ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, September 15, 2021

በአማራ እና አፋር ላይ ከወረራ ባለፈ ሽብርተኛው ህወሓት እና ጀሌው ንፁሃንን የገደለበት እና ንብረት የዘረፈበት ሦስት ምክንያቶች እና የህወሓትን መርዝ ለማምከን በቀጣይ መደረግ ያለባቸው አምስት ተግባራት።

Picture taken from business2community

==============
ጉዳያችን/ Gudayachn
==============
ሽብርተኛው ህወሓት እና ጀሌው በአማራ እና አፋር ክልል ላይ ለጆሮ የሚከብድ የሰው ልጅ በሰው ላይ ይፈፅመዋል የማይባል የአውሬነት ባህሪው ተገልጧል።ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የህወሓት አመራሮች በደም ተነክረው በሕዝብ አጥንት ላይ እየተራመዱ ቢኖሩም የአሁኑ በአማራ እና አፋር ላይ የሰሩት ግን ለምን? ብሎ መጠየቅ እና የሄዱበትን መንገድ ማምከን ያስፈልጋል።

ወደ ሶስቱ ምክንያቶች ከመሄዳችን በፊት ለዓመታት የኖረው በተለይ  በአማራ ማኅበረሰብ ላይ ያላቸው ጥላቻ እንዳለ መሆኑ በሰነድም የተደገፈ ስለሆነ ይህንን ምክንያት በቀዳሚነት እንዳለ ሆኖ ነው የወቅቱን ሦስት ምክንያቶች በደንብ መረዳት ያለብን።

ምክንያት አንድ - በአማራ እና በትግራይ ሕዝብ መሃል ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንበጥሰዋለን ብለው በማሰብ 

ህወሓት ለረጅም ጊዜ የትግራይን ሕዝብ ሌሎች በተለይ አማራ ሊያጠፋህ ነው በሚል ብዙ ፕሮፓጋንዳ ሰርቷል።ከአራት ዓመታት በፊት በጎንደር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን አስደንብሮ ወደ መተማ ካፈናቀለ በኃላ ህዝቡ ውሸት መሆኑን ሲያውቅበት መልሶ በአይሮፕላን ማመላለሱ ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚያስረዱት በአዲስ አበባ እና በቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ከአንድ ሚልዮን የማያንሱ የትግራይ ተወላጆች ዛሬም በሰላም በሀገራቸው እየኖሩ ነው።ህወሓት በተለያዩ መዋቅሩ ስር በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶቹ እነኝህን የትግራይ ተወላጆች ህዝቡ ሊፈጃችሁ ነው፣እኔ ከሌለሁ አበቃላችሁ እያለ መዓት ሲያወራ ከርሞ፣ህወሓት መቀሌ ሲገባ ምንም እንዳልተፈጠረ ሲታወቅ ውሸቱ ተጋልጧል። 

በመቀጠልም መከላከያ መቀሌ ሲገባ ሕዝብ ይፈጃል ጨረሳችሁ በሚል ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን አደናገረ። ሰራዊቱ መቀሌንም ትግራይንም ለቆ ሲወጣ ሕዝብ እየገደለ እና ንብረት እያወደመ ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ ነው ወጥቶ የሄደው። ይህንን ሕዝብ ይታዘባል። በመሆኑም እነኝህ ሁኔታዎች እየቆዩ በትግራይ ማኅበረሰብ እና በሚያጎራብቱት ክልሎች ማለትም በአማራ እና በአፋር ሕዝብ እንዲሁም በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር አንድነት መልሶ ይመጣል የሚል ስጋት ላይ ጣለው።ስለሆነም ጀሌዎቹን በጭካኔ በገበሬዎች ላይ ግድያ፣ዘረፋ እና ሴቶችን መድፈር እንዲደረግ እና ሕዝብ ከትግራይ ጋር ተቆራርጦ እንዲቀር ለማድረግ ሞከረ።

ምክንያት ሁለት -  ትግራይን የመገንጠል ሕልሙ የተፈጥሮ ሂደት እንዲሄድ ከማሰብ 

ህወሓት ትግራይን መገንጠል ይፈልጋል።ነገር ግን ይህ ከባድ እንደሆነ ከትግራይ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ያለው ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ትስስር የጠለቀ መሆኑ ገብቶታል።ስለሆነም ይህ የመገንጠል ሕልም የግድ የሆነ መሆኑን ሕዝብ እንዲያምን ለማድረግ የማይበርድ እሳት በትግራይ ሕዝብ እና በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሃል መክፈት እና ይህ ቁርሾ ሌላው ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ላይ በመሃል ሀገር ሳይቀር እንዲነሳ እና የዘር ፍጅት እንዲፈፀም ይፈልጋል። ህወሓት የተፈጥሮ ሂደት የሚለው ይህንን ነው።አንድ ሕዝብ ሌላ ሕዝብ በእኔ ላይ ተነስቷል ሊያጠፋኝ ነው ብሎ ለሕልውናው ከሰጋ እስከ መገንጠል ማሰብ የመጨረሻ ግቡ ነው።ስለሆነም ህወሓት አፋር እና አማራን ሲወር የመግዛት እና የመቆጣጠር ዓላማ ቢኖረው ኖሮ ሰላማውያንን ሳይነካ ወረራውን ያደርግ ነበር።የተፈለገው ግን የዘመናት ቁርሾ በመፍጠር በሕዝብ መሃል ፍጅት ፈጥሮ ትግራይ ከመገንጠል ሌላ አማራጭ የለም የሚል ትውልድ ለመፍጠር ነው። ይህም አልተሳካለትም። የአሁኑ ጦርነትን መነሻ ታሪካዊ ሂደት የታወቀ ነው።ህወሓት ትግራይን ሲጠብቅ የኖረውን የመከላከያ ሰራዊት በተኛበት ገድሎ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት የነገሩ መነሻ እንደሆነ እራሱ በሰኩቱሬ አማካይነት ያመነው ነው።ስለሆነም ትግራይን በተፈጥሮ ሂደት የመገንጠል ደረጃ ስሜት ለማድረስ ፈፅሞ አልቻለም። 

