ከፅሁፉ መጨረሻ ላይ ሙ/ጥ/ዲ/ዳንኤል ለአዲስ ዓመት ከኢቢሲ ጋር ያደረገው አዲስ ቃለ መጠይቅ ቪድዮ ያገኛሉ።
================
ጉዳያችን/Gudayachn
================
የተከበሩ የምክር ቤት አባል እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የኢትዮጵያዊነት፣የሀገር መውደድ፣በእምነት የመፅናት፣ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንደ ዕምነቱ የማክበር እና የመከባበር ምሳሌነት ሁሉ ምሳሌ በመሆን ያሳየ ኢትዮጵያዊ ነው።ዳንኤል አሁን በአንድ ሰውነት የሚታይበት ጊዜ አይደለም።ሲጀምር ላለፉት 30 ዓመታት በመላው ዓለም እየዞረ ወገኖቹ ኢትዮጵያውያንን አስተምሯል።ትምህርቱ ስለ ሃይማኖት ብቻ አይደለም።ኢትዮጵያን መውደድ እና ኢትዮጵያውያንን ማቀራረብ ላይ ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ ሰርቷል።በውጭ ሀገር ያያቸውን አዳዲስ አሰራሮች ሁሉ ለባለሙያዎች ለማካፈል ለፍቷል።ዛሬ ላይ ደግሞ ዳንኤል ከአንድ ሰውነት ባለፈ በሕዝብ ድምፅ ሕዝብ እንዲወክል የኢትዮጵያ ፓርላማ አባል ሆኖ ተመርጧል።በእዚህ አጭር ፅሁፍ ስለ ዳንኤል ለእዚህ ትውልድ እና ለኢትዮጵያ ያደረጋቸውን ለመዘርዘር ጊዜ አይበቃም። ታሪክ ወደፊት በራሱ መንገድ የሰራቸው መልካም ስራዎች እና በጎ ተፅዕኖዎች በራሱ ጊዜ የሚዘከር ስለሆነ ዛሬ እዚህ ላይ መዘርዘር አያስፈልግም።
ከሰሞኑ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ በአዲስ መልክ የተከፈተ የስም ማጥፋት ዘመቻ መሰል እየታየ ነው።ከእዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የሐሰት የስም ማጥፋት ሙከራዎች ሲደረጉ የነበረ ቢሆንም ከሰሞኑ ዲያቆን ዳንኤል ንግግር ባደረገበት አንድ ስብሰባ ላይ ''እነርሱ'' የምትለዋን አባባል ''እኛ እና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነን'' ባዮቹ የተረፈ ህወሓት አፈቀላጤዎች ከካናዳ እስከ አሜሪካ በመቀጠል ደግሞ ዛሬ የህወሓት አፈቀላጤዎች የሚያቀርቡለትን እንደ የገደል ማሚቱ የሚያስተጋባው ማርቲን ፕላውት ከእንግሊዝ በትውተር ገፁ ላይ ይህንኑ ህወሓት ሲነቀፍ የትግራይ ሕዝብ ማለት ነው የሚሉትን የሐሰት ወሬ ሲያሰራጭ ተስተውሏል።ከእዚህ ባለፈ የህወሓት ቲቪ (ዩቱብ) አፈቀላጤው አሉላን አቅርቦ ከሰሞኑ የላንቃ መክፈቻ ያደረጉት ዲያቆን ዳንኤልን ነው። ይህ ሁሉ መንጫጫት የሚያሳየው ግን ዳንኤል በእውነትም በምን ያህል ስፋት እና ጥልቀት ተፅኖ እየፈጠረ ብቻ ሳይሆን የጁንታውን ስስ ብልት እንደነካበት የሚያመላክት ነው።
ትናንትም፣ዛሬም ነገም የተከበሩ የምክር ቤት አባል ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ነቁጥ ቢፈልጉ ያጡት የህወሓት አፈቀላጤዎች አጣመው የሚያቀርቧቸው ሦስቱ ነጥቦች በአጭሩ እናንሳቸው እና እውነታዎቹን በአጭር እንመልከት -
