==============
ጉዳያችን/ Gudayachn
==============
በአማራ ክልል በዞን እና በወረዳ ደረጃ ያሉ አስተዳዳሪዎች ሕዝቡ ከደረሰበት የኢትዮጵያዊ ልዕልና አንፃር ብቻ ብንመዝነው የሀገር ፍቅር ያላደረባቸው በአንደበታቸው ብዙ የሚናገሩ በተግባር ግን የጁንታው የእጅ አዙር አስፈፃሚ በመሆን ሕዝቡን በማስመረር ለሌላ ወረራ የሚያዘጋጁ አሉ።ከሶስት ወራት በፊት ጉዳያችን በእስቴ እና ጋይንት አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች ጋር ስለ አካባቢው ችግሮች ለመወያየት ዕድል አግኝታ ነበር።በእዚህ መሰረት በወረዳ አስተዳዳሪ፣የመሬት ጉዳይ ኃላፊ እና የፖሊስ አዛዦች ዝርክር አሰራር፣ለሕዝብ ያላቸው ክብር ዝቅ ማለት እና የሽብርተኛው ህወሓት ወረራ ከመምጣቱ በፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች እና የስነ ልቦና ዝግጅቶች ከጥቂቶቹ በቀር ባብዛኛው በቂ ሥራ እንዳልሰሩ ቅሬታ አዳምጣለች።አንዳንዶቹ ኃላፊዎች ጁንታው ገና ሳይገባ ሕዝቡን ትተው ሲሄዱ ሕዝብ እያሰረ ለመንግስት ያስረከባቸው አሉ።ሁኔታውን ሕዝብ ለጠላት ዕድል ላለመስጠት ታግሶ አልፎታል።
አሁንም ግን የጁንታውን ዓላማ የሚያስፈፅሙ እስከሚመስሉ ድረስ በደቡብ ጎንደር ደብረታቦር ከተማ ከደቡብ ጎንደር ዞን ገጠር እና ከደብረ ታቦር ከተማ ልዩ ልዩ ምክንያት በመስጠት የሚታሰሩ የሀገሬው ሰዎች እየበረከቱ ነው።ከታሰሩት ውስጥ ቁጥራቸው የበዛ ገበሬዎች በደብረ ታቦር ፖሊስ ጣብያ እና አዳራሾች ታስረዋል።በእዚህም ገበሬው አዝመራውን ለመሰብሰብ በማሳው መገኘት አልቻለም የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ።ለእስር የተሰጡት ምክንያቶች ውስጥ ገበሬዎቹም ሆኑ የከተማ ነዋሪዎቹ ወደ ግንባር ለመዝመት ፈቃደኛ ሆነው ነገር ግን በድሮ መሣርያዎች መዝመት ስለማይችሉ የክላሽኮፕ ጠብመንጃ እንዲሰጣቸው እና እንዲዘምቱ መጠየቃቸው መሆኑ ተሰምቷል።በሌላ በኩል ከአስተዳደሩ የሚሰማው መሳርያ ባይሰጣችሁም ዝመቱ የሚል ክርክር ያቀርባል።
አስተዳደር ጥበብ ይጠይቃል።በእልህ እና በግፋ በለው የሚሰራ ሥራ አይደለም።በቀጣይ ጊዜዎች ውስጥ የጁንታው የውስጥ ''አርበኞች'' የመንግስት አሰራር በማበላሸት መንግስትን ከህዝብ ጋር ለማጣላት ብዙ ሰራዎች እንደሚሰሩ የታወቀ ነው።በእዚህ ገበሬው አዝመራውን በሚሰበስብበት ጊዜ ገበሬዎች በማይሆን ምክንያት አስሮ ይህንን ወርቃማ ጊዜውን ማቃጠል ሴራ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት አስፈጻሚው አካል ካለምንም በቂ ምክንያት የማሰር መብቱን ተጠቅሞ እና ፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ለቀናት አስሮ ህዝብ ማሰመረር ፍትሃዊ አይደለም።በመሆኑም መንግስት በቶሎ በህዝብ እና በመንግስት መሃል ክፍተት የሚፈጥሩ አመራሮችን በቶሎ ስርዓት ማስያዝ አለበት።
===============/////=============
No comments:
Post a Comment