ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ስለ ከበደኝ፣ እስኪ ዓለም ይወቀው፤ እቢሯቸው ድረስ ሔጃለኹ፣ ጠይቄአለኹ፤ መልስም አላገኘኹም፤ እንዲያውም አንዱ ተቆጣኝ፡፡ ስለ ተቆጣኸ፣ አንተ ተቆጣኸ ብዬ እኔ ዝም አልልም ብዬ ነው የወጣኹት፡፡

ስለዚህ እኛ መመሪያውን እንዲያው ልንገራችኹ፣ እናንተ ከምታስተምሩት ይልቅ ይኸው ዘመን ተቆጥሯል፤ ወደ ዐርባ ዓመት እየተጠጋ ነው፤ በኢትዮጵያ የተገለጸውን ችግር ለመቋቋም ለሕዝቡም ለመንግሥቱም ስናገለግል የምንኖረው እኛው ብቻ ነን – ሐቁን ለመናገር፡፡ እዛው ሥራ መሥራትም ይቻላል፡፡ ቅድም እንደተነገረው አትንኩን ነው እንጂ ተላልፈን የሰው ድንበር፣ የሰው ሥልጣን፣ የሰው ክብር ነክተንም አናውቅም፡፡ ለምንድን ነው ግን በሽፋን የምትጠቀሙብን? መንግሥት እኛን ሽፋን አድርጎ ነው ሲበዘብዘን የምንኖረው፡፡ ሌባውም፣ ቀጣፊውም፣ ሰርጎ ገቡም ሲያጭበረብረን፣ ሲያታኩሰን መንግሥትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝ፡፡



የወላይታ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የዚህ ታላቅ ጉባኤ ዕድምተኞች፤

ወንድሞቻችን ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› በሚል ርእስ ትምህርት አሰምተውናል፤ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን እኛን መቻቻል ብላችኹ ከነገራችኹን ከእናንተ ሥር ያሉት ምን እየሠሩ እንደኾን ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡

በወላይታ ኮንታ ሀ/ስብከት በበዴሳ ወረዳ አንድ የፍርድ ቤት ዳኛ÷ ‹‹ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ቄራ አንካፈልም፡፡ በመሠረቱ ቄራን የምታስተዳድረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳትኾን ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ በምንም ዐይነት ከኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ጋራ ቄራ አንካፈልም፡፡ ሁለተኛ፣ በትራንስፖርት፣ በመኪና ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን እምነት ተከታዮች ጋራ አንሄድም፡፡›› ዳኛው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ዳኛ ነው፡፡ ሕግ የሚያስተረጉም፣ ጥፋተኛውን በእርምት የሚያስተምር ሰው ነው፡፡ ‹‹እስከ መቼ ድረስ ነው አንገታችኹ ላይ መስቀል የምንታጠለጥሉት›› በሚል እስከ ገጠር ቀበሌዎች ድረስ ኦርቶዶክሳውያንን የማሸማቀቅ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

አሁን እንግዲህ እናንተ እዚህ መቻቻል እያላችኹ ነው፡፡ ዕድር ሙታን የሚሸኙበት የኖረ ማኅበረሰባዊ ተቋም ነው፡፡ ፕሮቴስታንቱ ዳኛ ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ጋራ አያስፈልግም በሚል 80 ዓመት የኖረን ዕድር ያስፈረሰ ሰው ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ለክልሉ አመለከትን፣ ለዞኑ አመለከትን አጣሪ ተብሎ መጣ፤ የተሰጠ መፍትሔ የለም፤ ሰውዬውም እስከ አሁን በሥራው ላይ ቁጭ ብሏል፡፡ ክርስቲያኖች እየተሸማቀቁ ነው ያሉት፤ ለምን? ግለሰቡ ዳኛ ስለኾነ፡፡ የመንግሥት አካል ስለኾነ፡፡ ይኼ መቻቻልን ያመለክታል ወይ? ዝቅ ብላችኹ ፈትሻችኋል ወይ? ይኼ እንዲሚመስለኝ እግሩን በጅብ እየተቆረጠመ ‹‹ዝም በል፤ ጅብ ነው›› እንዳለው ሰው ያለ ኹኔታ ነው፡፡

ሁለተኛ፣ ከትላንት ወዲያ ወደዚህ ልንመጣ ስንል በደረሰን ደብዳቤ አንድ ካህን፣ አስተዳዳሪ ነው፤ ሕይወቱን የሚመራበት ከቤተ ክርስቲያን ይዞታ ላይ ተቆርሶ ተሰጥቶታል፤ ነገር ግን በውስጥ ግብር ገብሮ ተገኘቷል፡፡ መሬቱን ልቀቅ በሚባል ጊዜ ምንድን ነው ያደረገው፣ ፍርድ ቤት ሄደን ከተካሰሥን በኋላ መጨረሻ ላይ 83,000 ብር ለግለሰቡ ክፈሉ የሚል ውሳኔ ነው የተወሰነብን፡፡ ይኼ ሕዝቡ እየተንጫጫበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ሕዝብ እንዲያው ዝም ብለኸ ተቻችለኽ ኑር ማለት እንችላለን ወይ? ለሌሎች የመንግሥት አካላት ብናመለክትም ሁሉም ለግለሰቡ ይከፈል ብለው ነው የፈረዱት፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ትክፈል የሚባል ከኾነ ታሪክ አይበላሽም ወይ? እንዴት ታዩታላችኹ?

ሦስተኛ፣ ቤተ ክርስቲያኑ ሩቅ ስለኾነ የሥርዐተ ቀብር ማስፈጸሚያ ቦታ ሦስት ዓመት ሙሉ ጠይቀን፣ አስከሬን ይዘን ለቀብር ስንሔድ ውኃ ነጥቆ እየወሰደብን ነው፡፡ ይህን ስንጠይቅ መልኩ ተቀይሮ፣ ‹‹የፖሊቲካ ጉዳይ ነው፤ ሕዝብን በሃይማኖት ሽፋን ታንቀሳቅሳላችኹ›› እየተባልን፣ እየተሸማቀቅን ያለንበት ኹኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን እንዴት ታዩታላችኹ? መቻቻልስ የሚመጣው ከምን አኳያ ነው? ዝም ብለን የምንቀመጥ ከኾነ ምናልባት ሓላፊነት ለመውሰድ ስለሚከብደን ይህን ወርዳችኹ እንድትፈትሹ ለማለት ነው፡፡ አመሰግናለኹ፡፡

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።