1) የመጀመርያው ሰሞኑን እየቀረበ ያለው ዲያቆን ዳንኤል የህወሓት ከፋፋይ አስተሳሰብ፣አሰራር እና የጥፋት መንገድ ሁሉ ከምድረገፅ መጥፋት አለበት፣ከአእምሮአችን ሁሉ መፋቅ አለበት።ለመጪው ትውልድም ማውረስ የለብንም።የሚለውን ንግግር የትግራይ ሕዝብ ላይ የተነገረ በማስመሰል ከንግግሩ መሃል ገብተው በመቁረጥ ''እነርሱ'' የሚለውን ሁሉ ለትግራይ ሕዝብ እንደተነገረ አጣመው በእንግሊዝኛ ለማቅረብ ሞክረዋል።በንግግሩ ላይ ከፍ ብሎ የሚሰማው ግን በትክክል ያነሳው የህወሓት አመራር እና አስተሳሰቡን ነው።እነርሱን ያለውም ህወሓትን እንጂ የትግራይን ሕዝብ አይደለም።ዳንኤል የትግራይን ሕዝብ የትግራይ አፈቀላጤ ነን ከሚሉት በላይ በታሪክም በአካልም ያውቀዋል።ለአክሱም ሙዚየም የልማት ኮሚቴ ውስጥ ሲያገለግል፣የዛሬ አፈቀላጤዎች ዱባይ እና ሸራተን ውስኪ ሲያንቃርሩ ነበር።እነርሱ መቀሌን የሚያውቁት ለለቅሶ ወይንም ሰርግ ሲጠሩ ወይንም ለስብሰባ እንጂ ኑሯቸው በአዲስ አበባ ቅምጥል ቤቶች አድርገው ነው የኖሩት።ዛሬ ደርሰው እነርሱ ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው ለማለት ሲንደረደሩ መመልከት የቀልብ መሳት ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?
2) የእስልምና እምነትን ነቀፈ የሚለው ቪድዮም ተመሳሳይ የቅጥፈት እና የሐሰት አቀራረብ ይዟል። በውጭ ሀገር እና በሀገር ውስጥ ዲያቆን ዳንኤል ካደረጋቸው ገለጣዎች ውስጥ በአክራሪ እና ፅንፈኛ እስልምና ላይ የተናገረው ነው።ፅንፈኛ እና ነውጠኛነትን እስልምና ሆነ ክርስትና የሚቀበሉት አይደለም።የእምነት እኩልነት መከበር በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የተቀመጠ ነው።ፅንፈኛነት እና ነውጠኛነት ግን ከሁለቱም እምነቶች ውጭ ነው።አሁንም ነውጠኝነት እና ፅንፈኛነት መደገፍ በየትኛውም የዓለም ክፍል ተቀባይ አይደለም።ይህንኑ ጉዳይ የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችንን ለመንቀፍ እንደቀረበ ተደርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ሙከራ ሁሉ ደካማ ሙከራ ነው።
3) ሦስተኛው እና ውሃ የማይይዝ ጉዳይ መናፍቅነት የሚለው ነው።ይህንን በተመለከተ አንዲት መድረክ ላይ መናፍቅ የሚለው ሌላ ትርጉም አለው ወይ? ስድብ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ መጠየቁን የህወሓት አፈቀላጤዎች የሚያሳዩት ቪድዮ ነው። መናፍቅ የሚለው ቃል መጠራጠርን የሚያሳይ ነው።ማንም ዕምነት የእርሱን እምነት የማይቀበል የእኔን ይጠራጠራል ሲል ምንፍቅና ይለዋል።መናፍቅ የሚለው ቃል ደግሞ በትርጉምም በአገላለጥም በቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ቃል ነው።ይህንን ዛሬ ዲያቆን ዳንኤል ተነስቶ የፈጠረው አዲስ ቃል አይደለም።ቃሉንም ሊቀይረው አይችልም። የህወሓት አፈቀላጤዎች በአዲስ አበባ አንዲት መፃህፍት ቤት ሳይሰሩ 30 ዓመታት ስላሳለፉ ማገናዘብ ብሎ ነገር አልፈጠረባቸውም።