ምክንያት ሦስት - ሕዝብ በማሸበር ተፈሪ ለመሆን ነው።

ሶስተኛው ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቀጠቅጠውን ይፈራል ብሎ የሚያስቡ ኃላ ቀር መካሮች አሉት።27 ዓመት የኢትዮጵያን ሕዝብ ስለቀጠቀጥነው  ነው የገዛነው ብለው ያምናሉ።የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨካኝ አይፈራም።ጨካኝ ይንቃል፣ያረክሳል በመጨረሻም  በልዩ አቀጣጥ  ይቀጣል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃገሩ እንዳትበተን ክፉ ቢነግስም ታግሶ ቀን ያሳልፋል እንጂ ፈርቶ አንድ ቀን አያድርም።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እንዳሉት ሃገሩ እንዳትበተን  ያደፍጣል።አድፍጦ ሁነኛ አደረጃጀት ተደራጅቶ ይነሳል። ህወሓት በአማራ እና አፋር ላይ በጭካኔ ሰላማዊ ሕዝብ በመግደል ሕዝብ የሚፈራት እና የማትቻል አድርጎ የሚያስባት መስሏት ነበር። የኢትዮያ ሕዝብ ''ባለጌን ካሳደገ የገደለ ፀደቀ'' የሚል ሕዝብ ነው። ጨካኝ እና ባለጌ በመግደል ፅድቅ አለ ማለት ነው።ምክንያቱም እንደ ሽብርተኛ ህወሓት ዓይነቱን ማጥፋት ሌላ እንዳይገድል እና እንዳያበላሽ ማድረግ ስለሆነ ፅድቅ ነው ብሎ ነው የሚያምነው።በመሆኑም ህወሓት ሶስተኛው ምክንያትም አልተሳካላትም።

የሽብርተኛው ህወሓት መርዝ ለማምከን መደረግ ያለባቸው አምስት ተግባራት 

የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን አሁን የመጨረሻው መጨረሻ አፋፍ ላይ ደርሷል።ይህም በወታደራዊው ብቻ ሳይሆን በርዕዮት አንፃርም በራሱ በትግራይ ሕዝብ ውስጥም መሞቱ አይቀርም።ለእዚህ የትግራይ ሕዝብ በቀላሉ ስሌት ሊደርስበት ይችላል።የትግራይ ህዝብም ሆነ መሰረተ ልማቱ የወደመው የኢትዮጵያ መከላከያ ከመቀሌ ከመውጣቱ በፊት ነው ወይንስ በኃላ ብሎ እነ ደብረ ፅዮን ተመልሰው መቀሌ ከገቡ በኃላ ስንት የትግራይ የህክምና ዶክተሮች፣የዩንቨርስቲ መምህራን እንዳስጨረሱ እና መሰረተ ልማቱን በማይገባ ጦርነት ውስጥ እንደማገዱ መመልከት  በቂ ነው።አሁን መደረግ ያለበት - 

1) በሕግ ማስከበር ሂደቱ ላይ በትግራይ ተፈፀሙ የተባሉት የሰብዓዊ ጥፋቶች ላይ መንግስት በራሱ፣የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን ጋር በጋራ እያጣሩ መሆኑ ይታወቃል።ይህ በመንግስትም ሆነ በሰብዓዊ ኮሚሽኖች የተመሰረቱት አጣሪዎች በአማራ ክልል እና በአፋር የተፈፀመውን ጥቃት እና ጥፋት አብሮ እንዲያጣሩ ማድረግ እና ይህ ሂደት ያለበትን ሁኔታ ከስር ከስሩ ለሕዝብ ማሳወቅ እና ከተጣራ በኃላ መጪው የኢትይጵያ ምክር ቤት ሁኔታዎቹን የሚያርሙ ውሳኔዎች በማሳለፍ አጥፊዎች እንዲታረሙ የተጎዱ ደግሞ ተገቢው ካሳ እንዲሰጥ መወሰን።

2) በህወሓት በኩል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከማቀናበር እስከ መፈፀም የደረሱ እና በኃላ በአማራ እና አፋር ላይ ወረራ ያደረጉ፣ያስተባበሩ፣የረዱ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ።

3) የትግራይ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ ማድረግ እና ህዝቡ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለስ ማድረግ።

4) ህወሓት በትግራይ ሆነ በየትኛውም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፍ እግዱን ማፅናት።

5) በትግራይ፣አማራ እና አፋር ክልሎች መሃል ያለውን ግጭት በተመለከተ ሕዝብ ከህዝብ እየተነጋገረ በሃይማኖትም ሆነ በሽምግልና እንዲፈታው ማድረግ።የወልቃይት እና ሰሜን ወሎ አከላለሎች ቀድሞ ከሕወሓት በፊት ለዘመናት ወደነበረበት አከላለል መመለስ እና ማኅበራዊ ግንኙነቱን ማለስለስ የሚሉት ናቸው። 
===========////==============

================================
ማስታወቂያ 
============
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 


No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።