.....ምን ይጠቅም መሰለህ? አዎን ሰዎችን ስትመለከታቸው ዘውጋቸው ቋንቋቸው ሲሆን ተመልክተህ ይሆናል።ናላቸው በቋንቋ እና የትውልድ መንደር ብርብራ እንደቀመሰ አሳ ተሳክረው ይሆናል።ይህ ሁሉ ግን ኢትዮጵያዊነትህ ላይ ነቁጥ እንዳያንጠባጥብበት ተጠንቀቅ።ልብ አለማለታቸውን ልብ አላሉት ይሆናል እንጂ በዙርያ ንግግር እናትህ ስትወልድህ የት መውለድ እንዳለባት እየመከሩህ አንተም ከመወለድህ በፊት በእናትህ ሆድ ሳለህ ለእናትህ የት መውለድ እንዳለባት ማሳሰብያ ቢጤ አለመስጠትህን ከኃጢያት ቆጥረውብህ እኮ ነው።
እናት ምን አጠፋች? ልጅስ ምን አጠፋ? እናት መውለጃዋ ሲደርስ መንደር መምረጥ ነበረባትን? ቆይ የመውለጃ ጊዜዬ ደረሰ ልጄን ይህንን አልያም ያኛውን ቋንቋ ከሚናገሩት መንደር ወይንም ሀገር ወስጄ ልውለድ ልትል ይቻላታልን? ልጅስ የት መወለድ እንዳለበት በእናቱ ሆድ ሳለ መወሰን ይገባው ነበርን? እናቱንስ ገና ከማህፀን ሳለ የለም እናቴ ከእዚህ መንደር አትውለጅኝ ከዛኛው መንደር ውለጅኝ ፣ይህንን ቋንቋ አልናገር ያኛውን ግን ልናገር ማለት ይችላልን? ደግሞስ ኢትዮጵያ ሁሉ እንደየ እጣው የመጣባት ምድር አይደለችምን?
ሰዎች እንደፈለጉ በጥላቻ እና በቋንቋ ለመለያየት ይጋልቡ።ባለስልጣኖቹ በአፈሙዝ በነጠቁት ስልጣን ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጋጩ እና እየለያዩ ደቂቃዋን ያራዝሙ አንተ ግን እራስህን ከጥቃቅን ቋንቋን እና ትውልድ መንደርን እየሸነሸኑ ኢትዮጵያዊነትህን ልያዘናጉህ ''ለእኔ እስካልተመቸችኝ ስለመንደሬ ብቻ የማትዘምር ኢትዮጵያ ምን ታድርጋለች'' ከሚሉህ ጥቃቅን ቀበሮዎች እራስህን ጠብቅ።
ጥቃቅን ቀበሮዎቹ ሲጮሁ፣ሲፅፉ፣እንደፈለጉ ህዝብን ከህዝብ ጋር ሲያጋጩ ሀገሬ፣እኔነቴ፣ሰላሜ ኢትዮጵያ ነች መንደሬ አይደለም ያሉቱ ወይ አይፅፉ ወይ ተዉ አይሉ ዝናብ እንደመታው የደጋ በግ ቢፈዙብህም አንተ ግን አሁንም እራስህን ከጥቃቅን ቀበሮዎች ጠብቅ።ከመንደርህ ሀገርህ፣ከእድርህ ኢትዮጵያዊነትህ በመጨረሻ ላይ እንደሚያሸንፍ ቅንጣት ታክል አትጠራጠር።
ክፍል ሁለት ከመቃብር የተላከ ደብዳቤ ተጠናቀቀ።
ክፍል ሶስት ካልተወሰነ ጊዜ በኃላ ከመቃብር እንደሚላክ ይጠበቃል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ ጥቅምት 15/2006 ዓም
ጉዳያችን GUDAYACHN
No comments:
Post a Comment