በሌላ በኩል ትውልድ ስያንኮላሹ ስለኖሩ በለመደ ስለታቸው ዛሬ እውነትን በመመስከሩ እና ከሁሉም በላይ ለሀገሩ ትልቅ ፍቅር ያለውን፣ሀገሩን በመውደዱም ሕዝብ በድምፁ በፓርላማ ወክለን ብሎ የመረጠውን ሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ላይ ያልተናገረውን እያጣመሙ በእንግሊዝኛ በውሸት ትርጉም ሰዎችን ለማሳሳት የሚሞክሩት ሰዎች የስብዕናቸው ደረጃ በምን ያህል መውረዱን እራሳቸውን በራሳቸው አጋልጠውበታል።ዩንቨርስቲ መግባት፣መማር በእዚህ ደረጃ በውሸት ያሳብዳል እንዴ? እስኪባል የእዚህ ዓይነት የሃሰት የእንግሊዝኛ ትርጉም ከቪድዮ ጋር የሚያቀናብሩት ውስጥ ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ውድድር በዘር ገመድ ብቻ እና ብቻ በመተብተብ ላብ እያጠመቃቸው ዘመቻ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።ዛሬ የዘረኝነት ጭጋግ ዓይናቸውን ሸፍኖት በአንድ ወቅት ሲሰብኩት የነበረውን በሐሰት አትመስክር እና ወንድምህን እንደራስህ ውደድ የሚለውን ቃል ዛሬ ማላገጫ አድርገውት የህወሓት ጀሌ በአማራ እና በአፋር ንፁሃን እጁን በደም ሲታጠብ ስለት አቀባይ ሆነው ቀርበዋል።
ባጠቃላይ የሐሰት የስም ማጥፋት ዘመቻው ይቀጥላል።በኢትዮጵያዊነት እና በኢትዮጵያ ላይ የተነሱ ሁሉ ግን ውርደታቸውን በቀሚሳቸው እና በሙሉ ሱሪያቸው ስታቀፉ እንጂ አንዳች እርምጃ ስራመዱ ታሪክ እና ሕዝብ አይቶ አያውቅም።የኢትዮጵያ እውነተኛ ልጆች፣ለኢትዮጵያ የለፉ፣ሕዝብ ከህዝብ ለማለያየት ሳይሆን አንድ ለማድረግ የደከሙ፣የራሳቸውን ጥቅም ሳይሆን የሀገር ጥቅም ያስቀደሙ እና ሕልማቸው ሁሉ የሀገራቸው ማደግ እና ነፃነት የሆኑት እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያሉት ሁል ጊዜ ስማቸው በሕይወት እያሉ ብቻ ሳይሆን ከመቃብር በኃላም ትውልድ የሚያነሳው ነው።ምናምንቴ አስተሳሰብ የያዙ ያፍራሉ።የእርጅና ዘመናቸውንም በትካዜ ይገፉታል። ኢትዮጵያ በትዝብት እያየች እንዳሸማቀቀቻቸው ዕድሜ ዘመናቸውን ይፈጃሉ።
ከእዚህ በታች ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለዘንድሮው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ያደረገው ቃለ መጠይቅ ይመልከቱ።
ርዕስ = የመሻገሪያ ዘመን- ለሙኃዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር የተደረገ ቆይታ
መስከረም 1፣2014 ዓም
ኢ ቢ ሲ
No comments:
Post a Comment